አንድ የ2ኛ እና 13 የመጀመሪያ ዲግሪ ምሩቃን ይገኙበታል
አዲስ አበባ፦ በከተማዋ በሚገኙ ስምንት ካምፖች የማገገሚያ እንክብካቤ እየተደረገላቸው ከሚገኙት 3 ሺ 147 የጎዳና ተዳዳሪዎች መካከል 414ቱ በተለያዩ የትምህርት መስኮች የተመረቁ የአዲስ አበባ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ።
የአዲስ አበባ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማህበራዊ ችግር ተጎጂዎች መልሶ ማቋቋም ዳይሬክተር አቶ እንዳሻው አበራ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በመዲናዋ 58 ሺ 820 የጎዳና ተዳዳሪዎች መኖራቸው በቅርቡ የተደረገ ጥናት ተረጋግጧል። ከእነዚህ ውስጥ 3ሺ 147ቱ በተመረጡ ስምንት ማዕከላት ውስጥ እንዲገቡ ተደርገዋል። ከእነዚህ ወስጥ 414ቱ በተለያዩ የትምህርት መስኮች የተመረቁ ሲሆኑ ሁለቱ ኤርትራውያን ናቸው።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ በማዕከል ከገቡት የጎዳና ተዳዳሪዎች መካከል ሠርተው መለወጥ የሚችሉ ዜጎች መገኘታቸው ጉዳዩን አስገራሚ አድርጎታል። በተለይም አንድ የሁለተኛ ዲግሪ ምሩቅ እና 13 የመጀመሪያ ዲግሪ ምሩቃን ተገኝተዋል። 400 የሚደርሱት ደግሞ በዲፕሎማ እና በሰርተፍኬት በተለያዩ ሙያዎች ከቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተቋማት የተመረቁ ናቸው። አንድ
መቶ የሚሆኑት የመንጃ ፈቃድ ያላቸው ናቸው። በመሆኑም በመንግሥት የሥራ ዕድል ውስጥ መግባት ለሚችሉት ዕድሉ እንዲመቻችላቸው ሥራ ተጀምሯል። የተቀሩት ደግሞ ሙያቸውን ሊያጎለብቱ በሚችሉበት ስልጠና ተሰጥቷቸው እንዲቋቋሙ ይደረጋል።
ከጥር 25 ቀን 2011 ዓ.ም በተጀመረው በፈቃደኝነት የጎዳና ተዳዳሪዎችን ወደማዕከላት የማስገባት ሥራ ሲከናወን ችግሮች እንደነበሩ አስታውሰው፤ አስተዳደሩ ገንዘብ እና መሬት ሊሰጥ ነው በሚል ቤታቸውን ቆልፈው ወደማዕከላት የገቡ ሰዎች ብዙ ነበሩ። በመሆኑም የመለየት ሥራ ተከናውኖ ከ350 በላይ ሰዎች ወደመጡበት ተመልስዋል። በተጨማሪም 993ቱ ደግሞ ወደ ተለያዩ ክልሎች የሚመለሱ ናቸው።
የሁለቱ ኤርትራውያን ፍላጎት ወደ ቤተሰባቸው መመለስ በመሆኑ በፍላጎታቸው መሰረት ከኤምባሲው ጋር ተነጋግሮ ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ነው። የተቀሩት እና ሥራ መሥራት የማይችሉት አረጋውያን እና ሕፃናትን በዘላቂነት ለመንከባከብ እንዲቻል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅበት አስታውሰዋል።
እንደ አቶ እንዳሻው ማብራሪያ፤ በአዲስ አበባ ከተመረጡት ስምንቱ ማዕከላት መካከል ኮተቤ አካባቢ፣ ቦሌ ክፍለከተማ፣ አቃቂ፣ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አካባቢ፣ ሚኪሊላንድ አካባቢ፣ ጃንሜዳ የካቲት 66 ትምህርት ቤት አካባቢ እና ልደታ ክፍለከተማ ናቸው። ሰባቱ ማዕከላት የወንዶች ሲሆኑ አንዱ ሚኪሊላንድ አካባቢ የሚገኘው ደግሞ የሴቶች ካምፕ ነው።
ኮተቤ የሚገኘው ማዕከል አስተባባሪ አቶ አስፋው አንጄሎ በበኩላቸው፤ በአዲስ አበባ ከሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪዎች ማቆያ ካምፖች ትልቁ መሆኑን አስታውሰው፤ በማዕከሉ 837 የጎዳና ተዳዳሪዎች ይገኛሉ። በአሁኑ ወቅት የህክምና አገልግሎት እንዲሁም ምግብ እና አልባሳት እየቀረበላቸው ነው። ማንኛውም ሰው በማዕከሉ ሱስ አሲያዥ ነገሮችን እንዳይጠቀም የሚከለከል ህግ ከመኖሩ ባሻገር በባለሙያ የተደገፈ የሱስ ማገገሚያ ህክምና ይሰጣቸዋል።
አልፍ አልፎ ከማዕከሉ ሾልከው የሚወጡ የጎዳና ተዳዳሪዎች ቢኖሩም አብዛኛዎቹ ተመልሰው እንዲገቡ እየተደረገ ይገኛል። ችግሩን ለመከላከል በማዕከሉ ጥበቃ ሥራ ላይ የሚገኙ 40 የፖሊስ አባላት፣ 14 በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እና 26 ሠራተኞች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
እንደ አዲስ አበባ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ መረጃ፤ እስከአሁን ወደማዕከል የገቡትን ጨምሮ በ2011 ዓ.ም 10ሺ 9 የጎዳና ተዳዳሪዎችን ወደማዕከላት ለማስገባት እቅድ ተይዟል። 100 ሚሊዮን ብርም በአስተዳደሩ ተመድቧል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21/2011
በጌትነት ተስፋማርያም