የሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች የሚመሩትን ፕሮግራም ‹‹እየተዝናናችሁ የምትማሩበት›› ሲሉ እንሰማለን። እንደዚህ ብለው ግን የሚነግሩን ስለአንዲት የውጭ አገር ዝነኛ አርቲስት የእርግዝና ድግስ (ቤቢ ሻወር) ሊሆን ይችላል። በበኩሌ አያዝናናኝም አያስተምረኝም!
የዛሬ ትዝብቴ ግን ወቀሳ ሳይሆን አድናቆት ነው። በነገራችን ላይ ‹‹ትዝብት›› ሲባል ብዙዎቻችን ትዝ የሚለን ወቀሳ ብቻ ነው። አድናቆትም ትዝብት ነው። ለምሳሌ፤ እንደ ምርጫ ባሉ ትልልቅ ጉዳዮች ላይ ታዛቢ ተብለው የሚቀመጡ አሉ። ስህተትን ብቻ ለመታዘብ ሳይሆን ያስተዋሉትን ጥሩ ነገርም ለመመስከር ነው።
በትዝብት ስም ከሚጻፉ ጽሑፎች (የእኛን ጨምሮ) የምናነበው መስተካከል አለባቸው የምንላቸውን ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ነው፤ ወቀሳዎች ይበዛሉ። ትክክል ነው! መስተካከል ያለባቸው ነገሮች እንዲስተካከሉ መታዘብና መውቀስ ያስፈልጋል። በዚያው ልክ ግን ጥሩ የሆኑ ነገሮችንም ማድነቅ ሌሎች ጥሩዎችን መፍጠር ነው።
ወቅቱ የክረምት ወቅት ነው። ለተማሪዎች የእረፍት ወቅት ስለሆነ በየቤታቸው ናቸው። የእረፍት ወቅት ነው ማለት ግን ከትምህርት ይርቃሉ ማለት አይደለም። መስከረም ላይ ወደሚቀጥለው ክፍል ስለሚገቡ የሚቀጥለውን ክፍል የትምህርት አይነቶች ከወዲሁ ይጀምራሉ። ያለፉትን ክፍልም ለሚቀጥለው ስለሚያግዝ ይከልሳሉ።
እነዚህን ሁሉ ነገሮች ያስታወሰኝ ባለፈው እሁድ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የመዝናኛ ጣቢያ (ኢቲቪ መዝናኛ) ላይ ያየሁት ነገር ነው። ተማሪዎችን የሚያሳትፍ ትምህርታዊ ጥያቄዎችና ማብራሪያዎች ናቸው። ሙሉ የፕሮግራሙን ይዘት ለመግለጽ ደጋግሞ ማየት ቢጠይቅም ባየሁበት ዕለት፤ ጥያቄዎችን የሚያብራራ መምህር ከስቱዲዮ ከጋዜጠኛዋ ጋር ይቀመጣል። አየር ላይ ጥያቄ ይጠየቃል፤ ተማሪዎች በስልክ እየገቡ ይመልሳሉ።
ጥያቄዎቹ እንደሌሎቹ ጥያቄና መልስ ውድድሮች የጠቅላላ ዕውቀት ሳይሆኑ መደበኛ የትምህርት ጥያቄዎች ናቸው። ተማሪዎች በስልክ ይመልሳሉ፤ ከመለሱ በኋላ ስቱዲዮ ያለው መምህር ያብራራል። ልክ መማሪያ ክፍል ውስጥ የሚጠየቁት አይነት ማለት ነው። የቴሌቪዥኑ ስክሪን ላይ Which one of the Following…. የሚለውን ስመለከት ወደ ልጅነቴ ነው የተመለስኩት።
መጀመሪያ እንዳየሁት፤ እንዴት ይሄን ትምህርት የመዝናኛ ጣቢያ ላይ ያደርጉታል ብየ ነበር። እያደር ሳስበው ግን ተማሪዎች የእረፍት ጊዜ ላይ ስለሆኑ እየተዝናኑ የሚማሩት ነው። በዚያ ላይ ፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በሚተነተኑበት የዜና ጣቢያ ቢሆን ልጆች አያዩትም። እየተዝናኑ መማር ማለት ይህ ነው።
መምህራን አንዳንድ ጊዜ ‹‹እየተጨናነቃችሁ አታጥኑ›› ይላሉ። አሁን ወቅቱ ክረምት ነው፤ ተማሪዎች በፈተና የሚጨናነቁበት ጊዜ አይደለም። እስከ አሁን የተማሯቸውንና በሚቀጥለው ክፍል የሚማሯቸውን በዚህ ሁኔታ ማጥናታቸው ወደ ውስጣቸው እንዲሰርፅ ያደርጋል። በዚያ ላይ ደግሞ ጥያቄ ለመለሱ ተማሪዎች የመጽሐፍ ስጦታ ይሰጣቸዋል። ይህም ሌሎች ተማሪዎች እንዲነቃቁና እንዲከታተሉ ያደርጋል። እያዝናኑ ማስተማር እንዲህ ነው!
በዚሁ እግረ መንገድ በሌሎች የቴሌቪዥን ጣቢያዎችም አይቼ ካመሰገንኳቸው ልጠቃቅስ። ይሄም እያዝናና የሚያስተምር ሆኖ ያገኘሁት ነው። አዲስ ሚዲያ ኔቶርክ (አዲስ ቲቪ) ላይ ጋምቤላ ሆቴል ውስጥ የተዘጋጀ አንድ የመዝናኛ ፕሮግራም አየሁ። ተወዳዳሪዎቹ የሚጠየቁት በክረምት ወቅት አርሶ አደሩ የሚያንጎራጉራቸውን የስነ ቃል ግጥሞች ነው። ለከተሜ ነዋሪ ከባድ ይመስላል። ባለማወቃቸውም ስንኙን ራሳቸው በሚፈልጉት መንገድ (ቤት እንዲመታ ብቻ) ጨረሱት፤ ይሄ ያዝናናል፤ የአርሶ አደሩን ጥበብና ቅኔ ማስታወሱ ደግሞ ትምህርት ነው። መጨረሻ ላይ ጋዜጠኛዋ ጥያቄዎቹን በሚገባ ታብራራለች።
በቴሌቪዥን የመዝናኛ ፕሮግራሞች ብዙም አስተውየው የማላውቀውን ከዚሁ ከአዲስ ቲቪ ያስተዋልኩት አርሶ አደሩ ለሚያመርታቸው የቅመማቅመምና እህል አይነቶች ትኩረት መስጠቱ ነው። ተወዳዳሪዎቹ የእነዚያን የቅመማቅመም አይነቶች እንዲናገሩ መደረጉም ሌላው የተወዳዳሩበት ነበር። ቀላል ይመስለን ይሆናል፤ ዳሩ ግን ልብ ያልተባለና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ የአገር ምርት ነው።
አዲስ ሚዲያ ኔቶርክ የአዲስ አበባ ነው። አብዛኛው ተከታታዩ የከተማ ነዋሪ ነው። በመዝናኛ ፕሮግራም ይህን ያደረገውም ለዚህ ነው። ለገጠሩ ማህበረሰብ ቢቀርብ ምንም አያዝናናም ነበር። አንድን ገበሬ ‹‹ጤና አዳም ምንድነው?›› ብንለው ስቆብን ነው የሚያልፍ። የከተማ ነዋሪዎች ሲፈተኑበት ግን ያዝናናል። እያዝናኑ ማስተማር እንዲህ ነው።
ሌላው እያዝናኑ ማስተማር ያስተዋልኩት ደግሞ በኢትዮጵያ ብሮድካስት ሰርቪስ (ebs) ቴሌቪዥን ነው። በነገራችን ላይ ብዙ ሰው የኢ ቢ ኤስ እና ኢ ቢ ሲ ስም ይምታታበታል። ኢ ቢ ኤስ ‹‹ቅዳሜ ከሰዓት›› የሚባል ፕሮግራም አላቸው። ብዙ እያዝናኑ የሚያስተምሩ ፕሮግራሞች አሉት። ከእነዚህ ውስጥ በቅርቡ የተጀመረ ‹‹ተከፍሏል›› የምትል አጭር ፕሮግራም አለች። እያዝናናች የምታስተምር ናት።
ካሜራው ተሽከርካሪ ውስጥ በድብቅ ይቀመጣል። ጋዜጠኛዋ የተጎሳቆለች ሴትዮ መስላ፤ ፊቷን ተሸፋፍና አነስተኛ የንግድ ሥራዎች የያዙ (ለምሳሌ ጉሊት) አጠገብ ትሄዳለች። የያዙትን ነገር ትጠይቃለች። ዋጋውን ይነግሯታል። ብዙ የምትገዛ መስላ ታስቆጥራቸዋለች። መጨረሻ ላይ በዕለቱ ሊያገኙ የሚችሉትን ገቢ ትጠይቃቸውና የዕለቱን ገቢያቸውን ኢ ቢ ኤስ ቴሌቪዥን እንደሚሸፍን ትነግራቸዋለች። የተሸፋፈነችውን ተገልጣ፣ ራሷን አስተዋውቃ ድብቅ ካሜራ መኖሩን አሳይታ ከዝናብ ወይም ከፀሐይ ላይ ተነስተው ወደቤታቸው እንዲሄዱ ታደርጋቸዋለች። በዚያን ዕለት ገቢያቸውን ከቴሌቪዥን ጣቢያው አግኝተው ከፀሐይ ወይም ዝናብ እረፍት አደረጉ ማለት ነው።
በቆይታዋ ውስጥ ከሰዎቹ ጋር የምታደርጋቸው ጭውውቶች አስቂኝ ናቸው። በተለይም መጨረሻ ላይ የያዙትን ዕቃ ዋጋ ወይም በዕለቱ የሚያገኙትን ገቢ እንደሚከፈልላቸው እና እየተቀረጸ መሆኑን ሲያውቁ የሚያሳዩት ድንገተኛ ግርምት ያስቃል። እናቶችና አባቶች ከሆኑ ደግሞ አብዝተው ይመርቃሉ። እያዝናኑ ማስተማር ማለት እንዲህ ነው።
በብዙ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ የሚነሳው ቅሬታ የውጭ መገናኛ ብዙኃን አሰራሮችን መኮረጅ ነው። ከራስ ፈጠራ ይልቅ የውጭ አገራትን አይቶ ለማስመሰል መሞከር ነው። የራሳችን የሆነ ነገር የሚያዝናና አይመስለንም። ግን ደግሞ ለባህላችን ትኩረት አልሰጠንም እያልን እንታዘባለን፣ እንወቅሳለን።
ከእነዚህ ሦስት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ያስተዋልኳቸው ነገሮች እያዝናኑ ያስተማሩኝ ናቸው። ምንም እንኳን የተማሪዎች ጥያቄ ትኩረት የሚያደርገው ተማሪዎች ላይ ቢሆንም፤ ልጆችን በዚህ መንገድ መቅረጽ የእኛ የአዋቂዎች ድርሻ ነው። ልናበረታታው የሚገባን እኛ ነን። ለተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ለመምህራንም የሚሆን ነው፤ በየዘርፉ ለተሰማሩ ባለሙያዎችም የሚሆን ነው። የኬሚስትሪ ወይም ፊዚክስ ጥያቄ ሲጠየቅ ፋብሪካ ውስጥ የሚሰራ ሰው ይማርበታል፤ ጂኦግራፊም ወይም ሌላ የማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ሲጠየቅም እንደዚሁ በየዘርፉ ያለ ሰው እየተዝናና ይማርበታል።
የአርሶ አደሩን የስነ ቃል ጥበብ ውጤቶች ማስታወስ ለከተሜው እንደ አዲስ ያዝናናዋል፤ ለሚያውቀውም ያስታውሰዋል፤ ታሪክና ባህሉም እንዲሰነድ ያደርጋል።
በማህበራዊ ገጾች (ዩ ትዩብ) ‹‹ሰርፕራይዝ፣ ፕራንክ…›› እየተባለ የሚያዝናኑ ነገሮችን እናያለን። በዋናዎቹ መገናኛ ብዙኃን ደግሞ እንደነ ኢ ቢ ኤስ እያዝናኑ የሚያስተምርና የበጎ አድራጎት ሥራ የሚሰራ ፕሮግራም ሊመሰገን ይገባል። ያ ዕድል ያጋጠማቸው ሰዎች ቀኑን ሙሉ ጉሊት ቢውሉ ምናልባትም ምንም ሳይሸጡ ሊውሉ ይችላሉ። ቴሌቪዥን ጣቢያው ግን በዕለቱ ሊያገኙ የሚችሉትን ይከፍላቸዋል፤ በድርጊቱም ዘና ብለው ወደቤታቸው ይሄዳሉ። እያዝናናችሁ የምታስተምሩ መገናኛ ብዙኃንና ጋዜጠኞች ምሥጋና ይገባችኋል!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2014