የዛሬው ንባባችን ወደ ኪነጥበቡ፣ በተለይም ወደ ትያትሩ አለም ያዘነበለ ነው። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ዛሬ የምናስታውሰው ባለውለታችን ሙያዊ ማንነት በርእሳችን እንደገለፅነው መሆኑና በዚሁ ዘርፍ አንቱ የተባለ ባለሙያ መሆኑ ነው።
እንደማንኛውም ዘርፍ በኪነጥበቡ አለም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉ አንጋፎች ያሉ ሲሆን አንዱም ትያትርን ሕይወቱ አድርጎ ያለፈ፣ ራሱን ለሙያው አሳልፎ የሰጠ፤ ለ50 ዓመታት ለኢትዮጵያ ትያትር የጀርባ አጥንት ሆኖ የቆየ፣ በኢትዮጵያ ኪነጥበብ ታሪክ ውስጥ አሻራውን ያሳረፈ፤ በሙዚቃዊ ትያትር ዘርፍ ፈር ቀዳጅ ስራዎችን ወደ መድረክ ያመጣ፣ ታሪካዊ ትያትሮችን የሚገባቸውን ደረጃ ሰጥቶ የሚሰራ ( “ቴዎድሮስ”፣ ከስድስት ዓመት በሁዋላ ለመድረክ ያበቃው “አሉላ አባ ነጋ” እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሳተፉበት፣ የ”አድዋ”ን የክተት ዘመቻ የሚያሳይ እና በአዲስ አበባ መንገዶች ላይ ያቀረበው ትርኢት ይጠቀሱለታል) የተባለለት፣ በአባቱ ስም “መኩሪያ ቲያትር” መጽሔት ለህትመት የበቃለት፤ ሙያውን ሰርቶ ሳይጠግብ እድል በመነፈጉ “መድረክ እንዳላገኝ ተደርጌያለሁ” በማለት ብሶቱን ሲያሰማ የነበረው፤ ከማንም ጋር መግባባት የሚችለው … መራሄ-ተውኔት አባተ መኩሪያ ነው።
በብዙዎቻችን ”ጋሽ አባተ” በሚል ማህበራዊ ማእረግ የሚጠራው አባተ መኩሪያ ትያትር ሙያው የነበረ ሲሆን፤ ከባለ ሙያነት ባለፈም ለዘርፉ ልማት ከፍተኛ መስዋእትነትን የከፈለ፤ በዘርፉ በርካታ ስመ ጥር ባለ ሙያዎችን ያፈራና በሙያው አገሩን ለአለም ያስተዋወቀ፤ ሲበዛ ብርቱና በሚዲያው ዘርፍም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከተ አንጋፋ ባለውለታ ነው። (በጋሽ አባተ አማካኝነት 5ኛው የምስራቅ አፍሪካ የኪነጥበባት ፌስቲቫል እዚህ ኢትዮጵያ ሲካሄድ ይህ ጸሐፊ ከእሱ ጋር ለወራት (ካሳንችስ በነበረው ቢሮው) አብሮ የመስራት እድል ገጥሞት የነበረ በመሆኑ እነዚህን የጋሽ አባተን መለያዎች በቅርብ ተመልክቷል።)
ጥበብ የባተው አዘጋጅ፣ የውዝዋዜ አሠልጣኝ (ኬሪዮግራፈር)፣ ጸሐፌ ተውኔት፣ የፊልም አዘጋጅ የነበረው አባተ መኩሪያ በአገሪቱ የቴአትር ታሪክ ውስጥ ስማቸው በግዙፍ ከሚነሱትና አሻራቸውን ካሳረፉት መካከል አንዱ ነበር። በተለይ በተውኔት አዘጋጅነት ስመ ጥር ለመሆኑ ዘመን ተሻጋሪ ስራዎቹ ይመሰክራሉ።
በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ አገራት (ጀርመን፣ እንግሊዝ፣ አየርላንድ፣ አሜሪካ …) የትያትርና ሌሎች የጥበብ ስራዎች አዘገጃጀትን የቀሰመው፤ በተለያዩ አገራትም ትምህርታዊ ጉዞዎችን ያደረገው ጋሽ አባተ፤ ከሥራዎቹ መካከል ሀሁ በስድስት ወር (1966) አቡጊዳ ቀይሶ (1971)፣ መልእክተ ወዛደር (1971)፣ የመንታ እናት (1971)፣ መቅድም (1972)፣ ጋሞ (1973)፣ አሉላ አባነጋ (1979) ይጠቀሳሉ። (ብዙዎቹ አባተ ያዘጋጃቸው ተውኔቶች በሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን የተደረሱ ሲሆኑ ታሪክ ጠቃሽና ረዣዥም ቃለ ተውኔት ናቸው።)
በወርልድ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦፍ ኮንቴምፖራሪ ቴአትር እንደተገለጸው፣ አባተ ተውኔት ተመልካቹን በግሩም ሁኔታ መቆጣጠር የሚያስችል ክሂል ነበረው። በጸጋዬ የተተረጐሙት የዊልያም ሼክስፒር ማክቤዝ፣ ኦቴሎና ሐምሌት በታዳሚው ትውስታ ውስጥ የቃለ ተውኔቱ (ግጥም) ውበት ብቻ ሳይሆን፣ ተውኔታዊ ክዋኔዎች እንዲታወሱ የሆነው በአባተ መኩሪያ የአዘገጃጀት ስምረት ነው።
ራሱ ደርሶ ራሱ ያዘጋጀው ‹‹የሊስትሮ ኦፔራ›› (1982) በወቅታዊ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የተመሠረተ፤ በሙዚቃ የታጀበ ሥራው ለዓለም አቀፍ ሽልማት ያበቃው ጸሐፌ ተውኔት አባተ በኢትዮጵያ የተውኔት ታሪክ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፈው የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤን ‹‹አፋጀሽኝ›› ዳግም የመድረክ ብርሃን እንዲያይ ያደረገው እሱ መሆኑን ያስነበበን ደግሞ ጎልጉል ድረ ገፅ ነው።
በዩኔስኮ አፍሪካዊ ተውኔትን በደብሊን አቤይ ቴአትር እንዲያዘጋጅ የተመረጠው አባተ፣ የጸጋዬ ገብረ መድኅንን “Oda Oak Oracle” (የዋርካው ሥር ንግርት) ማዘጋጀቱን፤ ከእንግሊዛዊው ዕውቅ የቴአትር አዘጋጅ ሰር ፒተር ሆል ጋር በኮንቬንት ጋርደን ኦቴሎን ለማዘጋጀት ዕድል ማግኘቱን፤ መቀመጫውን በታንዛኒያ ያደረገውን የምሥራቅ አፍሪካ ቴአትር ኢንስቲትዩት በመሥራች አባልነትና በኃላፊነት ከመምራቱም ባሻገር፣ በአዲስ አበባ የመኩሪያ ቴአትር ስቱዲዮና መዝናኛ የተሰኘ ተቋምን መሥርቶ ‹‹ቴአትር ለልማት›› የሚባለውን የተውኔት አቀራረብ ፈለግ መሠረት በማድረግ ብዙ ትምህርት ሰጪ ተውኔቶችን በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ተመሥርተው በማዘጋጀት ለመድረክ አብቅቷል።
ለመድረክ ካበቃቸው ተውኔቶች መካከል ሕሊና፣ ጠለፋ፣ ጆሮ ዳባ፣ በሐምሌ ጨረቃ ጉዞ፣ ድንቅ ሴት ሲጠቀሱ ከዘጋቢ ፊልሞችም የፍትሕ ፍለጋ እና የመስከረም ጥቃት የመሳሰሉት እንደሚገኙበት፤ መኩሪያ ስቱዲዮ በየክልሉና በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ አማተር ከያንያን የቴአትር፣ የሰርከስና የሙዚቃ ሥልጠና መስጠቱን፣ ከኢትዮጵያ ውጪም ወደ ተለያዩ አገሮች እየተጓዘ ትርኢት ማቅረቡን … ድረ-ገፁ ይነግረናል።
ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪውን በእንግሊዘኛና በንኡስ ትምህርት (ማይነር) ድራማን በማጥናት ያገኘው ጋሽ አባተ (ሰኔ 1998 ዓ.ም ታትሞ የወጣው “መኩሪያ ቲአትር” መጽሔት የእንግሊዘኛ ቋንቋን በማጥናት ላይ እንዳሉ ዶ/ር ፊሊፕ በሚባለ የውጭ ዜጋ አማካኝነት “ኪነጥበብ ወ ቲያትር” የሚባል ክፍል ተቋቋመ እና የመጀመሪያው ተማሪ በመሆን ወደዚያ ተዛወሩ::” በማለት ማስፈሩ ይጠቀሳልና ወደ ፊት ይጠራል ብለን እንጠብቃለን)
አባተ መኩርያ በከተማ ጭብጦችና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ተወስኖ የቀረ ምሁር አይደለም። እንደ ዘመነኞቹ (ተስፋዬ ገሠሠ፣ አፈወርቅ ተክሌ፣ ገብረክርስቶስ ደስታ፣ መንግሥቱ ለማ፣ ዮሐንስ አድማሱ፣ ፀጋዬ ገ/መድህን፣ ዳኛቸው ወርቁ እና ሌሎችም) ሁሉ ታሪካዊና ኢትዮጵያዊ ማንነትን በግልፅ የሚያንፀባርቁ ስራዎችን ሰርቷል። ከእነዚህም አንዱ ”አድዋ” ሲሆን፤ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. በዳግማዊ ምኒልክ ጠቅላይ አዝማችነት፣ በወራሪው የኢጣሊያ ሠራዊት ላይ ኢትዮጵያ የተቀዳጀችው ድል በየዓመቱ ሲዘከር በቴሌቪዥን መስኮት የሚታይ የቅድመ ጦርነት ዝግጅት የቪዲዮ ምሥል የአባተ መኩሪያ ትሩፋት ነው።
ለረጅም ዓመታት በአዲስ አበባ ትያትር እና ባህል አዳራሽ በስራ አስኪያጅነት ያገለገለው ጋሽ አባተ በ1950ዎቹ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ‹‹መዝናኛ በክዋኔ ጥበባት›› (Entertainment in Performing Arts) በሚል ርዕስ በየሳምንቱ ዓርብ ለአንድ ዓመት የዘለቀ ፕሮግራም ማዘጋጀቱን (ፕሮግራሙም የአዝማሪ ጨዋታ በኢትዮጵያ ሕዝብና በክዋኔ ጥበባት ውስጥ የነበራቸውን ሚና ይዳስስበት፤ የተለያዩ ብሔረሰቦች ባህልን፣ እምነትን፣ ደስታን፣ ሐዘን፣ ወዘተ በጥበብ አንፃር ይታይበት፤ ቤተ ክህነት ለጥበቡ ዕድገት ያደረገችውን አስተዋጽኦ ከታዋቂ የጥበብ ሰዎች ካበረከቱት ሥራ ጋር የሚቀርብበት እንደነበር ፕሮግራሙን በቅርበት የሚያውቁ ይናገራሉ።
”ጸጋዬ ገብረ መድኅን ‹‹የከርሞ ሰው›› የሚለውን የጻፈውና ሙላቱ አስታጥቄ ለከርሞ ሰው ሙዚቃውን የሠራው በዚሁ የአባተ ፕሮግራም ነበር።” በማለትም በማስረጃ ያስረዳሉ።
አዲስ አበባ ከተማ የተመሠረተችበት 100ኛ ዓመት ኢዮቤልዩ በዓል ሲከበር ለበዓሉ ድምቀት ከተዘጋጁት አንዱ ንጉሠ ነገሥቱ ‹‹ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት›› ብለው ለዘመቻ ሲነቃነቁ ባለፉበት በባልደራስ አካባቢ በሚገኘው የቀበና ወንዝ ነባር ድልድይ አጠገብ አዲስ የተሠራው ‹‹የዓድዋ ዘመቻ መታሰቢያ ድልድይ›› የተመረቀው የዚያን ዘመን የክተት ስሪት በሚያሳይ መልኩ አምሳያ የተፈጠረላቸው ንጉሠ ነገሥቱን፣ እቴጌይቱን፣ መኳንንቱን፣ የጦር አዝማቾችን፣ ዘማቾቹን፣ ሴቶች አገልግል ተሸክመው ሁሉም እየፎከሩ እየሸለሉ የሚያሳየውን ‹‹የራስ አባተ ጦር እለፍ ተብለሃል…›› ወዘተ እየተባለ በ400 ተሳታፊዎች የቀረበው ክዋኔ ለዘመን ተሻጋሪነት የበቃው በመራሄ ተውኔት አባተ መኩሪያ መሆኑን ከላይ የጠቀስነው ምንጫችን ያስያል። አባተ ዓድዋንና ድሉን የሚዘክር ላቅ ያለ ይዘት ያለውን የዓድዋ ፊልም ፕሮጀክትን ቢቀርጽም (ለህዝብም በይፋ ተገልፆ ነበር)፣ በወቅቱም በ35 ሚሊዮን ብር በጀት ሊሠራ መታቀዱንና ፕሮጀክቱን ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ በበላይ ጠባቂነት እንደያዙት ቢነገርም እስካሁን ድምፁ እንዳልተሰማም ለንባብ አብቅቷል።
በ1988 “ኤዲፐስ ንጉስ”ን የመደረከው፤ በተወለደ በ76 ዓመቱ ሐምሌ 14 ቀን 2008 ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት የተለየን ጋሽ አባተ ሙያውን ከማበልፀግ አኳያም በርካታ ስራዎችን የሰራ ሲሆን፤ በተለይም ኃላፊነትን በአግባቡ ከመወጣት አኳያ የሄደበት ርቀት ቀላል አይደለም።
በወቅቱ ከተነገረውም ሆነ በተለያዩ ሚዲያዎች ሲንሸራሸሩ ከነበሩት መረጃዎች፤ እንዲሁም ከጋሽ አባተ የህይወት ታሪክ መረዳት እንደ ተቻለው፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ቤት (የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር) የቴአትር ዳይሬክተር፣ እንዲሁም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ኪነ ጥበባት ወቴአትር (ባህል ማዕከል) ዳይሬክተር ሆኖ ሠርቷል።
አባተ ከብሔራዊ ቴአትር ሌላ በአገር ፍቅር ቴአትር፣ በአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር አዳራሽ በአዘጋጅነት፣ በጸሐፌ ተውኔትና መራሔ ተውኔትነት፤ እንዲሁም በኃላፊነት ጭምር አገልግሏል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት አገልግሏል።
የጋሽ አባተ መኩሪያ የስራ ባልደረባ የቅርብ ወዳጁ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበባት ኮሌጅ ዲን የነበረው አቶ ነቢዩ ባዬ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባህል ማዕከል ‹‹ዝክረ አባተ መኩሪያ›› ብሎ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ስለ ጋሽ አባተ ‹‹አባተ የዩኒቨርሲቲ የቴአትር ትምህርት በትክክለኛው መሠረት ላይ እንዲገኝ የላቀ ሚና ተጫውቷል። በዩኒቨ ርሲቲው የኪነ ጥበብ የፈጠራ ማዕከል እንዲቋቋም አሻራውን አኑሯል። የተለያዩ የቴአትር ንድፈ ሐሳቦችን በማቅረብ ግንባር ቀደም አርቲስት ነው።›› በማለት የሰጠው ምስክርነት ጋሽ አባተን በሚገባ ይገልፀዋልና እዚህም ደግመን ልንጠቅሰው ግድ ብሎናል። ለሌላ ተጨማሪ ሀሳብም የፋንታሁን እንግዳን ‹‹ታሪካዊ መዝገበ ሰብ›› መመልከት ተገቢ ይሆናል።
ጋሽ አባተ ለሙያዊ አስተዋፅኦና የተዋጣለት መምህርነቱ ብዙዎች የሚመሰክሩለት ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል ፍቃዱ ተክለ ማሪያም እና አበበ ባልቻ ይገኙበታል።
ፍቃዱ በህይወት በነበረበት ወቅት ስለ ጋሽ አባተ ተጠይቆ ሲመልስ ‹‹ራሴን ፈልጌ እንዳገኝ የገራኝ፣ መንገዱን ያሳየኝ፣ የገሰፀኝ፣ ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃ ያበቃኝና ያሳደገኝ የጥበብ አባቴ ነው›› ማለቱና አርቲስት አበበ ባልቻም በተጠየቀ ቁጥር ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ የሆነ አስተያየቱን ሲሰጥ መስማት ስለ ጋሽ አባተ ሙያዊ አስተዋፅኦ ለመረዳት በቂ ነው ማለት ይቻላል።
አባተ መኩሪያ ሙያተኛ ብቻ ሳይሆን ለሙያው ማደግም ሁሌ እንደሚጨነቅ የሚያውቁት ብቻም ሳይሆኑ፤ ስለ’ሱ የከተቡ ሁሉ ይመሰክሩለታል። ለዚህም ‹‹ታሪካዊ መዝገበ ሰብ›› ላይ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ የራሱን ባህል አትኩሮ የሚያጣጥምና የሚወድ ነው። ቴአትር ቤቱ ይሞላል። ግን ከቴአትር አንፃር (ከድርሰቱ) ያየነው እንደሆነ ብዙ የሚተቹ ነገሮች አሉ። እንደ ቴአትር አዋቂ ተመልካች ቴአትሮቹን ብናያቸው ብዙ ግድፈቶች እናገኛለን። ተመልካቹ ለዚያ ሁሉ ደንታ የለውም። የራሱን ሕይወት ማየት ይወዳልና ይመጣል። በአሁኑ ጊዜ ጥበቡ ሳይሆን ተመልካቹ ነው የሚፈታተነን። ደግሞ የኛን አገር ቴአትር እንዳያድግ የገደለው ቴአትር ቤቶች በመንግሥት እጅ መሆናቸው ነው። ቴአትር ቤቶች አንድ ዓይነት ሥራ ነው የሚሠሩት።›› በሚል የሰፈረውን መጥቀስ ይበቃል።
ሰኞ ኅዳር 10 ቀን 1932 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አዋሬ ሠፈር ከአባቱ ከአቶ ስለሺ ማንደፍሮና ከእናቱ ከወ/ሮ ውብነሽ መኩሪያ የተወለደው አባተ መኩሪያ በዚህ ሁሉ የሙያና አገልግሎት ዘመኑ ሁሉ ነገር አልጋ ባልጋ እንዳልሆነለት ይነገራል። በርካታ መሰናክሎች አጋጥመውት የነበረ መሆኑም እንደዛው።
ምንጮቻችን ላይ ሰፍሮ እንዳገኘነው ቀዳሚው ፈተና በአአ ዩኒቨርሲቲ፣ ከትምህርቱ ጐን ለጐን በኪነ ጥበብ ወቴአትር (ክሬቲቭ አርት ሴንተር) በሚሠራበት ወቅት በነበረው የግጥም ጉባኤ ባለቅኔው ዮሐንስ አድማሱ ያቀረበው፤
ላም እሳት ወለደች በሬ ቀንድ አወጣ፣
በሥልጣን ሊቅ መሆን ይህም አለ ለካ።
ግጥም በዩኒቨርሲቲው ኃይለኛ ቁጣ በመቀስቀሱ (ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ደጃዝማች ካሣ ወልደማርያምን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አድርገው መሾማቸውን የሚጎንጥ በመሆኑ) ማዕከሉ ይዘጋል። አባተን ጨምሮ ሁሉም ባልደረቦቹ እንዲባረሩ መደረጉ አንዱ ነው። (ዮሐንስ አድማሱ ይህን ቅሬታ የሚያባብስ ግጥም በመግጠማቸው “ኪነጥበብ ወቲያትር” በሣምንቱ በእሣቸው ትዕዛዝ እንዲዘጋ፤ የክፍሉ ኃላፊ ዶ/ር ፊሊፕ ካፕላንም ኮንትራታቸው እንዲቋረጥ መደረጉን፤ እሱና ጓደኞቹ ከ”ኪነ ጥበብ ወቲያትር” መባረራቸውን … በህይወት እያለ ለመኩሪያ ቲአትር መጽሔት በሰጠው ቃለ መጠይቅ ተናግሯል።)
አቶ አባተ ከዩንቨርሲቲው “ኪነጥበብ ወቲያትር” ከተባረረ በኋላ አዲስ በመቋቋም ላይ በነበረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በአዘጋጅነት ተቀጠረ:: ቴሌቪዥን ሥራውን በጀመረ ጊዜ የሚያስተዳድሩት እንግሊዞች ስለነበሩ አቶ አባተ ለአራት ወራት እንዳገለገለ ግላስኮት ቴሌቪዥን ኮሌጅ ውስጥ ገብቶ እንዲማር ወደ እንግሊዝ አገር ተላከ:: በእንግሊዝ አገር ቆይታው ሚዲያ ኮሚዩኒኬሽን አጥንቶ፤ በቢቢሲ ጣቢያም በመስራት የሥራ ልምድ አግኝቶ ወደ አገሩ ተመለሰ:: ከዚያ እንደተመለሰ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እና በአገር ፍቅር ቲያትር ቤት አዘጋጅ፤ እንዲሁም አሰልጣኝ በመሆን ቀጠለ:: በመሃሉ የሲኒማቶግራፊ ትምህርት የመማር እድልን አግኝቶ ወደ ጀርመን መሄዱም የታሪኩ አካል ሆኖ ይነገርለታል።
የሁለት ልጆች አባቱና አንጋፋው አርቲስ አባተ መኩሪያ በሰባ ስድስት ዓመቱ ከዚህ አለም ሲለይ ”ተንቀሳቃሹ ቴአትር ቤት አረፈ” ነበር የተባለለት። ወደ ፊት ህይወትና ስራዎቹን በተመለከተ በሚገባ እንደሚጠና፤ በርካታ መረጃዎችንም እንደምናገኝ በመተማመን ለዛሬ በዚሁ እናብቃ።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18 /2014