ጋብቻ ማለት በስነ ልቦና፣ በስነ አእምሮ እና አካላዊ ጥምረት ቤተሰብ ለማስተዳደር ወይም ለመምራት አንድ ወንድ እና አንድ ሴት ባልና ሚስት ሆነው ወደውና ፈቅደው በፍቅር የሚጣመሩበት ትልቅ የቤተሰብ መመስረቻ ነው። በሂደቱም ያዳበሯቸውን ማህበራዊ ዕሴቶች በህግ አግባብ የሚተገብሩበት ነው።
አንዳንድ ፀሀፍት ጋብቻ “አንድ ወንድና አንድ ሴት ባልና ሚስት ሆነው ለመኖርና የህግ፣ ሃይማኖታዊና ማህበራዊ ኃላፊነትን ለመውሰድ ተስማምተው የሚመሰርቱት ግንኙነት ነው።” የሚል ጠባብ ትርጉም ሲሰጡት በሌላ በኩል “ጋብቻ በተለያየ የስርዓት አይነት፣ ቤተሰባዊ ትስስር ለመፍጠር፣ የሚመሰረት በህግ እውቅና የተሰጠውና የጋራ ጥቅም፣ ኃላፊነትና ግዴታ የሚያስከትል እንዲሁም የዝምድና ትስስር የሚመሰረት ግንኙነት ነው።” ሲሉ የሚገልፁትም አልታጡም።
በአጠቃላይ ግን ‹‹ ጋብቻ ›› በአንድ ወንድ እና በአንዲት ሴት ቤተሰብ የመመስረት ወይም የመፍጠር ነጻ ፍላጎት ባልና ሚስት የመሆን ፍቃደኝነት ላይ የሚመሰረትና በሁለቱ መካከል የሚገኙ ሰዎችን በዝምድና የሚያስተሳስር በባልና ሚስቱ እንዲሁም በማህበረሰቡ መካከል ትስስር የሚፈጥር ህጋዊ፣ ማህበራዊ እና ሃይማኖታዊ ኃላፊነት እና ግዴታን የሚያስከትል ግንኙነት ነው የሚል ጠቅላላ ግንዛቤን (ትርጓሜ) ይሰጠዋል።
የተለያዩ ፀሃፍት የተለያየ ትርጓሜ የሰጡት ትዳር ባልተፃፈ ህግ ማህበረሰቡ በልቡ በከተባቸው በተለያዩ ስርአቶች ይመራል። መከባበሩ፣ መዋደዱ፣ መተማመኑ ትዳርን ከሚያጠብቁት ገመዶች አንዱ ነው። አብሮ በመኖር መንገድ ውስጥ ፍሬ ማፍራቱ አብሮ ማርጀቱ የእድሜ ልክ ትስስሩ ለጋብቻ የተለየ ትርጉም እንዲኖረን ቢያደርግም ሁሉም ትዳር ግን እንቅፋት ሳይመታው ቀጥ ብሎ የተጓዘ ነው ለማለት አያስደፍርም። እንኳን ሰው እግር እና እግር እንኳን ይጋጫልና በትዳር መካከል ግጭቶች ፣አለመግባባቶችና ጭቅጭቆች ያጋጥማሉ። ይህም ግጭት በቀላሉ በእርቅ በይቅርታ የሚደመደም ሊሆን ይችላል። አንዳንዴ ደግሞ ግጭቱ የከረረ ይሆንና ጉዳዩ የፍትህ አካላት ደጅ ይደርሳል። አንቺ ትብሽ አንተ ትብስ ተባብሎ የተመሰረተው የተከበረው ትዳርም እንዲሁ ይበተናል።
በትዳር መካከል የሚያስቀና ትዳር ልክ እንደነእከሌና እከሊት የሚያስብል ደግሞ ያጋጥማል።ሚስት ቀኑን ሙሉ ደፋ ቀና እያለች አጣፍጣ ሰርታ ያቀረበቸውን ምግብ ባል ካንቺ በፊት አልጎርስም ሲል በመጀመሪያ ጉርሻው ፍቅሩን ሲገለጥላት፤ አረፍ በይ በሚል ቃል መተሳሰባቸውን የሚያሳዩበት፤ ከሁሉ በላይ ለብሳ ደምቃ እንድትታይ አዲስ አዲሱን መግዛት ማልበሱ ፍቅርን የሚያደረጁ የመተሳሰብ ምልክቶች ናቸው። ስለ ልጆቻቸው የጋራ ጉዳይ በጋራ መወሰናቸው ብቻ ሳይፃፍ መመሪያ ሳይወጣ በፍቅር መስመር ውስጥ የሚሰመር የህይወት ረጅም መንገድ ነው ። ይህ መስመር ደግሞ ከትናንሽ ግጭቶች አንስቶ እስከ ትላልቆቹ ጸብና ግጭት በመካከሉ በመፈጠሩ ትዳሩ ሰምሮ እንዳይሄድ መሰናከል ይሆናል። ለምን ግን በትዳር መካከል አባጣ ጎርባጣ ይበዛዋል፤ተዋደውና ተፋቅረው የተጋቡ ባልና ሚስት ለምን አይንሽን ላፈር ይባባላሉ?
የትዳር መንገድ
የዛሬዎቹ ባለታሪኮቻችን ገና በጠዋቱ የአፍላነት እድሜ ላይ ተጣምረው ለአመታት በትዳር ህይወት ቆይተዋል። በልጅነት እድሜያቸው ልጅህን ለልጄ በሚለው የአካባቢው ባህል መሰረት ተጣምረው መኖር ከጀመሩ ከራርመዋል። ለወትሮው እርስ በእርስ በፍቅር ከመተያየት ያለፈ ፀብ በቅጡም ታይቶባቸው አያውቅም ነበር፤ ከተራ የእለት ግጭት አልፎ አሳልፎ እስከመሰጣጠት የደረሰ ጥልም አልነበራቸውም ይላሉ የሚያውቋቸው።
በዚህ ልክ በባለቤቷ ላይ ያላትን እምነት አሳጥቶ ለበላንጣዎቹ አሳልፎ እስከመስጠት ያደረሳት ጉዳይ በውል አልታወቀም፤ እምነቷን የሸረሸረው ምንም ይሁን ምን ባለቤቷን አሳልፎ እስከመስጠት የደረሰ ጥላቻ ውስጥ ገብተዋል።
‹‹ከአንተ በፊት ያድረገኝ ፤ ካንቺ በፊት ያደርገኝ›› ሲባባሉ የኖሩት ባልና ሚስት ለወዳጅ ጎረቤት የሚያስቀናው ፍቅራቸው ወደ ጥላቻ ተቀይሮ በጥርጣሬ መተያየት ከተጀመረ እሷማ እኔን ለማጥፋት ታስባለች፤ እሱማ ቢገለኝ ደስታው ነው መባባልም ጀምረው እንደነበር አንዳንድ ወዳጆቻቸው ይናገራሉ። እንዲህ አንዲህ እያለ በቂምና ጥላቻ የተቋረጠው የፍቅር መንገድ ነው የትዳር አጋሯን ለጠላቶቹ አሳልፋ እንድትሰጥ ያደረጋት።
በቀላሉ በመነጋገር ሊፈቱ የሚችሉ ግጭቶች ተጠራቅመው በሆድ ውስጥ ውለው ሲያድሩ ቁርሾ ይሆናሉ። ያ ቁርሾ ደግሞ በበቀል ሊገለጥ ሲያስብ ‹‹ሰይጣን ምን ሰርቶ ይብላ›› እንዲሉ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሮ የራስን ግማሽ አካል አሳልፎ እስከመስጠት የሚያደርስ ቂም ያሳድራል።
የሞት ድግስ
ቂም የወለደው የሞት ድግስ ታህሳስ ሀያ ሁለት 2013 ዓ.ም ነው የሆነው። ወይዘሮ ሀና አዘዘና ባለቤቷ አደራው ከቤ በአንድ ቤት በፍቅር በመከባበር ይኖሩ ነበር። ሀና የሀያ ሁለት አመት ወጣት ናት። ጥንዶቹ በታዳጊ የእድሜ ክልል ላይ ሆነው ነው ትዳር የመሰረቱት። ነዋሪነታቸው በአማራ ክልል በጎጃም ክፍለ ሀገር አነደድ የተባለ ወረዳ ሻፎ በተባለ ቀበሌ ውስጥ ነበር። ጥንዶቹ ድርጊቱ በተፈፀመ እለት ማለትም ታህሳስ ሀያ ሁለት 2013 ዓ.ም ጁቤ ከተማ ሰፈር ሁለት በሚባለው አካባቢ አደራው ከቤና ሀና አዘዘ እንደ ሁልጊዜያቸው እራታቸውን በልተው ቤት ያፈራውን መጠጥ እየተጎነጩ ነበር። አደራው በደስታ የምታስተናግደው ሚስቱን እየተመለከት እያሳለፉት ስላለው የፍቅር ምሽት ያስባል፤ እሷ ደግሞ የቧላን መስከርና በልቧ ያሰበችውን እኩይ ተግባር ለመፈፀም በጉጉት ትጠባበቃለች።
በእለቱ ከባል ማለትም ከአደራው ጋር ፀብ የነበራቸው ሁለት ግለሰቦች ጋር የሸረበቻት ሴራ ነበረች። እነዚህ ላቄ ጫኔና ቢያድግ ሉሌ የተባሉ ሁለት ግለሰቦች በአርባዎቹ እድሜ ክልል ላይ የሚገኙት ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ጠላታችን ነው ወዳሉት ወደ አደራው ቤት በመምጣት ሚስቱን ያግቧቧት ጀመር።
ባልሽን መጠጥ አጠጥተሽ አስክሪልን ሲሉ ካግባቧት በኋላ ከአካባቢው ዞር ይላሉ። ወትሮም ሆዷ ጎሾ የነበረችው ሀና ባሏን አሳልፋ ለመስጠት አላንገራገረችም። እሷም የተባለችውን ለማድረግ ከወትሮው በተለየ ፍቅር ተንከባክባ ባለቤቷን ራቱን አብልታ ቤት ባፈራው መጠጥ በአናት በአናቱ እየደጋገመ እንዲጠጣ በመገፋፋት ታሰክረዋለች። በአናት በአናቱ የተቀዳለትን አረቄ መቋቋም ያቃተው ባል በስካር አቅሉን ሲስት ቀስ ብሎ አልጋው ላይ ጋደም ይላል። ያን ጊዜ ደመኞቹን ወደ ቤት ታስገባለች።
በሚገርም ሁኔታ ወይዘሮዋ ባሏ ከእነዚህ ሁለት ሰዎች ጋር በምን እንደተጋጨ ሳትጠይቅ ነበር ባሏን አስክራ ለበላንጣዎቹ አሳልፋ የሰጠችው። ፖሊስ ባጠናቀረው መረጃ ላይ ይች ሴት ባሏን እንዲህ በማድረጓ ምን እንደምትጠቀም አልተገለፀም።
የባላንጣዎቹ ክፉ እጅ
ከባላንጣቸው ቤት አቅራቢያ ተደብቀው እስኪጠሩ የሚጠባበቁት በቀል ያረገዙት ጓደኛሞች በስካር ደንዝዞ እንቅልፍ የወሰደው ግለሰብን ቤቱ ድረስ በመግባት በብረት አንገቱንና የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ቀጥቅጠው ህይወቱ እንዲያልፍ አድርገውታል። ይህንንም ያደረጉት ቀን ገበያ ደርሰው ሲመለሱ ጎራ ካሉበት መጠጥ ቤት አንድ ሁለት ሲባባሉ በተወራወሩት ቃል የተነሳ በያዙት ቂም ነበር። በይቅርታ መተላለፍ ወይም ወደ ህግ መሄድ ሲገባ ባልተገባ ሁኔታ በበቀል በመነሳሳት ክቡሩ የሰው ልጅ ህይወት እንዲጠፋ ሆነ። ቀጥቅጠው መግደላቸው ሳያንስ አስከሬኑን በኬሻ ጠቅልለው በአካባቢያቸው በሚገኘው ማሩ በተባለ ወንዝ ጥለውት ከአካባቢው ይሰወራሉ።
የፖሊስ ምርመራ
ይህ ድርጊት ከተከሰተበት ከታህሳስ ሀያ ሁለት እስከ ጥር አስራ ስድስት ድረስ ለአንድ ወር ጥቂት ቀን እስኪቀረው ድረስ የሟች መድረሻ ሳይታወቅ እምን ይግባ ሰማሁ አየሁ የሚል ጠፍቶ ቆየ። ሚስቲቱም ከባሏ መጥፋት በላይ የሰራችው ወንጀል ውስጥ ውስጧን እየበላት ጠፋ የተባለውን ባሏን በመፈለግና ባለመፈለግ መካከል ቆማ ትናውዝ ነበር። ከአንድ ወር በኋላ ግን ወደ ገበያ ሲሄዱ የነበሩ መንገደኞች አስክሬኑን አግኝተው ለፖሊስ ጥቆማቸውን ይሰጣሉ። የሟች አስክሬን ከተገኘ በኋላ ፖሊስ ም ርመራውን ይጀምራል።
ፖሊስ ምርመራውን የጀመረው ከቤተሰብ ወይም ከሟች ጋር ቅርበት ካላቸው ሰዎች አካባቢ ነበር። የሟች የቅርብ ጓደኞችን ወዳጅ ዘመዱን ሟች ከማን ጋር ፀብ እንደነበረው ያጠያይቃሉ። ሟች አመለሸጋ መሬት እየገመሰ እልፍ ምርት የሚዝቅ ጠንካራ ገበሬ እንደነበረ እንብዛም ከሰው ጋር የማይጋጭ ሲነኩት የማይወድ አይነት ሰው እንደ ነበረ ብዙዎች ይመሰክራሉ።
ባለቤቱም ባሏ ከጠፋ በኋላ ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ሆኖባት ብዙም የተረጋጋ መንፈስ ስላልታየባት የምርመራ አቅጣጫው ወደሷ መዞር ጀመረ። በምርመራውም የዚህ አሰቃቂ ወንጀል ተባባሪ ባለቤቱ ሀና አዘዘ መሆኗን ፖሊስ ይረዳል። ፖሊስ የምስክሮችን ቃል የታክቲክና የቴክኒክ ማስረጃዎችን በማጠናከር ተጠርጣሪዎቹን ለምስራቅ ጎጃም የወንጀል አቃቤ ህግ በማድረስ ጉዳዩን ወደ ፍርድ እንዲቀርብ ያደርጋል።
አቃቤ ህግም የምርመራውን ውጤት በመያዝ ክስ የመሰረተ ሲሆን፤ በፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎች ቀርበው የእምነት ክህደት ቃላቸውን በመስጠት ጉዳዩ ሲታይ ቆይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።
ውሳኔ
አቃቤ ህግ ከአይን እማኞችና ከተለያዩ ምርመራዎች የተገኙ ማስረጃዎችና መረጃዎች ተጠናክሮ የቀረበለትን ማስረጃ በመያዝ የምስራቅ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል። ፍርድ ቤቱ መረጃዎችን ሲመረምር ቆይቶ በተከሳሾቹ ላይ የመጨረሻውን ፍርድ ለማሳለፍ በቀነ ቀጠሮ ተገኝቷል። ፍርድ ቤቱ ቀደም ሲል ተከሳሾች በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ መሆናቸውን አረጋግጦ የክስ መከላከያቸውን እንዲያቀርቡ ዕድል ሰጥቷል። ተከሳሾቹም ወንጀሉን ፈጽመው አላስተባበሉም።
ሰኔ አስራ ሰባት ቀን 2013 ዓ.ም የምስራቅ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት አንደኛ ተከሳሽ ሃና አዘዘ እጇ ከተያዘበት ቀን አንስቶ በሚቆጠር በአስራ ስድስት አመት ፅኑ እስራት እንድትቀጣ ውሳኔ ተላልፎባታል። ሁለተኛ ተከሳሽ ሟችን በብረት በመደብደብ ህይወቱ እንዲያልፍ ያደረገው ላቄ ጫኔ በአስራ ሰባት አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኗል። እንዲሁም ሶስተኛ ተከሳሽ ቢያድግ ሉሌ በአስራ ስድስት አመት ፅኑ እስራት እጃቸው ከተያዘ ጀምሮ በሚቆጠር ‹‹ይቀጡልኝ›› ሲል ውሳኔውን በማሳለፍ መዝገቡን ዘግቷል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ነሐሴ 7 /2014