የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከፖለቲካ ወገንተኝነት፣ ከማንኛውም የመንግስት ወይም ሌላ አካል ተጽዕኖ ነጻ የሆነና ራሱን የቻለ የሕግ ሰውነት ያለው አካል ነው። ዋና ዓላማውም መሰረታዊ የሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያሉ ልዩነቶችን በማጥበብ በተቻለ ሁሉ እርስ በእርስ መግባባት እንዲኖር ማድረግ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኮሚሽኑ እስካሁን ስላከናወናቸው አንኳር ጉዳዮችና በ2015 በጀት ዓመት ሊተገብራቸው ስለያዛቸው እቅዶች አስመልክቶ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላም ጥናት ተባባሪ ፕሮፌሰር ከዶክተር ዮናስ አዳዬ ጋር ቆይታ አድርገን ያጠናቀርነውን እነሆ ለንባብ ብለናል ።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የዝግጅት ምዕራፉን አልፎ ወደተግባር እየገባ ይገኛል፤ ስለሆነም ኮሚሽኑ ምን ያህል በእቅዱ መሰረት እየተጓዘ ነው ?
ዶክተር ዮናስ፡- በጣም ጥሩ፤ ቀደም ሲል የነበረውን ለማስታወስ ያመቸን ዘንድ ዝግጅታችን ትኩረት አድርጎ ሲንቀሳቀስ የነበረው አምስት ምዕራፎችን ይዞ ነው። የመጀመሪያው ቅድመ ዝግጅት የሚባለው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ዝግጅት ነው፤ በሶስተኛ ደረጃ የተያዘው ሒደት ሲሆን፣ አራተኛው ደግሞ ትግበራ ነው። የመጨረሻው ቀደም ሲል የተጠቀሱት መሰራት አለመሰራታቸውን ሊያሳይ የሚችል ክትትልና ግምገማ ነው። ስራችንን የጀመርነው በእነዚህ አምስቱ ምሰሶዎች ስር ነው። በእርግጥ አንዳንዶች እነዚህን አምስቱን ምሰሶዎች ሶስትም እንዲሁም አራትም አድርገው ይከፍሏቸዋል። እንደዛም ማድረግ ይቻላል። እኔ በአገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ በኃላፊነትም፣ በተጠያቂነትም እንዲሁም በተጠሪነቱም ስለምሰራ በዚህ መልኩ የከፋፈልኩት ተግባቦቱ የበለጠ ግልጽ እንዲሆን ብዬ ነው።
በቅድመ ዝግጅቱ የተሰሩ ስራዎች በጥቅሉ ለስራው የተመረጥን አስራ አንዳችን ከተለያየ ቦታ የመጣን እንደመሆናችን የመጀመሪያው እርምጃ እርስ በእርስ መተዋወቅ ነበር። ይህ ጉዳይ በቀላሉ የሚታይ ሳይሆን በጣም ወሳኝና አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል።
እንዲህ ማለቴ የራሱ የሆነ ምክንያት ስላለው ነው። ሌላ ቦታ በአግባቡ ሳይተዋወቁ እንዲህ አይነቱን ስራ ጀምረው ከተለያየ ጎሳ የመጡ በመሆናቸው የመጡበትን አካባቢ አመለካከት፣ የድርጅታቸውን አመለካከት እንዲሁም የኃይማኖትን ርዕዮት ዓለም ከማንጸባረቃቸው የተነሳ ብሔራዊ ፕሮጀክቱ ራሱ የተነሳበትን ግብ ሳያሳካ የቀረበት ሁኔታ እንዳለ የሌሎች አገሮች ተሞክሮዎች ያሳያሉ።
በመሆኑም እንደእሱ አይነት ችግር በአገራችን እንዳይደገም ለማድረግ እርስ በእርስ የመተዋወቁን ጉዳይ በጥሩ ሁኔታ አከናውነናል። ለምሳሌ ከአስራ አንዳችን ውስጥ ማን ምን አይነት ዝንባሌ አለው? ምንስ አይነት የስራ ልምድ አለው? በፋይናንስ አካባቢ እውቀት ያለው ማን ነው? አጋርነት ላይስ መስራት የሚችለው ማን ነው? በዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ላይ ማን ልምድ አለው? በኮሙኒኬሽንና ሚዲያ ላይ እንዲሁም በሕግ ላይ የተሻለ እውቀት ማን ዘንድ ነው ያለው? በተለያየ ጉዳይ ላይ ማን ምን አለው የሚለውን በአግባቡ ለይተን የተመለከትነው ጉዳይ ነው።
እኔ ለምሳሌ እንግሊዝ አገር ሶስተኛ ዲግሪዬን የሰራሁት በሰላም ጥናት ላይ ነው። ቀደም ሲል ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳስተምር ነበር። ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመሆንም ዲፕሎማሲ ሳስተምርና ሳሰለጥን ነበር። ስለዚህ የእኔ ዝንባሌ ወደሰላም ግንባታ እንዲሁም ግጭት አፈታት ላይ ስለሆነ እኔ እና አምባሳደር መሃሙድ ድሪር በኮሙኒኬሽንና ሚዲያ ውስጥ ተመድበናል፤ ሌሎችም እንዲሁ በአምስቱ ምሰሶዎች ስር እንደየዝንባሌያቸው ተመድበው ስራቸውን በማከናውን ላይ ይገኛሉ። ይህ ስራችን ደግሞ በጋራ የምንሰራበት እንደኮሚሽን የተሻለ እንዲሆን የሚያስችል ስለሆነ ነው።
በጥቅሉ እርስ በእርስ ከተዋወቅንና እንደየዝንባሌያችን ስራ ከተከፋፈልን በኋላ ምክክር የሚለው አንኳሩ ጉዳይ ምንድን ነው? ምክክር ከሽምግልና፣ ከውይይት፣ ከድርድር፣ ከሙግት እንዲሁም ከዳኝነት የሚለየው በምንድን ነው? የሚለውንና ትንሽ ግር የሚያሰኘውን ጽንሰ ሐሳብ በመረዳት ደረጃ እየተመካከርን ለመማማር ብዙ ጊዜ ወስደናል። በዚህም መሰረታዊ የሆኑ ጉዳዮችን አውቀናል። በሒደት ደግሞ እያወቅንና እየተማርን እንሄዳለን። እኔም በአሁኑ ወቅት ከሰላም ጥናት ጋር በተያያዘ የተባባሪ ፕሮፌሰርነት ደረጃ ላይ እገኛለሁ። በመሆኑም በምክክሩ ጉዳይ ላይ ስንጽፍ ብሎም ስናስተምር ቆይተናል። ሌሎቹም እንደየችሎታቸው እንዲሁ እየሰሩ ነው። ምን ምን አይነት እውቀትና ክህሎት አለው የሚለውን በይበልጥ ለመረዳት መቀራረቡ ጠቅሞናል።
አዲስ ዘመን፡- ከትውውቁ በኋላ የመጀመሪያ የሆነው ስራ ምን ነበር?
ዶክተር ዮናስ፡- እርስ በእርስ ከተዋወቅን በኋላ የምንሰራበትን አውድና አገርን ማወቅ ሌላው ጉዳይ እንደመሆኑ ያቀናነው ወደዚያ ጉዳይ ነው። በእርግጥ ኢትዮጵያን ይወክላሉ ያልናቸው በተለይም የኃይማኖት መሪዎችን ምክንያቱም ብዙ ጥናቶች የሚያሳዩት 98 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድም በሌላ በኩል ኃይማኖተኛ ነው በሚል ነው። በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ፈሪሃ ፈጣሪ እንዳለ እንገነዘባለን። ስለዚህ ሕዝቡን የማወቂያ የመጀመሪያው መንገዳችን ሕዝቡን መወከል የሚችሉ መንፈሳዊ መሪዎችን ማግኘት ነበረብን። ስለሆነም ከመንፈሳዊ መሪዎች፣ ከኃይማኖት አባቶች፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከዋቄፈናዎች፣ ከአባገዳዎች፣ ከሰላም እናቶች፣ ከሴቶች ማህበራት ተወካዮች፣ ከወጣት ማህበር ተወካዮች ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልል በሚያስብል ደረጃ የመጀመሪያ ስራችን አድርገን ከእነርሱ ጋር መተዋወቅ ነበረብንና ከእነርሱ ጋር ተዋወቅን። መተዋወቅ ብቻም ሳይሆን እነርሱም ከእኛ ጋር እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።
በቀጣዩ ጊዜያችንም ኢትዮጵያን ማወቅ እንደመሆኑ የተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም እንዲሁም ከገዥው ፓርቲም ጋር ስለአገራችን በመምከርና በመነጋገር እንዲሁም ምክክር ስላስፈለገበትም ምክንያት በአግባቡ በመወያየት እንዴት መደጋገፍ እንዳለብን ስንመካከር ነበር። በዚህም ብዙዎቹ ፍኖተ ካርታ ሰርቶ እስከመስጠትና በዛ ላይ ምክር እስከመለገስ ደርሰዋል። አንዳንዶቹ ካላቸው ልምድና ክህሎት ተነስተው የሚያስተምሩና ወደኋላ የቀረን ሲመስላቸው የሚገስጹን ነበሩ። ይህ መልካም ድጋፍና ትብብር እየጨመረ መጥቷል። ከሲቪክ ማህበራትም ጋር እንዲሁ ስንመካከር ነበርና ቅድመ ዝግጅታን ይህን ይመስል ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ከቅድመ ዝግጅታችሁ አንዱ የሌሎች አገሮች ተሞክሮ ምን ይመስላል የሚለው ነውና ኢትዮጵያን ያጋጠማት አይነት ተቀራራቢ ችግር ያጋጠማቸውና ጉዳዩን የፈቱበትን መንገድ በምን መልኩ ዳሰሳችሁ?
ዶክተር ዮናስ፡- ሌሎች አገሮች ዘንድ ምን ተሰራ የሚለውንም አይተናል፤ ለምሳሌ የየመን ለምን ስኬታማ አልሆነም? የቱኒዚያ ደግሞ ምን ስለተጠቀሙ ነው የተሳካው? የሚለውን ለማየት ሞክረናል። ከእኛም ጋር ካለው ጉዳይ ጋር አወዳድረናል። የደቡብ አፍሪካና ኬንያ የተካሄደውም ልክ እንደቱኒዚያ ሁሉ የተሳካ ነበር። በከፊል ደግሞ የቤኒንም ተሳክቷል። የሱዳን ግን ሙሉ በሙሉ ውድቅ ሆኗል። ይህ ለምን ሆነ? ኢትዮጵያ ከዚህ ምን ትማራለች? የሚለውን በቲዮሪ ደረጃ (በመሰረተ ሐሳብ ደረጃ ማወቅ ነበረብን)።
ይህንንም የየአገሮችን ተሞክሮ ከወሰድን በኋላ የገባነው ከቅድመ ዝግጅት ወደዝግጅት ምዕራፍ ነው። ይህም መነሻ ያደረገው ከአዲስ አበባ መውጣት ነው። እኔ እና ሁለት የስራ ባልደረቦቼ ጅግጅጋ የተጓዝን ሲሆን፣ ሌሎቹም የስራ ባልደረቦቻችን እንዲሁ ወደተለያዩ የአገራችን ክፍል ተጉዘዋል። በዚህ መልኩ ከአፋርና ከትግራይ ክልል በስተቀር ሁሉንም አዳርሰናል። ወደተቀሩት ክልሎችም ለመድረስ በዝግጅት ላይ ነን።
አዲስ ዘመን፡- ወደተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ስትደርሱ በተጨባጭ የሰራችኋቸው ስራዎች ምንድን ናቸው?
ዶክተር ዮናስ፡- ወደተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ሔደን በዋናነት የሰራነው ከሕዝቡ ጋር መምከር ነው። በተለይ ደግሞ እኛንና የመጣንበትን ዓላማ በስፋት ከገለጽን በኋላ ምክክር የተባለው ነገር በራሱ ምን እንደሆነ አስረድተናል። በተለይ በ21ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ምክክር ለምን አስፈለገ የሚለውን በአግባቡ ለማሳወቅ ሞክረናል። እኛ የሰለቸን ጦርነት፣ ድህነት፣ ጉስቁልና ነው። በዋናነት ደግሞ የሰለቸን ነገር መከፋፈል ነውና በአንድነትና በትብብር መስራት የምንችለው ምን ቢሆን ነው በሚል አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ ማህበራዊ ውል እንዲኖር መፈለጉን ገልጸንላቸዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም እንዲኖር፣ ሰላምን እንዴት በሰላማዊ መንገድ ማምጣትና ባህል ማድረግ እንደሚቻል? እስካሁን ድረስ ለነበረን ውድቀት፣ ውድመት፣ ውስጣዊ ፍልሰትና ለመሳሰሉ ችግሮች መሰረታዊ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? ችግሮቹን የምንቀርፈውስ እንዴት አድርገን ነው? ዋና ዋና አንኳር የሚባሉ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? ከእናንተ ጋርስ እንዴት አድርገን እንወያያለን? የሚሉ መሰረታዊ ነገሮችን አንስተናል፤ ይህንንም በስፋት ለመጀመር ከቀበሌ አንስቶ ወረዳ፣ ዞን፣ ክልል በመጨረሻም በአገር አቀፍ ደረጃ ለማካሄድ እቅድ መያዛችንንም አሳውቀናል።
በየክልል ያሉ መስተዳድሮች ከምክትል ኮሚሽነሩ ጋር የሚገናኙበትን አገናኝ መኮንን ማቋቋም ነበረብንና ይህንንም አቋቁመናል፤ እዛ ውስጥ የምናገኛቸው ወጣት መሪዎችን፣ ሴቶችን፣ የአገር ሽማግሌዎችን፣ የኃይማኖት መሪዎችን እንዲሁም በአካባቢያቸው ተሰሚነት ያላቸውን ሁሉ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ምንስ ያጋጠማችሁ ነገር አለ? ሊያጋጥሟችሁ የሚችሉ የተለያዩ አመለካከቶች ይኖራሉና እነሱን ያስተናገዳችሁት በምን አይነት መንገድ ነው? ምንስ መልካም ነገር አይታችኋል?
ዶክተር ዮናስ፡- ያየነውና ያስተዋልነው ነገር በጣም የሚያስደነግጥ፣ በጣም የሚያስደምም በሌላ በኩል ደግሞ ኩራት ሊሆን የሚችለውን የሕዝብ ተነሳሽነትን ነው። በተለይ ከሰጠን ድጋፍ ተነስተን በሕዝቡ ውስጥ ያስተዋልነው ነገር ቢኖር ለሰላም ያለውን ጥማት ነው። እኔ እንደኮሚሽነርነት የተጣለብኝን የኃላፊነት ክብደት ለማስተዋል ችያለሁ። ይህ እውነት ነው፤ እኔ የምናገረው ለዲፕሎማሲ ወይም ለማሳመን አይደለም። እያንዳንዳችን የሰላምን ጥማት አይተን ለአገራችን ደግሞ ምን ያህል እንደቆረጥን የሚያሳይ የህብረተሰብ ክፍል ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ሕዝቡም ሲል የነበረው፤ ‹‹ኢትዮጵያ በጭራሽ አትፈርስም›› ነው። ደግሞም ይህ የሚያሳየው በጋራ መኖርን ብቻ ሳይሆን ወደፊት የመመልከትንም ሁኔታ ነው። ዛሬ በችግር ውስጥ ቢታለፍም የወደፊቱ ግን ብሩህ እንደሆነ የሚያምን ሕዝብ ነው። ሕዝቡ ሲናገር የነበረው ለልጅ ልጁ የሚያወርሰውን ኢትዮጵያን እንደሚፈልግ ነው። ደግሞም ለልጅ ልጅ ልትወረስ የምትችል ብሩህ ኢትዮጵያ እንድትኖር የሚያስፈልገውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን የሚያሳይ አቋም አለው። ይህ አስተሳሰብ በየሄድንበት ቦታ ሁሉ ያጋጠመን ነው። እንዳልኩሽ በተለይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ‹‹እኛ በአመለካከት ብንለያይም ለአገራችን ሲባል ግን መመካከር እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ እናምናለን›› ሲሉ ነው እየገለጹልን ያለው። ለዚህ ምክንያታቸው መቃወም ሆነ መፎካከርም የምንችለው አገር ስትኖር ነው የሚል ነው። ስለሆነም በአገራችን ጉዳይም ሆነ በውይይቱ ላይ ሁላችንም በጋራ እንቆማለን ሲሉ ነው በእርግጠኝነት ከእያዳንዳቸው ሲነገር የሰማነው።
ለምሳሌ እኔ ለዚህ ኮሚሽን በአባልነት በሚመረጥበት ወቅት የነበርኩት በጀርመን አገር ሙኒክ በምትባል ከተማ ነው። በወቅቱም በጀርመን የመገኘቴ ምስጢር በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ጉዳይ ላይ ጥናት ለማቅረብ ከመጡ አፍሪካውያን መካከል ኢትዮጵያን ወክዬ ነበር። ተደውሎ የተነገረኝ እዛ በነበርኩበት ወቅት ነው።
በመሆኑም በዝግጅት ምዕራፋችን አስቀድመንም እንደገለጽነው የሶስት ዓመት እቅድ ይዘን ነው እየተንቀሳቀስን ያለነውና ተጠሪነታችን ለፓርላማው እንደመሆኑ ለእሱ አቅርበንና ከፓርላማውም ሆነ ከሕዝቡም ግብዓት አግኝተን አጠናቀናል። አሁንም ወደተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በማምራት የመተዋወቂያ ጊዜያችንን እንዳጠናቀቅን ስትራቴጂካዊ እቅዳችንን በአጭሩ ካቀረብን በኋላ ከእነሱም ጠቃሚ የሆነ ግብዓት ማግኘት ችለናል። በተመሳሳይ ስትራቴጂካዊ እቅዳችንን በተለያዩ የአገራችን ክፍል በስፋት ለማሰራጨት ዝግጅቱ አለን። ይህ ዲያስፖራውንም ጭምር የሚያካትት ነው። ለዚህ ደግሞ ምክንያታችን የሒደቱ ባለቤት ራሱ ሕዝቡ ስለሆነ ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆን ስለምንፈልግ ከእነርሱ ጋር በመስራት ላይ እንገኛለን።
በዋናነት የመን ውስጥ በተካሄደው ሒደት ላይ ገንዘቡም እቅዱም ተዘጋጅቶ የተሰጣቸው በውጭ ኃይሎች ነበር። ከዚህ የተነሳም ሳይሳካ በመቅረቱ ወደቀ። የእኛ እንደዛ እንዳይሆን በሒደቱም ጭምር ከመጀመሪያ እስከመጨረሻው ሕዝቡ ባለቤት እንዲሆን እንፈልጋለን። ለዚህም ደግሞ በሚዲያ ሁሉ በግልጽ እየተነገረ ነው። ሕዝቡ ሒደቱን በግልጽ የሚያውቅ ከሆነ መካተትም መወገደም ያለበት ጉዳይ በግልጽ ሊናገር ይችላል። ገንቢ የሆነም አስተያየት በሚገባ መስጠት ይችላል።
የቱኒዚያው የተሳካበት ምክንያት ሒደቱ ራሱ አራት ሲቪል ማህበራት ከሕዝቡ ጋር በመነጋገርም ጭምር በመካሄዱ ነው። ስኬታማ መሆን የቻሉትም ሕዝብ በሕዝብ ሆኖ በመሰራቱ ነውና እኛም ከእነርሱ ተሞክሮ ስለወሰድን በሚደረገው ሒደት ሁሉ ሕዝቡ የራሱን የባለቤትነትና የበላይነት መብቱን እንዲያውቅም ስለፈለግን ነው።
አዲስ ዘመን፡- በሚመጣው 2015 ዓ.ም የእቅዳችሁን 60 በመቶ ለመስራት እንደወጠናችሁ ይታወቃል፤ ስራችሁን የምትጀምሩት ከምንድን ነው? 60 በመቶውንስ ለመሸፈን የሚያስችል መደላድል አለ ብላችሁ ታስባላችሁ?
ዶክተር ዮናስ፡- የዩኒቨርሲቲ ሕይወትሽን እንደምታስታውሺው በተፈጥሮ ሳይንስም ይሁን በማህበራዊ ሳይንስ የምርምር ስራሽን የምትጀምሪው መላምት አስቀምጠሽ ነው። የምታስቀምጪው መላምት መጨረሻ ላይ ስላለው ግብሽ ጠቋሚ ነው። ጠቅላላ ሂደትሽም ያንን እውነትነቱ አሊያም ሐሰትነቱን ለማረጋገጥ ነው። የሚነበቡ ነገሮች ሁሉ ላስቀመጥሽው መላምት ግብ መሳካት የሚያግዙ ነው የሚሆኑት። በተመሳሳይ ያቀድናቸው እቅዶች አሉ፤ አሁን ፍኖተ ካርታ አዘጋጅተናል። በየቦታውም አገናኝ መኮንኖችን ሾመናል። እንዲሁ ስብሰባዎች እንዲካሄዱ አድርገናል። እነዚህ እንዳቀድናቸው ኅዳር አጋማሽ አካባቢ የመጀመሪያ ዙር አገር አቀፍ ውይይት ማካሄድ የምንችል ከሆነ፤ ከእነዛ ውስጥ ደግሞ የአጀንዳ መረጣ ለምሳሌ የመጀመሪያ የአጀንዳ ሐሳብ ማፍለቅ አለ፤ ከእነዚህ ከፈለቁ አጀንዳዎች መካከል ግማሹ በክልል ገሚሱም በወረዳ ደረጃ ሊመለሱ የሚችሉ ይሆናሉ። ግማሹ ደግሞ በአጠቃላይ ኢትዮጵያን የሚመለከት በመሆኑ አገራዊ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ሕዝቡ እንደሚያነሳው እነዚህ ሁሉ ልክ በወንፊት እንደሚጣራ ሁሉ ተጣርተው ወደላይ ከመጡ በኋላ የመጀመሪያውን ዙር ስብሰባዎችን እናካሂዳለን፤ ከዚያ በኋላ የመጀመሪያውን ዙር ግምገማ ማካሄድ ከቻልን ካሉን ስራዎች 60 በመቶውን ማጠናቀቅ እንችላለን የሚል መላ ምት አስቀምጠናል። ይህ የሚከናወን ከሆነ ከሕዝቡም ሆነ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲሁም ከሁሉም አካላት የምንፈልጋቸው ጉዳዮችም ከተሟሉ ምክክሩም በዚህ ሁኔታ የሚካሄድ ከሆነ እስከ 2015 ዓ.ም ድረስ ያስቀመጥነውን ግብ ማሳካት እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ሒደት ማዕከል የሚያደርገውና የሚያካትተው እነማንን ነው?
ዶክተር ዮናስ፡- በተገላቢጦሽ የማይገቡት እነማን ናቸው? ቢባል ብዬ አስባለሁ። በማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1265/2014 አንቀጽ 3 ላይ የተቀመጡ መርሆዎች አሉ። የመጀመሪያው አካታችነት ነው። ይህ አካታችነት ሁሉንም የሚያካትት ነው። እኛ እንደኮሚሽን ለምሳሌ እነማን ናቸው የሚካተቱት? ቢባልና ሌላው ቀርቶ የኢትዮጵያ ፓርላማ በአሸባሪነት የፈረጀውን ሁሉ ያካትታል ቢባል መልሴ አዎ! ሁሉም ይገባል ነው። በዚህ ጉዳይ ደግሞ መንግስትም ሕዝብም ያምነናል። ምክንያቱም እኛ በኮሚሽኑ ውስጥ ስንገባ ስልጣን አሊያም ደመወዝ ፍለጋ አይደለም። የምንፈልገው በነጻነት ሕዝብን ማገልገል ነው። ፍላጎታችን ከማንም ሳንወግን በገለልተኛነት ማገልገል ነው። ስለሆነም ከዚህ ሒደት ማንም ወደኋላ የሚቀር አካል አይኖርም። መሪውም ተመሪውም የሚገኙበት ነው። ስለዚህም ጥያቄሽ በተገላቢጦሽ እነማናቸው የማይካተቱት ቢባል ምላሹ ማንም የሚል ነው የሚሆነው። በኃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በዘር፣ በስልጣን በየትኛውም ነገር ልዩነት ሳይፈጥር ሁሉንም አካታች ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፡- ህዳር አጋማሽ ላይ እንጀምራለን ያላችሁት ውይይት ላይ የሚነሱ ዋና ነጥቦች የሚባሉት የትኞቹ ናቸው? የሚጀምረውስ በእነማን ነው? አወያዮቹስ?
ዶክተር ዮናስ፡- የውይይቱን አንኳር ነጥቦች ከማንሳታችን በፊት በመጀመሪያ እነማን ናቸው ተወያዮቹ? አወያዮቹ? አመቻቾቹ? ቃለ ጉባኤ ያዦቹ? ታዛቢዎቹ ቀጥሎ ደግሞ አጀንዳው ምንድን ነው? አካሄዱስ እንዴት ነው? እነዚህ መሰረታዊ ጥያቄዎች ካነሳሻቸው ጥያቄዎች ጋር የተያያዙ ናቸው። አወያዮቹም ሆኑ ታዛቢዎቹና መሪዎቹ ራሱ ሕዝቡ የሚያምናቸውና በአካባቢው ታማኝነት ያላቸው እንዲሁም ተሰሚ የሆኑ ከራሱ ከሕዝቡ የሚመረጡ ናቸው። አመቻቾቹ ደግሞ እንዴት ማወያየት እንደሚቻል ስልጠና የወሰዱ ናቸው፤ ምክንያቱም ምክክር እውነትን ፍለጋ ወይም መጓዣ ሒደት ነው። ምክክር ሲባል ዝም ብሎ ድርድር ወይም ሽምግልና አይደለም፤ እውነትን ፍለጋ መንገድ ነው።
የአዋጁ መግቢያ ላይ ልብ ብለሽ ከሆነ ‹በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካና የሐሳብ መሪዎች እንዲሁም የኅብረተሰብ ክፍሉ መካከል እጅግ መሰረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሐሳብ ልዩነትና አለመግባባት የሚታይ በመሆኑ ይህንን ልዩነትና አለመግባባት ለመፍታት ሰፋፊ አገራዊ የሕዝብ ምክክሮችን አካታች በሆነ መንገድ በማካሄድ አገራዊ መግባባት መፍጠር አስፈላጊ ነው› ይላል። ስለሆነም እነዚህን የሚወክሉና መሰል አጀንዳዎች በመሰረታዊ ልዩነቱ ለምሳሌ መሰረታዊ ልዩነት ሲባል በራሱ ኢትዮጵያ እንደ አገር ትቀጥል ወይስ አትቀጥል? እንዲሁም ኢትዮጵያውያን አንድ ላይ እንኑር ወይስ አንኑር? እነዚህ መሰረታዊ ልዩነት የሚባሉ አይነት ናቸው። ይህ አይነቱ ብቻ አይደለም፤ ለምሳሌ በመኖር አለመኖር ጉዳይ ላይ እንኳ ልዩነት አለ። እነዚህን የሚወክሉ አጀንዳዎች ከህዝብ ከመረጥን በኋላ ውይይቱ መካሄድ ያለበት በእነዚህ ላይ ነው።
ማን ይወያይ? ወደሚለው ሲመጣ የሚያገባቸው ሰዎች ሁሉ የሚመረጡበት ነው። ውይይቱ ሲካሄድ ደግሞ ታዛቢዎች በግልጽ የሚመለከቱበት ሁኔታ አለ። ተወያዮቹ ሲናገሩ በድምጽም በምስል የሚወስድ አካልም ይኖራልና በአጭሩ አካሄዳችን ይህን ይመስላል።
አዲስ ዘመን፡- አስቀድመው ወደሌሎቹ ክልሎች መሄዳችሁን ጠቅሰዋል፤ የቀራችሁ ሁለት ክልል ሲሆን፣ እነሱም አፋርና ትግራይ ናቸው፤ ወደእነዚህ ክልሎች በተለይ ደግሞ ወደትግራይ መቼ ለመሄድ አሰባችሁ?
ዶክተር ዮናስ፡- ለአፋር ደብዳቤ ጽፈን ልከናል። መልስም በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን። በተመሳሳይ ደግሞ ወደ ትግራይ ያሰብነው ጉዳይ አሁን ከተፈጠረው ምቹ ሁኔታ አለመኖር ጋር በተያያዘ በእንጥልጥል ላይ ነው ያለው።
አዲስ ዘመን፡- ከህዝቡ ምን ትጠብቃላችሁ?
ዶክተር ዮናስ፡- የመጀመሪያ ከሕዝቡ የምንፈልገውና የምንጠብቀው ቀና አመለካከትን ነው። የምንሻው መንፈሳዊ ሞራላዊ ድጋፋቸውን ነው። ይህ ትልቁ ነገር ነው። በአመራር ላይ፣ በተለይ ሰላም ግንባታ ላይ ከችሎታሽም የበለጠ የአንቺን ከፍታ የሚወስነው አመለካከትሽና አስተሳሰብሽ ነው የሚባል አባባል አለ። በመሆኑም ትልቁ ነገር ይቻላል ብሎ ማሰብ ነው። ችግራችንን መፍታት እንችላለን፤ ለዚህ ደግሞ ጉልበቱ አለን ብሎ ማሰቡ የመጀመሪያው ወሳኙ መንደርደሪያ ነው። አገራችን ኢትዮጵያ የአባባል ሀብታም እንደሆነች ይታወቃል።
አንድ ሰው ገና ከቤቱ ሳይወጣ የሚሄድበትን አቅጣጫ ሳይወስን ከተንቀሳቀሰ ሁሉም አቅጣጫ መንገዱ እንደሆነ ነው የሚያስበው። አስቀድሞ ወስኖ ለወጣ ሰው ግን አካሄዱም ሆነ ግቡ ግልጽ ነው። ስለዚህም በመጀመሪያ ደረጃ አስተሳሰባችንና አካሄዳችንን ካስተካከልን ምንም እንኳ ዛሬ ፈተናዎች ቢጋረጡብንም፤ ግጭቶችም ቢያጋጥሙንም ይህንን ማለፍ እንችላለን፤ ደግሞም ዛሬ ሁሉ ቦታ ሰላም ነው። ነገር ግን አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶችን በማየት ተስፋ ሳንቆርጥ በእሳት ውስጥም ቢሆን እንኳ መራመድ እችላለሁ ማለትን ባህል ማድረጉ ተገቢ ነው። ተስፋ የሕይወት መንኮራኩር፤ የሕይወት ሞተርም ጭምር በመሆኑ ከሕዝቡ በመጀመሪያ የስነ ልቦና ዝግጅታቸውን እንፈልጋለን።
ሚዲያዎችም ቢሆኑ ሲዘግቡ የቃላት አጠቃቀም ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እንሻለን። ለሕዝቡ አዎንታዊ የሆነ ኃይል እንጂ አሉታዊ የሆኑ ነገሮችን ከማንጸባረቅ መራቁ ተመራጭ ይሆናል። በተለይ ደግሞ የሚዲያን ድጋፍ በጣም እንፈልጋለን፤ ምን አይነት ድጋፍ ከተባለ ለምሳሌ ምክክር ምንድን ነው? ከድርድርስ የሚለየው በምንድን ነው? የሚለውን ለሕዝቡ በአግባቡ ማስጨበጥ አንዱ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምን በሰላማዊ መንገድ ማምጣትን እንዴት ባህል ማድረግ ይቻላል? እንዴትስ አድርገን ነው የሰላምን ባህል በአገራችን የምንገነባው? የሚለውንም ከቤተሰብ ጀምሮ፣ አጸደ ሕጻናት ብሎም በቤተ እምነቶችና በሌሎችም ዘንድ ግንዛቤው እንዲኖር ማድረግ ከሚዲያው የሚጠበቅ ተግባር ነው። በተለያዩ ቦታዎች ትንሽ ልዩነት ሲኖር ወደ መሰዳደብና ወደ መገዳደል መሄድ ሳይሆን ወደመነጋገር መምጣትን ባህል ማድረግ እንዲኖር ሚዲያው እንዲሰራ እንፈልጋለን።
ሌላው ደግሞ ቁሳዊ ድጋፎችን እንሻለን። ለምሳሌ ገንዘብ የሚያስፈልግበት ጊዜ አለ። ሎጂስቲክ የሚያስፈልግበት ቦታ አለ። እስካሁን ከነበረው የበለጠ የሕዝቡን ቅን ትብብር እንፈልጋለን። ከመንግስትም በኩል ያለው ለምሳሌ በአዋጁ የተደነገጉት ጉዳዮች በተባለው መመሪያ መሰረት ለኮሚሽነሮች የሚያስፈልገው ድጋፍ ከደህንነት ጥበቃ ጀምሮ እንዲሟሉልን እንሻለን።
ተፎካካሪ ፓርቲዎች እጅግ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉልን ነው። ይህንኑ ድጋፋቸውን ሳያቋርጡ እንዲቀጥሉ እንፈልጋለን። አኩርፈው የወጡም ማለትም አልተወከልንም ያሉ ሰዎች ቆም ብለው በማስተዋል እንደገና ወደንግግሩ እንዲመጡ (በእርግጥ ይህ ተጀምሯል) እና አዎንታዊ ተሳትፏቸውን እንዲያደርጉ እንፈልጋለን። ያለችን አንድ የሆነችው ኢትዮጵያን በጋራ እንድንገነባ እንሻለን። በጥቅሉ ሁላችንም በሐቀኝነትና በአዎንታዊ አስተሳሰብ ልክ እጅ ለእጅ ተያይዘን ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድባችን እንዳደረግነው አይነት መረባረብና አንድነት ሁሉ አገራችንንም ለማዳን እንድንነሳሳ በአክብሮት ጥሪዬን አቀርባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ኮሚሽኑ ለሰላም የበኩሉን እያደረገና ያቀደውንም ተግባራዊ እንዲሆን እየተንቀሳቀሰ ነው፤ ይህ ባለበት ሁኔታ ግን ከአንዳንድ ምሁርም ሆነ ከማህበረሰብ አንቂዎች ዘንድ በማሕበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ያልተገቡ መልዕክቶች ሊስተዋሉ ይችላሉና ይህ እንዳይሆን እነዚህን አካላት ከወዲሁ ምን ማለት ይፈልጋሉ?
ዶክተር ዮናስ፡- እነዚህን አካላት እግዚአብሔር ይባርካችሁ ማለት እፈልጋለሁ። ምክንያቱም ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚለው፤ ታላቁ ጌታ በመስቀል ላይ ሲሰቀል ያልተገባ ነገር የሚያደርጉትን አይቶ ‹የሚያደርጉትን አያውቁምና አባት ሆይ ይቅር በላቸው› የሚል አይነት ምላሽ ነው የምንሰጣቸው። ሰላምን በሰላማዊ መንገድ ሲባል ምን እንደሆነ ለመግለጽ ያህል ለሰላም መንገድ የለውም፤ ወደሰላም መድረሻ መንገድ እራሱ ሰላም እንደሆነ ነው የምንናገረው። ሌላው ደግሞ ተቃውሞ ቢኖር ምንም አያስደንቀንም። ምክንያቱም ምክክር የእውነት ፍለጋ መንገድ ነውና። ስለዚህ ኑ! አብረን እንወያይ፤ ዛሬ ያስቆጣን፤ በአሉታዊ መንገድ እንድንጽፍ ያደረገን ሁልጊዜ በዛው አይቀርምና፤ ነገ ለውጥ ይኖራል። ስለዚህም ላለችን አንድ አገር አብረን እንስራ እንላለን። ጨለማውን ፈርተን ብርሃን ከማየት አንጉደል እንላቸዋለን። ልዩነቶቻችንንም በንግግርና በምክክር መፍታት እንችላለን። ትልቁ የስልጣኔ ምልክት ባኮረፉ ቁጥር ጫካ መግባትና መሳሪያ ማንሳት ሳይሆን በተጠይቅያዊ አካሄድ ተወያይተን መፍታትም ስልጡንነት ነው እንላለን።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ምንም ያህል ተቃውሞ ቢያጋጥመን እንኳን ተቃውሞ እንደመስፈንጠሪያ አቅም እንጠቀምበት እንደሆን እንጂ ከግባችን የሚያስቀረን አይሆንም። ደግሞም ተቃዋሚ በመኖሩም ነው መመካከሩ አስፈላጊ ሆኖ ስራ መስራት የተጀመረው። ስለሆነም በመቃወማቸው እናመሰግናለን፤ ለዚህም ነው እግዚአብሔር ይባርካቸው ስል መልስ መመለስ የጀመርኩት። የሚቃረን ነገር ካለም አብረን እንፍታ እንላለን። ሁላችንንም አገራችንንም ፈጣሪ አምላክ ይባርክ እላለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ዮናስ፡- ሰላም ይብዛልን፤ እኔም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 2 ቀን 2014 ዓ.ም