ሁለተኛው የ 2022 የወጣቶች አመራር ጉባኤና ውድድር ‹‹ድምፄ ለግድቤ›› በሚል መሪ ቃል ሴፍ ላይት ኢኒሺዬቲቭ በተሰኘ ድርጅት አዘጋጅነት ከኢፌዴሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለሶስት ተከታታይ ቀናት አካሂዷል::
የወጣቶች አመራር ጉባኤና ውድድር ዋና አላማ እየመጡ ያሉ አዳዲስ ወጣት አመራሮችን በህዝብ ፊት ንግግር ክህሎት፣ በድርድር፣ ዲፕሎማሲና የፖለቲካ አስተሳሰብ ብቃት ማገዝ ነው:: የዘንድሮው ደግሞ የወጣቶችን የአመራር ክህሎት በቀጠናዊ፣ በአህጉራዊና በአለም አቀፍ ደረጃ ለማዳበር ታስቦ ተዘጋጅቷል::
በሴፍ ላይት ኢንሼቲቭ የአለም አቀፍ ግንኙነት ሃላፊ አምባሳደር ምህረት ህሩይ እንደሚያብራሩት ሴፍ ላይት ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ሲሆን እ.ኤ.አ ከ2018 ጀምሮ በወጣቶች ላይ ሲሰራ ቆይቷል:: በተለይ ደግሞ አዳዲስ እየመጡ ያሉ ወጣት ዲፕሎማቶችን ማውጣት ላይ ስራዎችን ይሰራል:: እስካሁንም በርካታ ወጣቶችን አሰልጥኗል:: ለዚህም ‹‹3 H›› የተሰኘ አካሄድ ይከተላል::
ይህም ጭንቅላት/Head/ ወይም ደግሞ አመለካከት ላይ ወጣቶች በአእምሮ የዳበረና እውቀት ያለው የአመራር ጥበብን እንዲላበሱ ስልጠናዎች እንዲሰጣቸው ይደረጋል:: ልብ /Heart/ ላይ ወጣቱ አስተሳሰቡ ተቀይሮ በልቡም እንዲቀየር ባህሪ የመገንባት ስራዎች ይሰራል:: ለአብነትም ወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶችን እንዲሰጡና ከልብ የመነጨና ትክክለኛ ባህርይ ብሎም የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያሳዩ ይደረጋል:: እጅ /Hand/ በተሰኘው አካሄድ ደግሞ ድርጅቱ በአእምሮና በልባቸው የተቀየሩ ወጣቶች እጃቸው እንዲዘረጋና እንዲሰራ ወይም ድጋፍ እንዲያደርግ ስራ ፈጠራና ከህሎት ላይ ይሰራል:: ዲፕሎማሲና ትምህርት ላይም ተመሳሳይ ስራዎች ይሰራሉ::
እንደ ሃላፊዋ ገለፃ የወጣቶች አመራር ኮንፍረንስና ውድድር አምና የተጀመረ ሲሆን ሀገርኛና ሀገርን በሚያስተዋውቁ ስራዎች ላይ በይበልጥ ያተኮረ ነበር:: በዚህ የመጀመሪያ ኮንፍረንስ ወጣቱ ሀገሩን ማስተዋወቅ እንዲለማመድ ታሳቢ በማድረግ ከ120 በላይ ወጣቶች እንዲሳተፉ ተደርጓል:: በዚህ ኮንፍረንስም በሁሉም የአዲስ አበባ ከተማ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ወጣቶች ተመርጠው እንዲካፈሉ ሆኗል::
ወጣቶቹ በጤና፣ ትምህርት፣ የህዝብ አገልግሎትና ቢዝነስ ዘርፎች ገብተው እንዲወዳደሩና የተሻሉ የመፍትሄ ሃሳቦችን በየሴክተሩ እንዲያመጡ ከተደረገ በኋላ በሁለተኛው የወጣቶች አመራር ኮንፍረንስና ውድድር በአንክሮ ማሰብ፣ በህዝብ ፊት የመናገር ክህሎት፣ በዲፕሎማሲ ሰላማዊ ንግግርና አመራርን እንዲለማመዱ መድረኩ ተዘጋጅቷል:: ይህም የሚሆነው ወጣቶቹ በቅድሚያ ከወራት በፊት ምዝገባ አካሂደው ከሴፍ ላይት ኢኒሺዬቲቭ ጋር እንዲሰሩና እንዲያጠኑ ከተደረገ በኋላ ነው::
ይህንኑ መሰረት በማድረግ ‹‹ድምፄ ለግድቤ›› በሚል መሪ ቃል በተለይ ወጣቶች የአፍሪካን መፍትሄ በአፍሪካ ወጣቶች እንዲሆን በማሰብ አፍሪካ ህብረትን በአንደኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፀጥታውን ደግሞ በሁለተኛው ኮሚቴ ውስጥ በማድረግ ሁለተኛው የወጣቶች አመራር ኮንፍረንስና ውድድር በአዲስ አበባ ተካሂዷል::
የአባይ ጉዳይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ድረስ ሄዶ ስለነበር ወጣቶቹ በዚህ ምክር ቤት የታላቁ ህዳሴ ግድብን በሚመለከት ሀሳባቸውን ለማንጸባረቅ እንዲያስችላቸው በኮሚቴው ውስጥ ልምምድ ያደርጋሉ::
በአፍሪካ ህብረት ኮሚቴ ውስጥ ያሉት ደግሞ የአፍሪካ ሀገራትን ወክለው ሃሳባቸውን ያቀርባሉ:: አፍሪካውያን ወጣቶች ሀገራቸውን ወክለው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ጥናት አድርገው ፅሁፍ እንዲያስገቡ ከተደረገ በኋላ በኮንፍረንሱ ላይ ክርክር እያካሄዱ ለታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የመፍትሄ ሀሳብ አቅርበዋል:: ሴፍ ላይት ኢኒሺዬቲቭ ደግሞ ይህን የመፍትሄ ሀሳብ በአንድ ጨምቆ ለሚመለከተው አካል ሰጥቷል::
ከዚህ በፊት የተካሄደው የወጣቶች አመራር ኮንፍረንስና ውድድር ወጣቶች የአመራር ብቃት ማደግ ላይ የራሱን አስተዋፅኦ በማድረጉ በርካታ ወጣቶች ከሴፍ ላይት ኢኒሺዬቲቭ ጋር በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ:: አብዛኛዎቹ ደግሞ ገና በትምህርት ገበታቸው ላይ እያሉ በተለያዩ የአመራርነት ቦታዎች ላይ ገብተው መስራት ችለዋል:: በውስጣቸው ያለውን እምቅ የአመራርነት ክህሎት እንዲያወጡም አስችሏቸዋል::
ይህ ኮንፍረንስ የሚዘጋጀው ወጣቶች የአመራር ብቃታቸውን አስቀድመው እንዲያዳብሩ ለማስቻል ብቻ ሳይሆኑ ብቃቱ ያላቸውን ወጣቶችን ለመሰብሰብ በመሆኑ በሴፍ ላይን ኢኒሺዬቲቭ ውስጥም ሆነ በሌሎች ተቋማት ገብተው በአመራርነት እየሰሩ የሚገኙ ወጣቶች አሉ:: ፕሮግራሙ ሲዘጋጅ በማስተባበር ሲሰሩ የቆዩ ወጣቶችም ነበሩ::
ባለፈው ዓመት ኮንፍረንስ ላይ የነበሩ ወጣቶችንም በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ቤት ለትምህርት ቤት አምባሰደር በማድረግ ይህንኑ እንዲለማመዱ እየተደረገ ይገኛል:: በቀጣይም በአዲስ አበባ ከተማ ባሉ ሁሉም የግልና የመንግስት ትምህርት ቤቶች ሞዴል የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ማቋቋምና ይህንንም ደግሞ በየትምህርት ቤቶቹ ላይ ራሳቸው ተማሪዎች እንዲተገብሩት ይደረጋል::
ለአብነትም ወጣቶቹ በሴፍ ላይት ኢኒሼዬቲቭና በትምህርት ቤቶች መካከል ድልድይ ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ:: መምህራንና ርእሰ መምህራንን አማክረው የጋራ መግባቢያ ስምምነት አስፈርመው ክለብ ያቋቋሙ ወጣቶችም አሉ::
ሃላፊዋ እንደሚገልፁት በዚህ የአመራር ጉባኤና ውድድር የሚሳተፉ ወጣቶች እድሜያቸው ከ24 እስከ 30 ያሉ ቢሆንም አንዳንዴ እስከ 35 ዓመት ያሉም እንዲሳተፉ ይደረጋል :: ወጣቶቹ በጉባኤው እንዲሳተፉ የሚደረገው አንድም በእንዲህ ዓይነቱ መድረክ ላይ የሚሳተፉትን ለመመልመል በሌላ በኩልም ማንኛውም በአመራር ጉባኤና ውድድር ላይ መሳተፍና በዲፕሎማሲ ላይ መስራት የሚፈልግ ወጣት ሴፍ ላይት ኢኒሺዬቲቭ ጋር ሄዶ በመመዝገብ ነው:: ለዚህም ድርጅቱ ዩኒቨርሲቲዎች ድረስ በመሄድ ወጣቶች በአመራርና በዲፕሎማሲ ጉባኤ ላይ እንዲሳተፉ እያደረገ እግረመንገዱንም ራእዩን እያስተዋወቀ ይገኛል::
ወጣቱ የሀገሪቷ እምቅ ሃብት ያለው በመሆኑ በቅድሚያ ትምህርት በመስጠት፣ በየትምህርት ቤቶች በመሄድና የድርጅቱን ራእይ በማስተዋወቅ ወጣቶቹ እንዲቀላቀሉ ይደረጋል:: ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ደግሞ ተመዝግበው እንዲህ ዓይነቱን ኮንፍረንስ እንዲሳተፉ ይደረጋል::
በቀጣይም እንደ ሴፍ ላይት ኢኒሺዬቲቭ ድርጅቱን ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያውያን ወጣቶችንና የተለያዩ ሀገራት ወጣቶች መካከል ድልድይ ሆኖ የመስራት ፍላጎት አለ:: በተለያዩ ሀገራት ያሉ ወጣቶችን ወደ ኢትዮጵያ ማምጣትና ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ የሀገሪቷን በጎ ገፅታ የመገንባት ስራ ይከናወናል::
በሴፍ ላይት ኢኒሺዬቲቭ በትንሹ የተጀመረው ስራ አሁን አድጎ ከፌዴራል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር ጋር በመተባበር እየሰራ ነው:: ሁሉንም ክልሎች ያካተተ ነው:: በቀጣይ ደግሞ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ስራዎች የሚሰሩ ይሆናል::
በሴፍ ላይት ኢኒሺዬቲቭ የኮሚዩኒኬሽን ሃላፊ አቶ ስምኦን ጌትነት እንደሚናገሩት ድርጅቱ በቅድሚያ ወጣቶች ቀና እንዲያስቡ ስልጠናዎችን ይሰጣል፤ ልምድም ያካፍላል:: በመቀጠል ደግሞ በወጣቶች እችላለሁ ወይም አደርጋለሁ የሚለውን ፅንሰ ሃሳብ እንዲይዙ በአስተሳሰብ ለውጥ ላይ ይሰራል:: በኋላ ላይ ደግሞ ወጣቶች የተለያዩ ክህሎቶችን ለማዳበር በሚያስችሏቸው ጉዳዮች ላይ ይሰራል::
ድርጅቱ እነዚህን ስራዎች ሲሰራ የሶስት፣ አስርና የሰላሳ ዓመት እቅዶችን ይዞ ሲሆን በአሁኑ ግዜ ግን በአብዛኛው ትኩረቱን አድርጎ እየሰራ ያለው አመራርነት ላይ ነው:: በመቀጠልም ወጣቶች የስራ ቅጥር ላይ እንዳይቸገሩና በስራ ቅጥር ልምዳቸውን እንዲያዳብሩ ስራዎችን ይሰራል::
ወጣቶች ወደ ስራው አለም ለመቀላቀል የሚያስችሉ መንገዶችንም ድርጅቱ ያመላክታል:: አዳዲስ ተመራቂ ወጣቶች ያላቸውን ብቃት ተረድተው በየትኛው መስክ ላይ መስራት እንደሚችሉና ራን መግለጫ (ሲቪ) እንዲፅፉ ያግዛል:: ከወጣቶች ጋር አንድ ላይ ለመስራት የሚያስችሉ ስልጠናዎችም ይሰጣሉ::
ለአብነትም የእንጨት ስራ ስልጠናን መጠቀስ ይቻላል:: የራሳቸውን ቢዝነስ እንዲጀምሩም የስራ ፈጠራ ስልጠናዎችንም ይሰጣል:: በተመሳሳይ ዲጂታል ትምህርት ላይም ድርጅቱ ለወጣቶች ስልጠና ይሰጣል::
ወጣቶች እነዚህ ስልጠናዎችና የክህሎት ትምህርት የሚያገኙት በድርጅቱ ማህበራዊ ድረገፅ http://www.safelightet.org/ እና የፌስቡክ አድራሻ ላይ የሚወጡ መረጃዎችን በማየትና በአካል የድርጅቱ ቢሮ በመሄድ በመመዝገብ ነው::
ድርጅቱ ለትርፍ ያለተቋቋመ ቢሆንም ትርፍ ላልሆነ ፕሮጀክቱ ፈንድ መጠየቅ እንጂ በራሱ ማሰባሰብ የማይችል በመሆኑና በዚህም እየተቸገረ በመሆኑ መንግስት ሲፈቅድ በቀጣይ ወደ ትርፍ መስራቱ የሚገባ ይሆናል::
የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደሚገልፁት የኢትዮጵያ ወጣቶች ፖሊሲ ወጣቱ አገራዊ አንድነት እንዲያመጣ፣ የክፍለ አህጉራዊ፣ አህጉራዊና አለም አቀፍ ግንኙነትና አጋርነትን በመፍጠር የወጣቶች ሁለንተናዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ በትብብር እና በመተሳሰብ ለወጣቶች ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንዲቻል ተደርጎ ተቀርጿል::
መንግስትም ወጣቶችን በሰላም ሂደት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ፣ የሰላም አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች ሆነው ለቀጠናዊ፣ ለሀገር አቀፍ እና ለአለም አቀፍ ሰላም፣ ልማት እና ብልፅግና አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
በሴፍ ላይት ኢኒሺዬቲቭ የተጀመረው የወጣቶች የአመራር ኮንፍረንስና ውድድርም ወጣቶች ራሳቸውን ለተለያዩ ፈተናዎችና ድሎች እንዲያዘጋጁ ፣ ራሳቸውን እንዲያበረታቱ ፣ እንዲወዳደሩ ፣የሌላውን አመለካከት እንዲያከብሩና የመሪነትን ባህሪን እንዲያዳብሩ የሚያስችል በመሆኑ ፋይዳው የጎላ ነው::
የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ክብርት ሙና አህመድ በበኩላቸው እንደሚሉት የወጣቶች የአመራር ክህሎት ውድድርና ኮንፈረንስ የኢትዮጵያን የወደፊት መሪዎች በአለም አቀፍ እና አህጉራዊ መድረክ ላይ በእውቀትና በበሳል የአመራር ጥበብ እንዲያድጉ መሰረት ይጥላል ።
ኮንፈረንሱ ወጣት መሪዎች ወደፊት የሀገርን ጥቅም ለማስከበርና ሀሳባቸውን በአለም አቀፍ ደረጃ በነፃነት እንዲገልጹ ያስችላቸዋል:: በተለይም ኮንፍረንሱ ወጣቶች በአመራር ረገድ ያላቸውን እውቀት እንዲያዳብሩና በቀጣይ ለሚኖራቸው ሃላፊነት አገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ወዳጅነትን ለመፍጠርና ብሄራዊ ጥቅምን ለማስከበር የላቀ ሚና ይኖረዋል::
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 27 /2014