
አዲስ አበባ፡- የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በቀጣይ ሁለት ተኩል ዓመታት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ ታስቦ እየተሰራ መሆኑን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ገለጹ፡፡ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 83 ነጥብ ሦስት በመቶ መድረሱንም ጠቁመዋል፡፡
የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ተርባይን ኃይል ማመንጨት ማብሰሪያ ሥነ ሥርዓት ትናንት በጉባ በተካሄደበት ወቅት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በ2014ዓ.ም ለማከናወን ከተያዙት አበይት እቅዶች መካከል በሁለት ተርባይነሮችና ጀኔሬተሮች ኃይል ማመንጨት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ እቅዱ ተሳክቶ በሁለቱም ዩኒቶች ኃይል ማመንጨት እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ ሁለት ተኩል ዓመታት ጊዜ ውስጥም ግድቡን ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ ታስቦ እየተሰራ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ኢንጂነር ክፍሌ እንደገለጹት፤ ከለውጡ በኋላ በፕሮጀክቱ ላይ የማስተካከያ እርምጃ ከተወሰደ ወዲህ በሦስት ዓመታት ውስጥ በግድቡ ውስጥ መተከል የነበረባቸውን የውሃ ማስተላለፊያ የብረታ ብረት ሥራዎችን በማጠናቀቅ የመካከለኛውን የግድብ ከፍታ ከ25 ሜትር ወደ 100 ሜትር ማድረስ ተችሏል፡፡ እንዲሁም የግድቡን ግራና ቀኝ በትንሹ እስከ 645 ሜትር ማድረስ ተችሏል፡፡ ከባህር ጠለል በላይ እስከ 645 ወይም 145 ሜትር ከመሠረት ከፍ ያለ፤ እንዲሁም በትንሹ እስከ 111 ሜትር ከፍ በማድረግ ሁለት ሙሌቶችን ማከናወን የተቻለ ሲሆን፤ ሦስተኛው ሙሌት በሂደት ላይ ይገኛል፡፡
ከምንም ደረጃ ተነስቶ ሁለት ተርባይነሮችና ጀኔሬተሮች በመትከል ኃይል ማመንጨት ተችሏል ያሉት ኢንጂነሩ፤ የሲቪል ስራዎች ግንባታ ወደ 95 በመቶ፣ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ፍብረካና ተከላ ሥራ ወደ 61 በመቶ ከፍ በማድረግ እንዲሁም የውሃ ማስተላለፊያ የብረታ ብረት ሥራዎችን ወደ 73 በመቶ በማድረስ ዛሬ ላይ የፕሮጀክቱን አፈጻጸም 83 ነጥብ ሦስት በመቶ ለማድረስ እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ ሁለት ተኩል ዓመታት ውስጥ ግድቡን ሙሉ ለሙሉ በማጠናቀቅ በየደረጃው ሙሌት በማከናወን ቀሪ ዩኒቶችን በመትከል ኃይል በማመንጨት ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ታስቦ እየተሰራ እንዳለም ኢንጂነር ክፍሌ ተናግረዋል፡፡
ኢንጂነር ክፍሌ፤ “ባለፉት ሁለት ዓመታት ከምንጊዜም በላይ አገራችን ከውስጥና ከውጭ የተፈተነችበት፤ እንዲሁም ፕሮጀክቱን ለማሰናከል ከፍተኛ ርብርብ የተደረገበት ወቅት ቢሆንም፤ በመንግስት ሙሉ ድጋፍና ክትትል ፈተናዎችን ሙሉ በሙሉ በማለፍ የፕሮጀክቱ ግንባታ ሳይስተጓጎል በሚያስደንቅ ሁኔታ ከጠላቶቻችን ጭምር ከፍተኛ አድናቆት የተቸረው ሆኖ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱን ምንጊዜም በመደገፍና አመራር በመስጠት ከጎናቸው ላልተለዩ፤ በተገኘው ውጤት ሳይኩራሩ ለተጨማሪ ግብ እንዲሰሩ ለሚያተጓቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድና ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እንዲሁም ለሌሎች ከፍተኛ የአመራር አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 6 ቀን 2014 ዓ.ም