ለወጣቱ የስራ እድል ለመፍጠር ከዚህ ቀደም በመንግስት በኩል በርካታ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል:: ከነዚህ ጥረቶች ውስጥ አንዱ ወጣቶች በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው እንዲሰሩ ማድረግ ነበር:: አብዛኛው ብድር ሳይመለስ ቀረ እንጂ ለወጣቶች የተመደበው የ10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድም ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ነበር:: ሆኖም ካለው የስራ ፈላጊ ወጣት ቁጥር አንፃር አዋጭና ውጤታማ የስራ መፍጠሪያ ስርአቶች ጉድለት በመኖሩ በሚፈለገው ልክ ለወጣቱ የስራ እድል መፍጠር ሳይቻል ቀርቷል::
‹‹ከዚህ ቀደም በመንግስት በኩል ለወጣቱ የስራ እድል ለመፍጠር ሲደረጉ የነበሩ ያለፉ ሙከራዎች ጥሩ ቢሆኑም ከፍተኛ የስራ ፍላጎት፣ የወጣት ቁጥርና የህዝብ እድገት በመኖሩና የዛኑ ያህል ደግሞ ሀገሪቱ ውስጥ ያለው ገበያ ይህን መሸከም የሚችል ባለመሆኑ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አልተቻለም:: በመሆኑም ለወጣቱ ጤናማ የስራ እድል ለመፍጠር ሞያዊ ምክረ ሃሳቤ ይህ ነው›› ይላሉ የብሩህ ማይንድስ ኮንሰልት መስራችና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ደሳለኝ::
እርሳቸው እንደሚሉት ድርጅታቸው ‹‹ብሩህ ማይንድስ›› አማካሪ ድርጅት ሲሆን ስራውን እ.ኤ.አ በ2014 በይፋ ጀምሯል:: የጥናትና ምርምር ስራዎችንም ሲያከናውን ቆይቶ እ.ኤ.አ ከ2020 ወዲህ በማህራዊ፣ ቢዝነስና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ አስራ ሁለት ያህል ስልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል:: በአሁኑ ግዜ ደግሞ በሚታወቅበት የንግድ ስራ ማጎልበት አገልግሎት ይሰጣል::
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ በኢትዮጵያ በርካታ የስራ ፍላጎት አለ:: ይህም አሁን በስራ ላይ ካለው ሰው በተጨማሪ በየዓመቱ 2 ሚሊዮን ወጣቶች ከከፍተኛ የትምህርትና የቴክኒክና ሞያ ስልጠና ተቋማት ተመርቀው ወደ ስራ ገበያ ይመጣሉ:: በተጨባጭ መሬት ላይ ያለው እውነታ ሲታይ ግን የኢንዱስትሪውና የግብርናው ዘርፍ ባለማደጉ፣ ያለው የንግድና የግብይት ስርአትም በሚገባ መስመር የያዘ ባለመሆኑ ከፍተኛ የስራ አጥነት ችግር አለ::
ይህም ስራ ፈላጊ በብዛት አለ እንጂ ስራ መፍጠር የሚያስችል ምህዳር የለም ማለት ነው:: ይህን ችግር በማየት መንግስት በአሁኑ ግዜ የስራና ክህሎት ሚንስቴር፤ ከዚህ ቀደም ደግሞ የስራ ፈጠራ ኮሚሽንን አቋቁሟል:: ጥቃቅንና አነስተኛ በሚል ኢንተርፕራይዞችን ለማደራጀትና ስራ ለመፍጠር ያለሙ ጥረቶች ሲደረጉም ቆይተዋል:: በመንግስት በኩል ሲደረጉ የነበሩ ያለፉ ሙከራዎች ጥሩ ቢሆኑም ታዲያ ከፍተኛ የስራ ፍላጎት፣ የወጣት ቁጥርና የህዝብ እድገት በመኖሩና በዛው ልክ ደግሞ ሀገሪቱ ውስጥ ያለው ገበያ ይህን መሸከም የሚችል ባለመሆኑ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አልተቻለም::
ብዙ ስራ መፍጠር የሚያስችል አቅም እያለ ለወጣቱ ስራ መፍጠር አልተቻለም:: ወጣቱ ጋር እውቀት፣ ክህሎት፣ ጉልበትና ግዜ አለ:: ይሁንና የመስሪያ ቦታና መነሻ ካፒታል ትልቅ ማነቆ ሆኗል:: ሆኖም ይህን ችግር ፈጠራ የታከለባቸው የአሰራር ስሪቶችን በመከተል፣ በመደራጀትና በመቀናጀት ብሎም በጋራ በመስራት መቅረፍ ይቻላል::
ጥቅም ላይ ሳይውሉ የቀሩና የመከኑ በርካታ እድሎች አሉ:: የተዘዋዋሪ ፈንድን ጨምሮ በመንግስት በኩል የተደረጉ የገንዘብ ድጋፎችም ነበሩ:: በወጣቶችም ዘንድ እነዚህን እድሎች ወስዶ ከመጠቀም ይልቅ እንደ ልገሳና እርዳታ ወስዶ ተጠቅሞ ዞር የማለትና ብድርን ያለመመለስ ችግሮች ይታዩ ነበር:: በዚህም በርካታ ብድሮች ተበላሽተዋል:: ይህም በቀጣይ ለሚፈጠረው የስራ እድል እንቅፋት ሆኗል::
መንግስትም ሆነ ሌሎች አካላት ወጣቶችን ማመን ይፈልጋሉ:: መተማመን ከሌለ ማበደርም መስራትም ያስቸግራል::ዕድሉን ያገኙ ወጣቶች የተሰጣቸውን ሼድ ለሌላ ወጣቶች ከአምስት አመት በኋላ ካልለቀቁ የስራ እድል መፍጠር አይቻልም:: በሌላ በኩል ደግሞ በትክክል የቀረቡ ወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ጥያቄዎች ሲያነሱ በአግባቡ ምላሽ የሚያገኙበት ስርአት አልተዘረጋም::
በዛው ልክ በጣም በርካታ የስራ እድል መልሰው የሚፈጥሩ፣ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩ፣ የፍጆታ እቃዎችን ችግር የሚቀርፉ፣ የኑሮ ውድነትን የሚያቃልሉ የፈጠራ ሃሳቦች ያሏቸው ወጣቶች ሲመጡ አደራጅቶ፣ አሰልጥኖ፣ አብቅቶ፣ የብድር አመላለስንም ባህልን ፈጥሮ፣ በቁጠባ በኩል ያለውንም ባህል አሳድጎ የሚሰጥ ስርአት አልተበጀም:: በዚህም ምክንያት በርካታ ሀብት ባክኗል::
ዳይሬክተሩ እንደሚያብራሩት የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ቢሰሩ፣ ከመስሪያ ቦታና መነሻ ካፒታል ከማቅረብ አንፃር ምቹ ሁኔታ ቢፈጠር፣ የአካሄድም፤ የአስተሳሰብም፤ የአሰራርም፤ የህግ ማሻሻያዎች ቢደረጉ የሚገኙትን ትሩፋት በማሰብ መንግስትም ፍቃደኛ በመሆኑና በልማት ባንክ በኩልም የተደረጉ ጥረቶች አበረታች በመሆናቸው፣ ወጣቶችም ከበፊቱ ይልቅ አሁን ጥሩ መነሳሳት ያላቸው በመሆኑ ጤናማ የስራ እድል መፍጠር ይቻላል:: ነገር ግን ደግሞ ወጣቶቹ የቅርብ እገዛና ክትትል ያስፈልጋቸዋል::
ከዚህ አኳያም ብሩህ ማይንድስ ከኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ጋር በጋራ ለመስራት ያነሳሳው ደጋፊ አካላትና ወጣቱ በመሀል ያለውን ክፍተት መቅረፍ እችላለሁ ብሎ በማሰቡ ነው:: ምንም እንኳን ድርጅቱ ለትርፍ የተቋቋመ ቢሆንም እንደግሉ ዘርፍ ማህበራዊ ሃላፊነትም ያለበት በመሆኑ በመንግስትም ሆነ መንግስታዊ ባለሆኑ ተቋማት የሚሰሩ የስራ እድል ፈጠራ ስራዎች ላይ የራሱን አስተዋፅኦና አሻራ ማኖር አለብኝ ብሎ ያምናል::
በተለይ ስራ ፈጠራ ሃሳብ ማመንጨትን ስለሚጠይቅ የግሉ ዘርፍ ለስራ ፈጠራ ቅርብ ነው ተብሎ ይታመናል:: ካለው አካሄድና አሰራርም ተወዳዳሪነት ላይ ተመስርቶ የሚሰራ ስለሆነ ስራን ለመፈፀም ሳይሆን ስራን ለነገ አበርክቶ የተሻለ ውጤት ለማምጣት የግሉ ዘርፍ ይሰራል:: በመሆኑም ሁሌም ውድድር ስላለ ሁሌም ነቃ ያለ አስተሳሰብ፣ አሰራርና ለየት ያለ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ያለበት በመሆኑ የግሉን ዘርፍ ተሞክሮ ማምጣትና ማገዝ ያስፈልጋል::
አብዛኛው ስራውን የሚፈጥሩት ወጣቶችና የኢንተርፕራይዞች ሆኖ የመንግስት ሚና ከመስሪያ ቦታና መነሻ ካፒታል አንፃርና ህጎችን ፍቃድ ከማውጣት ጀምሮ ያሉ ቢሮክራሲዎችን በማቅለል በገበያ ውስጥ ይበልጥ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ፣ የመንግስት ትልቅ ግዢዎችም ከኢንርፕራይዞች እንዲከናወኑ በማድረግና በማገዝ ማሳደግ ይቻላል::
ብሩህ ማይንደስም የወጣቶቹ ችግር ምን እንደሆነ በጥናት በመለየት መፍትሄዎችን ይጠቁማል:: ለአብነትም ቴክኖሎጂ ላይ የሚደራጁ ወጣቶች መብራትና ውሃ አይፈልጉም:: ከዚህ ይልቅ የዲጂታል መሰረተልማት ይፈልጋሉ:: ባላቸው መሰረተልማት ውስጥ ገብተው ፈጠራ በታከለበት መንገድ ብዙ አገልግሎት መስጠት ይችላሉ:: ከዚህ አኳያ በህክምና፣ በግብርና፣ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፎች ወጣቶች ሃሳብ ካላቸው ያንን ስራ ለመስራት የሚያስችል መሰረተ ልማት ያስፈልጋቸዋል::
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት ኢንተርፕራይዞችን የሚመሩ የመንግስት አካላት ለሁሉም ኢንተርፕራይዞች ወጥ የሆነ ድጋፍ ነው የሚያዘጋጁት:: ከዚህ አንፃር ብሩህማይንድስን የመሰሉ አማካሪ ድርጅቶች መምጣት ለእያንዳንዱ ኢንትርፕራይዞች የትኛው መፍትሄ እንደሚሰራ፣ ምን አይነት ክፍተት እንዳለባቸው፣ የገበያ ትስስር እንዲኖራቸው ለመጠቆም ይረዳል:: ይህም በስልጠና፣ መረጃ በመስጠት አልያም ቴክኖሎጂ በማበልፀግ ሊሆን ይችላል::
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ወጣቶችን መልምሎ፣መዝግቦና አደራጅቶ ድጋፍ ያደርጋል:: ብሩህማይንድስ ደግሞ ሞያዊ እገዛ ለማድረግ ከዚህ ተቋም ጋር የጋራ ስምምነት አድርጓል:: በመንግስት ድጋፍ የተሳካላቸው ኢንተርፕራይዝ ቢኖሩም ምንያህሉ ናቸው የሚለው ግን አጠያያቂ ነው:: እየተደረገላቸው ያለው መንግስታዊ ድጋፍ እንዳለ ሆኖ ታዲያ በርካቶች እንዲሳካላቸው እየተደረገላቸው ያለውን የድጋፍ አካሄድ፣ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ላይ ያለውን አጠቃቀምና ተቀናጅቶ መስራት ላይ ያለውን ድክመት ማስተካከል ያስፈልጋል::
በኢንተርፕራይዞችና ድጋፍ አድራጊ ተቋማት በኩል ድክመት እንዳለ ይታወቃል:: በሁሉም ኢንትርፕራይዞች ውስጥ ወጥ የሆነ ድጋፍ የማድረግ ችግር አለ:: ከዚህ አንፃር የፋይናንስ፣ ቴክኖሎጂ የሚፈልግ የቴክኖሎጂ፣ የማርኬቲንግ ድጋፍ ማድረግ ይገባል:: ኢንተርፕራይዞቹ ሲደራጁም ምን አቅም አላቸው፣ ምን ይጎላቸዋል የሚለውን ማየት ያስፈልጋል::
ብሩህ ማይንድስ ከኢትዮጵያ ኢንትርፕራይዝ ልማት ውጪ ከሌሎች መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማትና ከግል ድርጅቶች ጋር ይሰራል:: ለአብነትም መንግስታዊ ካልሆኑት ውስጥ ከሶስት ሀገር በቀል ድርጅቶችና ከሁለት አለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የስድስት ወር የንግድ ስራ ማጎልበት አገልግሎት ድጋፍ በመስጠት በተለያዩ መስኮች 60 ኢንተርፕራይዞችን ወደ ስራ ማስገባት ተችሏል:: ባለፉት ስድስት ወራቶች ውስጥም ካፒታላቸው እያደገ ነው፤ አባላቶቹም አልተለያዩም::
በቅርቡ ደግሞ ከአንድ የግል ድርጅት ጋር በመተባበር የሚሰሩ ስራዎች 25 ኢንተርፕራይዞች ከትርፍ፣ከደምበኛ አያያዝና ድርጅታዊ ቅርፃቸውን ጠብቆ ከመሄድ አንፃር ውጤታማ መሆን ችለዋል፤ ከፍተኛ ለውጥ እየታየም መጥቷል:: የአምራች ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ እንደሀገር ሲታሰብ በርካታ ገንዘብ የሚፈስበት እንደመሆኑ ብዙ ለውጥ ይመጣበታል:: ለወጣቱ በርካታ የስራ አድል ይፈጠርበታል ተብሎ ይታሰባል::
ዳይሬክተሩ እንደሚገልፁት ብሩህ ማይንድስ ‹‹ ልዩ ምልከታ›› በሚል ርዕስ በስራ አድል ፈጠራ ላይ የሚያተኩር የፖሊሲ የውይይት መድረክ በየወሩ ያካሂዳል:: ከፖሊሲ ውይይቱ ባሻገር የስራ እድል ፈጥረው ለሌላው አርያ የሆኑ ወጣቶች ልምዳቸውን በዚህ መድረክ ያካፍላሉ:: ይህ መድረክ አራት መሰረታዊ ዓላማ ያለው ሲሆን የመጀመሪያው የባለድረሻ አካላት የስራ እድል ፈጠራ ምህዳሩ እንዲሰፋ በጋራ እንዲቀናጁ ማደርግ ነው:: ይህም አጋርነታቸውንና ቅንጅታዊ አሰራራቸውን ማሻሻል ነው::
ሁለተኛው ዓላማ ደግሞ የፋይናንስ ተደራሽነትን በተለይ ደግሞ የስራ ማስኬጂያ መነሻ ካፒታል ተደራሽነትን መጨመር ነው::ይህም በአንድ ወገን በመንግስት ወይም መንግስታዊ ባልሆነ ተቋም አልያም በግሉ ዘርፍ ብቻ የገንዘብ ብድርና ድጋፍ ለዚህ ሁሉ ጀማሪ ስራ ፈጣሪ ማድረስ ስለማይቻል ስራው ቢቀናጅና ወደ አንድ ማእከል ቢሰበሰብ የፋይናነስ ተደራሽነቱን ማስፋት ይቻላል::
ሶስተኛው ዓለማ ደግሞ የስራ ጀማሪዎች ትልቁ ፈተና የሆነውን ቢሮክራሲ /ውጣውረድ/ መቀነስ ነው:: በጣም ውስብስብ የሆነው ነገር እንዲቀል ባለድርሻ አካላት እየተመካከሩ ህጋዊነቱን የጠበቀ ነገር ግን ቀላልና ቀልጣፋ የሆነ የንግድ ስራ ቢጀመር ስራ ፈጣሪዎች ሃሳቡ በመነጨላቸው ሰአት መብታቸው ተከብሮ ፍቃድ አውጥተው ወዲያው ወደስራ ይገባሉ:: ይህም በርካታ የስራ እድል ይፈጥራል::
አራተኛውና የመጨረሻው ‹‹የልዩ ምልከታ›› ዓላማ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ማምጣት ነው:: በሀገሪቱ 28 ከመቶ ያህሉ ስራ አጥ ወጣት ነው:: ለስራ ፈጠራ የሚመደበው በጀት ደግሞ አነስተኛ ነው:: በዚህ ዘርፍ የሚመደቡት ባለሞያዎች ምን ያህል ብቁ ናቸው የሚለውም አጠያያቂ ነው:: መንግስት ለሌሎች ዘርፎች የሚሰጠውን ያህል ትኩረት ለስራ እድል ፈጠራ በትክክል ትኩረቱ ከበጀት፣ ከውሳኔ፣ ከክትትል አንፃር ይሰጣል ወይ የሚለውም አነጋጋሪ ጉዳይ ነው:: ከዚህ አኳያ የተሻሉ ፖሊሲዎችና አሰራሮች ቢመጡ ተቋማትም የራሳቸውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ::
ለአብነት ከፖለሲ አኳያ ከገንዘብ ተቋማት ውስጥ ባንኮችን ማየት ቢቻል ማስያዣ ስለሚያስፈልግ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ብድር አይሰጡም:: ነገር ግን ኢንተርፕራይዞቹ ያለማስያዣ ብድር የሚያገኙበትና መንገስትም ግማሽ ዋስ የሚሆንበት ሁኔታ ቢፈጠር፣ ከባንኮችና ማይክሮ ፋይናነስ ተቋማት በህግ ደረጃ ተቀባይነት ያለው የብድር ስርአት ቢመቻች ወጣቶቹ በአጭር ግዜ ውስጥ አምራች ሆነው በስራቸው ለሌሎች በርካታ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር ይችላሉ::
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 29 ቀን 2014 ዓ.ም