በርካታ የዓለማችን ሀገራት ወድቀውና ደክመው መነሳታቸውን ታሪካቸው ይመሰክራል። ከውድቀታቸው ማገገም ተስኗቸው በዚያው አሸልበው የቀሩ ወይንም “ሉዓላዊው ክብራቸው ተገፎ” በአስገባሪዎቻቸው ብርቱ ጡንቻ በመደገፍ እየተብረከረኩ ያሉ ሀገራትም ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም። በህልፈተ ሕይወት ምክንያት ከዓለም ጂኦግራፊም ላይ የመንግሥትነት “እስትንፋሳቸው ጨልሞ” በነበር የሚዘከሩ ሀገራት ዝርዝም የትዬለሌ ነው።
በሁለት እግራቸው መቆም ተስኗቸው እየተብረከረኩ ያሉትም ሆኑ “ግባ መሬታቸው” የተፈጸመው ሀገራት የውድቀትና የድቀት ምክንያታቸው በሁለት ዋና ምክንያቶች ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው። አንደኛው ምክንያት፤ የውስጥ ችግራቸውን በጥበብና በማስተዋል ከመፍታት ይልቅ ተሸናፊና አሸናፊ በሌለው ትግል እርስ በእርስ በመፋለም ራሳቸውን ስላራቆቱ ሲሆን፤ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የውጭ ኃይላትን ወረራና ሴራ መቋቋም ተስኗቸው እጅ መስጠታቸው እንደ ዋና ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ።
የውስጥ ችግር ብለን የጠቆምነው ፈተናቸው መልኩና ዝርዝሩ ዝንጉርጉር ስለሆነና በርከትም ስለሚል የጥቁምታ ያህል ለማስታወስ የሚሞከረው “ሁሉ አወቅ” የሆነውንና ጥቂቶችን ብቻ ይሆናል። በተፈጥሮ ሀብት ተንበሽብሸው ነገር ግን እርስ በእርስ ተስማምቶ መብላቱ ስለተሳናቸው ማዕዳቸው በባዕዳን የተወረሰባቸው ወይንም “በራሳቸው ዳቦ ልብ ልቡን ያጡ” ሀገራት ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። ለእዚህ እውነታ ማሳያዎቹ የእኛዎቹ ዘመዶች አፍሪካዊያን ሀገራት ናቸው።
የእኔ ጎሳ፣ ብሔሬ፣ ቋንቋዬ፣ ባህሌ፣ ሃይማኖቴ፣ አካባቢዬ ወዘተ. ተዘንግቷል፣ ተጨቁነናል፣ ወይንም ተገፍተናል የሚለው ማመካኛ የየሀገራቱ የመናቆሪያ ሰበብ ነው። በእነዚህም ምክንያቶች የተነሳ ከቤታቸው ሰላም ርቆ በትንሽ በትልቁ ሰበብና ምክንያት የአረር ድምጽና የባሩዱ ሽታ ሱስ ሆኖባቸው የሚናውዙ ሀገራት በርካታ ናቸው።
ሁለተኛው ምክንያት “እንቅልፍ በዐይናቸው ዞሮ የማያውቀው” የውጭ ሴረኞችና ወራሪዎች ብዙ ሀገራትን አሽመድምደው አቅመ ቢስ ማድረጋቸው ነው። የእጅ አዙርና የቀጥታ የቅኝ ግዛት መስፋፋቶች ለዚህን መሰሉ ምክንያት በዋናነት ይጠቀሳሉ። አምባገነን ሀገራት፣ ቡድኖችና ግለሰቦች በእብሪት ሲፈጽሟቸው የኖሩት የእብሪት ወረራዎች እንደ ዋቢ ማስረጃ ሊታወሱ ይችላሉ። ዝርዝሩን መተረኩ ከዋናው የመነሻ ሃሳባችን ስለሚያርቀን ለመንደርደሪያ ያህል ይህ የወፍ በረር ቅኝት ይበቃ ይመስለናል።
እኛና የእኛ ታሪክ፤
የእኛይቱ ኢትዮጵያ ታሪክም ከሌሎች ሀገራት ታሪክ የተለየ አይደለም። ለሀገራቱ የጠቀስናቸው ሁለቱ ዐበይት ምክንያቶች ውጤታቸውና ፍጻሜያቸው ይለይ ካልሆነ በስተቀር በዘመናት ጉዞ ውስጥ አብረውን የዘለቁ የእኛም ተግዳሮቶች ነበሩ። ዛሬም ድረስ ተገላግለናቸው እፎይ ያለማለታችን ሌለው መለያችን ነው። ጥቂት ማሳያዎችን ለማስታወስ እንሞክር።
እንደ ዋዛ “በፈተና” ስም የምንጠቅሳቸው ታሪኮቻችን በቀላሉ ያለፉ ሳይሆን እጅግ ብዙ ዋጋ የተከፈለባቸውና በላብና በደም ጭምር የወረዛ የመስዋዕትነት አሻራ የታተመባቸው ተግዳሮቶቻችን ነበሩ። የውስጥ ችግሮቻችን የነበሩት በመልክም በባሕርይም ልዩነት ቢኖራቸውም በቅርብ ዘመናት ውስጥ ኢትዮጵያ ተሻግራ ያለፈችባቸውን አንዳንዶቹን ብቻ ጠቅለል አድርገን እናስታውሳቸው።
የዳግማዊ አጤ ምኒልክን ዜና እረፍት ተከትሎ የተግለበለበው ለሥልጣን የሚደረገው የእቴጌ ጣይቱ፣ የልጅ ኢያሱ፣ የራስ ተፈሪ፣ የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱና በጎራ ተቧድኖ የነበረው የወቅቱ ሹማምንት “የጥሎ ማለፍ” ሽኩቻ ብዙ ነፍስና የሀብት ውድመት፣ የዲፕሎማሲ አናሳነትና የልማት ድህነት አስከትሎብን ዛሬም ድረስ ግርሻው አለቀቀንም።
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ሥርዓቱን ለማስወገድ በተደረጉ ሙከራዎች የፈሰሰው የንጹሐን ደምና የወደመው ሀብት ለምን ያህል ጉስቁልና እንደዳረገን “ወይ ነዶ” እያሰኘ “በቁጭት ብንንገበገብም” አስታውሶ ማለፉ ለእኛ ለዛሬዎቹ ለእውቀትም ለጸሎትም ያግዝ ይመስለናል።
ድህረ ፋሽስት ዓመታትን ተከትሎ ብልጭ ድርግም ይል የነበረውና በኋለኛው ዘመንም ፍሬውን ገምጠን መራራ ክስተቶችን ያስተናገድንበት የፀረ ፊውዳል የአመፅ እንቅስቃሴዎች የታሪካዊ ሰንሰለት ርዝመት “ይህ ልክህ” የሚባል ዓይነት አልነበረም። ንጉሡን ለመገልበጥ የተጠነሰሰውና የከሸፈው የደጃዝማች ታከለ ወ/ሐዋርያት ግልብ ስሜት፣ የቀዳማይ ወያኔ የትምክህት እንቅስቃሴ፣ የጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ፣ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተለኩሶ ሀገሪቱን ከዳር እስከ ዳር የናጠው የእውር ድንብር የወጣቶች ተቃውሞ እና ሌሎች ያልተጠቀሱ “መርገምቶች” የሀገሪቱን እድገት የገቱና ሺህ ምንተ ሺህ የሕይወት መስዋዕትነት የተከፈለባቸው “መርገምቶቻችን” ነበሩ። ከድርቁና ከቸነፈሩ፣ በየአካባቢው ይስተዋሉ የነበሩ መቆራቆሶችን ብናክልበትማ “እግዚዮታ” ሲያንስብን ነው።
በወታደራዊው የደርግ ዘመን፣ በሴረኛውና በአልጠግብ ባዩ የኢሕአዴግ የአገዛዝ ዓመታት የተፈጸሙ ግፎችን፣ እልቂቶችንና የሀብትና የንብረት ውድመቶችን መዘርዘሩ የብዕራችንን ቀለም በእምባችን እንድናቀጥን ግድ ስለሚለን “በተከድኖ ይብሰል” ብሂል መጠቅለሉ ይበጅ ይመስለናል።
ዛሬም ቢሆን የውስጡ አበሳችንና መከራችን ለድምድማት በቅቶ በሃሌ ሉያ ዝማሬ የማሸብቡ ወግ ደርሶናል ማለት አይደለም። በተለይም በአሸባሪው ሕወሓት ከሚሉት እኩይ ቡድን የፈላጭ ቆራጭነት ፀሐይ ጠልቃ ሕዝቡ ከመዠገሮቹ ንክሻ በተላቀቀ ማግስት “ያዳቆነ ሰይጣን…” እንዲሉ በሀገሪቱ ላይ እደረሰ ያለው መከራ “ለቀባሪ የማርዳት” ያህል ስለሚያስቆጥር “በሆድ ይፍጀው” መብሰልሰልና “በእህህታ” አስታውሶ ማለፉ ይመረጣል።
ከውጭ ኃይላት ጋር ስንፋለም የኖርንባቸውንና ከሽንፈት የራቁ የድሎቻችንን ታሪክ በተመለከተ ግን እንደ ብሔራዊ መዝሙራችን በነጋ በጠባ ሁሉም ዜጋ እያንጎራጎረ የኖረበት ስለሆነ ከአድዋ ድል ጀምረን እንተርክ ብንል “የአዋጁን በጓዳ” እንዳይሆን በጥቁምታ ብቻ ማለፉ ይመረጣል።
በዚህ ሁሉ የትንታኔ ጋጋታ ሊተላለፍ የተፈለገው አንኳር መልእክት ግልጽና አጭር ነው። ኢትዮጵያን የገፉ እጅግ በርካታ የውስጥና የውጭ ክንዶች እንደነበሩ ባይካድም ጽኑዋ ሀገሬ ግን ለየትኛውም ፈተና “ገበርኩ!” ብላ ተሸንፋ አታውቅም። እንኳን ተሸንፋ ልትወድቅ ቀርቶ ተንገድግዳም ከመሠረቷ የተዛነፈችበት የታሪክ አጋጣሚ አልነበረም።
እርግጥ ነው እንደማኛውም ሀገር ምክንያቱ በቂ ይሁንም አይሁን በውስጥም ይሁን በውጭ ኃይላት ደጋግምን ተጠቅተናል፣ ተፈትነናል፣ ተቸግረናል፣ አምጠናል፣ ተስፋ እስከ መቁረጥም ተደርሶ ሊሆን ይችላል። ይህ ሁሉ መገፋት ኢትዮጵያን አጠንክሯት ካልሆነ በስተቀር ጉልበቷን አላልቶ አላብረከረካትም።
በኤሎሄ ጣሯ ውስጥ “በሃሌ ሉያ” ቅኝት ዘምራለች። በፍልሚያ ጎራ ውስጥ የድል ብስራት እያበሰረች ዓለምን አስደምማለች። በውጭ ወራሪ ጠላት አቅምና ፉከራ ተደናግጣ ቀድማ እጆቿን ለካቴና በመስጠት “ባርነትን” አላስተናገደችም። የዛሬ ወርቃማ ታሪኳ የተቀረጸው በልጆቿ የደም ማህተም ታትሞ የመሆኑ ምሥጢር ይህ ነው።
ዛሬስ!?
እንደ ትናንቱ ታሪካችን ሁሉ የዛሬዋ ጀንበራችን እያሳያችን ያለውን ብርቱ ፈተና የምንክደው አይደለም። መራራ ነው፤ ይጎመዝዛልም። የበረሃ ደም አማትቶት የተወለደው የጫካው ውላጅ ወያኔ ይሉት አበሳችን ላለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል ሀገሪቱን እንደተጣባት፣ ጦር መዞ እንዳማዘዛት፣ በንጹሐን ዜጎች የደም ግብር ዕድሜውን እንዳራዘመ፣ ከጓዳ እስከ አደባባይ በዘረፋና በማውደም ሱሱ እንደተቅበዘበዘ፣ የልማትና የእድገት ራእዩዋን ለማጨለም እንደተጋ እነሆ ከዳዴ እስከ ሽበት ዘልቆበታል።
አምጦ በወለዳቸው ብጤዎቹና አምሳያዎቹ አሸባሪዎች አማካይነት ሀገርን እንዳመሰ፣ ለታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋሻ ጃግሬ በመሆን ማሸርገዱንና ማሸበሩን ሥራዬ ብሎ ተያይዞታል። የትግራይን ሕዝብ ጋሻ፣ መሬቱን መሸሸጊያ ከማድረግ አልፎ ተርፎ ወደ ሰላማዊ ክልሎች “የእብሪት ለሀጩን በማዝረብረብ” በወረራ ልክፍት መቅበዝበዙ ተደጋግሟል። ዛሬም ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን፣ የአፋር፣ የአማራና የተቀሩት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን የልዩ ኃይልና የሚሊሽያ ተርቦች ይህንን የእኩይ ተግባራት ማሕጸን ለማምከን ተጋድሏቸውን እያፋፋሙ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ ደክማም ሆነ ታክቷት ለየትኛውም የጥፋት ኃይል ራሷን አሳልፋ ሰጥታ አታውቅም። ይህ ታሪኳም ባህሏም አይደለም። ክፉዎችና የጥፋት ኃይላት ተኝተውላታ ባያውቁም ሁሉም እየተንበረከኩ ሰገዱላት እንጂ ገፍትረው አልጣሏትም፤ ሊጥሏት ቢሞክሩም ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ይረዱታል።
ሀገር ለምን ተፈተነች አይባልም። መፈተኗ ግድ ነው። ከፈተና በኋላ እንደ ወርቅ አብረቅርቃ እንደምትወጣ ትናንት ምስክር ነው፤ ዛሬም እውነታ ነው። የገፏት አልተቋቋሟትም። የተገዳደሯትም ረትታዋት አላስገበሯትም። ብርታቷ ጀግኖች ልጆቿ ሲሆኑ ረዳቷም አምላኳ ነው።
ሕወሓት ይሉት የክፋት ጥግ ቡድን እየተመራ ያለው ሰብዓዊነት ይሉት እምነትና እውነትን በካዱ ጥቂት ሴረኞች መሆኑ ቆመንለታል ለሚሉት የትግራይ ሕዝብ ለምን ሊገለጥ እንዳልቻለ ዕንቆቅልሽ ነው። “ወያኔ ማለት ሕዝቡ ጠቅላላ ነው” እያለ ሲደሰኩርም “ተው በስማችን አትነግድ” እያሉ ለምን እንደማይገስጹትና ስማቸውን እንደማያድሱ ግራ ያጋባል።
ከወራት በፊት በወረራቸው የሀገራችን አካባቢዎች የፈጸማቸውን አረመኔያዊ ድርጊቶች በማሳያነት በማቅረብ “በቃችሁ!” ሊላቸው ግድ ነበር። ዛሬ ድርጊቱን ሲደግምም ዝም ማለታቸው አግባብ አይደለም። ይህ የእኩዮች ጥርቅም ቡድን መከራ ለማዝነብ እየሞከረ ያለው በተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ላይ አይደለም። የራሴ በሚለው የትግራይ ሕዝብም ላይ የሚያደርሰው ሰቆቃና በደል መጠንም ልክም የለውም። አልፎም ተርፎ በሰላም ተዘልሎ በተቀመጠ የጎረቤት ሀገር ኤርትራ ላይም ትንኮሳ እየፈጸመ መቅበዝበዙ የቡድኑን “ጭር ሲል ያለመውደድ” ባህርዩን በሚገባ የሚገልጽ ነው።
የመልእክታችን ማሳረጊያና መደምደሚያ ግልጽ ነው። ኢትዮጵያ ደክማ አትዝልም። ወድቃ የምትሰበር የሸክላ ስሪትም አይደለችም። ስሜታዊ ፉከራ ሳይሆን ታሪኳ የሚመሰክርላት፣ ጠላቶቿ ያረጋገጡትና ወዳጆቿ እውነት ነው በማለት የተከራከሩላት እውነታ ነው። ከሁሉም በላይ ፈጣሪዋ ክንዷ፤ ልጆቿ መከታዎቿ ናቸው።
ኢትዮጵያ እያበበች እየተዋበችና እየደመቀች ትገሰግሳለች እንጂ ፊቷ በመከራና በሽንፈት ወይባ የምትቆዝም ምስኪን አይደለችም፤ ሆናም አታውቅም። ኢትዮጵያ ለዘለዓለም በዚህ ሞገሷ ለምልማ ትኖራለች። በብርቱ ልጆቿ ክንድና በፈጣሪዋ ተራዳዒነትም በድል እንዳሸበረቀች ለዓለም ሀገራት ምሳሌ ሆና ትቀጥላለች።
ጠላቶቿም ከእግሯ ሥር ወድቀው እንደሚሰግዱ ጥርጥር አይገባንም። ምስክርነት በሦስት ስለሚጸና የውስጥና የውጭ ፈተናዋ ውበቷን አድምቆ እንደሚያወጣ እኛ የዛሬ ትውልዶች፣ የነገ ተረካቢ ምትኮችና ታሪክ ጭምር ማስረገጫ ዋቢዎቻችን ናቸው። ሰላም ይሁን!
በ(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ነሐሴ 28 /2014