አዲስ አበባ ፦ የደን ውጤት ከህትመት ስራዎች ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ስላለው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ገለጸ።
የድርጅቱ አመራር እና ሰራተኞች ለ19ኛ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል ድሬ ግድብ አካባቢ ትናንት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አካሂደዋል።
በመርሃ ግብሩ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ እንደገለፁት፤ ለህትመት አገልግሎት የሚውለው ወረቀት የደን ውጤት እንደመሆኑ የድርጅቱ ሰራተኞችና አመራሩ በኦሮሚያ ክልል ድሬ ግድብ አካባቢ ቦታ በመረከብ ባለፉት አሥራ ስምንት ዓመታት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ሲያካሂዱ ቆይቷል።
‹‹የደን ልማት ከኢንዱስትሪው ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት አለው፣ ትግበራውም ውጤት አምጥቷል፣ የደን ውጤት ከድርጅት ስራ ጋር አብሮ ስለሚሄድ ማተሚያ ቤቱ ትኩረቱን በአገር በቀል ችግኞች ላይ በማተኮር ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል›› ብለዋል አቶ ሽታሁን።
በአካባቢው ዛፎች ባይተከሉ የድሬ የውሃ ግድብ በደለል ሊሞላ ይችል እንደነበር ተናግረዋል። የአካባቢውን ህብረተሰብ በማሳተፍ የተሰራው ስራ ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።ድርጅቱ ወደፊት የአረንጓዴ አሻራ ተግባሩን በማጠናከር የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም አስረድተዋል።
ሌሎች ድርጅቶችም ከብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ልምድ በመውሰድ የራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱ አሳስበዋል።
የደን ውጤት ከህትመት ጋር የጎላ ቁርኝት ስላለው ድርጅቱ በትኩረት ይሰራል ብለዋል አቶ ሽታሁን፤ ህብረተሰቡ ለተግባሩ ትኩረት በመስጠት ለውጥ ማምጣት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።
በማተሚያ ቤቱ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ የተሰራው ስራ ውጤት ያመጣ በመሆኑ ሌሎች ተቋማትም ከድርጅቱ ተሞክሮ ቢወስዱ በዘርፉ የተሻለ ውጤት ያስመዘግባሉ ብለዋል።
ፀጋዬ ጥላሁን
አዲስ ዘመን ሀምሌ 25 ቀን 2014 ዓም