አዲስ አበባ :- በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በግንባታ ላይ የሚገኘው ታላቁ የህዳሴ ግድብ እስከሚጠናቀቅ ድረስ አስፈላጊውን ድጋፍና አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ አብረሃም ስዩም በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት አገሪቱ በምታካሂደው ሁለንተናዊ ልማት ውስጥ ዲያስፖራው እየተጫወተ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው። በተለይም ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታን በተመለከተ ያለው አተያይ ከሌሎች ዘርፎች ጠንከር ያለ በመሆኑ ለግድቡ የግንባታ ሂደትም ሆነ መጠናቀቅ የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ ወደኋላ አይልም ሲሉም አስረድተዋል።
ከመንግሥት ቀጥሎ በከፍተኛ የማልማት ሥራ ላይ የተሰማራ አካል ቢኖር በውጭ የሚኖረው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሲሆን ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር በኩልም ከመንግሥት ቀጥሎ በ2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ዲያስፖራው ነው የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይም ያለው አስተዋፅኦ ቀላል አይደለም ብለዋል፡፡ በአገራችን የነበረውን የለውጥ እንቅስቃሴና እሱን ተከትሎ የመጣውን የአመራር ለውጥ ምክንያት በማድረግ የግድቡ ግንባታና ሂደቱ መቀዛቀዙ በዲያስፖራው በኩል ቅሬታን አስከትሎ እንደነበር የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ስለግድቡ ያለውን ብዥታና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ለማጥራት ከህዳሴ ግድብ ምክር ቤት ጋር በመሆን ተከታታይ መድረኮችን በማዘጋጀት ባለሙያዎች ቀርበው ማብራሪያ እንዲሰጡ በማድረግ መግባባት ላይ መድረሳቸውንም አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ዲያስፖራው ሚናው ወሳኝ ነው የሚሉት አቶ አብረሃም በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ከሚያፈሰው መዋዕለ-ንዋይ ውጪ ባለፈው ዓመት ብቻ ያለውን እንኳን ብንወስድ አምስት ቢሊዮን ዶላር ከውጭ ተልኮ (ሬሚተንስ) ለአገሪቱ ልማት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉንም አስታውቀዋል። ከተመሰረተ ሰባት ዓመት የሆነውና 10ሺህ አባላትን የያዘው ይህ የዲያስፖራ ማህበር ዲያስፖራው ለአገሩ የሚችለውን ሁሉ እንዲያደርግ ሁኔታዎችን ሲያመቻች መቆየቱን እና በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ትውልደ ኢትዮጵያንን በማስተባበርና ወደ አገር ቤት እንዲገቡ በማድረግ በተለያዩ ዘርፎች በተለይም በህክምና፣ ትምህርትና ሌሎች ሙያዎች እውቀታቸውን እንዲያካፍሉ፣ የእውቀት ሽግግር እንዲደረግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የበኩሉን ሲወጣ መቆየቱን አብራርተዋል።
ከኢትዮጵያ ውጭ በየትኛውም አገር የሚኖር፣ ሁለት ዓመት እና በላይ የኖረና የመኖሪያ ፈቃድ ያለው ሁሉ ”ዲያስፖራ” በሚለው ይታቀፋል የሚሉት አቶ አብረሃም ማህበራቸው ለሁሉም እኩል በሩ ክፍት እንደሆነ፤ በተዘረጉ የተለያዩ የኮሚዩኒኬሽን መስመሮች እንደሚገናኙ እና እዚህ ስላለው አጠቃላይ ሁኔታ፤ እንዲሁም ስላለው የኢንቨስትመንት ዕድልም ወቅታዊ መረጃ እንደሚለዋወጡ ይናገራሉ።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ በአጠቃላይ ከሦስት እስከ አራት ሚሊዮን የሚገመት ትውልደ ኢትዮጵያዊ በዓለም ይገኛል። አብዛኛው ዲያስፖራም እየተከናወነ ባለው ለውጥና በዶክተር አቢይ አመራር ከፍተኛ እምነት አለው። በመሆኑም መንግሥትና አገሪቱ በፈለጉት ዘርፍ፣ ጊዜና ቦታ ሁሉ ለመገኘትና የበኩሉን ኃላፊነት ለመወጣት ምን ጊዜም ዝግጁ ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2011
ግርማ መንግስቴ