አዲስ አበባ፡- ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት የዜጎች መፈናቀልና የፀጥታ መደፍረስ ችግሮች ጎልተው በመምጣታቸው ለአገሪቱ ሰላም መረጋገጥ ከመንግሥት ጋር በመሆን እንደሚሠሩ የኦሮሞ ዴሞክራሲ ግንባርና የአረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት ፓርቲዎች አስታወቁ።
የኦሮሞ ዴሞክራሲ ግንባር ፕሬዚዳንት አቶ ሌንጮ ለታ በተለይም ለአዲስ ዘመን እን ደገለፁት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ ወደሥልጣን በመጡባቸው የመጀመሪያ ወራት በአገሪቱ አንፃራዊ ሰላም ታይቷል። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭትና የህዝብ መፈናቀል በመታየቱ መጠነኛ የሰላም መድፍረስ ተከስቷል። በመሆኑም ፓርቲው የአገሪቱን ሰላም ለማረጋገጥ ከመንግ ሥት ጎን ሆኖ ይሠራል።
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለፃ፤ በአንድ አገር ውስጥ ለውጥ ሲመጣ የፀጥታ መደፍረስ ሁሌም የሚከሰትና የሚጠበቅ ነው። በኢትዮጵያ ደግሞ ህዝቡ ለረጅም ዓመታት በብሶት ውስጥ የቆየ ከመሆኑ አኳያ ሰላም መደፍረሱ ሊደንቅ የሚገባ ጉዳይ አይደለም። ህዝቡ ህግ አክባሪ፣ ጨዋና ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው በመሆኑም የሰላሙ መናጋት እምብዛም አደጋ ላይ አልጣለውም።
በአሁኑ ወቅት የሚታየው የሰላም ሁኔታ ከቁጥጥር ውጪ የወጣ እንዳልሆነና በቀላሉ ማረጋጋት እንደሚቻል የገለፁት ፕሬዚዳንቱ፤ ለዚህም የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል። ፓርቲያቸው ከኦሮሞ ዴሞክራሲ ያዊ ፓርቲ ጋር ለመዋሃድ ከውሳኔ ላይ መድረሱን የጠቆሙት አቶ ሌንጮ፣ በቀጣይም በፀጥታና በሰላም ጉዳዮች ዙሪያ ከፓርቲው ጋር በትብብር እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
የአረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ እንደገለፁት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ አብዛኛው ህዝብ ለውጡን ሲደግፍ ቆይቷል። ይሁንና ህዝቡ የመጣውን ለውጥ በተጨባጭ መጠየቅ በመጀመሩና ተግባራዊ እንዲሆን በመሻቱ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ግጭቶችና መፈናቀሎች እንዲሁም የፀጥታ መደፍረሶች ተከስተዋል። ይህም ሊሆን የቻለው በኢህአዴግ ፓርቲ ውስጥ ያለመግባባት በመኖሩና ሁሉም ወደየራሱ ብሔር እየገባና ፉክክር የያዘ በመሆኑ ነው።
እንደ ሊቀመንበሩ ገለፃ፤ ለአገሪቷ ሰላም መረጋገጥ ሁሉም ኃላፊነት አለበት። በተለይም ሁሉም የመንግሥት አካላት ህገ መንግሥታዊ ሥርዓትንና ፀጥታን የማስከብር ግዴታ አለባቸው። በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የቁጥጥር ሥርዓቱን ማጠናከርና ህዝቡም በመንግሥት ላይ ተስፋና እምነት እንዲኖረው ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ፓርቲያቸው ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ለሰላም መሆኑንም ሊቀመንበሩ ገልፀው፤ የህዝብ ህልውና እንዲጠበቅ፣ በአገሪቱ መረጋጋት እንዲሰፍንና ዴሞክራሲ እንዲረጋገጥ በጋራ እንደሚሠራም ጠቁመዋል።
በቅርቡ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ‹‹አዲስ ወግ›› በሚል ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ‹‹የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና ማፅናት በኢትዮጵያ ተግዳሮቶችና ቀጣይ አካሄዶች›› በሚል ርእሰ ጉዳይ ላይ ሁለቱ ፓርቲዎች ሃሳባቸውን መግለፃቸው ይታወሳል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2011
በአስናቀ ፀጋዬ