አዲስ አበባ፡- ባለፈው አንድ ዓመት በተለይ በውጭ ግንኙነት ረገድ የተከናወኑ ስኬታማ ተግባራትን ቀጣይ ለማድረግ የዲፕሎማቶችን አቅም ይበልጥ ማጎልበትና ምደባቸውም ብቃትን መሰረት ያደረገ ሊሆን እንደሚገባ ተጠየቀ።
ከአዲስ ዘመን ጋር ቆይታ ያደረጉት የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እንደገለፁት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ባለፈው አንድ ዓመት ከፍተኛ ልዩነት ከፈጠሩባቸው ጉዳዮች አንዱ የዲፕሎማሲ መስክ ነው። በተለይ ኤርትራን ያለሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት በሰላም በማቀፍ የቆየውን ልዩነት በማፍረስ ሰላማዊ ግንኙነት እንዲመሰረት ማድረጋቸው የሚደነቅ ነው።
ይህን ስኬት ቀጣይ ለማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች ዋነኛ ተዋናይ የሆነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተሻለ መልኩ በእውቀትም በልምድም መጎልበት እንደሚገባው አፅንኦት የሰጡት ፕሮፌሰር መረራ፤ «በየአገሩ የሚመደቡ ዲፕሎማቶችም በድርጅት ኮታ የሚመደቡና ለገዥው ፓርቲ የሚታመኑ ሳይሆን የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ሊያስከብር በሚችል እውቅትና ችሎታ እንዲሁም ለአገር ባላቸው ታማኝነት መመስረት ሊመደቡ ይገባል» ሲሉ ገልፀዋል።
የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሥልጠናና የማማከር ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዋቅጋሪ ነገሪ፤ ባለፈው አንድ ዓመት ዶክተር ዐብይ ከተለያዩ አገራት ጋር በፈጠሩት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ኢትዮጵያ አንገቷን ቀና እንድታደርግና በሁለት እግሯ ቆማ እንድትታይ ማድረግ መቻላቸውን አብራርተዋል።
ከሁሉ በላይ ጎረቤት አገራትን ወደ ሰላም ለማቅረብ ጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ እንዲሁም ደቡብና ሰሜን ሱዳንን ለማስማማት በአሸማጋይነት በመሳተፍ የቀጣናው የህዝብ ቁርኝት በዘመናዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠብቅ ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት በሄዱባቸው ቦታዎችም እስር ላይ የነበሩ ኢትዮጵያውያን እስረኞችን በማስፈታት ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ ማድረጋቸውም ትልቅ ስኬት መሆኑ ሊዘነጋ እንደማይገባው አፅንኦት የሚሰጡት ዶክተር ዋቅጋሪ፤ «ተግባሩ ዜጎችን ማስቀደምና ለሰው ልጅ ክብር መስጠትን ያሳያል፤ አንድ የአገር መሪ መሰረቱም ሆነ የሚያገለግለው ህዝብን ስለመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከሁሉ በፊት ህዝብ የሚል መርህ እንዳላቸው ምስክር ይሰጣል» ብለዋል።
ይህን ስኬት ቀጣይ ለማድረግ የዲፕሎማሲው ተግባራት የሚከታተሉና የሚቆጣጠሩ፤ ወጥና የተሰናሰለ ሥርዓት መገንባት እንደሚያስፈልግ ያመላከቱት ዶክተር ዋቅጋሪ፤ በዲፕሎማሲው መስክ የሚመደቡ ዲፕሎማቶችም አገሪቱ ልትደርስበት ያስቀመጠችውን ከፍታና ግብ ማሳካት በሚያስችል መልኩ ይበልጥ በብቃታቸው የሚመረጡ ሊሆኑ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ከቀናት በፊት በወቅታዊ አገራዊና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት፤ በአንድ ዓመት የሥልጣን ቆይታቸው ከፍተኛ ልዩነት ከፈጠሩባቸው ጉዳዮች አንዱ የውጭ ግንኙነት ስለመሆኑ መመስከራቸው ይታወሳል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2011
በ ታምራት ተስፋዬ