በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው እምቅ የቱሪዝም ሃብት ሲነሳ የሰሜኑ ክፍል የታሪክ፣ የማይዳሰስና የሚዳሰስ ቅርስ፣ የተፈጥሮና ተመንዝሮ የማያልቀው የባህል ሃብት ተጠቃሽ ነው። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ጎንደር የራሷን ድርሻ ትወስዳለች።
ጎንደር ከኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ 656 ኪ.ሜ እንዲሁም ከአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህር ዳር 175 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ በቀደምት ዘመናት የነገሥታት መናገሻ የነበረች ታሪካዊ ከተማ ናት። በ17ኛውና 18ኛው መቶኛ ክፍለ ዘመን የተሰሩ ታሪካዊ ቅርሶቿ የከተማዋ መገለጫዎች ናቸው። ታሪካዊ ቅርሶቿ የቱሪስቶች መዳረሻ ለመሆን አብቅተዋታል። በታሪክና በባህል ነፀብራቅነቷም ትታወቃለች::
የጎንደር ከተማ ዋነኛ የቱሪስት መስህብ የሆኑት አብያተ መንግሥታትና አብያተ ክርስቲያናት በወርቃማው ዘመኗ የኢትዮጵያ ነገሥታት ያሠሯቸው ናቸው:: አብያተ መንግሥታቱ በከተማው መሐል በሚገኘው ከፍተኛ ስፍራ ላይ ይገኛሉ፤ የተሠሩት ከድንጋይ፣ ከእንጨትና ከኖራ ሲሆን፣ የጥንት ኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ ረቂቅነትን ያንፀባርቃሉ:: የፋሲል ግንብ የኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ አሻራ ያረፈበት ግንባታ ነው። አገራችን የራሷ ግብረ ሕንፃ አሠራር እንደነበራት ዓለም የመሰከረው ይህ ግብረ ሕንጻ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት /UNESCO/ እ.ኤ.አ ጥቅምት 1979 ዓ.ም በዓለም ቅርስነት መዝግቦታል::
ኢትዮጵያ የሚዳሰሱና በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ የበርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት ናት:: ከማይዳሰሱ ሃብቶች መካከል በጎንደር ከተማና አጠቃላይ ስፍራ የሚከበሩ የጥምቀትና መስቀል እና ልዩ ልዩ ባህላዊ ሥርዓቶች ተጠቃሽ ናቸው። በደቡብ፣ በሰሜን፣ ምስራቅና ምዕራብ የሕዝቡን ረቂቅነትና ስልጡንነት የሚያሳዩ ትልልቅ ባህሎች አሉ። አለባበሱ፣ ሙዚቃው፣ የሀገር ፍቅር ስሜትና ወኔው ጎንደርን ልዩ ከሚያደርጓት መካከል በዋናነት የሚነሱ ናቸው።
ጎብኚዎችም እነዚህን መስህቦች ለማወቅ፣ የሁነቱ አካል ለመሆን በስፍራው በፍፁም ፍላጎትና ደስታ ይገኛሉ። የሰሜኑ የመስህብ ሃብት ነፀብራቅ የሆነችው የጎንደር ከተማን ለመጎብኘት ባህርና ውቅያኖስን አቋርጠው ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮችን ዘልቀው የሚመጡ ቱሪስቶች ብዙ ናቸው። የታሪክ፣ የባህል የስነ ሕንፃ ጥበብና አያሌ መስህቦችን ከመመልከት ባሻገር ቀደም ያሉ የኢትዮጵያን የስልጣኔ አሻራ ለቀሪው ዓለም በአድናቆትና በግርምት የሚያስተዋውቁና የአገራችንን ገፅታ የሚገነቡ ናቸው።
ከቱሪስት መስህብነትና ከቀዳሚ መዳረሻነት አንፃር ጎንደር የሚነገርላት በርካታ ነገሮች ቢኖራትም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የተቀዛቀዘ ድባብ ገጥሟታል። በተለይ ከሁለት ዓመት በፊት ተከስቶ የነበረው የኮቪድ ወረርሽኝን ጨምሮ አሁን ድረስ በስጋትነት የዘለቀው የሰላምና ፀጥታ ችግር ብዙ ሺ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው ደጇን የሚረግጡ ቱሪስቶችን የሚያርቁና ቀዝቃዛ መንፈስ የሚፈጥሩ ሆነዋል።
በተለይ በሰሜኑ በኩል ያለው አለመረጋጋትና ወላፈን ከአፎቱ ከሚደርሳቸው የሀገሪቱ ክፍሎች መካከል ቀዳሚዋ አድርጓታል። ይህ አጋጣሚ በቱሪዝም ፍሰቱ ላይ እክል ከመፍጠሩም ባሻገር፣ ማኅበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋቶችን ፈጥሯል። ይሁን እንጂ የክልሉ መንግሥትና የከተማዋ የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ልዩ ልዩ የማነቃቂያ ስልቶችን በመንደፍ የተዳከመውን የቱሪዝም ዘርፍ ቀና ለማድረግ እየሠራ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል በዛሬው የባህልና ቱሪዝም አምዱ በኢትዮጵያ ከላይ ባነሳናቸው ሁለት ምክንያቶች በዋናነት ደግሞ በሰላምና ፀጥታ ችግር የተከሰተውን የቱሪዝም ፍሰት መቀዛቀዝ “በጎንደር የተገኙትን ስኬታማ ስልቶች እንደ መነሻ በምን መልኩ መጠቀም ይቻላል?” በሚለው ጉዳይ ላይ የተወሰኑ ነጥቦችን ለማንሳት ይወዳል። በከተማዋ በ2014 ዓም በቱሪዝም ዘርፍ የተሠሩና የተገኙ ስኬቶች ምን እንደሆኑም ከዞኑ ቱሪዝም መምሪያ ያገኘንውን መረጃ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አቶ ቻላቸው ዳኘው የጎንደር ከተማ የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ፤ የኮቪድ ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ እጅግ ከፍተኛ የሚባል ጫና አሳድሮ ነበር፤ ጎንደርንም እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የዚህ ወላፈን አግኝቷታል:: የሕልውና ዘመቻውና የሕግ ማስከበር እንቅስቃሴው ከጎንደር ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ ነው የተካሄደው። ይህ ሁኔታ በተለይ በስራ እድል ፈጠራውና አጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ ከባድ አሉታዊ ተፅእኖ አሳርፏል::
“ይህንን ችግር መቋቋምና መለወጥ አስፈላጊ ነበር” የሚሉት አቶ ቻላቸው፣ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አሕመድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ገብተው የተዳከመውን የቱሪዝም ፍሰት ለማነቃቃት እንዲያግዙ ያደረጉትን ጥሪ ተከትሎ በከተማዋ የተዳከመው የቱሪስት ፍሰት ዳግም እንዲነቃቃ በጎ ተፅዕኖ እንደነበረው ይጠቅሳሉ። ከዚያ ባሻገር በርካታ መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም በከተማዋ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች እንዲገኙና ዓመታዊ ክብረ በዓሎች ላይ ሲታደሙ ስጋት እንዳይገባቸው መረጃዎችን የማድረስና የማሳመን ተግባሮች ማከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
“በወርሐ ጥር የተከበረውን ሃይማኖታዊውን የጥምቀት በዓል ምክንያት በማድረግ የመጡ እንግዶች በርካቶች ናቸው” የሚሉት የመምሪያ ኃላፊው፣ የከተማዋ ነዋሪ፣ የፀጥታ ኃይሉ፣ እንዲሁም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ምንም ነገር ኮሽ ሳይል እንግዶች ታሪካዊ ቦታዎችን እንዲጎበኙ፣ በባህሉ፣ በሙዚቃውና በገበያው የተሟላ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ይገልጻሉ። ይህም በተገባደደው 2014 ዓም የተዳከመው የቱሪስት ፍሰት በአዲስ ስልት እንዲነቃቃ ምክንያት እንደሆነ ነው ያመለከቱት።
“ዓለም አቀፍ ቱሪስቱ ወደ ሀገር ውስጥ የመግባቱ ጉዳይ በእጅጉ ቢቀንስም የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ወደ ከተማዋ በብዛት እንዲመጡ ስልቶችን ቀይሰን ስንሠራ ነበር” ያሉት የመምሪያ ኃላፊው፣ ከዚህ ውስጥ እንደ ዋና ምሳሌ የሚያነሱት “ጥምቀትን በጎንደር” ንቅናቄ ነው። ሌላው የአፄ ቴዎድሮስን “ቁንዳላ” ወይም ሹሩባ ወደ ከተማዋ እንዲመጣ የተደገረበት ሁኔታም ቱሪዝሙን የማነቃቃትና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ወደ ጎንደር እንዲያማትሩ ምክንያት እንደሆነ ገልፀዋል። በዚህ ረገድ ሁሉም የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን እንዲሰጡት በማድረግ ብሎም በከተማዋ የሚገኙ ተጨማሪ የመስህብ ስፍራዎች እንዲጎበኙ ቅስቀሳ ተደርጓል።
በውጪ ሀገር ቱሪስቶች ላይ ተወስኖ የቆየው የከተማው የቱሪዝም ዘርፍ በኮቪድና በሰላም እጦት ምክንያት ተቀዛቅዞ መቆየቱ አዲስ አማራጭ ለመቀየስ ምክንያት ሆኗል ይላሉ። በ2011 ዓም የተጠናከረው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የጎንደር ከተማ ወደ 26 ሺህ በሚሆኑ የውጪ አገር ቱሪስቶች ተጎብኝታለች።ይህ አኃዝ በ2013 ዓም ወደ 531 ቱሪስት ዝቅ ብሏል። በ2014 እንዲሁ በተመሳሳይ ወደ 531 ቱሪስቶች ብቻ ወደ ጎንደር መምጣቸው ተረጋግጧል። በዚህ ደረጃ ቱሪስቱ እንዲያሽቆለቁል ምክንያቱ ዓለም አቀፍ ወረርሽኙና የፀጥታ ችግሩ ነው።
ይህ ገፊ ምክንያት በተጠናቀቀው የ2014 በጀት ዓመትም የሀገር ውስጥ ቱሪዝሙን ለማሳደግ ስልት እንዲነደፍ ምክንያት ሆኗል። የተደረገው ጥረት ውጤት እንዲገኝ መነሻ መሆኑን የመምሪያ ኃላፊው አመልክተዋል። በተለይም የገና እና የጥምቀት በዓላት ለቱሪዝሙ መነቃቃት አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል:: በተጨማሪም የአጼ ቴዎድሮስ ቁንዳላ ወደ ጎንደር ከተማ መጥቶ ለሕዝብ እይታ ክፍት መደረጉና የከተማውን የቱሪዝም ሀብትና ጸጋዎች ለማስተዋወቅ የተደረገው ጥረት ሀገር ውስጥ የቱሪዝም ፍሰቱን አሳድጎታል ብለዋል::
አኃዞችን እንደ ማሳያ ያቀረቡት ኃላፊው፤ በ2013 በጀት ዓመት የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር 57 ሺህ እንደነበር ያስታውሳሉ፤ በ2014 በጀት ዓመት ይህ አኃዝ ወደ 325 ሺህ ማደጉን ተናግረዋል:: ከሀገር ውስጥ የቱሪዝም ዘርፉም ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱንም ነው ያመለከቱት። ይህም በከተማው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መነቃቃት ላይ አስተዋጽኦ ማበርከት መቻሉን አስረድተዋል:: ይህ ገቢ በ2014 የበጀት ዓመት አጠቃላይ የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥርን መሠረት ያደረገና በቆይታ ጊዜያቸው ፈሰስ ሊያደርጉት የሚችሉትን የገንዘብ መጠን በሳይንሳዊ ቀመርና በተደራጀ መረጃ በማስላት የተገኘ መሆኑንም ጠቁመዋል።
እንደ መምሪያ ኃላፊው ገለጻ፤ በ2015 በጀት ዓመትም ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራል:: በ2013 ዓም 17 ሺህ የነበረው የአገር ውስጥ ጎብኚ በ2014 ዓም ወደ 325ሺህ ሊደርስ ችሏል። አሁን ደግሞ የጎብኝዎችን ቁጥር ከ325 ሺህ ቁጥርም ወደ 700 ሺ ለማድረስ እቅድ ተነድፎ ወደ ሥራ ተገብቷል::
የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግም በትምህርት ቤቶችና በመንግሥታዊ ተቋማት የሀገርህን እወቅ ክበባት የሚጠናከሩበትንና በአዲስ መልክ የሚደራጁበትን አቅጣጫ በማስቀመጥ ወደ ሥራ መገባቱን ይገልፃሉ።
“ቱሪዝም የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሠራር የሚጠይቅ ነው” የሚሉት አቶ ቻላቸው፤ ሁሌም ስለ ቱሪዝም እድገት ስናወራ ብንውል ሀገሪቱ ሰላም ካልሆነች አንድ እርምጃ መራመድ አንችልም ይላሉ። ከዚሁ ጋር በተመሳሳይ የአገልግሎት አሰጣጡ፣ የቅርሱ አጠባበቅ ደረጃ መሻሻል እንዲሁም የመረጃ ፍሰትና ሃብቶቹን በተገቢው መልኩ ከማስተዋወቅ አንፃርም ጉልህ ሥራዎች ካልተሠሩ ውጤት ማምጣት ፈተና እንደሚሆን ይገልፃሉ። ስለዚህ በቀጣይ በጀት ዓመት እነዚህን በማሻሻል የቱሪዝም ዘርፉ እመርታዊ ለውጥ እንዲያመጣ እንደሚሠራ ነው ያስታወቁት።
“በተዳከመ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ውስጥ ኩነት ማብዛት ዘርፉ እንዲያገግም የላቀ ድርሻ ያበረክታል” የሚሉት የመምሪያ ኃላፊው፤ በ2015 ዓም በጎንደርና አካባቢው ልዩ ልዩ ቦታዎች ላይ የፊልም መንደር እንዳለ ሁሉ፣ የሙዚቃ መንደር (የአዝማሪዎች ፌስቲቫሎች) እንዲኖሩ እንደሚሠራ ተናግረዋል። ከዚህ ባሻገር የኮንፍረንስ ቱሪዝም በጎንደር በስፋት እንዲካሄድና ከ2008 ጀምሮ የተዳከመው ኢኮኖሚና የንግድ እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ ለመሥራት እቅድ መያዙን ይናገራሉ።
“በተያዘው በጀት ዓመት በጎንደር ከተማ የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶች እንዲጠበቁና አስፈላጊው እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ይሠራል” የሚሉት የመምሪያ ኃላፊው፣ የመዳረሻ ልማቶችን በዋናነት የሚሠሩት ግን የክልሉ መንግሥትና የፌደራል መንግሥት መሆናቸውን ይናገራሉ። በተጨማሪ በእነዚህ አካላት በዋናነት ከቅርስ ጥበቃ ባለስልጣንና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጋር በመሆን ሦስት ታሪካዊ መዳረሻ ቦታዎች በጥናት መለየታቸውንም ይጠቅሳሉ፤ ለእዚህም ጥገናና መልሶ ልማት 750 ሚሊዮን ብር ገደማ እንደሚያስፈልግ ተገምቷል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ አጠቃላይ ጥገናውን የሚወስነው የጥናት ሰነድ እንዲዳብር ውይይት እየተደረገበት ነው። ስለዚህ ይህ ዋና ጥገና እስኪጀመርና ሁሉም የድርሻውን ኃላፊነት ተከፋፍሎ ሥራ እስኪጀምር ድረስ የጎንደር ከተማ አስተዳደርና መምሪያው ምቹ ሁኔታዎች የመተግበርና ቅርሶቹ እስኪጠገኑ ጠብቆ የማቆየት ሥራ ያከናውናሉ።
ኃላፊው በማጠቃለያቸው ጎንደር ውስጥ ቢያንስ በ100 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ ዓለም አቀፍ ቅርስ ማለትም የፋሲል አብያተ ቤተ መንግሥት፣ የራስ ዳሸን ተራራ፣ የጣና የእንስሳትና እፅዋት ብዝኃ ሕይወት፣ የሰሜን ብሔራዊ ፓርክ እንዲሁም ሁሉንም የቱሪዝም መስህብ ያማከለ ሃብት ያለበት መሆኑን ጠቁመው፣ እነዚህን ለመጠበቅ፣ ለማስተዋወቅና ከዚያ የሚገኘውን ጥቅም ለማስጠበቅ ባለሙያ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ስለዚህ የሰው ሃብት ልማት ላይ ትኩረት ተደርጎ ድጋፍ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። “ችግር ከማወቅ ነው የሚጀምረው” የሚሉት ኃላፊው፣ እላይ ያሉት መሪዎች እዚያው ቅርሶቹና የመስህብ ስፍራዎቹ ዘንድ በመገኘት ማየት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
እኛም በተለያዩ ምክንያቶች የተዳከመው የቱሪዝም ዘርፍ ዳግም እንዲነቃቃ ለማስቻል በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ፣ በክልሉና በጎንደር የዘርፉ አመራሮች በ2014 ዓም የተወሰዱ እርምጃዎችንና ስልቶችን አስፍቶ በመላው አገሪቱ ዘርፉ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግብ መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመን እንሰናበታለን።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 1 ቀን 2014 ዓ.ም