ከዚህ በፊት፣ ምናልባትም ከሁለት ወራት በማይበልጥ ጊዜ፣ ከዛሬው እንግዳችን ጋር በተመሳሳይ ተግባር የሚታወቁ ሁለት አንጋፋና የአገር ባለ ውለታ ምሁራንን አስታውሰን፤ ባለውለታነታቸውንም ዘክረን ነበር።
‹‹’አስተማሪዬ መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ የጀመሩትን ግዕዝ አማርኛ ግስ እንድጨርስ አዘውኝ ነበር። እነሆ እስከ ዛሬ ደክሜበታለሁ፤ አልተጠናቀቀልኝምና አንተ ተረክበኸኝ ሥራውን ቀጥል። ዘርሁን፤ ዘር ይውጣልህ’ ብለው አለቃ ኪዳነ ወልድ ለአለቃ ደስታ አደራ ሰጥተው ነበር። አለቃም አደራውን ጠብቀው በ1948 ዓ.ም. ከመደበኛ ሥራቸው ውጭ ሌት ከቀን በመሥራት ‹‹መጽሐፍ ሰዋሰው ወግስ፤ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ›› የተባለውን የመጀመሪያ ታላቅ መዝገበ ቃላት አሳትመዋል፡፡” የሚለውን ሀሳብም (የትውልድ ቅብብሎሽን በሚያሳይ መልኩ) ምንጭ ጠቅሰን አስፍረናል።
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌን በተጨማሪ ”አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ (ሐምሌ 19 ቀን 1893 ዓ.ም – ጳጉሜን 2 ቀን 1977 ዓ.ም)” በሚል ርእስም ስለ አለቃ ደስታ ገፃችን የፈቀደልንን ያህል ብለናል። የዛሬውም የዛው ”ፓኬጅ” ተደርጎ ይወሰድልን ዘንድ እየጠየቅን ባለውለታችንን፣ በስማቸው ”ከሳቴ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት” (ወደ ፊት አንድ ዩኒቨርሲቲ በስማቸው መሰየሙ መቸም አይቀርም) የተሰየመላቸውን ታላቅ ሰው ወደ መዘከሩ ተግባር እንሸጋገራለን።
ስለ አማርኛ መዝገበ ቃላት ሲነሳ የዛሬ 60 እና 70 ዓመት የአሜሪካ መንግስት ያዘጋጀው አማርኛን በድምጽ የሚያስተምርና የሚተረጉም መሳሪያና በ1841 ዓ.ም በዊልያም ኢዘንበርግ የተጻፈው ”የአማርኛ መዝገ በቃላት” ፤ እንዲሁም በ1690 ዓም የታተመው የአማርኛ እና ላቲን መዝገበ ቃላት ወደ አእምሯችን መምጣታቸው አይቀርም። A Dictionary of the English Language፤ በሌላ ስሙ Johnson’s Dictionary (1775)ም እንዲሁ።
በ1859 ዓ.ም በቤንጋል፣ ህንድ የታተመው የአማርኛ–ኡርዱና–እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላትም ሆነ በ1833 ዓ.ም በቄስ ቻርለስ ዊሊየም ኢዘንበርግ እንግሊዝ (ለንደን) የታተመው የአማርኛና እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት እንደ አንድ ቀዳሚ ስራ ሳይታወሱ የሚታለፉ አይደሉም።ይህ መዝገበ ቃላት በመጀመሪያ ክፍሉ አማርኛን ወደ እንግሊዝኛ የሚተረጉም ሲሆን፤ በሁለተኛ ክፍሉ መልሶ እንግሊዝኛን ወደ አማርኛ የሚተረጉም መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
(ቻርለስ ኢዘንበርግ (እ.ኤ.አ. መስከረም 5 ቀን 1806 ስቱትጋርት — ጥቅምት 10 ቀን 1864) የአንግሊካን ቤተክርስቲያን ቄስ የነበረና ባለፈው ዘመኑ የቆርቆሮ ብረት አንጥረኛ የነበር ሰው ነው። ቄስ በነበረበት ዘመኑ ወደ ኢትዮጵያ እና ህንድ የተላከ ሚሲዮናዊ ሲሆን ይሄውም (እ.ኤ.አ) ከ1832-1864 መሆኑ ነው። ኢዘንበርግ፣ ከ’34-38 በአድዋ ትግራይ የኖረ ሲሆን ከአካባቢው ቀሳውስት ጋር መግባባት ስላላሰየ ሊባረር በቅቷል። በሚቀጥለው አመት፣ 1839፣ በሸዋው ንጉስ ሣህለ ሥላሴ ግብዣ እርሱና ሌሎች ሁለት ሚስዮኖች ሸዋ ሄዱ። ከ4 ወር ቆይታ በኋላ ኢዘንበርግ ወደ ለንደን እንግሊዝ ተመልሶ ሄደ። በለንደን ቆይታው ብዙ መጻህፍትን በአማርኛ ና ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አሳትሟል። እነርሱም አፋርኛ፣ኦሮምኛ (ከሉድቪግ ክራፍ የተወሰደ) እና አማርኛ መዝገበ ቃላት (1840-42)፣ የአማርኛ ሰዋሰው፣ የቤተክርስቲያን ታሪክ፣ ጂኦግራፊ፣ እና የዓለም ታሪክን ያቅፋሉ። ኢዘንበርግ በ1842 እንደገና ወደ ሸዋ ለመመለስ ሞክሮ ነበር፤ ሆኖም ግን ፍቃድ ስለተከለከለ ወደ ትግራይ በማምራት በዚያ እስከ 1843 ተቀመጠ። ደጃዝማች ውቤ በዚሁ አመት ከትግራይ ስለአባረሩት ወደ ለንደን አመራ። በ1844 የአቡ ሩሚን የቆየ አማርኛ መጽሓፍ ቅዱስ ትርጓሜ በማረም ከክራፕፍ ጋር አሳተሙ። በዚያው አመት አራቱን ወንጌሎች በትግርኛ ቋንቋ ሊያሳትም በቃ። ይህ የትግርኛ መጽሀፍ ቅዱስ በበርሊን፣ ጀርመን ይገኛል። የሚለውን ከድረ-ገፅ የተገኘ መረጃ እዚህ ጋ በቅንፍ አስቀምጠነዋል ።)
ከዘመናዊነት (የቅርብ ህትመት ከመሆኑ) አኳያ፣ 90 አመታትን የፈጀውና (በ1921 የጀምሮ በ2011 የተጠናቀቀው) በ26 ጥራዞች የተዘጋጀው፤ ከ2500 ዓ.ዓ ጀምሮ እስከ 100 ዓ.ም በሶርያ፣ በቱርክ፣ በኢራቅና በኢራን ይነገሩ የነበሩትን ቋንቋዎችና ቀበሌኛዎች ያካተተው፤ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የቺካጎ ዩኒቨርሲቲ የምሥራቃዊ አገሮች ጥናት ተቋም ያዘጋጀውና በዘርፉ ባለሙያዎች ዘንድ ትኩስ ዜናነቱ ቀዝቀዝ ያላለው ከ9ሺህ 700 የሚበልጡ ገጾች ያሉት ”የአሥር ቋንቋ መዝገበ ቃላት” (The Assyrian Dictionary) …. እና ሌሎች በርካታ ስራዎች ይታወሱን ይሆናል።
ከመለስተኛ 2ኛ ደረጃ እስከ 2ኛ ደረጃ የዘለቀ፣ አምሳሉ አክሊሉ ከፈረንጁ ጓደኛቸው ጋር ያዘጋጇትን ”አማርኛ እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት” ማን ይረሳል? አቅም ያለውና ህይወቱ ከምርምር ስራዎች ጋር የተቆራኘ ዌብስተርና ኦክስፎርድን ከጠረጴዛው ላይ እንደማያጣው ሁሉ፤ ባለፈውም ሆነ ዛሬ እዚህ የምናስታውሳቸው ባለውለታዎቻችን (አለቃ ኪዳነ ወልድ፣ አለቃ ታዬ እና የዛሬው ከሳቴ ብርሀን) ስራዎችም እንዲሁ ከጠረጴ ላይ የሚጠፉ አይደሉም። ይላቅ ኃይለማርያም ያሳተሙት ሐበሻ የአማርኛ መዝገበ ቃላት (1995)ም አለ። የደራሲ ባህሩ ዘርጋውም እንዲሁ ይጠቀሳል። በተለይ ሊታይ ይገባል ካልተባለ በስተቀር የሥርግው ሐብለሥላሴ (ዶ/ር) ”የአማርኛ የቤተክርስቲያን መዝገበ ቃላት”ም ተጠቃሽ ነው።
ሁሉም ይጠቀሱ እንጂ የቀደምቶቹን ያህል የተፈላጊነትን ስፍራ የተቆጣጠረ አለ ለማለት የሚያስደፍር አንዳች ምክንያትም ሆነ ማስረጃ የለም።
በ”የአማርኛ መዝገበ ቃላት” (ከሳቴ ብርሃን ተሰማ፣ 1951 ዓ.ም፣ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ) እውቅና ዘመን ተሻጋሪ (ብዙዎች አውደ ጥበብ (ኢንሳይክሎፔዲያ ነው ይሉታል – ከመዝገበ ቃላት በላይ መሆኑን ለመግለፅ)) ስራቸው ከፍ ብለው የሚታወቁት ተሰማ ሀይለሚካኤል በደራሲያን ማህበር የአንድ ወቅት አጀንዳ ላይ የሚከተለው ሰፍሮላቸው ለንባብ በቅቷል፤
ተሰማ ሀብተሚካኤል በሰሜን ሸዋ በሰላሌ አውራጃ ጎሐጽዮን በ፲፰፻፹፪ (1882) ዓ.ም. ተወለዱ። ተሰማ የዓባይን ወንዝ አቋርጠው ወደ ጎጃም በመሄድ ዜማ፣ ትርጉም (ትርጓሜ፣ ቅኔን … በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ተከታትለዋል። በተለይ ዲማ ወደ’ሚገኘው እውቅ ገዳም በመሄድ ዜማና ቅኔ ተምረዋል። የቤተክርስቲያን ከፍተኛ ትምህርታቸውን ከተከታተሉ በኋላ በ፲፱፻፩ (1901) ዓ.ም. በመንግሥት ሥራ በመቀጠር ወደ ሐረርጌ ጠ/ግዛት ሄዱ። ተሰማ በጥሩ እጅ ጽሑፋቸውና በተለየ የፊደል አጣጣላቸው ይታወቁ ነበር። ብዙ የሃይማኖት መጻሕፍት እንዲገለብጡ ይታዘዙ የነበረውም ለዚህ ነው። በጡረታ እስከተገለሉበት ፲፱፻፭፬ (1954) ዓ.ም. ድረስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት እንዲያዘጋጁ በትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ሠርተዋል። “ከሣቴ ብርሃን” የተሰኘው ሥራቸው ጠንካራ፣ ዋነኛና ትልቁ ሥራቸው ነው።
በማህበሩ አጀንዳ ላይ እንደ ተገለፀው፣ በዚህ መዝገበ ቃላት ዝግጅት ላይ እንደነበሩ ብዙ ችግሮችና መሰናክሎች ገጥመዋቸዋል። አማርኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ሲሆን፤ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ አደሪኛ እና ግዕዝ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ይህን የቋንቋ ዕውቀታቸውንም በተለያዩ ሥራዎቻቸው ላይ በሚገባ አውለውታል። ጥንካሬያቸውም “ከሳቴ ብርሃን” በተባለው መዝገበ ቃላት ዝግጅት ላይ ተገልጧል፡፡
ከአሥር ዓመታት በኋላ ባለ 1ሺህ 398 ገጾች መዝገበ ቃላት ሲያዘጋጁ፣ መዝገበ ቃላቱም 33ሺህ ድርሰቶች፣ አገባቦች እና 1ሺህ 278 ሥዕሎች ሲኖሩት ከተጀመረ 12 ዓመታት በኋላ በገበያ ላይ ለመዋል ችሏል። ስሙም ለደራሲው ክብር ሲባል “ከሣቴ ብርሃን ተሰማ” እንዲባል በትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር ተመርጦ ተሰየመ። ይህም ለተሰማ ሀብተሚካኤል እንደ ሽልማት ተቆጠረ፡፡
እኝህ ብዙም ያልተነገረላቸው፣ ያልተፃፈላቸው … ባለውለታ ታሪካቸው ወደ ፊት ተበጥሮ ይወጣል የሚል እምነት ያለን ሲሆን፤ ለአሁኑ ማለት የምንችለው ከማንም በላይ የለፉ ሆነው፤ ከማንም በላይ የተጉ ሆነው … ሳለ ብዙም ሲነገርላቸው አለመሰማቱ ተገቢ አይደለም የሚል ትዝብት የለንም ማለት ግን አይደለም።
ዛሬ ”መዝገበ ቃላት” የሚለውን አስቀድመው ወይም አስከትለው (እንደየ ቋንቋው ማለት ነው) አደባባይ የወጡ መዝገበ ቃላት በርካቶች ናቸው። በእውነት ደስ ይላል።
እርግጥ ነው አንድ መዝገበ ቃላት በዋናነት ቢያንስ አምስት ጉዳዮችን ማስተናገድ (ጥያቄዎችን መመለስ) አለበት የሚል ሙያዊ ድምዳሜ አለ። ወይም እራሱ የመዝገበ ቃላት አዘገጃጀቱና አላማው እነዚህን ዋና ዋና ጉዳዮች በመሰረታዊነት ሊይዝ ይገባል።
እነዚህ ዋና ዋና ጉዳዮች (ወይም፣ ሊመለሱ የሚገባቸው ጥያቄዎች) ንበት (ፕሮናውንሴሽን)፣ ብያኔ (ዴፊኒሽን)፣ ትርጉም (ሚኒንግ)፣ ቃሉ መቼ እንደተፈጠረ፣ የቃሉን የንግግር ክፍል (ስም፣ ግስ…)፣ የት እንደተፈጠረ … መመለስ ሲሆን፤ ”ዛሬ በተለያዩ የአገራችን ቋንቋዎች እየተዘጋጁ ያሉት ምን ያህል እነዚህን መሰረታዊ ጉዳዮች አስተናግደዋል?” የሚለውን እዚህ መነጋገር ባይቻልም፤ በዛን ዘመን የተዘጋጀው የተሰማ ሀይለሚካኤል ”ከሳቴ ብርሀን የአማርኛ መዝገበ ቃላት” (የመጽሐፉ የ2008 እትም ዛሬም mereb.shop ላይ 36.05 ዶላር እየተቸበቸበ ይገኛል፤ ይህም ውድ ዋጋ መሆኑን ልብ ይሏል።) ግን በዚህ እንደማይታማ ተደጋግሞ የታየ፤ የተመረመረ፤ ተመርምሮን ይሁንታን ያገኘ ጉዳይ ነው።
መቼም ጥናትና ምርምርንም ይሁን ማንኛውንም አይነት በሳል ጽሑፍ የሚያዘጋጅ ሰው የከሳቴ ብርሃን ተሰማን ”የአማርኛ መዝገበ ቃላት”፤ የኪዳነ ወልድ ክፍሌን ”መጽሐፈ ስዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ”ንና ሌሎችንም ሳይጠቅስ፤ ወይም፣ ከእነዚህ መካከል አንዱን ዋቢ ሳያደርግ ይቀራል ማለት ዘበት ነው። በተለይ ለቃላት ብያኔን መስጠት የግድ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ እነዚህን ቱባ ቱባ ራዎች ማገላበጥ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታ ነው። ይህንን በምሳሌ እንየው ካልን በአንድ መጣጥፍ ውስጥ ያለውን፤ ስለ ”ኑፋቄ” ምንነት የሚያብራራውና፤
እንደሚሰጡት ፍቺ ከሆነ፣ “ኑፋቄ” “ነፈቀ – ከሃይማኖት ወጣ፣ ተጠራጠረ፣ መናፈቅን፣ ከሓዲን ኾነ ነፈቀ፡፡” የሚል ትርጉም ይይዛል። በዚህ ትርጉም መሠረት “ነፈቀ” ማለት ከትክክለኛው የእምነት መንገድ ወጣ፣ ሳተ ወይም ትክክለኛውን እምነት ካደ፣ ተጠራጠረ ማለት ነው። የኪዳነ ወልድ ክፍሌም፤ ”መጽሐፈ ስዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ” ደግሞ “መናፍቅ (ቃት፣ ቃን) ናፈቂ፣ አናፈቂ፣ የሚጠራጠር፣ የሚያጠራጥር፣ ጠርጣሪ፤ ሃይማኖቱ ሕጹጽ የሆነ፣ ሙሉ እና ፍፁም ትክክል ያይደለ፤ መንፈቁን አምኖ መንፈቁን የሚክድ፡፡” አለቃ ኪዳን ወልድ ክፍሌ በበኩላቸው መናፈቅ ማለት እምነቱ ትክክል ያልሆነ፣ ግማሽ እውነት ግማሽ ሐሰት የሆነ እምነት ማለት ነው የሚለውን ያክላሉ፡፡
የሚለውን። እንዲሁም፣ ”በገና” የሙዚቃ መሳሪያ (መንፈሳዊ)ን በተመለከተ ከቀረበ ጽሑፍ ያገኘነውን እንመልከት፤
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ “መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ መዝገበ ቃላት ሐዲስ” በሚል መጽሐፋቸው በሁለት መልኩ ማለት “ሲጠብቅና ሲላላ” ብለው በማመሳጠር እንዲህ ብለው ተርጉመውታል። በገና፡- በዕብራይስጥ ናጌን ይባላል ካሉ በኋላ ሲተረጉሙት፡- ነዘረ፣ መታ፣ ደረደረ፣ ማለት ነው። ሲጠብቅ ግን፡- ነደደ፣ ተቆጣ… ያሰኛል ብሏል፡፡
በገና፡- በቁሙ መዝሙር ማለት ነው ብለውም ፈትተውታል። (አለቃ ኪዳነ ወልደ ክፍሌ፡ መጽሐፈ ስዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ) አባ ዮሐንስ ገ/እግዚአብሔር የትግርኛ መዝገበ ቃላት በተባለ መጽሐፋቸው፡- በገናን በቁሙ በገና ብለው ተርጉመውታል። (አባ ዮሐንስ ገ/እግዚአብሔር፣ ትግርኛ አማርኛ መዝገበ ቃላት፣ 1948፣ አሥመራ) ከሳቴ ብርሃን ተሰማ “የአማርኛ መዝገበ ቃላት” በተሰኘ መጽሐፋቸው እንዲህ ዓይነት ትርጉም ሰጥተውታል፡፡
– በገና፡- በአሥር አዉታር ጅማት በገናን ሠራ፣ ቃኘ፣ ደረደረ፣ ድምጽን እያጣራ፣ እያጣቀሰ፣ እየነዘረ… በገናን በገነ… ካሉ በኋላ – በገነኛ፡- የሚለው ደግሞ በገናን የሚመታ፣ በገናን የሚያውቅ ደርዳሪ… ማለት ነው ብለው ተርጉመውታል፡፡
ከዚህ የምንገነዘበው የመዝገበ ቃላት ፋይዳ ከዚህ በመላስ የማይባል ብቻ ሳይሆን፤ ፋይዳው የማይተካና የማይታለፍም መሆኑን ነውና ባለፈው ያስታወስናቸው ባለውለታዎቻችንም ሆኑ የዛሬው (ከሳቴ ብርሃን ተሰማ) ተሰማ ሀብተሚካኤል (ልክ የእንግሊዝኛ ዲክሽነሪ ሲነሳ Father of the Modern Dictionary በሚል ማህበራዊ ማእረግ ስሙ የሚታወቀው ሳሙኤል ጆንሰን ሳይነሳ እንደማይታለፈው ሁሉ) ”ሰው ያደረጉን” ናቸውና ሌሎችም አርኣያነታቸውን ሊከተሉ እንደሚገባ ይሰማናል። በሌላው አለም ለእነሱ አይነት ሰዎች የሚሰጠው ማህበራዊ ስፍራ ወደዚህም መጥቶ እነሱም ተገቢ ውለታቸው ይከፈላቸዋል፤ በመጪው ትውልድም ሲዘከር ይኖራል ብለን እናምናለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11 /2014