
– ሶስተኛው ዙር የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በስኬት ተጠናቋል
አዲስ አበባ፡- ከአባይ ውሃ በሚገባቸው ልክ መጠቀም እንዳለባቸው የማያምኑ ካሉ የተፈጥሮን ሕግ ያዛባሉ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በትናንትናው ዕለት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን አስመልክቶ ባደረጉት የእንኳን ደስ አላችሁ ንግግር፤ የፈጣሪ ስጦታ የሆነውን የዓባይ ወንዝን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ለዓባይ 85 በመቶ የሚሆነውን ውሃ እያመነጨች ለዘመናት ሳትጠቀም መቆየቷ የሚያስቆጭ ቢሆንም፤ አሁን የሚገባንን ተጠቅመን የሚገባቸውን ለወንድሞቻችን ሰጥን በጋራ ለማደግ ዝግጁ ነን ብለዋል።
የዓባይ ውሃ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለም የተሰጠ ወንዝ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ውሃው በተለይ ለኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ ብሎም ለአፍሪካና ለዓለም እንዲጠቀሙበት ከፈጣሪ የተሰጠ ነፃ ስጦታ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የዓባይ ውሃ በነፃ የተሰጣቸው ሀገራት ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ሦስቱ ሀገራት ይህን ውሃ በነፃ የመጠቀም ዕድል የተሰጣቸው በመሆኑ የሚገባቸውን ድርሻ በአግባቡ መጠቀም ከቻሉ ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የአፍሪካ ወንድም እና እህቶችም ጭምር መጥቀም የሚችሉ በርካታ ሥራዎች መሥራት ይችላሉ ብለዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ፤ ከኢትዮጵያ፣ ከሱዳንና ከግብፅ የተሰጣቸውን ሀብት መገንዘብ፤ በተሰጣቸው ልክ መተባበር እና በጋራ መቆም ይጠበቃል። ነገር ግን ዓባይ ለሦስቱ ሀገራት እንደተሰጠና ሀገራቱ በሚገባቸው ድርሻ መጠቀም እንዳለባቸው የማያምኑ ኃይሎች ካሉ የተፈጥሮን ሕግ ያዛባሉ። ዓባይ ወንዝም በተፈጥሮ ይህን መፋሰሻ ሲይዝ ኢትዮጵያ የሚገባትን ተጠቅማ ሱዳንና ግብፅ ወንድሞችም እንዲጠቀሙበት በነፃ የተሰጠ ስጦታ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል።
አፍሪካም የዓባይ ውሃ ተጠቃሚ እንደምትሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል። የአፍሪካን ኢኮኖሚ ለማስተሳሰር የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውን በማንሳት አህጉሯን በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር አንዱ መንገድ ኢነርጂ መሆኑን አንስተዋል። የህዳሴው ግድብ ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ሲያመነጭ ለጎረቤት ሀገራት ብቻ ሳይሆን ከዚያም ተሻግሮ የሚጠቅም በመሆኑ ለአፍሪካ ሀገራ ኢኮኖሚያዊ ትስስር የራሱ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
የዓባይ ውሃ ከኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ ባለፈ የአፍረካ ሀገራትን መጥቀም የሚችል መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ በተመሳሳይ ለዓለምም ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ተናግረዋል። የዓለም ሕዝቦች ወደ አካባቢው በመምጣት እንዲዝናኑና ጊዜያቸውን በደስታ እንዲያሳልፉ የሚያስችል ከፍተኛ ብቃት አለውም ብለዋል። በታላቁ ህዳሴ ግድብ 70 የሚሆኑ ከፍተኛ ቦታዎችና ደሴቶች መኖራቸውን አንስተው ዓለም አካባቢው ምቹ መሆኑን ተገንዝቦ ለመጠቀምና ኢንቨስት ለማድረግ ዝግጁ መሆን እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።
በተጨማሪም የህዳሴው ግድብ ከሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል በተጨማሪ ሥነምህዳራዊ ጥቅሞች እንዳሉት ለዓሣ ርባታ ተስማሚ መሆኑንና በዓሳ ማስገር ለሚዝናኑ ቱሪስቶች ተዝናኖት እንዲሁም ለተራራ ላይ ጉዞ ለሚያዘወትሩ እና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ዘርፎች ምቹ መሆኑን ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዓባይ የኢትዮጵያ ኩራት፤ የብልፅግናዋ ጅማሮ መነሻ፤ ኢትዮጵያዊነት እና የኢትዮጵያ ከፍታ የሚለመልምበት ቦታ መሆኑን ተገንዝበን ኢትዮጵያዊ ሁሉ በጋራ በመደመርና አንድ ላይ በመቆም ብልፅግናችንን ዕውን እናድርግ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ለተሳተፉ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እና በዕውቀትና በጉልበት የተሳተፉ እንዲሁም በገንዘብ ድጋፍና በዲፕሎማሲ መስክ የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ላበረከቱ ምሥጋና ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ለግድቡ ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ መላው ኢትዮጵያውያንና አፍሪካውያን ወንድሞች እንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ግድቡ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 575 ሜትር ይፈስበት የነበረው ከፍታ በዘንድሮው ዓመት በ25 ሜትር ከፍ ብሎ 600 ሜትር ላይ የውሃው ፍሰት ይታያል። በግራና በቀኝ በኩልም ያለው ርዝመት 585 ሜትር የነበረ ሲሆን ዘንድሮ 611 ሜትር በመድረስ ውሃ የመያዝና ኃይል የማመንጨት አቅሙ ክፍ ብሏል።
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታው የተጀመረው በ2003 ዓ.ም ሲሆን ከትናንትና በስቲያ የሁለተኛው ተርባይን ኃይል የማመንጨት መርሃግብር ተበስሯል። በትናንትናው ዕለት ደግሞ የግድቡ ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት ተጠናቆ ውሃው በግድቡ አናት ላይ መፍሰስ ጀምሯል።
ውብሸት ሰንደቁ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 7 /2014