•አሁን ትኩረት የምንሰጠው የሕዝቡን አመኔታ መመለስ ላይ ነው
• ሚዛናቸውን የሳቱ የሚዲያ ዘገባዎች የህብረተሰቡ ድጋፍ እንዲቀዛቀዝ አድርገዋል
አዲስ አበባ፡- በተያዘው 2011 ዓ.ም በዋናነት የሚሠራውና በቀጣይም ትኩረት የሚደረግበት የሕዝቡን አመኔታ መመለስ ላይ እንደሆነ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የግድቡ የኃይል ማመንጫ ጊዜ ከታሰበለት ጊዜ ወደኋላ መቅረትና የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ሥራዎች መዘግየትን አስመልክቶ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተሰጡትን መረጃዎች ተከትሎ በተፈጠረው ጥርጣሬ የህብረተሰቡ ድጋፍ መቀዛቀዙም ተገልጿል፡፡ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለጹት የህብረተሰቡ የገንዘብ ድጋፍ ሊሰበሰብ የሚችለው ሕብረተሰቡ አምኖና ፈቅዶ ሲሰጥ በመሆኑ ዘንድሮ ገቢ ላይ ያተኮረ ሥራ አይሠራም፡፡
የሕዝቡን አመኔታ ለማግኘት እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት በአሁኑ ወቅት የመጣ ለውጥ አለ የሚሉት ዋና ዳይሬክተሯ ግድቡን እንደገና የመሥራት ያክል በሚመስል መልኩ ትልቅ ችግር እንደደረሰበት የሚያስመስሉ ሚዛናቸውን የሳቱ ዘገባዎች በመገናኛ ብዙሃን መሰንዘራቸው ሕብረተሰቡን ለቁጣ ዳርገውታል ብለዋል፡፡ እንደ ወይዘሮ ሮማን ገለፃ ባለፈው ዓመት ከህብረተሰቡ ድጋፍ 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ማግኘት የተቻለ ሲሆን፤ የግድቡ የኃይል ማመንጫ ጊዜ ከታሰበለት ጊዜ ወደኋላ መቅረትና የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ሥራዎች መዘግየትን አስመልክቶ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተሰጡትን መረጃዎች ተከትሎ ግን ሕብረተሰቡ ውስጥ በተፈጠረው ጥርጣሬ ባለፉት ስድስት ወራት 484 ሚሊየን ብር ብቻ ሊገኝ ችሏል፡ ፡
ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ አነስተኛ ቢሆንም አሁንም ግን ሕዝቡ ድጋፉን እንዳላቆመ ያሳያል፡፡ ህብረተሰቡ እክሎችን ሲመለከት ቁጣውን ማሳየቱ የሚጠበቅ ነው ያሉት ወይዘሮ ሮማን ይህንን መነሻ በማድረግም ዳሰሳ ጥናት ተደርጓል ብለዋል፡ ፡ በጥናቱ እንደተረጋገጠው፤ 45 ነጥብ 7 በመቶ የሚሆነው የሕብረተሰብ ክፍል ‹‹ችግር እንደገጠመ እናውቃለን፤ ግድቡም ዘግይቷል፡፡ ነገር ግን ምንም ችግር ቢገጥመውም መቀጠል ይኖርብናል›› በሚል ምላሻቸውን መስጠታቸውንና ቀሪዎቹ ደግሞ ‹‹ግድቡ መገንባት አለበት፤ እኛ ግን ምንም ድጋፍ አናደርግም›› ማለታቸውን ገልጸዋል፡፡
በዳሰሳዊ ጥናቱም ‹‹ያደረግነው አስተዋፅዖ ባልተገባ መንገድ ጥቅም ላይ ከዋለ እኛ አንቀጥልም፤ መንግሥት ይቀጥልበት›› የሚለው ምላሽ ከፍተኛ ቁጥርን ሊይዝ እንደቻለና ሁለቱም ወገን ግን በግድቡ ማለቅ ላይ ልዩነት እንደሌላቸው ተረጋግጧል ብለዋል ዋና ዳይሬክተሯ፡፡ ግድቡ ላይ የተፈጠሩ መዘግየቶችን አስመልክቶ መንግሥት ችግሮቹን መለየቱንና 130 ቢሊየን ብር በጀት ከመመደብ ጀምሮ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡንም ወይዘሮ ሮማን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ከሁለት ዓመታት በኋላ ሁለቱም ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት ይጀምራሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ከአራት ዓመታት በኋላ ደግሞ እንደሚጠናቀቅ ይታሰባል ብለዋል፡፡ በመጀመሪያም ቢሆን ፕሮጀክቱን በራስ አቅም ለመገንባት በእቅድ ተይዞ ብሔራዊ መግባባት የተፈጠረበት በመሆኑ ጽሕፈት ቤቱ ከምንም ነገር በላይ የሕዝብ አመኔታን ማረጋገጥ ቀዳሚ ሥራው አድርጎ ይዞ እየተንቀሳቀሰበት እንደሚገኝም ዋና ዳይሬክተሯ አረጋግጠዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2011
ፍዮሪ ተወልደ