የፌስቡክ ድርጅት የነጮችን ብሔርተኝነትና መለያየትን የሚያሞግሱና የሚደግፉ ፅሑፎችን ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ከፌስቡክና ከኢንስታግራም ገፆች እንደሚያግድ አሳወቀ።
ትልቁ የማህበራዊ ሚዲያ ፌስቡክ በኒውዝላንድ የተፈጸመውን ድርጊት በማውገዝ የሽብርተኝነትና የጽንፈኝነት ይዘት ያላቸውን ይዘቶች ከድህረገፁ ላይ ለመለየትና ለማስወገድ እንደሚሠራ ቃል የገባ ሲሆን፤ የፈረንሳይ ሙስሊሞችን የሚወክል አንድ ቡድን በፌስቡክና በዩትዩብ ምስሉን በመልቀቁ በገፃቸው ያስተላለፉ ድርጅቶች መከሰሳቸውን ገልጸዋል።
ፌስቡክ ከዚህ በፊት የነጮችን ብሔርተኝነት የሚያሳዩ ይዘቶችን እንደ ዘረኝነት ስለማይቆጥራቸው በገፁ ላይ እንዲገኙ ፈቅዶ ነበር። የአሜሪካ አክራሪ የነጮች ቡድንና በስፔን ያለው የባስክ ተገንጣይ ቡድኖች አስፈላጊ የሰዎች ማንነት ክፍል እንደሆኑት ሁሉ የነጭ ብሔርተኝነትም ተቀባይነት ያለው እንደሆነ ተደርጎ ይወሰድ ነበር።
ነገር ግን ድርጅቱ ረቡዕ ዕለት ገፁ ላይ ባሰፈረው ፅሑፍ እንዳስነበበው፤ ፌስቡክ ለሦስት ወራት ከህብረተሰብ አካላትና ምሁራን ጋር ምክክር ካደረገ በኋላ፤ የነጮችን ብሔርተኝነት ከነጮች የበላይነትና ከሌሎች የተደራጁ የጥላቻ ቡድኖች መለየት አይቻልም ብሏል። ከአሁን በኋላ ይህን ዓይነት አመለካከት የሚያራምዱ ደንበኞችንም በማህበራዊ ገጹ ላይ እንደማያስተናግድ ድርጅቱ አስታውቋል።
ድርጅቱ በኒውዝላንድ ለ50 ሰዎች ህይወት ማለፍ ምክንያት የሆነው በኒውዚላንድ በሁለት መስኪዶች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች በቀጥታ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ከተላለፈ በኋላ የማህበራዊ ሚዲያዎች ጫና እንደበዛባቸው ገልጹዋል።
ድርጅቱ እንደገለጸው፤ ለ50 ሰዎች ህልፈት ምክንያት የሆነው የኒውዚላንዱ ጥቃት ምስል ከማህበራዊ መድረኩ ላይ ከመውረዱ በፊት ከአራት ሺ ጊዜ በላይ እንደታየ ፌስቡክ ያስታወቀ ሲሆን፤ ድርጅቱ በ24 ሰዓት ውስጥ የምስሉ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቅጂዎችን ከማሰራጨት ከልክሏል። 300 ሺ የሚሆኑትን ደግሞ ከድረ ገፁ ላይ እንዲጠፋ መድረጉን ገልጹዋል።
የኒውዚላንዷ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደን ስለማህበራዊ ሚዲያዎች እንደገለጹት፤ መልዕክቱን የለቀቀው ሰው ብቻ ሳይሆን አሳታሚዎቹም ብሄርተኝነትንና መለያየትን የሚያሞግሱና የሚደግፉ ይዘቶች ሲለቁ ኃላፊነት ሊወስዱ ይገባል፡፡ በህግም ሊጠየቁ ይገባል ብለዋል።
በኒውዚላንድ የተደረገውን ጥቃት ተከትሎ ብዙ መሪዎች የማህበራዊ ሚዲያዎች በገፆቻቸው ላይ ለሚለጠፏቸው ፅንፈኛ ይዘቶች ኃላፊነቱን መውሰድ እንዳለባቸውና በህግ እንደሚጠየቁ አስጠንቅቀዋል።
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስቴር ዳክተር አብይ አህመድ በሀገሪቱ ሰዎች የማህበራው ሚዲያን በመጠቀም የውሸት መረጃ እና የጥላቻ መልዕክት በማስተላለፍ ወደ እርስ በእርስ ብጥብጥ የሚከት በመሆኑ፤ በአገሪቱ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሊስተካከል እንደሚገባ በቅርቡ ማሳሰባቸው ይታወሳል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2011
ሶሎሞን በየነ