አዲስ አበባ፡- የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የአንድ ዓመት የሥራ እንቅስቃሴን የሚያሳይ የፎቶ ዐውደ ርዕይ ትናንት በሚሊኒዬም አዳራሽ ተካሄደ፡፡ ዐውደ ርዕዩ የትናንቱን ታሪክ ለማወቅና ቀርፆም ለማቆየት ከማገዙም በላይ ከትናንት ተምሮ ነገን በማለም ለአዲስ ሥራ የሚያዘጋጅ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ዐውደ ርዕዩን በንግግር ያስጀመሩት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው እንዳሉት፤ ፎቶ ታሪክ ከሚጠበቅባቸውና ከሚተላለፍባቸው መንገዶች አንዱ ነው፡፡ ያለፈን ትዝታ መከሰቻ፣ ዛሬን ማወቂያና ነገንም ማለሚያ ጥበብም ነው፡፡ በዕለቱ የቀረበው የፎቶ ዐውደ ርዕይም ትናንት የታለፈበትን መንገድ ለመመለከት፣ ታሪኩንም ቀርፆ ለትውልድ ለማስተላለፍና ዛሬ ላይ ቆሞም ስለነገ ሥራ ለማለም የሚያስችል ነው፡፡
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ የፎቶ ዐውደ ርዕዩ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የአንድ ዓመት የሥራ እንቅስቃሴ በፎቶ ለማቅረብ ከመሞከሩ በተጓዳኝ የኢትዮጵያ የፎቶ ግራፍ ጥበብና ዕድገት ለማየት ያስቻለ ነው፡፡ ፎቶም የስሜት፣ ሁነትና የታሪክ ገጽታን አመልካች እንደመሆኑ፤ በአንድ ዓመት ውስጥ ምን ተሠራ፣ ምንስ ጠንካራ ነገሮች ነበሩ፤ መታረም የሚገባቸውስ ጉዳዮች ምንድን ናቸው፣ የሚሉትን ለመገምገም ያግዛል፡፡ ከዚህ ጉዞ በሚገኝ ምልከታም ዛሬ ላይ ስለነገ ሥራዎች ማሰብና ማለም የሚቻልበትንም ዕድል ይሰጣል፡፡ ዐውደ ርዕዩም የትናንቱን ለማወቅና ለትውልድ ለማስተላለፍ፤ በተገኘው ልምድም ነገ ምን መሥራትና ወዴት መሄድ እንደሚገባ ለማለም የሚያግዝ ነው፡፡
በዐውደ ርዕዩ በፎቶ ግራፍ ዕድገትና ፈተናዎች በተለይም ባለፈው አንድ ዓመት የነበሩ የፎቶ ዘገባ ሂደቶች ምን እንደሚመስሉ የሚዳስሱ የመወያያ ሃሳቦች የቀረቡ ሲሆን፤ በውይይቱም ያለፈው አንድ ዓመት በመልካምም በመጥፎም የሚነሱ የፎቶ ዘገባዎች የተስተዋሉበት ስለመሆኑ ተነስቷል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥራ እንቅስ ቃሴዎችና የፎቶ ዘገባ ሂደቱም የቀደመውን የመሪዎች አካሄድ የሰበረና የቤተኝነት ስሜትን የፈጠረ ስለመሆኑም ተጠቁሟል፡፡
በውይይቱ እንደተገለጸው፤ ፎቶ ሁነቶችን በምስል ይዞ ለማቆየት፣ ትዝታን ለመቀስቀስና ስሜትን ለማነሳሳት አቅም ያለው ጥበብ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ባለፈው አንድ ዓመት የመሪዎችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ሁነቶች በቀየረ መልኩ እነዚህን እውነቶች መመልከት ተችሏል፡፡ በዚህም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ደስታና መከፋታቸው፣ ስኬትና ፈተናቸው ሁሉ የህዝቡ ስሜት እስኪመስል የቤተኝነትን ስሜት የፈጠረ የፎቶ ዘገባን መመልከት ተችሏል፡፡
ይሁን እንጂ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያው የተሳሳቱ፣ የጊዜው ያልሆኑና የሐሰት ፎቶዎች ሲስተናገዱ ታይተዋል፡፡ ይህ ደግሞ የአገርን ገጽታና ደህንነት ብሎም የሰዎችን ስብዕና የሚጎዳ እንደመሆኑ ሊታረም ይገባዋል፡፡ ከፎቶ ዶክመንቴሽንና መሰል ጉዳዮች ጋር ያሉ ችግሮችንም መፈተሸ ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2011
ወንድወሰን ሽመልስ