ከአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ እስከ ወታደራዊ የደርግ መንግስት ድረስ ከአርባ አመት በላይ በውትድርናው መስክ አገራቸውን አገልግለዋል። በተለይ በሰሜንና ምስራቅ ጦር ግንባሮች የክፍለ ጦር ምክትል አዛዥና ዋና አዛዥ በመሆን አገራቸው የጣለችባቸውን ግዴታ ተፈጥሮ በቸረቻቸው ድንቅ ስጦታ በብቃት ተወጥተዋል። ከጦር አዛዥነታቸው በበለጠ ደግሞ የኢትዮጵያን ሠራዊትና ቤተሰቡን ብሎም ውድ እናት አገራቸውን በወታደራዊ የሕክምና ባለሙያነት አገልግለዋል።
ከውትድርናው መስክ ባሻገርም በበጎ አድራጎት ስራዎችም ለአገራቸው ጉልህ አስተዋፅ አበርክተዋል። በተለይ ደግሞ ቀይ መስቀልን ከግማሽ ምእተ አመት በላይ በማገልገል የዜግነት ግዴታቸውን ተወጥተዋል። የኢትዮጵያ የህፃናት ልብ ህሙማን ማህበርን ከኮለኔል ዶክተር በላይ አበጋዝ ጋር በመሆን ከመሰረቱ በጎ አድራጊዎች ውስጥም አንዱ በመሆናቸው በበርካታ ኢትዮጵያውን ዘንድ ይታወቃሉ- ምርጥ፣ ፀባይ ሸጋውና በቅርቡ ህይወታቸው ያለፈው አንጋፋው የአገር ባለውለታ ብርጋዴር ጄነራል ጥላሁን ቢሻኔ።
ብርጋዴር ጄነራል ጥላሁን ቢሻኔ የተወለዱት በ1911 ዓ.ም በቀድሞው የሐረርጌ ክፍለ አገር ጅጅጋ አውራጅ ከአባታቸው ከባሻ ቢሻኔ እርጎዬና ከእናታቸው ወይዘሮ አለሚቱ በዳሾ ነው። አብዛኛውን የልጅነት ግዜያቸውን ያሳለፉትም እዛው በተወለዱበት ጅጅጋ አውራጃ ነው። እንደማንኛውም በግዜው እንደነበሩት ልጆች ቤተሰባቸውን በተለያዩ መንገዶች በማገዝ አድገዋል።
ገና በልጅነታቸው ጥሩ የእንግሊዘኛ ቋንቋ የመናገር ችሎታ የነበራቸው ብርጋዴር ጄነራል ጥላሁን ቢሻኔ ከጣሊያን ወረራ በኋላ ለእንግሊዛውያን በአስተርጓሚነት ሰርተዋል። በ1939 በሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት/ በዛሬው የኢትጵያ ወታደራዊ አካዳሚ/ የ12ኛ ኮርስ ተወዳዳሪ እጩ መኮንን ሆነው ወደ ውትድርናው ዓለም በመቀላቀል ወታደራዊ ስልጠና ወስደው ከኮርሳቸው በመወዳደር ከእጩ መኮንኖች በወታደራዊ ትምህርት ችሎታቸው አንደኛ ሆነው አጠናቀዋል።
በሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት በነበራቸው ቆይታ የውትድርናን ትምህርት በላቀ ውጤት አንደኛ ሆነው በማጠናቀቃቸው ወደ አሜሪካ አቅንተው ፎርት ሊበን ዎርዝ ካንሳስ ግዛት በሚገኘው የጦር አካዳሚ የወታደራዊ ጥበብ ተምረው በማዕረግ ተመርቀዋል። ተፈጥሯዊ እውቀታቸው፣ አንድን ነገር ለማወቅ ጉጉ መሆናቸውና ጉብዝናቸው ተጨምሮበት ትምህርታቸውን በጥሩ ውጤት ለማጠናቀቅ አስችሏቸዋል።
ከአሜሪካ የወታደራዊ ሳይንስ ትምህርት ቆይታቸው በኋላ ብርጋዴር ጄነራል ጥላሁን ቢሻኔ ወደ አገራቸው በመመለስ፤ በቅድሚያ የ9ኛ እግረኛ ብርጌድ አዛዥና እንደዚሁም የደቡብ ክፍለ አገራት አስተዳዳሪ በመሆን ለሦስት ዓመታት ያህል አገልግለዋል። ከዛም በ1961 ዓ.ም ወደ ኤርትራ ክ/ሃገር አሥመራ በመዛወር በዚያ ይገኝ የነበረውን ሁለተኛ ዋልያ እግረኛ ክፍለ ጦር በምክትል አዛዥነት ለአራት ዓመታት መርተዋል።
በቀድሞው የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ለሰላሳ ዓመት ያገለገሉት፤ በሞያቸው ታንከኛ የነበሩትና በአንድ ወቅት ከብርጋዴር ጄኔራል ጥላሁን ቢሻኔ ጋር አብሮ የመስራት አጋጣሚ የተፈጠረላቸው ብርጋዴር ጄነራል ዋስይሁን ንጋቱ ሲናገሩ ‹‹በ1964 ዓ.ም ከኦጋዴን ተዛውሬ አስመራ ስሄድ ከብርጋዴር ጄኔራል ጥላሁን ቢሻኔ ጋር ተገናኝቼ የመስራት አጋጣሚ ተፍጥሮልኛል። በወቅቱ እርሳቸው የሁለተኛ ዋልያ እግረኛ ክፍለ ጦር ምክትል አዛዥ የነበሩ ሲሆን እኔ ደግሞ የዚሁ ክፍለጦር የታንክ ሻምበል አዛዥ ነበርኩ። በኤርትራ ውስጥ የነበረውን ጦርነትና ኦፕሬሽኑን የሚያካሂዱትና አስተዳሩንም የሚመሩት እርሳቸው ነበሩ›› ብለዋል።
‹‹በግዜው ብርጋዴር ጄነራል ጥላሁን ቢሻኔ በትምህርት ችሎታቸው የላቁና በአሜሪካን ካንሳስ ግዛት ፎርት ሊበን ዎርዝ በሚገኘው የጦር ጥበብ አካዳሚ ገብተው ጠለቅ ያለ ወታደራዊ ጥበብ ቀስመው ወደአገራቸው የተመለሱና በባህሪያቸውም ጨዋና አርቆ አስተዋይ ነበሩ›› ሲሉ ብርጋዴር ጄነራል ዋስይሁን ንጋቱ መስክረዋል።
ከኤርትራ አሥመራ መልስ ጄነራል ጥላሁን ቢሻኔ በአዲስ አበባ ከተማ የአንደኛው ክፍለ ጦር ምክትል አዛዥ በመሆን የከፍተኛ የጦር መኮንንነታቸውን ወታደራዊ ግዳጅ ተወጥተዋል። በመቀጠልም ወደ ሐረር ሦስተኛ አንበሳው ክፍለ ጦር በመዛወር የክፍለ ጦሩ ዋና አዛዥ ሆነዋል።
ብርጋዴር ጄነራል ጥላሁን ቢሻኔ፤ የሦስተኛ አንበሳው ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ሆነው በሠሩበት አጋጣሚ በኢትዮጵያ የሕዝባዊ አብዮት ንቅናቄ የተፈጠረ በመሆኑና በአራቱም የአገሪቱ አቅጣጫዎች የሚገኙ የጦር ክፍሎች የሠራዊቱን ተወካዮች ወደ ማዕከል እንዲልኩ የለውጡ ሂደት አጠቃላይ ሁኔታ የግድ በሚልበት አጋጣሚ፤ ሦስተኛ አንበሳ ክፍለ ጦርን ወክለው ወደ አዲስ አበባ ለሚያመሩትና በሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያም እንዲመሩ ለተደረጉት የጦር መኮንኖችና የበታች ሹማምንት አባላት የውሎ አበል አዘው አስፈላጊውን የሽኝት ደብዳቤ ፅፈዋል።
ጄኔራሉ የሦስተኛ አንበሳው ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ሆነው ሲሰሩ ኋላ ላይ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የሆኑት ኮሌኔል መንግስቱ ሀይለማሪያም የዚሁ ክፍለ ጦር ባልደረባና የስደስተኛ ሜካናይዝድ ብርጌድ የሎጀስቲክ፣ ንብረትና መሳሪያ ግምጃ ቤት አዛዥ ነበሩ። ኮለኔሉ በጄነራል አማን አንዶም ላኪነት ሁለት ግዜ ወደ አሜሪካን አገር አቅንተው ሜሪላንድና ዋሽንግተን ዲሲ መሰረታዊ የመሳሪያ ጥገና ትምህርት የተከታተሉትም በዚህ ወቅት ነበር።
የሦስተኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ሆነው የክፍለ ጦሩን ሠራዊት በመሩበት አጋጣሚ፤ በክፍሉ ከነበሩት ከፍተኛና መስመራዊ መኮንኖች ጋር መልካም የነበረ አስተዳደራዊ፣ የአዛዥና የታዛዥነት ግንኙት የነበራቸው ብርጋዴር ጄነራል ጥላሁን፤ የካቲት 1966 ዓ.ም ብሔራዊ አብዮትን ተከትሎ በሠራዊቱ ውስጥ በተስተዋለው ግልጽ የነበረ የዕዝ ሰንሰለት መዛባት ምክንያት ቅር የተሰኙ በመሆናቸው፤ በወቅቱ የምድር ጦር ሠራዊት ኤታ-ማዦር ሹም ለነበሩት ጄነራል መኮንን ‹‹ሥራዬን በፈቃዴ መልቀቅ እፈልጋለሁ›› የሚል ማመልከቻ አቅርበው፤ በማመልከቻ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ያገኘ በመሆኑ በወቅቱ የኢትዮጵያ ርዕሰ-ብሔር በነበሩት በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ትዕዛዝ ተገቢው የአገልግሎት ዘመን መብታቸው ተከብሮ ሠራዊቱን በጡረታ ተሰናብተዋል።
ይህንን በተመለከተ ብርጋዴር ጄኔራል ዋስይሁን ንጋቱ ሲናገሩ ‹‹ ጄኔራሉ እኔ የማዘው መኮንንና የበታች ወታደራዊ ጦር የማይታዘዘኝ ከሆነ የኔ ጄኔራልነት ዋጋ የለውም፤ ስልጣኔንም በገዛ ፍቃዴ እለቃለሁ ብለው ለኮለኔል መንግስቱ ሃይለማሪያም እንዳመለከቱና ጥያቄያቸውም ተቀባይነት አግኝቶ ከነሙሉ ክብራቸው በጡረታ የተሰነባቱ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ጄነራል›› ናቸው ሲሉ ገልፀዋቸዋል።
በግዜው ደርግ ወደ ስልጣን ሲመጣ በርካታ የጦር ጄኔራሎችን ሲያስርና ሲረሽን ብርጋዴር ጄኔራል ጥላሁን ቢሻኔ ‹‹ እጃቸው ከምንም ነገር የፀዳ በመሆኑ፣ ሁኔታውን አይተው በመተንበያቸውና ወደዚህ ምስቅልቅል ሁኔታ ውስጥ ሳይገቡ አስቀድመው በገዛ ፍቃዳቸው ጡረታ በመውጣታቸው ከርሸናው ተርፈዋል እንጂ እርሳቸውም አይቀርላቸውም ነበር›› ይላሉ ብራጋዴር ጄነራል ዋስይሁን ንጋቱ።
ከሁሉ በላይ ብርጋዴር ጄነራል ጥላሁን ከጦር አዛዥነታቸው በበለጠ፤ የኢትዮጵያን ሠራዊትና ቤተሰቡን ብሎም ውድ እናት አገራቸውን ያገለገሉት በወታደራዊ የሕክምና ባለሙያነት ተግባር ነው። በዚህ የሕክምና ባለሙያነታቸው የየጦሩን ክፍሎች የጤና ማዕከላት፣ ሆስፒታሎችን በሰው ኃይልና በቁሳቁስ፣ በመድኃኒትና በሕክምና መርጃ መሣሪያዎች ከማደራጀትና የአስተዳደሩን ሥራ ሁሉ በአግባቡና በልዩ የኃላፊነት ስሜት በመምራት እጅግ ምስጉን የሆኑበትን ተግባር አከናውነዋል።
በዚሁ ዘርፍ በጥቅሉ ለሃያ አምስት ዓመታት ስራቸውን በትጋት አከናውነዋል። በዚህም በኢትዮጵያ የምድር ጦር ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ሥር በሚገኘው ዋነኛው የሕክምና መምሪያ ያከናወኗቸው አያሌ ሥራዎች በዋቢነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። ከዚሁ የጄኔራሉ ወታደራዊ ህክምና ሞያ አመራርነታቸው ጋር በተያያዘ የቀድሞ የስራ ባልደረባቸው ጄነራል ዋስይሁን ንጋቱ ሲናገሩ ‹‹ብርጋዴር ጄነራል ጥላሁን ቢሻኔ ከወታደራዊው መስክ ይልቅ በህክምናው ዘርፍ በአዛዥነት ከሃያ አምስት ዓመት በላይ ሰርተዋል። በዚሁ መስክም እነ ጄኔራል ዶክተር ሃይሉ ከፈኔን፣ ዶክተር ጋጋንና ሌሎችንም ወደ ውጪ አገር ጭምር በመላክ እንዲሰለጥኑና የህክምና ሞያ እውቀት እንዲጨብጡ አድርገዋል›› ብለዋል።
‹‹በተጨማሪም ጄነራሉ የምድር ጦር ህክምና መምሪያ ሆነው በቅንነት በማገልገልና የአሁኑ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል በሰው ኃይልና በቁሳቁስ እንዲሻሻልም ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። በወታደራዊ ህክምና አመራር ችሎታቸው የተካኑ ሊሆኑ የቻሉትም ጣልያን ከአገሪቱ ወጥቶ እንግሊዞች በኢትዮጵያ በነበሩ ግዜ ከህክምና ባለሞያዎች ጋር ባስተርጓሚነት መስራታቸውና ሃሳብ አመንጪ ስለነበሩ ነው እንጂ ያን ያህል የህክምና እውቀት ኖሯቸው አይደለም። ነገር ግን ደግሞ ወታደራዊ አዛዥነታቸው ህክምናውን ለመምራት ሳይረዳቸው አልቀረም›› ይላሉ ብርጋዴር ጄነራል ዋስይሁን ንጋቱ።
በኢትዮጵያ ቀዳማይ የጦር ክፍሎች ያከናወኗቸው በሳልና እጅግ ፍሬያማ የአስተዳደር፣ የመሪነትና የሕክምና ሙያ አመራር ተግባራት እርሾ የሆኗቸው ጄነራል ጥላሁን ቢሻኔ፤ ከሠራዊቱ ከምስጋና ጋር በጡረታ ከተሰናበቱ በኋላ በነበራቸው ልምድ፣ ችሎታና ብቃት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበርን ለስልሳ አራት ዓመታት በነፃ አገልግለዋል። ለወገን ባላቸው የተቆርቋሪነት ስሜትና ተፈጥሮ ባደለቻቸው የሰብዓዊነት ባሕሪ፤ ከኮሎኔል ዶክተር በላይ አበጋዝና ከሌሎችም ቅን የኢትዮጵያ ልጆች ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ሕፃናት የልብ ህሙማን ማኅበርን በመመስረትም የዜግነት ግዴታቸውን ተወጥተዋል።
ይኸው የቀይ መስቀል ነፃ አገልግሎታቸውና የበጎ አድራጎት ተሳትፏቸው ከደርግ ውድቀት በኋላ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘም በኋላ ቀጥሏል። አንጋፋው የቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት በቅርቡ እንደገና ሲቋቋምም የእርሳቸው ሚና ከፍተኛ ነበር።
ጄነራል ጥላሁን ቢሻኔ፤ በእሳቸው ሥር በመስመራዊ መኮንንነት ሲሠሩ የነበሩና በስተኋላ ለጄነራልነት ማዕረግ የበቁ፣ እስከ ኮሎኔልነትና ሻለቃነት ማዕረግ የደረሱ አያሌ የጦር አዛዦችና ጀግና፤ ቆራጥ የሠራዊት መሪዎች ዘንድም በእጅጉ የሚደነቁና የሚከበሩም ነበሩ።
በእርሳቸው ስር ተምረው የጄነራልነት ማእረግን ከተቆናጠጡት ውስጥም አንዱ ብርጋዴር ጄነራል ዋስይሁን ንጋቱ ሲሆኑ ‹‹ከእርሳቸው ጋር በቅርበት በመስራቴ ከፍተኛ ኩራት ይሰማኛል፤ ከጅጅጋ ወደ ኤርትራ ተዘዋውሬ የሰራሁትም ከእርሳቸው ጋር ነው። በዚህም ከእርሳቸው ሰፊ እውቀትና ልምድ አግኝቻለሁ›› ይላሉ።
ብርጋዴር ጄነራል ጥላሁን ቢሻኔ የ12ኛ ኮርስ ተወዳዳሪ እጩ መኮንን ሆነው ወደውትድርና ዓለም በመቀላቀል ወታደራዊ ስልጠና ወስደው ከኮርሳቸው በመወዳደር ከእጩ መኮንንኖች በወታደራዊ ትምህርት ችሎታቸው አንደኛ በመውጣታቸው ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እጅ የምክትል መቶ አለቅነት ማዕረግና ዲፕሎማ ተቀብለዋል።
በወታደራዊና ህክምና ሞያ አዛዥነት ብቃታቸውም በተለያዩ ግዜያት የሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል። ቀይ መስቀልን ለረጅም አመታት በነፃ በማገልገልም የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል። በተጨማሪም ከአለም አቀፍ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማህበር የእድሜ ልክ አገልግሎት ሜዳሊያ ሰርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል። በበጎ አድራጎት ስራዎች ተሳትፏቸው፤ በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ህፃናት ልብ ህሙማን ማህበርን በመመስረት ሂደት ባደረጉት አስተዋፅኦ ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እውቅናን አግኝተዋል።
ስመ- ጥር፣ አስተዋይና ቀደምት ኢትዮጵያዊ ከፍተኛ ጄነራል መኮንኖች ውስጥ አንዱ የነበሩት ብርጋዲየር ጄነራል ጥላሁን ቢሻኔ ሐሙስ ሐምሌ ሰባት ቀን 2014 ዓ.ም በ103 አመታቸው በድንገተኛ ህመም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
በዕለተ ዕሁድ ሐምሌ 10 ቀን 2014 ዓ.ም ቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት ባልደረቦች፣ ጄነራሎችና ሌሎች ከፍተኛ መኮንኖች እንደዚሁም በኢትዮጵያ ቀይ መስቀልና በልብ ሕሙማን መርጃ ማዕከል በከፍተኛ ኃላፊነት፣ አስተባባሪነትና መስራችነት የሚያውቋቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን አክባሪ ወገኖቻቸው በተገኙበት በሙሉ ወታደራዊ የማርሽ ባንድ በመካኒሳ ገብረመንፈስ ቅዱስ አቦ ቤተክርስቲያን የቀብር ሥነ-ሥርዓታቸው ተፈፅሟል።
እኚህ አርዓያነታቸው የላቀ ጄነራል ረጅም እድሜ የተጎናፀፉ መንፈሰ-ጠንካራ ኢትዮጵያዊ የነበሩ ሲሆን፤ ከባለቤታቸው ወይዘሮ ትርሲት ቸኮል ጋር ትዳር መስርተው ሰባ አንድ ዓመት ኖረው አምስት ወንድና አንዲት ሴት ልጅ በማፍራት ለቁም-ነገር ያበቁ፤ አስራ አንድ የልጅ ልጆች አያት ለመሆን የታደሉ የአገርና የወገን አውራ ነበሩ።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 4 /2014