‹‹የኢትዮጵያ ባለ ልዩ ጣዕም ምርትን ይግዙ›› በሚል መሪ ቃል ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ቀን በፓናል ውይይት እና በአውደ ርዕይ ተከብሯል። በወቅቱም በተመረጡ ላኪዎች ከግብርና፣ ከኢንዱስትሪና ከማእድን የተመረጡ 12 አይነት የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ምርቶች ለእይታ ቀርበዋል።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ለመጀመሪያ ጊዜ ያካሄደው ይህ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ቀን መድረክ የኢትዮጵያን ምርቶች መለያ ለማድረግ፣ የገበያ ፍላጎቶችንና መዳረሻዎችን ለማስፋትና አዳዲስ ምርቶችን ወደ ወጪ ንግድ ገበያው ለማስገባት፣ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ አንደሚጠቅም ተጠቁሟል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በውጭ ምንዛሬ እጥረት በብዙ እየተፈተነች ያለችው ኢትዮጵያ ካለፉት ዓመታት በተሻለ በተጠናቀቀው 2014 በጀት ዓመት በወጪ ንግድ አፈጻጸም አመርቂ ውጤት አስመዝግባለች። ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በወጪ ንግድ አበረታች ውጤት ካስመዘገበችባቸው ዘርፎች መካከል ደግሞ የአንበሳውን ድርሻ የወሰደው የግብርናው ዘርፍ እንደሆነም ተጠቁሟል። ከግብርናው ዘርፍ ደግሞ ቡና በታሪክ ታይቶ በማያውቅ መልኩ ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ አስገኝቷል። ግብርና ከአጠቃላይ የወጪ ንግድ ገቢ 20 በመቶውን መሸፈኑንም መረጃዎች ያመለክታሉ።
እውቅና ከተሰጣቸው ላኪዎች መካከል በሆርቲካልቸር ዘርፍ የተሰማራውና በእስራኤላውያን ባለሃብቶች የሚመራው ጆይ ቴክ የተሰኘው ድርጅት አንዱ ነው። የድርጅቱ የእርሻ ሥራ አስኪያጅ አቶ ብሥራት ኃይለስላሴ እንደገለጹት፤ ድርጅቱ በቢሾፍቱና ለገዳዲ አካባቢዎች አንድ መቶ ሺ ካሬ ሜትር ስፋት ባለው መሬት ላይ በሆርቲካልቸር የሥራ ዘርፍ ተሰማርቷል። ላለፉት 20 ዓመታትም የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን እንዲሁም የእጸጣዕም ምርቶችን እያመረተ ለውጭ ገበያ እያቀረበ የሚገኝ ሲሆን፣ በዋናነት ለአውሮፓ ገበያ ራሺና ኖርዌ ምርቶቹ በስፋት ይልካል።
ከድርጅቱ ምርቶች መካከል እጸጣዕም በዋናነት ይጠቀሳል፤ እጸጣእም ለምግብ ማጣፈጫነት የምንጠቀምባቸውና አንዳንዶቹም የመድሃኒትነት ባህሪ ያላቸው እንደ ሮዘመሪኖ፣ ናና፣ ጦስኝ፣ ድንብላል፣ ጠጅሳርና የመሳሰሉትን የሚያካትት ሲሆን፣ ድርጅቱም አጠቃላይ 26 የሚደርሱ የእጸጣዕም ምርቶችን ያመርታል። ከአትክልትና ፍራፍሬ መካከልም የአበባ ጎመን፣ ብሮኮሊ፣ ፍሬንች ቶማቶ፣ ቲማቲም፣ ሰላጣ፣ ኩከንበርና የመሳሰሉትን በማምረት ለውጭ ገበያ በስፋት ያቀርባል።
በተያዘው በጀት ዓመትም ድርጅቱ በመጠን ከፍ ያለ ምርት ወደ ውጭ ገበያው በመላክ ዳጎስ ያለ የውጭ ምንዛሪ ማስገባት መቻሉን አቶ ብስራት ጠቅሰው፣ በዋናነት የወጪ ንግድ ሥራ ሲሰራ በዓመት ውስጥ ምን ያህል ምርት ወደ ውጭ ገበያ መላክ እንዳለበትና የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ግምት ውስጥ በማስገባት ዕቅድ ተይዞ እንደሚሠራ ይገልጻሉ። በተጠናቀቀው 2014 በጀት ዓመትም አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኪሎ ምርቶችን ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ አቅዶ፣ እቅዱንም ሙሉ ለሙሉ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል። በዚህም ድርጅቱ ከ25 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ማስገኘት በመቻሉ ተሸላሚ መሆን ችሏል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያዘጋጀው መድረክ በአይነቱ የተለየና እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ አቶ ብስራት በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ገልጸዋል፤ በተለይም በወጪ ንግድ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አካላት ምርቶቻቸውን ለእይታ በማቅረብ ምን አይነት ምርቶች ወደ ውጭ ገበያ እየተላኩ እንደሆነ መረዳት ተችሏል ይላሉ። በተጓዳኝም የተለያዩ ምርቶችን በማየት የልምድ ልውውጥ ማድረግ መቻሉንና አጠቃላይ አገሪቷ በወጪ ንግድ ዘርፉ የት ላይ እንዳለች ግንዛቤን መፍጠር ማስቻሉንም ይናገራሉ።
አገሪቷ የተለያዩ ፈተናዎችን ተቋቁማ በተለይም ለአገሪቷ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት የሚችለው የወጪ ንግድ ሳይቆራረጥ ማስቀጠልና የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉ ትልቅ ነገር ሆኖ እንዳገኙት ጠቅሰው፣ መንግሥትም ለዘርፉ ተዋናዮች ዕውቅና መስጠቱ እጅግ የሚያበረታታና ጥሩ ስሜት መፍጠር የቻለ መሆንም ተናግረዋል። ይህም በቀጣይ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከዚህ በበለጠ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ማስገባት እንዲቻል የሚያነሳሳ የሞራል ስንቅ እንደሆነ ነው ያስረዱት።
በመድረኩ የተገኙት የዘርፉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ከባለድርሻ አካላት እንዲገነዘቡ መደረጉና ችግሮቹንም ለመፍታት ቃል መግባታቸውን አንደ ስኬት የተመለከቱት አቶ ብስራት፣ ችግሮቹም በኃላፊዎቹ የሚፈታ ስለመሆኑ እምነት አድሮባቸዋል። ይህም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚያስችል ይጠቁማሉ፤ መድረኩንም የተሳካ ሲሉ ገልጸውታል።
እንደ አቶ ብስራት ገለጻ፤ ድርጅቱ በግብርናው ዘርፍ የተሰማራ እንደመሆኑ በቀጣይ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ገቢውን በዛው መጠን ከፍ ለማድረግ አቅዷል። የበለጠ ዘመናዊ መንገድን በመከተል ተጨማሪ ምርት ለማምረት መታቀዱንም ያመለክታሉ።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ለውጡን ተከትሎ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የንግድ ስርዓቱን ለማዘመን እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሻሻል የሪፎርም ስራ መከናወኑን አስታውቀዋል። የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከዓለም ንግድ ስርዓት ውስጥ ተገቢው ስፍራ እንዲኖረው ለማስቻል በየዘርፉ የሚያስፈልጉ ፖሊሲዎችን ከመቅረፅ ጀምሮ የተለያዩ ንቅናቄዎች መደረጋቸውንም ነው ያመለከቱት። በዚህም ለበርካታ አመታት ሲሰራበት የነበረውን የንግድ ህግ የማሻሻል ስራ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህግ ሆኖ እንዲወጣ መደረጉን አንስተዋል።
አፈ ጉባኤው የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የወጪ ንግድ ገቢን በማሳደግ በአለም መድረክ የኢትዮጵያን ተሳትፎ ከማሳደግ በላይ በችግሮች ውስጥ ሆኖም ጠንካራና የማይበገር ኢኮኖሚ መገንባት እንደሚቻል የታየበት ነው ብለዋል። በቀጣይም እምቅ ሀብቶችን በመጠቀም የውጭ ዕዳ እንዲቀንስ እና ኢኮኖሚው እንዲዳብር ውጤታማ አሰራር እንደሚከተል ማስታወቃቸውን የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች አመልክተዋል።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው 2014 በጀት ዓመት በወጪ ንግድ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ እንደቻለች ጠቅሰዋል። ለተገኘው ውጤትም የተጀመሩ ሁለንተናዊ የሪፎርም ሥራዎች ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ሚኒስትሩም ጠቁመዋል።
ከሪፎርም ስራዎቹ መካከል ከ60 ዓመት በላይ ያስቆጠረው የአገሪቱን የንግድ ህግ ከማሻሻል ጀምሮ በሥራ ላይ የነበሩ የኢንቨስትመንት ህጎች ላይ ማሻሻያዎች ማድረግ፤ የካፒታል ገበያን ለመጀመር የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ማከናወን፣ የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ሂደቶችን ለማጠናቀቅ የተሰሩ ሥራዎች፤ የአህጉራዊ የንግድ ቀጠና ስምምነቶችን በመፈረም ወደ ተግባር መግባት፣ የንግድ ፖሊሲ የወጪ ንግድ ስትራቴጂ እና የጥራት ፖሊሲዎችን የማዘጋጀት ሥራዎች እንደሚጠቀሱ አብራርተዋል። እነዚህ ስራዎች የአገራዊ ለውጡ ትልቅ አካል ተደርገው የሚወሰዱ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
ለተመዘገበው ከፍተኛ የወጪ ንግድ ገቢ የመንግስት ተቋማት እና የግሉ ዘርፍ የበኩላቸውን ሚና እንደተወጡ ተናግረው፣ በቀጣይም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በትብብር እንሰራለን ብለዋል። እውቅና እና ሽልማት የተሰጣቸው ላኪዎች በበኩላቸው በቀጣይ የበለጠ ለመስራት እንዲሁም በግልፀኝነት እና በታማኝነት ለማከናወን ሽልማቱ የሚያበረታታቸው እንደሚሆንም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ በ2014 በጀት ዓመት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አራት ነጥብ አንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ከወጪ ንግድ ተገኝቷል። አፈጻጸሙም ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር 13 ነጥብ ስምንት አንድ በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። ይህም በዘርፍ ደረጃ ሲታይ ግብርና፣ ኢንዱስትሪና ማዕድን ከፍተኛውን ደረጃ ይዘዋል፣ ለተመዘገበው ውጤት ሁሉም ዘርፎች ከፍተኛ ርብርብ አድርገዋል።
የወጪ ምርቶች በመጠንም ሆነ በጥራት ጨምረዋል። ለአብነትም ቡና በከፍተኛ ደረጃ በመጠን የጨመረ ሲሆን፤ የቁም እንስሳት፣ ጥራጥሬና የቅባት እህሎችም እንዲሁ በከፍተኛ መጠን ለውጭ ገበያ ተልከዋል። ከፍተኛ መጠን ያላቸው የተለያዩ ምርቶች በኮንትሮባንድ እየወጡም፣ የወጪ ምርቶቹ መጨመር መቻላቸው አገሪቷ በወጪ ንግዱ ከፍተኛ አቅም እንዳላት ያመለክታል። አገሪቷ በጦርነት፣ በጸጥታ ችግርና በተለያዩ ችግሮች ውስጥም ሆና በአሁኑ ወቅት የወጪ ምርቶች መጠን መጨመር መቻሉ አበረታች ሊባል ይገባዋል።
ኢትዮጵያ የምትታወቅባቸውን የወጪ ንግድ ምርቶች ለዓለም ገበያ ይበልጥ በማስተዋወቅ የገበያ ፍላጎቶችንና መዳረሻዎችን በማስፋት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ የማሳደግ ዕቅድ መያዙንም ነው አቶ ገብረመስቀል ያስታወቁት። ለዚህም በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ ገቢ
ማስመዝገብ የቻሉ የወጪ ንግድ ላኪዎች በመድረኩ ምርቶቻቸውን እንዲያሳዩ መደረጉን፣ በወቅቱ ለናሙና የቀረቡት ምርቶችም የዓለም ገበያን ሰብረው በመግባት ከሌሎች አገራት ጋር ተወዳዳሪ መሆንና ከፍተኛ መጠን ያለውን የውጭ ምንዛሪ ወደ አገሪቷ ማስገባት የቻሉ ናቸው ብለዋል።
በአገሪቱ ከሚገኙና በሺዎች ከሚቆጠሩ የወጪ ንግድ ላኪዎች መካከል ከ25 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ለአገራቸው ማስገባት የቻሉት ላኪዎች ‹‹አርበኞች›› ስለመሆናቸው የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ ላኪዎቹ ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ መጠን ያለውን የወጪ ምርቶች ለወጪ ንግድ እንድትልክና የተሻለ ውጤት እንድታስመዘግብ በማድረግ ከፍተኛ ድርሻን መወጣት ችለዋል ሲሉ ገልጸዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ከፍተኛውን ገቢ በማስገኘት ረገድ የግብርናው ዘርፍ ቀዳሚ በመሆን የምጣኔ ሀብቱ ዋነኛ የገቢ መሰረት እንደሆነም ቀጥሏል። በአጠቃላይ ለወጪ ገቢ ንግዱ የግብርናው ዘርፍ 72 በመቶ፣ የኢንዱስትሪው ዘርፍ 12 በመቶ እንዲሁም የማዕድን ዘርፉ 14 በመቶ አስተዋጽኦ ማበርከት ችሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ስድስተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ አመት የሥራ ዘመን 16ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ኢትዮጵያ በወጪ ንግድ ዘርፍ ያስመዘገበች እምርታ በጣም በጣም ግዙፍ ነው ብለውታል። ይህንን ውጤት አስጠብቆ ለጥቂት ዓመታት መጓዝ ከተቻለ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የንግድ መዛባትና የውጭ ምንዛሬ ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል ሲሉ አስታውቀዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ በ2002 በጀት አመት ሁለት ቢሊዮን ዶላር ኤክስፖርት አድርጋ እንደነበር፤ ጉድስ (goods/ ሸቀጦች) ከ2002 እስከ 2012 ዓ.ም ሶስት ቢሊዮን ለመድረስ ትንገዳገድ ነበር። በ10 ዓመት ውስጥ አንድ ቢሊዮን ገደማ መጨመር ተችሏል። ባለፈው በጀት አመትና በዘንድሮው በጀት ዓመት በተከናወነው የሪፎርም ሥራ በሁለት ዓመት ውስጥ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ በመጨመር ዛሬ በጉድስ እና ሰርቪስ/በሸቀጦችና አገልግሎት/ ኤክስፖርት ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ መገኘት ተችሏል።
በጉድስና በሰርቪስ ባለፈው ዓመት ከነበረው ዘንድሮ ጭማሪ አሳይቶ ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ኤክስፖርት ውጤት ተገኝቷል። ሰርቪስ ደግሞ በ25 በመቶ አድጎ ከስድስት ቢሊዮን ዶላር በላይ አግኝተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በሰርቪስና በኤክስፖርት አስር ቢሊዮን ሲገባ ደግሞ በሁለቱ ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ የሚገመት ተጨማሪ ሃብት ማፍራት መቻሉን ተናግረዋል። የሰርቪስ ከፍ ይላል፤ በዚህ ደግሞ በሁለቱ ዓመት ውስጥ አንድ እንጨምርበታለን። ይሄ በጣም ትልቅ እምርታ ነው። ግን ሊያዘናጋን አይገባም፤ ከምንፈልገው አሁንም ሩቅ ስለሆንን ብዙ ሥራ ይጠበቅብናል ማለታቸው ይታወሳል።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በ2015 በጀት ዓመት ደግሞ የወጪ ንግድ ገቢን ወደ አምስት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማሳደግ ታቅዶ እየሰራ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2014