በኢትዮጵያ የስራ ፈላጊው ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።ከዚህ በእጅጉ እየተበራከተ ከመጣው ስራ አጥ ማህበረሰብ ውስጥ ደግሞ ወጣቱ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል።በሀገሪቱ ካሉ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የሚመረቁ ተማሪዎች ቁጥር እያደገ መምጣት ደግሞ የስራ አጥ ቁጥሩን ከዚህም በላይ ከፍ እንዲል አድርጎታል፡፡
በስራ እድል ፈጠራ ዙሪያ በመንግስትም ሆነ በግሉ ዘርፍ እጅግ በርካታ ስራዎች ቢሰሩበትም አሁንም ድረስ ችግሩን ማቃለል አልተቻለም።ከዚህ አንፃር በአዳዲስ የስራ እድል ፈጠራ መስኮች ላይ ማማተር አስፈላጊ እየሆነ መጥቷል።ነባር የስራ እድል ፈጠራ መስኮችንም ማዘመንና ማስፋት የግድ ብሏል።ወጣቶችም የራሳቸውን ስራ እንዲፈጥሩና እንዲሰሩ የሚያስገድዱ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በቅርቡ በጅማ ከተማ ‹‹ስለ ኢትዮጵያ›› በሚል መሪ ቃል ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ ፅሁፍ ያቀረቡት ወይዘሮ መቅደስ ገብረወልድ እንደሚናገሩት፤ ከሁሉ በፊት ሁሌም የሚያሳስበው ጉዳይ ኢትዮጵያ በእጇ ላይ ያለውን የሰው ሀብት እንዴት ትጠቀም? የሚለው ነው፡፡ሰውና ክህሎት ሲባል የሚያጠነጥነው ሰው ላይ ነው።
በአለም አቀፍ ደረጃ በመሻገርና በለውጥ ሃሳቦች ዙሪያ 70 ከመቶ ያህሉ ያሰቡትን ማሳካት አይችሉም።ውድቅ የሚሆኑበት ምክንያት ደግሞ ሰዎች ለውጡን የተረዱበት አተያይ የተለየ ሲሆን ነው።በተለይ ሰዎች ለውጡን በደንብ ሳያወቁት ሲቀሩ አቅማቸውን መስጠት አይችሉም።እውቀት ብዙ አይኖራቸውም፤ ቅንነትም ያጣሉ።
እንደ ኢትዮጵያ ሰፋ ያሉ የለውጥ ሃሳቦችን ማውጣት ከተፈለገ ህዝቡ ምን ያህል ተረድቷል የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል።ከዚህ እንፃር ስለለውጥ ሲታሰብ መፍጠር መቻል /innovation/ የሚለውን ማየት ይገባል።ይህም እንዴት ለችግሮች መፍትሄ ላምጣ የሚለውን ሃሳብ ከማምጣት ጋር የተያያዘ ነው፡፡
እንደ ወይዘሮ መቅደስ ገለፃ ለውጥና መፍጠር አንድን ነገር በጥልቀት ከመረዳት የሚመጣ ሲሆን የፈጠራና የለውጥ ሀሳቦች ከእለት ጉርስ እያለፉ አይደለም።ወደ ስራ እድል ፈጠራም ሲኬድ ቁርስና ምሳ መብላት የሚችል ትውልድ እየተባለ ጠቧል።ከዚህ አኳያ ይህን የተረዱ ሰዎች በዓለም ላይ የተለያዩ የኢንዱስትሪ ለውጦችን ለማጣት ተገደዋል።በተለይም በአግባቡ የማያስብ ትውልድ እርሱንም ሀገሩንም ማሻገር አይችልም።
በደንብ ያልሰራ ትውልድ ወደ አራተኛው የስራ አብዮት መሻገር አይችልም።ይህ አብዮት አዲስ ነገር ይዞ አልመጣም፤ ይልቁንም ያለሰው እንዴት እንኑር ነው የሚለው።የአራተኛው የስራ አብዮት አለም የሚፈልገው ደግሞ በራሳቸው መረጃ ፈልገው፣ በራሳቸው ድርጊቶችን አምጥተው፣ ራሳቸው ተቆጣጠርው ሌላ ሰው ሳይጨመርበት ስራውን የሚያስፈፅሙ ስማርት ማሽኖችን ነው።
ይህም የሶስተኛውን የስራ አብዮት ያልተረዳ ወደ አራተኛው አብዮት መግባት አይችልም ማለት ነው።ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ታዳጊ ሀገራት ወዴት ይሄዳሉ የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው።አራተኛውን የስራ አብዮት ለመቀበልም ከኔትዎርክ፣ ከእወቀትና ከፍላጎት ችግሮች ጀምሮ በርካታ ውጣ ውረዶች አሉ።ከዚህ አንፃር የሰው ሃይሉ ካልነቃ በስተቀር ለውጥ ለማምጣት ያስቸግራል።
በመሆኑም የሰው ሃይል አቅም ላይ መስራት ያስፈልጋል።ለዚህ ደግሞ ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል።የሰው ሃይል አቅም ለማሳደግ እውቀቱ ምን አይነት እንደሆነ፣ ልምዱስ ምን እንደሆነና ባህርዩ ምን አይነት እንደሆነ መረዳት ይገባል።አይቶ እሴት ለመጨመር የሚሄድ ትውልድን እንዴት መፍጠር እንደሚገባም ማጤን ግድ ይላል።እሴት ለመጨመር ደግሞ ግንዛቤ ያስፈልጋል።ምን አይነት ህዝብ እንደሆንንና የት ደረጃ ላይ እንዳለን ካላወቅን መሄጃው ግራ ይገባል።ስለዚህ ነበራዊ ሁኔታዎችን ተረድቶና አውቆ ሊያሻግር የሚችል መሪና መሻገር የሚፈልግ ህዝብ ያስፈልጋል።
ስለዚህ ዋናው ጥያቄ የሰው ሀብት ልማትን እንዴት እንየው ነው? የሚለው ነው። የሀገር ዋነኛ የሀብት ክምችቷ የሰው ሀብት መሆኑን ልብ ማለት ይገባል።ከዛም ልምድ፣ ብቃት፣ክህሎት እያለ ይቀጥላል።በኢትዮጵያ ደግሞ በሁሉም የእድሜ ክልል ውስጥ መስራትና ማምረት የሚችል የሰው ሃብት አለ።በዋናነት ደግሞ ወጣቱ ትውልድ ፍጥነትን ሊጨምርና ፈጣን ለውጥ ሊያመጣ በሚችል መልኩ በሰው ሃይል ሀብት ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል።
ወይዘሮ መቅደስ እንደሚያስረዱት፤ እንደ ኢትዮጵያ ብዙ ከጎደሉ ሀብቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የሰው ሃይል ሃብት ነው።ይህን ሃብት እንዴት እንስራው የሚለውም ተረስቷል።በርካታ መስሪያ ቤቶች የሚወድቁበት፣ ሰራተኞችም ከነዚህ መስሪያ ቤቶች ጋር መቀጠል የማይፈልጉበት ምክንያት የስራ ባህሉና ሰው ላይ የበለፀገ ነገር ባለመኖሩ ነው።ስለዚህ በሰው ሀብት ላይ መስራትና ወደዛ መሻገር ያስፈልጋል።
ሽግግሩ እንዳይወድቅ የሰው አቅም ማደግ አለበት።ሰዎች የሚበቁበትና የሚሰለጥኑበት መንገድም የማስታወስ ችሎታቸውን ከሚሞክር አስተምሮ በመውጣት ኢንተለጀንስ ወደሚጨምር አስተምሮት መግባት ይኖርበታል። ኢንተለጀንስ ደግሞ የሚጨመረው ማንነት ላይ ነው።
ከዚህ ባለፈ በርካታ የስራ ፈጠራ ሃሳቦች፣ ለዚህ አጋዥ የሆኑ ፖሊሲዎችና መሰረተ ልማቶች አሉ።የዛኑ ያህል በርካታ ስራ አጥ ወጣት አለ።ስለሆነም ከማወቅ መጀመር ያስፈልጋል።ለዚህም የመንግስት መዋቅሮች መስተካከል አለባቸው።የቴክኒክና ሙያ ዩኒቨርሲቲዎችም የት ጋር እንዳሉ፣ ምን መስራት እንዳለባቸውና ወደ የሰው ሃይል ልማት መሸጋገር እንዳለባቸው ሊያውቁ ይገባል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዶክተር ሙፈርያት ካሚል እንደሚሉት፤ ኢኮኖሚው ሀገራዊ፣ቀጣናዊ፣አህጉራዊና አለምአቀፋዊ እድሎች አሉት።ይህም በተለመደው መስክ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም ተሞክረው በማያውቁና በአዳዲስ መስኮች ያሉ እድሎችን ያካትታል።የሚታወቁ መስኮችን ደግሞ ለማዘመን የሚያስችሉ እድሎች አሉ። ይህም የግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝምና የማእድን ዘርፎችን ያጠቃልላል።
ከዚህ በፊት ግብርናን በዘመነ መንገድ ለመለወጥ የሚያስችል በሆነና ለወጣቶች ሳቢ በሆነ መንገድ፣ የአባቶችንና እናቶችን ድካም በሚቀንስ መልኩ፣ የልፋታቸውን ውጤት ማግኘት በሚያስችል ልክ ለመሄድ የሚያስችሉ እድሎች አልነበሩም።ሆኖም ለውጡ ህግ ከማውጣትና ከሚመደብ በጀት ጀምሮ እውነተኛ ድጋፍ ለግብርናው ዘርፍ ለማድረግ የሚያስችል ርምጃ ተወስዶበታል። ተጨባጭ የሆኑ ችግር ፈቺ ስራዎች መስራትም ተጀምረዋል።
የግብርናው አቅም ገና አልተነካም።ለስራ እድል 44 ከመቶ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ይጠበቃል። ነገር ግን እስካሁን ያለው አፈፃፀም 26 ከመቶ ገደማ ነው።ከዚህ አንፃር የግብርናው ዘርፍ ገና ያልተነካና ረጅም ጉዙ ይዞ መሄድ የሚያስችል ትልቅ አቅም አለው።
በተመሳሳይ የኢንዱስትሪው ዘርፍም ከ50 በመቶ በታች በሆነ አቅም ነው እያመረተ ያለው። ነገር ግን በሙሉ አቅሙ ቢያመርት ምን ያህል የስራ እድል እንደሚፈጥርና ምን ያህል በክህሎት የሰለጠነ የሰው ሃይል እንደሚፈልግ ይታወቃል። ይህ ሆኖ ሳለ ታዲያ ግብርናን ጨምሮ በሌሎች መስኮች ውጤት ማስመዝገብ ተጀምሯል።
እንደ ሚንስትሯ ማብራሪያ እነዚህን እድሎች አሟጦ ለመጠቀም የአሰራር፣ የአደረጃጀት፣ ስርአተ ስልጠናዎችን የመቀየር ሰፋፊ ስራዎች ተጀምረዋል።በአህጉር ደረጃም ገና ያልተነካ ሰፊ ገበያ በመኖሩና በተለይ በኢትዮጵያ 70 ከመቶ ያህሉ ትኩስ የወጣቶች ሃይል የሚገኝበት በመሆኑ ይህ ትልቅ የመወዳደሪያ አቅም ሆኖ ያገለግላል።
ይህን የመወዳደሪያ አቅም ብቃት ባለው ስርዓተ ስልጠና፣ የአስተሳሰብ ለውጥና፣ ለስራና ክህሎት ያለውን ክብር ለማጎልበትና እነዚህን ክህሎቶችን ለማበልፀግ በአደረጃጀትም በአሰራርም፤ የተቋማትን አቅም በመገንባትም የተጀመሩ ሰፋፊ የለውጥ ስራዎች አሉ።ይሁንና ገና ረጅም ጉዞ ይቀራል።
በሌላ በኩል ደግሞ ህጎች የሚታወቁት በመቆለፍ እንጂ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር አይደለም።ይህንኑ ለመፍጠር አዳዲስ ስራ ፈጣሪዎችን ወደገበያው ለማስገባት ህግ የማውጣት ስራ ረጅም ርቀት ተሂዷል፤ የማፅደቅ ደረጃ ላይ ደርሷል።
እንደ ሚኒስትሯ ማብራሪያ ሁለት ነገሮች ወደፊት ለመስፈንጠር ገፊ ምክንያት ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ።እነዚህም በጉጉት የሚጠበቀው የወደፊት መፃኢ ሁኔታና አሁን ያለው አስፈሪና አስቸጋሪ ሁኔታ ናቸው።ትልቁን ስእል ለማሳካት የሚደረገው ጥረት አሁን ላይ አስቸጋሪ የሆኑ ነገሮችን ለመመለስም ትልቅ እድል የሚከፍት ይሆናል።
ክህሎት ላይ በደንብ ከተሰራ ጥራት ያለው የስራ እድል ለመፍጠር ጉልበት ይሆናል።በባህሪም በስነምግባር፣ በስራ ባህል የታጀበ እጁን ፣ ሃሳቡንና አእምሮውን በወጉ ማገናኘት የቻለ ሰው መፍጠር ሲቻል የተጀመረውን ኢኮኖሚያዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ማሳካት ይቻላል።
ይህን በማሳካት ሂደት ደግሞ የእለት ጉርስ ጉዳይ መልስ ያገኛል።ስለዚህ ስለስራ ሲወራ በዕለት ጉርስ መቆም ሳይሆን ከዚህም በላይ መሻገርን ስለሚጠይቅ አጭር መንገድ ለመሄድና ረዘም ያለ ጉዞ ለመጓዝ የሚነሳበት ሰአት፣ የሚኬድበት ፍጥነት፣ ጥቅም ላይ የሚውለው የመጓጓዣ አይነት፣ የሚዘጋጀውና የሚያዘው ስንቅ ይለያያል።
ትልቁን ሀገራዊ ህልም መሰረት በማድረግ የሚሰራ ከሆነ በነዚህ ዘርፎች ላይ የሚፈለገውን ክህሎት፣ የሀገር ውስጥ፣ ቀጣናዊና አለማአቀፋዊ ገበያው ምን እንደሚፈልግ ደንብ ለመተንበይ፤ እግረመንገዱን ደግሞ የዳቦ መሰረታዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ ትልቅ ትርጉም አለው።የሚወጣው ሃይልና የሚከተልበት መንገድ ብሎም የሚወሰደው አማራጭ ላይ ልዩነት ይኖራል።
መግቢያው ቴክኒክና ሙያ ሆኖ በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ የሚሰጡ ጥራት ያላቸው ስልጠናዎች በየትኛውም መስክ ወደዚህ ለመድረስ ትልቅ ትርጉም አላቸው።
የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የእድል በር ይሁኑ ስለተባለ በአስተሳሰብም በስነ ምግባርም የተሻሉ እንዲሆኑ ይፈለጋል።ባላቸው ትላልቅ ወርክሾፖች፣ ማሽነሪዎችና የሰለጠነ የሰው ሃይላቸው ደግሞ ሙያተኞች ተገቢውን ክህሎት እንዲጨብጡና ወደ ስራው አለም እንዲሰማሩ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ከሰላም ጋር በተያያዘም በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ለሰላም እጦት መንስኤ የሆኑ መዋቅራዊ ጉዳዮች ምንድን ናቸው ተብሎ መልስ ካላገኘ ያለውን ሃብት በአግባቡ መጠቀም አይቻልም።ከዚህ አንፃር የስራ ባህል ላይ መስራት ከተቻለ ግጭቶችን የመቀነስ እድል ይኖራል።ስለዚህ ሰላም ውጤትም ሂደትም ነው።ሰላም እስኪመጣ ተብሎ ቁጭ ማለትም አያስፈልግም።
ስራና የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ መስራት ከተቻለ ተመልሶ የሰላም ሁኔታ ላይ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል።ስለሆነም ኢትዮጵያን ለመበጥበጥ የሚነሳው ሃይል ተቀጣጣይ ቤንዚን አያገኝም ማለት ነው።ስለዚህ የሰላም ጉዳይ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የፍትሃዊነት፣ የስራ አጥነትና የሌሎች መዋቅራዊና ዲሞክራሲያዊ እጦት ጉዳይ በመሆኑ በነዚህ ላይ ጠንካራ ስራዎችን መስራት ይጠይቃል።አሻፈረኝ ለሚለው አካል ደግሞ የህግ ማስከበሩ ጉዳይ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
የለውጡ ጉዞ አንዳንዴ የተመቸ ሌላ ጊዜ ደግሞ ገጭ ገጭ ያለ በመሆኑ ለዚህ የተመቸ ምክክር ያስፈልጋል።ከዛ በተረፈ የሰው አስተሳሰብና ብቃት ላይ መስራት ከተቻለ በርካታ ባልተነኩ የስራ ዘርፎች ላይ ሰፊ የስራ እድል መፍጠር ይቻላል።በአለም አቀፍ ገበያ ለመግባት ግን ምርቶችን ተወዳዳሪ ማድረግ ግን ከሁሉም ይጠበቃል።
በወጣቶች ላይ የተጀመሩ ስራዎች አሉ።ነገር ግን ረጅም ርቀት መሄድ ይጠይቃል።በተለይ ከሱስ የማላቀቅ ስራ ረጅም ርቀት መሄድ አለበት።ለዚህም የሃይማኖት ተቋማት፣ የእምነት አባቶች፣ አባገዳዎች እገዛ ያስፈልጋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2022