ብዙ ጊዜ እንደምንለው ባለውለታዎቻችን ብዙ ናቸው። የዛሬውን አያድርገውና፣ ጠላት የለንም እስክንል ድረስ ወዳጆቻችን ተቆጥረው አያልቁም ነበር። ከአፍሪካ እስከ ምስራቁ አለም – ሩሲያ፣ ቻይና … ድረስ፤ ምእራቡን አካልሎ፣ አሜሪካንን ጨምሮ፤ እሲያን አዳምሮ ወዘተርፈ ሁሉ ጥብቅ ወዳጆቻችን፤ አጋርና አርአያነታችንን ፈላጊዎች ነበሩ። ወደ ግለሰቦችም ስንመጣ ጉዳዩ ያውና ሲበዛም ተመሳሳይ ነው። ለዚህ ደግሞ ከጥንታዊያኑ ባለቅኔ ሆሜር ጀምሮ እንደ እነ ፕሮፌሰር ፓኦሎ ማራሲኒ፣ አሌሳንድሮ ባውዚ፣ ሪቻርድ ፓንክረስት እና ሀሮልድ ማርከስ ያሉትን መጥቀሱ ብቻ በቂ ነው።
በተለይም ወደ ምሁራኑ አምባ ጎራ ስንል የምናገኛቸው አፍቃሬ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያም አብዝተው ያሰቡ፣ አስበውም የተመራመሩ፣ ተመራምረውም በሰሯቸው በርካታ ስራዎች እውነቱን ቁጭ ያደረጉ አያሌ ሲሆኑ፣ አንዱም ዛሬ የምናስታውሳቸው ባለውለታችን ጁላይ 10 1919 ወደ’ዚህ ዓለም የመጡትና ጁን 24 2012 ከዚህ አለም የተለዩት አለም አቀፍ ምሁሩ ፕሮፌሰር ሰምነር (Claude Sumner, SJ) ናቸው።
በዜግነት ካናዳዊ፣ በምርጫቸው ኢትዮጵያዊ የሆኑት ፕሮፌሰር ሰምነር ከኢትዮጵያ ጋር የነበራቸው የማይበጠስ ቁርኝት የሚጀምረው ለ50 ጥቂት ፈሪ አመታት ወዳ ስተማሩበት፣ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከመጡበት 1953 ጀምሮ ሲሆን፤ ይህም በዘመን አይሽሬ ስራዎቻቸው ከመገለፁ ባሻገር እስከ’ለተ ሕይወታቸው ፍፃሜ ድረስ የአንገት ማተባቸው ሆኖ ዘልቋል። (ይህንን ሰፋ ባለ መልኩ ለመረዳት በቴዎድሮስ ኪሮስ የተጠቀሰውንና ከ”Ethiopian Review” (July 1994) ጋር ያደረጉትን ቃለ-መጠይቅ፤ እንዲሁም በዚሁ ሰው “Doing African Philosophy: Claude Sumner’s Work on Ethiopian Philosophy” በሚል የተዘጋጀውን ጥናት ይመለከቷል።)
በተለይ የ’ኛኑ ፈላስፋ ወርቅዬ (ዘርዓ ያዕቆብ (1599– 1692))ን እና ደቀ መዝሙሩ ወልደሕይወት (ምትኩ) ን፤ እንዲሁም ፍልስፍናቸውን (ሀተታዎች – ዝቅ ብለን የምንጠቅሳቸው ሥሜነህ “ሐተታ” የተባለው የፍልስፍና መንገድ አንድን ጉዳይ ደረጃ በደረጃ እየጠየቁ ጥልቅ ወደ ሆነ ምርምር የመግባትና በዚህም አንድ እውነተኛ እውቀት ላይ የመድረስ ሂደትን ያመለክታል።ያሉትን መያዙ ጠቃሚ ነው።) ለድፍን አለም ከማስተዋወቅ እና የፍልስፍናቸውን መሰረት (በተለይ ”በአስራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን የሕይወት ታሪኩንና የፍልስፍና ስራውን ብራና ዳምጦ፣ ቀለም በጥብጦ፣ በመጻፍ ያቆየልን ኢትዮጵያዊ አመክኗዊ (rational) ፈላስፋ” ስለመሆኑ እውቅናን ያገኘው ዘርአያዕቆብ ታላቅ ስራ መሆኑ የተመሰከረለትንና ተለይቶ የሚታወቅበትን ”ሀተታ” ፈልፍሎ ከማውጣት አኳያ ያለምንም ተወዳዳሪም ሆነ ተፎካካሪ ተጠቃሽ የሆኑት ሰምነር በዚሁ ስራቸው አለም አቀፍ እውቅናን ማግኘት ብቻ ሳይሆን፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይቀር የክብር ዶክተሬት ዲግሪን አግኝቷል። (በአለማችን የዘመናዊ ፍልስፍና ፈር ቀዳጅ የኢትዮጵያ ፍልስፍና፣ በተለይም የዘርዓያዕቆብ ፍልስፍና ነው የሚል ማጠቃለያ ላይ የደረሱት ሰምነር ኢትዮጵያን በተመለከተ በርካታ ስራዎችን ያከናወኑ ሲሆን፤ በተለይ Ethiopian Philosophy, vol. I: The Book of the Wise Philosophers, Ethiopian Philosophy, vol. II: The Treatise of Zara Yaecob and Walda Hewat: Text and Authorship፣ Ethiopian Philosophy, vol. III: The Treatise of Zara Yaecob and Walda Hewat: An Analysis, Ethiopian Philosophy, vol. IV: The Life and Maxims of Skandes, Ethiopian Philosophy, vol. V: The Fisalgwos, Classical Ethiopian Philosophy ስራዎቻቸው በቀዳሚነት ይጠቀስላቸዋል።)
ሰምነር ልክ በዚሁ ዘመን በፈረንሳይ በዴካርቴስ እንደተጀመረው ሁሉ፣ ዘመናዊው የምክንያታዊነት (አመክኗዊነት?) ፍልስፍና በዘርአያዕቆብ አማካኝነት በአፍሪካ ተጀመረ (He argued that modern rationalist philosophy began in Africa with Zera Yacob at the same time that it began in France with Descartes.) የሚል ድምዳሜ ላይ በመድረስም በአፍሪካ፤ በተለይም በኢትጵያ ፍልስፍና ላይ የነበረውን የተዛባ የነጮቹን አለም አተያይ ፉርሽ አድርገዋል።
በካንሰር ህመም ምክንያት በ92 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት የተለዩት ካናዳዊው የፍልስፍና ፕሮፌሰር ክላውድ ሰምነር ባደረጓቸው ዘርፈ ብዙና ሁሉን አቀፍ ጥናታቸው”Philosophical tradition, the main source of African philosophy.” (የአፍሪካ ፍልስፍና ምንጭ የመፈላሰፍ ልማድ ነው) የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሱ ሲሆን፤ በተለይም ኢትዮጵያን በተመለከተ፤
(ኢትዮጵያ የሁለቱም፤ ማለትም የተፃፈም ያልተፃፈም፣ ጥንታዊ እና ስር ነቀላዊ፣ መንፈሳዊና ገሳጭ፣ ህዝባዊና ግላዊ ፍልስፍናዎች መገኛ ነች። የተለያዩ የፍልስፍና አገላለፆች [ቋንቋዎች]፤ እንዲሁም፣ ዘመናዊ አስተሳሰብ የሚገኝባት ምድር ነች።) “Ethiopia therefore harbours both types of philosophy: oral and written, traditional and radical, sapiential and critical, popular and personal. It is the land of diverse expressions of philosophy and the birthplace of modern thought” (Sumner, 1998, African Philosophy, p. 333) በማለት ያሰፈሩት ኢትዮጵያና ፍልስፍናዋን በተመለከተ ሀሳብ በተነሳ ቁጥር ሁሌም ሳይጠቀስላቸው የማይታለፍ ድምዳሜያቸው ነው።
ከጥናቶቻቸውም ባለፈ በ1961 በአፍሪካ ሕብረት አዳራሽ በመገኘት ለመሪዎችና አጠቃላይ ታዳሚው “The Existence and Nature of African Philosophy— Problématique d’une philosophie africaine,” በሚል ርእስ በወቅቱ ታዳሚውን እጅግ ያስደመመና እጅን ከንፈር ላይ ያስጫነ ጥናት ያቀረቡ ሲሆን፤ በዚሁ ጥናታቸውም የኢትዮጵያን ፍልስፍና (እሳቸው written philosophical literature of Ethiopia ያሉት) እና መሰረቱን ከፍ አድርገው ማሳየታቸውን በThe Proverb and Oral Society (1999) ስራቸው ላይ ለንባብ አብቅተውት እናገኛለን።
ሰምነር በእነዚህ ጥልቅ የምርምር ስራዎቻቸው አማካኝነት ሶስት አበይት ተግባራትን ማከናወናቸው የሚነገርላቸው ሲሆን፣ አንዱም ግዕዝን በተዋጣለት የእንግሊዝኛ ትርጉም አማካኝነት ለአንባቢያን፤ በተለይም በዘርፉ ጥናትና ምርምር ለሚያደርጉ ሰዎች፣ እንዲሁም ለአካዳሚው ማህበረሰብ ማቀበላቸውና የኢትዮጵያን ፍልስፍና ለአለም አደባባይ ማብቃታቻው (በClassical Ethiopian Philosophy መጽሐፉ መጽሐፈ ፊሳልግዎስ፣ አንጋረ ፈላስፋ፣ የስክንድስ ህይወትና አባባሎቹ፣ ሀተታ ዘርዓያዕቆብ እና ሀተታ ወልደ ሕይወት የፍልስፍና ስራዎችን ከግዕዝ ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ ተርጉመው አሳትመዋል፡፡) መሆኑ ስለ እሳቸው በተሰሩ ጥናትና ምርምር ስራዎች ውስጥ ተጠቅሶ ይገኛል። (”Cultural Heritage and Contemporary Change Series II. Africa, Volume 15”ን ተመልከት። እድሉ የሚገኝ ከሆነም የሰምነር ስራዎች ብርቅና ድንቅ የሆኑበትን፣ በአለማችን ድንቅ የተሰኘውንና አሜሪካዊውን Library of Congressን መጎብኘት፤ እንዲሁም The Source of African Philosophy: The Ethiopian Philosophy of Man, እና Oromo Wisdom Literature (ቅፆች ያሉት) መመልከት ይቻላል።)
ከትውልድ ወደ ትውልድ በቃል የሚተላለፉ ማኅበረሰባዊ ፍልስፍናዎች በስነቃል (ተረትና ምሳሌ፣ በምሳሌያዊ አነጋገሮች፣ በቃል ግጥም፣ በዘይቤዎች፣ በቅኔዎችና በወጎች ወዘተ)፤ መዝሙሮች፣ ኃይማኖታዊ ስነስርአቶች፣ ግለታሪኮች፣ የፀሎት መፃህፍት … አማካኝነት እንደሚገለጡ አሳምረው የሚያውቁት ሰውየው የኢትዮጵያን ፍልስፍናና ተያያዥ ጉዳዮችን አይን ከሰበከት አገላብጠው የፈተሹ በመሆናቸው ፍሬያማነታቸው የተመሰከረላቸው ናቸው።የመቀሌ ዩኒቨርሲቲው የፍልስፍና መምህሩር ብሩህ አለምነህ ስራዎችንም መመልከት ስለ ሰምነር ሌላው የመረጃ ምንጭ ነው።
ሰምነር ብዙ የሰሩ ብቻ ሳይሆን ብዙ የተባለላቸውም ምሁር ናቸው። በአበረከቱት የማይተካ አስተዋፅኦ ምክንያት ኢትዮጵያዊ ዜግነት ለማግኘት የቻሉት ፕሮፌሰር ሰምነር በጥንታዊ የኢትዮጵያ ፍልስፍና ዙሪያ የሚያጠነጥኑ በርካታ መጻሕፍትን (በቅፆች)፣ ጥናታዊ ጽሑፎችንና መጣጥፎች አሳትመዋል። በተጨማሪም የኦሮምኛ የሥነ-ቃልና የሥነ-ተረት ፍልስፍናዊ አንደምታን የሚያትቱ ሁለት ድርሳናትን ጽፈዋል። ”ዕድሜ ለፕሮፌሰር ሰምነር፣ ዛሬ በአፍሪካ ፍልስፍና (African philosophy) ዙሪያ የሚጻፉ መጻሕፍት የዘርዐ ያዕቆብን እና የወልደሕይወትን ሥም ሳይጠቅሱ አያልፉም።
ኢትዮጵያ ገና ያልተጠኑ የበርካታ ጥንታዊ ሥነጽሁፎች ባለቤት፤ ዘመናትን ያስቆጠሩ ቃላዊና የጽሁፍ ፍልስፍናዎች ምድር ወዘተ መሆኗን አጥብቀውና ደጋግመው የሚናገሩት ሰምነር የመጪው ዘመን ተመራማሪዎች ትኩረታቸውን በዚሁ ላይ እንዲያደርጉና እውነቱ ላይ እንዲደርሱም ሳይሳሱ ይመክራሉ።
ከአስራ ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች በተለየ መልኩ በርከት ያሉ የፍልስፍና ስራዎችን በመስራት በቀዳሚነት የምትጠቀሰው ኢትዮጵያ፤ በጥንታዊው የግእዝ ቋንቋ ከተጻፉት የፍልስፍና ስራዎቿ መካከል አብዛኞቹ እንኳን ሊጠኑ ገና ምናቸውም አልተነካም የሚሉት የፍልስፍና ምሁሩ እነዚህ ሁሉ በአግባቡ ከተጠኑ የኢትዮጵያ፤ እንደ አጠቃላይም የአፍሪካ ማንነትና ፍልስፍና አደባባይ ይወጣል የሚል ፅኑ እምነት አላቸው።
በዚሁ ጉዳይና የሰምነር ባለውለታነት ላይ ሀሳባቸውን ለንባብ ያበቁ ብሎገር (”ስሜነህ ጌታነህ@ DireTube” በሚል መለያ የሚጽፉ)፤
በኢትዮጵያ የሥነጽሁፍና ታሪክ ውስጥ በመጀመሪያው ክፍል እንደተጻፈ የሚነገርለት የመጀመሪያው የፍልስፍና የጽሁፍ ስራ መጽሐፈ ፊሳልግዎስ (physiologus) ይባላል።ይህ የፍልስፍና ስራ በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተጻፈ የሚነገርለትን የጥበብ ስራ ከግሪክ ወደ ግእዝ ቋንቋ በመተርጎም የተሰራ ሲሆን ትርጓሜውም ተራ ሳይሆን ከኢትዮጵያ የባህልና የቋንቋ አውድ ጋር በማዛመድ የተሰራ ነው።ፊሳልግዎስ በአምስተኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ወይም አጋማሽ አካባቢ ከፍተኛ የመጽሐፍ ክምችት በሚገኝበት ምናልባትም በግብጽ ሀገር በሚገኝ ገዳም ውስጥ በሚኖር ኢትዮጵያዊ ጸሐፊ እንደተጻፈ ይገመታል።ፈላስፋው ሰምነር የጥንታዊ ድርሳናት ተመራማሪው (philologist) ፍሪትዝ ሆሜል (Hommel) በ1877 ዓ.ም በለንደን፣ ፓሪስና ቬና ቤተመዛግብት ውስጥ የሚገኙ የግእዝ ብራና ፊሳልግዎስ መጻህፍትን ከጀርመንኛ ትርጓሜው ጋር በማገናዘብ ካዘጋጀው የተስተካከለ ቅጽ (critical edition) ላይ የተረጎመው ሲሆን ከካርሎ ኮንቲ ሮሲኒ የ1951 ጣልያንኛ ትርጉም ጋርም አመሳክሮታል።ፊሳልግዎስ ለመጽሐፉ ደራሲ የተሰጠ ስያሜ ሲሆን ይህም እንስሳትን፣ ዕጽዋትናና የማዕድናትን ምንነት የሚገልጽና በተምሳሌት (symbolism) የሚያስቀምጥ ነው፡፡
በማለት ያሰፈሩትን፤ እንዲሁም:-
በኢትዮጵያ የስነጽሁፍ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ግምት በሚሰጠውና ሁለተኛው ክፍለ ዘመን በመባል በሚታወቀው የአጼ ዘርዓያዕቆብ ዘመነ መንግስት (1434-68)፤ ”መጽሐፈ ፈላስፋና የስክንድስ ሕይወትና አባባሎቹ” የተባሉ ሁለት የፍልስፍና መጻህፍት ወደ ግእዝ ቋንቋ ተተርጉመዋል።ምናልባት ”እነዚህ ትርጉም ስራዎች እንዴት የኢትዮጵያ ፍልስፍና የሚል ስያሜ ሊሰጣቸው ቻለ?” የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል።ሰምነር እንደሚለው፤ ምንም እንኳ ስራዎቹ ትርጉም ቢሆኑም ኢትዮጵያውያን ዝም ብለው እንደ ወረደ አይተረጉሙም፤ የራሳቸው የሆነ የአተረጓጎም ስልት ስላላቸው ትርጉሞቻቸው ኢትዮጵያዊ አሻራን ይይዛሉ። “Ethiopians never translate literally: they adapt, modify, add, subtract. A translation therefore bears a typically Ethiopian stamp” (ኢትዮጵያውያን በትርጉም ሂደት ላይ ከራሳቸው ባህልና አውድ ጋር ለማዋሃድ ሆን ብለው የማወራረስ፣ የመቀነስና የማሻሻል ባህል ስላላቸውና ፍጹም ኢትዮጵያዊ አሻራ አንዲኖረው በማድረግ ስለሚተረጉሙ ነው፡፡)
በማለት ስለ ሰምነር የሰጡትን ውለታ ከፋይ ማብራሪያ እዚህ መጥቀሱ የባለውለታውን የእውነትን ፍለጋ ሩጫ ያሳያልና አንባቢያን ሙሉውን ጽሑፍ ፈልገው ቢመለከቱት ያተርፋሉ ባይ ነን።
በአጠቃላይ በጥንታዊት ኢትዮጵያ (በአስራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን (1599-1692)) የትምህርት ሥርዓት፤ በንባብ ቤት፣ በዜማ ቤትና በቅኔ/ሰዋስው ቤት ያለፈ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ሲሆን እርሱ በነበረበት ዘመን የነበሩ ሃይማኖታዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ሥነምግባራዊ አስተሳሰቦችን በአመክኗዊ ሐተታ (rational inquiry) በመታገዝ ይመረምርና ይተች የነበረው ፈላስፋ ዘርዓያዕቆብ (”ዘርዓ ያዕቆብ የፍልስፍና ትምህርት ቤት” የሚል ተቋም ከፍተው ፍላጎት ያላቸውን እያስተማሩ ያሉትን በዚህ አጋጣሚ ማመስገን ያስፈልጋል)፤ እንዲሁም ደቀመዝሙሩ ወልደሕይወትና ስራዎቻቸው (ሀተታዎቻቸው) በፕሮፌሰር ክላውድ ሰምነር አማካኝነት ተፈትሸውና ያሉበት የፍልስፍና ደረጃ ተመርምሮ ይዘታቸው ብቻ ሳይሆን ፋይዳና ቀዳሚነታቸው ሁሉ ተረጋግጧል። ጥናቶች በተደጋጋሚ እንደሚሉት ሁሉ ”ዛሬ የዘርዓያዕቆብ ፍልስፍና በዓለም ሊታወቅ የቻለው ካናዳዊ ዜግነት ባለው ፕሮፌሰር ክላውድ ሰምነር አማካኝነት ነው፡፡” ይህም ሰምነርን በዘርፉ የምሁራን ሁሉ ቁንጮ (በተለይ ያልተነካውን በመንካት) ከማድረጉም በላይ፤ መታወቂያቸውም ሊሆን በቅቷል (ስለሳቸው ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ ሁሉ Best known by Ethiopian philosophy እንደሚሉት)።እኛም ለሰሩት ስራ፣ ላበረከቱት አስተዋፅኦና ላፈሯቸው ፍሬዎች ማስታወሻ ይሆን ዘንድ ይህንን መዘክር ስናበረክት ደስታ እየተሰማን ሲሆን፤ ወደ ፊትም ሆነ አሁን ከስራዎቻቸው ጋር ትውውቅ ለሚፈጥሩ ሁሉ መልካሙን እንመኛለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27 ቀን 2014 ዓ.ም