ጥሩ ጦርነትና መጥፎ ሰላም የለም እንደሚባለው ጦርነት ያው ጦርነት ነው። የጦርነት ጥሩና የሰላም መጥፎ የለውም። ሁለቱም ፍጹም የሚቃረኑ ነገሮች ናቸው። በጦርነት ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት ይረግፋል፤ ሴቶች፣ ሕጻናትና አረጋውያ በብርቱ ይጎዳሉ፤ ስደት ጉስቁልና ይበረታል።
ሰዎች አካባቢያቸውን በመተው ይሰደዳሉ፤ ይራባሉ፣ ይጠማሉ፣ ይታረዛሉ። ሰላም ደግሞ በተቃራኒው ነው፤ የሰው ልጆች በጦርነት ምክንያት ያጡትን አንድ ሺ አንድ በጎ ነገሮችን ማጎናጸፍ ያስችላል። ሰላም ሲኖር ረሃብ የለም ጥጋብ ነው፤ ውሃ ጥም አይኖርም እርካታ ነው፤ ስደት ጉስቁልና የለም መረጋጋት ነው፤ ሀዘን የለም ፍስሀና ደስታ ነው።
ሰዎች በሰላም ሲኖሩ የሚያገኙትን ትርፍና ደስታ፤ በጦርነት ውስጥ ደግሞ የሚያጎድሉትን ጎደሎ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ያም ቢሆን ግን ጦርነት ይገጥማሉ። እርግጥ ነው ጦርነት የግድ የሚሆንበት ወቅት አለ። በተለይም የትኛውም አገር ቢሆን በውጭ ወራሪ ኃይል ሲደፈር ጦርነት መግጠሙ የግድ ነው። የሉዓላዊነት ጥያቄ ነውና።
ይህ አዲስ አይደለም በመላው ዓለም ያጋጠመ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያም በዚሁ የጦርነት ታሪኳ በብዙ ተፈትናለች። ወርቅ በእሳት እንደሚፈተነው ሁሉ ከጥፋት ሊያድኗት በሚችሉ እልፍ ልጆቿ ተፋልማ የማይቻል የሚመስለውን ሁሉ ችላ አሸንፋለች። ዛሬም ይህ ሊሆን የግድ ነው። ፈተናዎቿ የቱንም ያህል የበዛ ቢሆን በድል የመጣን ወራሪ ኃይል በጦርነት አሸንፎ ወደመጣበት መመለስ ለኢትዮጵያውያን አዲስ አይደለም።
‹‹ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይተውም›› እንዲሉ አበው አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ዛሬም የጦርነት ትንኮሳውን ጀምሯል። እርግጥ ነው እሱ በለኮሰው እሳት የሚለበለበው ደሃው ነው። ምንም የማያውቀው አርሶ አደር ህጻን ልጁን እንዲሰጥ ይገደዳል። እሱም ቢሆን ሞፈሩን ጥሎ መሳሪያ አንግቦ ዓላማና ግብ የሌለውን ጦርነት እንዲቀላቀል አፈሙዝ ተደቅኖበታል። ከአፈሙዙ ማምለጫ መንገድ የለውምና ነጻ አውጪ መስሎ ይቀላቀላል። አሁን በአገሪቱ ሰሜኑ ክፍል ባለው ጦርነት እየሆነ ያለው ይኸው ነው።
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን የተቀዛቀዘ ይመስል የነበረውን ጦርነት በሚያስደነግጥ ሁኔታ ህጻናትን ከፊት አሰልፎ ጀምሮታል። ቡድኑ ለሶስተኛ ጊዜ በጀመረው ጦርነት ምንም የማያውቁና ዘለው ያልጠገቡ ህጻናት ተስተውለውበታል። ህጻናትን በጦርነት ማሳተፍ የጦር ወንጀል በመሆኑ ድርጊቱ በጦር ወንጀል ህግ የሚያስጠይቀው ይሆናል። ያም ቢሆን ግን ከድርጊቱ አልተቆጠበም። ዘመን ያለፈበት የጦርነት ስልት በሆነው የሰው ማዕበል ተጠቅሞ ህጻናቱን የጥይት እራት እያደረጋቸው ይገኛል።
ቡድኑ የትግራይን ህዝብ መያዣ በማድረግ ወደ ለየለት ጥፋት እየተንደረደረ ቢሆንም ቆም ብሎ ማሰብ ከሁሉም ይጠበቃል። በተለይም የጦርነቱን አስከፊነት ለመረዳት ጊዜው አሁን ይመስላል። ምክንያቱም አሸባሪው የሕወሓት ቡድን እንደቀደመው ጊዜ ሁሉ ፈላጭ ቆራጭ መሆን አይችልም። ለበርካታ ዓመታት ተቆጣጥሮት የነበረው በትረ ስልጣን በህዝቦች ትግል ከእጁ ወጥቷል። ይህን አምኖ መቀበል አልቻለም። ‹‹ባልበላውም ጭሬ ልበትነው›› እንዳለችው ዶሮ የህዝቦችን አንድነትና ሰላም መያዣ በማድረግ የውር ድንብር ጉዞውን መጀመሩም ለዚሁ ነው።
ታድያ የዚህን የጥፋት ቡድን እኩይ ተግባር ከመረዳትም በላይ መረዳት ዛሬ ያስፈልጋል። ሕወሓት መቼም ቢሆን የዚህች አገር ፈላጭ ቆራጭ እንዲሆን የሚፈቅድለት ህዝብ የለም። ይህ ሊሆን እንደማይችል ደግሞ እሱም ያውቀዋል። ዳሩ አሁን ላይ በህዝብ ማዕበል ውስጥ ሆኖ ትግሉን ፈታኝ ቢያደርገውም ጽዋው ሞልቶ መፍሰሱ አይቀርም።
ያኔ ታድያ ከኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም ከትግራይ ህዝብ ጫንቃ ሳይወድ በግዱ ይወርዳል። ለዚህ ድል መብቃት የሚቻለው ታድያ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በአንድነት መቆም ሲችል ነው። አንድነት ኃይል ነው እንደሚባለው፤ ህዝብ በአንድ ልብ አስቦ አንድ ቃል መናገር ከቻለ የማይወጣው ተራራ የማይፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም።
ድፍን ሁለት ዓመታትን ሊያስቆጥር ምንም ያህል ያልቀረው ይህ ጦርነት ቡድኑን በሚደግፉ የውጭ ኃይሎች ድጋፍ መራዘሙ ዕሙን ነው። በጥቂት አምባገነኖችና ስግብግብ ስልጣን ፈላጊ ግለሰቦች ምክንያት አገር ምጧ ሲበረታ ሊያጠቋት የከጀሉ ብዙዎች ናቸው። በምጧ መርዘም የሚሰቃዩት ዜጎቿም የቸገረ ነገር ሆኖባቸዋል።
ቡድኑ የትግራይን ህዝብ መያዣ ከማድረግ ባለፈ መሸሸጊያ ጥላ ማድረጉ የጦርነቱን መቋጫ ቢያራዝመው እንጂ ድሉን አያስቀረውም። ያም ቢሆን ግን በጦርነቱ አካባቢም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ያለው ህዝባችን በአንድነት ሆኖ ከመንግሥት ጎን ሠራዊቱን መደገፍና በጦርነቱ ምክንያት መከራን እየገፉ ያሉ ንጹሃንን መታደግ ያስፈልጋል።
እርግጥ ነው የጦርነት መፍትሔው ጦርነት ብቻ አይሆንም። አጥፊና አውዳሚ የሆነውን ጦርነት ወደ ጎን በመተው ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ተነጋግሮ መፍታት ይቻላል። ዳሩ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በሰላማዊ መንገድ ተነጋግሮ የሚፈታው ችግር የለውም። አሸባሪ ደግሞ ከስሙ እንደምንረዳው ዓላማው ያው ማሸበር ነው።
ጦርነቱ መቋጫ እንዲያገኝና ሰላማዊ መፍትሔ ለማምጣት ንግግር ወሳኝ ነው። ስለሆነም የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከሰሞኑ ለሶስተኛ ጊዜ ያገረሸው ጦርነት እንዲቆም መጠየቁም ለዚሁ ነው። ኮሚሽኑ በጠላትነት መተያየት እንዲያቆምና በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ ለማምጣት ንግግር እንዲጀመር ጠይቋል።
መንግሥት በተደጋጋሚ ያቀረበውን የሰላም ጥሪ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ቢገፋውም ዳግም ማስታወሱ አይከፋም። ለዚህም የሲቪል ማህበራት፣ የመገናኛ ብዙሃን፣ የሃይማኖት መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች ከመንግሥት ያላነሰ ድርሻ አላቸው። ጦርነቱ እንዲቆም ካለፈው ጊዜ በበለጠ ዛሬ ሊተጉ ይገባል። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ጦረኛውን ሕወሓት በማውገዝ ሰላም እንዲመጣ የበዛ ጥረት ሊያደርግ ይገባል። ያን ጊዜ ሩቅ የመሰለው ይቀርባል፤ የጦርነቱ መቋጫም ሰላም ይሆናል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 28 /2014