ገና ከልጅነታቸው አንስቶ ለንግድ ሥራ የተሰጡ ናቸው:: በሕይወት ዘመናቸው ችግር ነው ያሉትን ሁሉ ወደ እድል ለመቀየር ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ:: በጥረታቸውም ስኬታማ መሆን ችለዋል:: ለጊዜ ትልቅ ዋጋ የሚሰጡና የጊዜን ጥቅም በሚገባ መረዳት የቻሉም ናቸው:: ማንም ሰው ጊዜውን በአግባቡ መጠቀም ከቻለ ስኬታማ መሆን ይችላል የሚል ጠንካራ እምነት አላቸው::
ይህን እምነታቸውን በተግባር በማዋል የወጣትነት ጊዜያቸውን በሥራና ሥራ ላይ ብቻ አድርገዋል:: ተማሪ እያሉ ጀምሮ ትርፍ ጊዜያቸውን ትናንሽ በሚባሉ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ አሳልፈዋል:: ከልጅነት ጊዜያቸው ጀምረውም ንግድ አዋጭ የሆነ ሥራ ስለመሆኑ በተግባር መረዳት ችለዋል:: በመሆኑም ከልጅነት እስከ ዕውቀት የተሰማሩበትን የንግድ ሥራ በማሳደግ ዛሬ ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ያስቻሉ ሶስት ኢንዱስትሪዎች ባለቤት ለመሆን በቅተዋል::
ተወልደው ባደጉበት አካባቢ ከትናንሽ ንግድ ጀምረው፤ በተለያዩ ወጪ ገቢ የንግድ ሥራዎች ውስጥ የተሳተፉት የዛሬው እንግዳችን አቶ ታዬ ተፈሪ ጂማ ይባላሉ:: አቶ ታዬ፤ በአሁኑ ወቅት በቡራዩ ከተማ በታጠቅ ኢንዱስትሪ መንደር ሁለት ፋብሪካዎች እንዲሁም በድሬዳዋ የቡና ማቀነባበሪያ ፋብሪካ አላቸው:: በቡራዩ ከሚገኙት ፋብሪካዎች አንደኛው ኒው ፍላወር ፎም ይባላል፤ ሁለተኛው ደግሞ ኒው ፍላወር የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ነው::
የእነዚህ ሶስት ድርጅቶች መስራችና ባለቤት የሆኑት አቶ ታዬ፤ ሰሜን ሸዋ ሰላሌ አካባቢ ተወልደው ሀረር ከተማ ነው ያደጉት:: በጫትና በንግድ በምትታወቀውና ሞቅ ደመቅ ባለችው ሀረር ከተማ ያደጉት አቶ ታዬ፤ በአካባቢው ማደጋቸው በንግዱ ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆኑ እንዳገዛቸው ነው የሚናገሩት::
ከአርሶ አደር ቤተሰብ የተገኙት አቶ ታዬ፤ በቤተሰብ እቅፍ ውስጥ ሆነው ምቾታቸው ተጠብቆ ለመኖር አልታደሉምና ከቤተሰብ ተለይተው ሀረር ላይ ከዘመድ ጋር ነው ያደጉት፤ ከቤተሰብ ውጭ ማደግ በራሱ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳለው ጠቅሰው፣ ለተለያዩ ፍላጎቶች በቀላሉ መልስ ማግኘት አያስችልም ይላሉ:: እሳቸውን ግን ጠንካራና ብርቱ ሳያደርጋቸው እንዳልቀረም ይናገራሉ::
ጎዶሎዎችን ለመሙላትም ሆነ ጎዶሎውን አምኖ ለመቀበል ግን የሰውዬው ምርጫ ወሳኝ ነው፤ ብለው የሚያምኑት አቶ ታዬ፤ ታዲያ የነበራቸው ምርጫ አንድና አንድ ጎዶሏቸውን በጥረታቸው መሙላት ነበር:: እናም ከቤተዘመድ ጋር ሲያድጉ ይገጥማቸው የነበሩ ችግሮችን ሁሉ በራሳቸው ጥረት ለመፍታት ከላይ ታች ብለዋል፤ ወጥተዋል፤ ወርደዋል፤ ሰዎች የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለማለፍ በሚያደርጉት ጥረት ልክ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉና ችግር በራሱ ዕድል እንደሆነ የሚያምኑት አቶ ታዬ፤ በቤተዘመድ እጅ ውስጥ ማደጋቸው ራሳቸውን ለማሸነፍ ጥሩ መንገድ እንደሆነላቸው ይናገራሉ::
ሰዎች ድህነትን እንደ ጥሩ አጋጣሚ ሊጠቀሙበት ይገባል ብለው የሚያምኑት አቶ ታዬ፤ በሕይወታችን ማግኘት የምንፈልጋቸውን ነገሮች ለማግኘት የምንጠቀመው ጥረትና የምናወጣው ኢነርጂ ኃይል ሊፈጥር እንደሚችል ያስረዳሉ:: ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ደግሞ ይበልጥ ፍሬያማ ሊያደርግ የሚችል ቁልፍ መሳሪያ እንደሆነ በመጥቀስ ጊዜያቸውን በአግባቡ ተጠቅመው ከልጅነት እስከ ዕውቀት ኑሮን በማሸነፍ ትግል ውስጥ አልፈዋል:: በዚህም ከሱቅ በደረቴ ንግድ ተነስተው ወጪ ገቢ ንግድን አሳልጠው ለበርካታ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችሉ ሦስት ፋብሪካዎች ባለቤት ለመሆን በቅተዋል፡፡
ወደ ንግድ እንዲገቡ ምክንያት የሆናቸው ችግር ቢሆንም፣ ለንግድ ሥራ ከፍተኛ የሆነ ውስጣዊ ፍላጎት የነበራቸው መሆኑን አቶ ታዬ ያስታውሳሉ:: ሀረር የጫት አገር እንደመሆኑም ለውዝን ጨምሮ የተለያዩ ሸቀጦችን በእጃቸው ይዘው ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው ነግደዋል::
ይህ አይነት ንግድ በአካባቢው አጠራር ‹‹ጀብሎ›› ይባላል:: የጀብሎ ንግድ አዲስ አበባ ከተማ ላይ ሱቅ በደረቴ የሚባለው የንግድ አይነት መሆኑ ነው:: ጊዜያቸውን በአግባቡ የተጠቀሙት አቶ ታዬ፤ ከአፍላ ዕድሜያቸው ጀምረው ሀረር ከተማ ላይ የተለያዩ ሸቀጦችን በማዞር የጀብሎ ንግድን አቀላጥፈው ነግደዋል:: በትንሹ የጀመሩት ንግድ መሰረት እስኪይዝ ድረስም በርካታ ውጣውረዶችን አሳልፈዋል::
ከጀብሎ ንግድ ቀጥለው የተለያዩ አልባሳትና የአንሶላ ጨርቆችን በሀረር ዙሪያ በሚገኙ የገጠር ከተሞች በሙሉ ተመላልሰው የነገዱት አቶ ታዬ፤ ለአብነትም ቆቦ፣ ለገገባ፣ ቆሬና አረርቲ፣ ገንደሮባ፣ ዳዱ፣ በደኖና በሌሎችም ገጠራማ አካባቢዎች መኪና በማይታሰብበት በዚያን ወቅት ወጣትነት ትኩስ ኃይል ሆኗቸው በእግራቸው ተመላልሰው መነገድ በመቻላቸው እነሆ ዛሬ ከከፍታው ማማ ላይ ደርሰዋል::
በአሁኑ ወቅት በቡራዩ ከተማ የኢንዱስትሪ መንደር ሁለት ፋብሪካዎችን እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ የቡና ማቀነባባሪያ ፋብሪካን እያስተዳደሩ የሚገኙት አቶ ታዬ፤ ቡናን ከሚያለሙ በሀረር አካባቢ ከሚገኙ አርሶ አደሮችና በሌሎች አካባቢዎች ከሚገኙ አርሶ አደሮች ጋር ትስስር በመፍጠር በያመቱ ቡና ለውጭ ገበያ ያቀርባሉ::
በድሬዳዋ ከተማ በአስር ሺ ካሬ ሜትር ስፋት ቦታ ላይ ባረፈው በዚህ የቡና ማቀነባበሪያ ፋብሪካቸው ከአርሶ አደሩ የሚሰበሰበውን ቡና በማቀነባበር በመቀሸር፣ በማበጠርና በመልቀም ለሳውዳረቢያ፣ ለአሜሪካ፣ ለጃፓንና ለኮሪያ ገበያ ይቀርባል:: በዚህም ለአገሪቷ የውጭ ምንዛሪ ግኝት የድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ::
በኒው ፍላወር የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ባለ ሁለት፣ ሶስትና አራት እግር ተሽከርካሪዎች ይገጣጠማሉ፤ በተለይም ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ የሆነው ባጃጅ ለበርካታ የአገሪቱ ወጣቶች የሥራ ዕደል በመፍጠር ትልቅ አበርክቶ እያደረገ ይገኛል:: ለማህበረሰቡ የትራንስፖርት ችግርን ከመቅረፍ ጀምሮ ለወጣቶች የሥራ ዕድል እየፈጠረ በመሆኑ ፋብሪካው በተለይ ባለ ሶስት እግር ባጃጆችን በስፋት እንደሚገጣጠም አቶ ታዬ ያብራራሉ::
በአሁኑ ወቅት በየአካባቢው እየተርመሰመሱ ለሚገኙት ባለ ሶስት እገር ባጃጆች እርሳቸው ድርጅት የሆነው ኒው ፍላወር የመኪና መገጣጠሚያ ትልቅ ድርሻ አለው:: በርካታ ቁጥር ያላቸውን ህንድ ሰራሽ ባጃጆች አካላትን ከህንድ እያስመጡ በህንዳውያን ባለሙያዎች በመገጣጠም ለገበያ እያቀረቡ ናቸው::
አብዛኞቹ የባጃጅ ዕቃዎች ከህንድ የሚመጡ ቢሆንም፣ በአገሪቷ አቅም ልክ የሆኑ የተወሰኑ ዕቃዎች ግን በአገር ውስጥ የሚገኙ ስለመሆናቸው አቶ ታዬ፤ ይናገራሉ:: በአገር ውስጥ የማይገኙት ዕቃዎች ደግሞ ከህንድ አገር የሚመጡት የባጃጅ አካላት በአገር ውስጥ ተገጣጥመው በኤጀንቶች አማካኝነት ለገበያ እየዋሉ እንደሆነ ተናግረዋል::
‹‹ከህንዶቹ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ባጃጆቹን ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ መመረት እንዲችሉ የማድረግ ዕቅድ አለኝ›› ያሉት አቶ ታዬ፤ በአሁኑ ወቅትም በተለያዩ የሥራ ክፍሎች ውስጥ እንዲሰሩ ከህንድ አገር ቀጥረው ያስመጧቸው 20 የሚደርሱ ህንዳውያን ስለመኖራቸው አንስተዋል:: ህንዳውያኑም በዘርፉ ያላቸውን ዕውቀት ለኢትዮጵያውያን በማሸጋገር ኢትዮጵያውያኖች ሰልጥነው ብቁ ሲሆኑ እንደሚመለሱ ነው ያጫወቱን:: በቀጣምይም ይህንን አጠናክሮ በማስቀጠልና አስፈላጊ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን በማሟላት ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ ለመሥራት ጥረት እያደረጉ እንደሆነም አቶ ታዬ ይጠቁማሉ::
ለአልጋ፣ ለሶፋ፣ ለመኪና እና ለሌሎች ተግባራት የሚውለው ፎምም እንዲሁ በኒው ፍላወር ፎም ፋብሪካ ተመርቶ ለተለያዩ ጅምላ ሻጮች ወይም ደግሞ ወኪል አከፋፋዮች ይቀርባል:: በእነዚህ ወኪል አከፋፋዮች አማካኝነትም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ምርቱ ተደራሽ ይሆናል::
በእነዚህ ሶስት ፋብሪካዎች ውስጥ ሰርተው የሚውሉ፤ እንጀራ መብላት የቻሉና ከራሳቸው አልፈው ቤተሰብ ማስተዳደር የጀመሩ 1400 የሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ስለመሆኑ አቶ ታዬ አጫውተውናል::
ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድም አቶ ታዬ፤ የተለያዩ አገልግሎቶችን እየሰጡ ናቸው:: ለአብነትም በቡራዩ ከተማ የእርሳቸውን ሁለት ፋብሪካዎች ጨምሮ በርካታ ፋብሪካዎች ለሚገኙበት ታጠቅ የኢንዱስትሪ መንደርና በአካባቢው ለሚገኘው የፌስቱላ ሆስፒታል ጭምር አገልግሎት መስጠት የሚችል የአስፓልት መንገድ ሲሰራ በኢንዱስትሪ መንደር ውስጥ የሚገኙ የፋብሪካ ባለቤቶችን በማስተባበር ሰርተዋል::
አቶ ታዬ፤ በወቅቱ ሃሳቡን ያነሱት በዋናነት በፋብሪካዎች ውስጥ የሚመረቱ የተለያዩ ምርቶች ምግብና መጠጥን የሚጨምሩ እንደመሆናቸው ከብክለት ነጻ እንዲሆኑ በማሰብ ነው:: ከዚህ ባለፈም በአካባቢው ከሁለት መቶ ሺ እስከ ሶስት መቶ ሺ የሚደርሱ ሠራተኞች የሚጠቀሙበት መንገድ መሆኑም ጭምር የመንገዱ አስፓልት መሆን የግድ እንደነበር ነው የሚናገሩት:: ይሁንና በጋራ የጀመሩት የአስፓልት ሥራ ዳር ሳይደርስ ከህዝብ የተሰበሰበው ገንዘብ በአጭበርባሪዎች ተበልቶ ቀርቷል::
ለዚህም ምክንያቱ በሥራው ያላቸው ልምድና ዕውቀት ማነስ እንደነበር ያነሱት አቶ ታዬ፤ በድርጊቱ ቁጭት ገብቷቸው ‹‹ተጀምሮ የሚቀር ሥራ የለም›› በማለት የመንገድ ሥራው እንዲጠናቀቅ በግላቸው ተንቀሳቅሰው ብዙ ዋጋም ከፍለው መንገዱ እንዲጠናቀቅ አድርገዋል::
የአስፓልት መንገድ ሥራውም በአስር ኮንስትራክሽን የተሠራ ሲሆን፣ አቶ ታዬ በግላቸው 35 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ የመንገድ ሥራው እንዲጠናቀቅ በማድረግ ቁጭታቸውን ተወጥተዋል:: በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የአስፓልት መንገዱ ለአካባቢው ማህበረሰብ፣ በኢንዱስትሪው ውስጥ ለሚሠሩ ሠራተኞችና በፌስቱላ ሆስፒታል ተገልጋይ ለሆኑ ተጎጂዎች ጭምር ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል::
ከዚህ በተጨማሪም ስድስት ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ለመንገዱ መግቢያ ያሰሩ ሲሆን፤ ከመግቢያው ጀምሮ አጠቃላይ መንገዱ በጀነራል ታደሰ ብሩ ስም ተሰይሟል:: ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያትም ጀነራሉ በጀግንነት የአገራቸውን ሉዓላዊነት ከማስከበር ባለፈ በአገሪቱ አንድነትን፣ ትምህርትንና ሌሎች በጎ ተግባሮችን በማበርከት ያላቸውን የአገር ፍቅር ስሜት በተግባር ያስመሰከሩ አገር ወዳድ በመሆናቸው ነው ይላሉ::
የአስፓልት መንገዱ ሁለት ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር ርዝመትና 10 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፤ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለውም አቶ ታዬ አስረድተዋል:: መንገዱ በአካባቢው ከሚገኙ ነዋሪዎችና ሠራተኞች ባለፈ የኢንዱስትሪ መንደሩ ምርቶች ንጽህናው በተጠበቀና በተቀላጠፈ መንገድ ለገበያ እንዲቀርቡ በማድረግም መላው የአገሪቱ ህዝብም ተጠቃሚ መሆን እንዲችል የተደረገበት መሆኑን ያብራራሉ::
በእነዚህና በሌሎችም የልማት ሥራዎች በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ የሚገኙት አቶ ታዬ፤ በተለይም አገራዊ ለሆኑ ማንኛቸውም ጥሪዎች ምላሽ ለመስጠት ቀዳሚ ናቸው:: በዚህም ጥቂት የማይባሉ የምስክር ወረቀቶችንና ዋንጫዎችን ከቡራዩ ከተማ እንዲሁም ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ተበርክቶላቸዋል::
በቀጣይም በተሰማሩበት የሥራ ዘርፎች ይበልጥ ጠንክረው በመሥራት ውጤታማ ለመሆን ዕቅድ እንዳላቸው ያጫወቱን አቶ ታዬ፤ ‹‹እያንዳንዱ ሰው ጊዜውን በአግባቡ ተጠቅሞ ከሰራ ውጤታማ መሆን ይችላል›› በማለት ሀሳባቸውን ቋጭተዋል::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 7 /2014