በጎ ፍቃደኝነት በመንግስት አቅም መስራት የማይችሉና ህብረተሰቡ በግሉ ሊሰራቸው የማይችሉ ተግባራትን በጎ ፍቃደኞች ጥቅም ሳይፈልጉ ተሰባስበውና ተደራጅተው በጉልበታቸው፣ በእውቀታቸውና በገንዘባቸው የሚያከናውኑት ተግባር ነው:: በዚህ በጎ ተግባርም በአለም አቀፍ ደረጃ በርካታ እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች በየአመቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ::
በኢትዮጵያም የበጎ ፍቃድ አገልግሎት አስተሳሰብ በህብረተሰቡ በተለይ ደግሞ በወጣቱ ዘንድ እየዳበረ በመምጣቱ፤ በመንግስትም በኩል አገልግሎቱ ተቋማዊ እንዲሆን በመደረጉ ለበርካቶች ተደራሽ ለመሆን በቅቷል:: በዚህም በርካታ እርዳታ የሚሹ ዜጎች ተጠቃሚ ለመሆን በቅተዋል:: በዚሁ አገልግሎት የሚሳተፉ በጎ ፍቀደኛ ወጣቶች ቁጥርም እያደገ መጥቷል::
ብዙ በተባለለት የዘንድሮው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በአስራ አንድ የተለያዩ ዘርፎች በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እየተሰጠ የሚገኝ ሲሆን፤ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ከ19 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ተሳትፈዋል:: በሚከናወነው በዚሁ የበጎ ፍቃድ አገልግሎትም መንግስትና ህብረተሰቡ ሊያወጡ የሚችሉት 11 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ወጪ ይድናል ተብሎ እንደሚጠበቅ መረጃዎች ጠቁመዋል:: አገልግሎቱም ከሰኔ 15 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ እንዲከናወን መርሃ ግብር ተይዞለታል::
በአዲስ አበባ ከተማም ወጣቶች በተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ውስጥ በመሳተፍ በገንዘብ ሊተመኑ የማይችሉ ከፍተኛ ስራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ::በዘንድሮ በጀት ዓመትም በከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ግንዛቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ በተለያዩ ዘርፎች በተሰራው ሥራ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከሶስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማዳን ተችሏል::
የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሁሌም በየአመቱ ክረምትን ጠብቆ የሚከናወን እንደሆነ ቢታወቅም የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ማህበር ‹‹በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ክረምት ተሻጋሪ ስራዎችን እያከናወንኩ ነው፤ ዘንድሮም አከናውናለሁ›› ይላል::
ወጣት ይሁነኝ መሀመድ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ማህበር ዋና ፀሃፊ ነው:: እርሱ እንደሚለው አጠቃላይ የበጎ ፍቃድ ተግባር በዋናነት የተጀመረው የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ከተመሰረተ ከሀያ አራት አመት በፊት ነበር:: በተደራጀ መልኩ ‹‹የክረምት›› በሚል የማህበሩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የተጀመረው ግን በ1995 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ቤታቸው የሚመለሱ ወጣት ተማሪዎች በስራቸው ያሉ ወጣቶችን እንዲያስተምሩ በማድረግ ነው::
ከዛ በፊት በነበሩት ሁኔታዎች የኤች አይ ቪ ኤድስ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር የፔፕሲ ሱቆችን የማምጣት ስራዎች በማህበሩ በኩል ሲከናወኑ ቆይተዋል:: በኋላ ላይ የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት በጨመረበት ጊዜ የኤች አይ ኤድስ ታማሚዎችን የመንከባከብ፣ህክምና እንዲያገኙ የማድረግ፣ የማብላት፣ የማጠጣትና የመደገፍ ሲሰሩ ነበር:: ‹‹በኤች አይ ቪ ኤድስ ታማሚዎች ላይ የሚደርሰው ማግለልና መድልኦ ይቁም!›› የሚሉ እንቅስቃሴዎች ሲጀመሩም ማህበሩ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ነበር::
ከዚሁ ጋር ተያይዞም ማህበሩ የኤች አይ ቪ ኤድስ ታማሚዎችን፣ ዝቀተኛ ገቢ ያላቸውንና የአቅመ ደካማ አረጋውያንን መኖሪያ ቤቶች የማደስ ስራዎችን በጊዜው በስፋት ሲሰራ ቆይቷል:: የችግኝ ተከላና እንክብካቤ እንዲሁም የፅዳት ስራም በወጣት ማህበሩ በኩል ሲካሄድ ነበር::
እንደ ዋና ወጣት ይሁነኝ ገለፃ በነዚህ ሂደቶች ሁሉ መንግስት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ ስራዎች ብቻ ሳይሆን የወጣቶችን ጉዳይ በአደረጃጀት ደረጃ የሚመለከት ተቋም አልነበረም:: በጊዜው የወጣቶች አደረጃጀት በወረዳ ደረጃ በማህበራዊ ዘርፍ ውስጥ ታቅፎ ነበር ሲሰራበት የቆየው እንጂ ራሱን የቻለና ወጣትን የሚመለከት ተቋም አልነበረም:: ከዚህም በኋላ ነው ወጣቶችን የሚመለከት ራሱን የቻለ ተቋም መቋቋም የጀመረው::
የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ እንዳለ ሆኖ ወጣቶች የሚውሉባቸው ቦታዎች በሙሉ የሚታወቁ ባለመሆናቸው ማህበሩ ቀደም ብሎ ቦታዎች ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተረክቦ የወጣቶች ማእከል ሊገነባ ይገባል በሚል በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቦታ አስፈቅዶ የወጣቶች ማእከል ገንብቶ እንደናሙና አሳይቶ በመላ ከተማዋ ሌሎች የወጣት ማእከላት እንዲገነቡ በር ከፍቷል::
ማህበሩ በበጋ የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ትራፊክ የማሳለጥ፣ አረጋውያንን የመንከባከብ፣ የቤት እድሳት፣ የኤች አይ ቪ ኤድስ ምርመራ፣ የስነ ተዋልዶ ጤና ትምህርት፣ ከአዲስ አበባና አጎራባች ክልሎች ጋር ያሉ ወጣቶችን በስራ የማገዝ ስራዎችን ያከናውናል:: በከተማዋ ደግሞ ‹‹በጎነት በሆስፒታል›› በሚል ከተማዋ የኢትዮጵያ ዋና መናገሻ እንደመሆኗ ከመላው ኢትዮጵያ ሪፈር ተፅፎላቸው ከተማዋ ውስጥ ባሉ የመንግስት ሆስፒታሎች ውስጥ ህክምናቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ታካሚዎችን የመንከባከብ ስራም በማህበሩ በኩል ይከናወናል::
በተለይ ደግሞ ታማሚዎች ከሃኪሞች ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት የቋንቋ ችግር ሲገጥማቸው በማስተርጎም የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከባለፈው አመት ወዲህ በየካቲት አስራ ሁለትና አቤት ሆስፒታሎች ጀምሯል:: በዚህና በሌሎች መስኮች የማህበሩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እየሰፋ መጥቷል:: አገልግሎቱ ወደ ህብረተሰቡ ይበልጥ ተደራሽ እየሆነ መጥቷል:: ወጣቱም ከራሱ አልፎ ለሌሎች ማድረግን እየተለማመደ መጥቷል::
ወጣት ይሁነኝ እንደሚናገረው የበጎ ፍቃድ አስተሳሰብ በመንግስት አቅም መሰራት የማይችሉና ህብረተሰቡ በግሉ ሊሰራቸው የማይችሉ ተግባራትን በጎ ፍቃደኞች ተሰባስበውና ተደራጅተው በጉልበታቸው፣ በዕውቀታቸው ከፍ ሲል ደግሞ ባላቸው አቅምና የሌሎችን አቅም ተጠቅመው የሚያከናውኑት ተግባር ነው:: ከዚህ አንፃር የማህበሩ ወጣቶች እነዚህን በጎ ስራዎች ሲያከናውኑ መንግስት ጥርጊያ መንገዱን ካመቻቸ ከመንግስት አቅም በላይ የሆኑ ስራዎችን ይሰራሉ::
በዘንድሮው የ2014 ዓ.ም የክረምት የወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ማህበር የተለያዩ የበጎ ፍቃድ ስራዎችን እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን ከያዘው ዕቅድ በላይ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ሊያወጡ የሚችሉ ተግበራትን አከናውኗል:: ወጣቶች እስከ 50 ሺ የሚሆኑ በግማሽና ሙሉ ቀን እንዲሁም በሳምንት ውስጥ በሚደረጉ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ውስጥ እየተሳተፉ ይገኛሉ::
የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ የበጀት አመቱ መዝጊያ ላይ የተጀመረ ቢሆንም ማህበሩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱን በበጋም ጭምር የሚያከናውን እንደመሆኑ በክረምት የሚሰራቸውን የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች እያከናወነ ወደ በጋው ይሻገራል::
በዚሁ የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የማህበሩ አባላት በተለያዩ አስራ ሶስት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዘርፎች እየተሳተፉ ይገኛሉ:: ከነዚህ ውስጥም በኪነ ጥበብ ዘርፍ ሙዚቃ፣ ቲያትርና የውዝዋዜ ዘርፎች ይገኙበታል:: በጎነት በሆስፒታል በሚለው ዘርፍም ቋንቋ በማስተርጎም፣ በህሙማን እንክብካቤ፣ ህሙማን በከተማዋ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ቦታዎችን በማሳየትና ከኮሮና ጋር የተያያዙ ስራዎችን የሚሰሩ ወጣቶች አሉ::
በተጨማሪም የሆስፒታሉን ዳታ ኢንኮድ የማድረግ፣ ፋይል የማደራጀትና በሌሎችም አምስት ዘርፎች ስራዎችን ያከናውናሉ:: በስፖርት ዘርፍም እንደዚሁ በእግር ኳስ፣ በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ቅዳሜና እሁድ ነዋሪውን ስፖርት በማሰራት ስፋት ያለው የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶችን እያከናወኑ ይገኛሉ:: በፀጥታና ሰላም ጉዳዮች ላይም ወጣቶቹ በበጎ ፍቃድ ተሳታፊ ናቸው::
ከዚህ ባለፈ ወቅቱ ክረምት ነውና ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት የጎርፍ ተጋላጭነት መከላከል ስራዎችንም ወጣት ማህበሩ ሰርቷል:: የጎርፍ ጉዳት የደረሰባቸው የተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ላይም የቤት ማደስ ስራዎች ተከናውነዋል:: ወደፊትም የጎርፍ ቅድመ መከላከል ስራዎች በበጎ ፍቃድ የሚከናወኑ ይሆናል::
ወጣት ይሁነኝ እንደሚገልፀው፤ በአሁኑ ወቅት የበጎ ፍቃድ አስተሳሰብ በመንግስትም ጭምር ትልቅ ትኩረት እያገኘ የመጣና በአስተዳደር ደረጃም ለጉዳዩ እውቅና እያገኘ መጥቷል:: በገንዘብ መደገፍ፣ ጉልበት መስጠትና በእውቀት ማገዝ ባይቻል እንኳን በጎ ፍቃደኞች እያከናወኑት ያለው ተግባር ጠቃሚ ነው የሚለው አስተሳሰብ በስፋት ተደራሽ እየሆነ ይገኛል:: ይህም እንደጠንካራ ጎን የሚወሰድ ነው::
አንዳንድ ተቋማትም በጎ ፍቃደኝነትን በውል በመረዳት ለስራው አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን በማቅረብ እገዛ እያደረጉ ይገኛሉ:: ከክልል ተፈናቅለው ለመጡ ዜጎችና የጎዳና ተዳዳሪዎች ለሚደረገው ምገባም በቀናነት የእውቀት፣ የገንዘብና ሌሎችንም ድጋፎች ያደርጋሉ:: ይህም የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ግንዛቤው በይበልጥ እየሰፋ መምጣቱን ያሳያል::
የማህበሩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራ ክረምትን ተሻግሮ በበጋ ወቅትም የሚከናወን ነውና ወጣት በጎ ፍቃደኝነት በትምህርት ቤት፣ በአካባቢና በሰፈር ያለ በመሆኑ በቀጣይም በተለያዩ መልኩ የሚከናወን ይሆናል:: ከዚህ ባሻገር በመንግስት በኩል በበጎ ፍቃድ ሊሰሩ የሚችሉ ተግባራትን በውል ለይቶ በመደበኛነት ሌሎች ተግባራትን በአቅሙ ማከናወን ይጠበቅበታል::
ለአብነት ቤት ማደስ የወጣቶች የበጎ ፍቃድ ስራ ቢሆንም መንግስት ቤት ለሌላቸው ገንብቶ መስጠት አለበት:: ለዘላቂነት በጎ ፍቃደኝነቱ እንዳለ ሆኖ የተረጂነት አስተሳሰብ እንዳይጎለብት ጥረት መደረግ አለበት::መንግስት መሰረታዊ ነገሮችን ለዜጎች ሠርቶ በጎ ፍቃደኞች መንግስት መሸፈን ያልቻላቸውን ስራዎች ማከናወን ይጠበቅባቸዋል::
የማህበሩ ቀጣይ ትኩረትም በበጎ ፈቃድ ስራ የከተማዋንና እና የሀገሪቱን ሰላምና ጸጥታ ማስጠበቅ፣ የወጣቶችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እና የለማች ሀገር ለማድረግ በሚደረገው ሁለተናዊ ጥረት ወጣቱ ጉልህ ተሳታፊ እንዲሆን ማድረግ ነው::
የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር የወጣቶች የበጎ ፈቃድ ተግባርን መሰረት አድርጎ ከተቋቋመ 25 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ሁሉም ሰው በበጎ ፈቃድ ሥራ መሳተፍ አለብኝ ብሎ እንዲያስብ እና ባህል እንዲሆን የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል::
ሀገር ተረካቢ ወጣቶችን ከማፍራት አኳያም ማህበሩ በክረምት ወራት በቤታቸው የሚገኙ በርካታ ተማሪዎች ጊዜያቸውን በአልባሌ ቦታ እንዳያሳልፉ ከማድረግ በተጨማሪ በገንዘብ የማይተመን የማጠናከሪያ ትምህርት የመስጠት ስራም ሰርቷል::
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 13/2014