ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክትር አብይ አህመድ በትረ ሥልጣናቸውን ከተረከቡ አንድ ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ በአንድ ዓመት የሥራ ጉዟቸው በርካታ ተግባራትን ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡ ቀጥሎ የተጠናቀሩት በሐምሌ ወር 2010 ዓ.ም ካከናወኗቸው ተግባራት መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
• የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያና ኤርትራ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነታቸውን ወደ መደበኛነት መመለስ የሚያስችል የሠላምና የልማት ስምምነት ፈፀመዋል፡፡ በኤርትራ የሁለት ቀናት ጉብኝት በማድረግ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የሁለቱ አገራት ሁለንተናዊ ግንኙነት በሚቀጥልበት መንገድ ላይ መክረዋል፡፡
• በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራውን ልዑካን ቡድን ከቦሌ አየር ማረፊያ እስከ ቤተመንግሥታቸው ድረስ ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ ከቤተመንግሥት የምሳ ግብዣ በኋላ ወደ ሐዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክን ለጎብኘት ወስደዋቸዋል፡፡ የሐዋሳና አካባቢዋ ነዋሪዎችም ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
• ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ተዘግቶ የቆየውና ስታዲየም ፊት ለፊት የሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ የሁለቱም አገራት መሪዎች በተገኙበት በይፋ ተከፍቷል፡፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም የኤምባሲውን ቁልፍ ለኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አስረክበዋቸዋል፡፡
• የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ሠላም እንዲመጡ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ከተባበሩት ዐረብ ኢምሬቶች የአገሪቱ ከፍተኛ የኒሻን ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ መሪዎቹ ሁለቱ አገሮች ታሪካዊ የሠላም ስምምነት ላይ መደረሳቸችው ለሌሎች አገራት አርአያ የሚሆን ተግባር በመሆኑ ሽልማቱን ማግኘታቸውም ተገልጿል፤ ሽልማቱንም የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች አልጋ ወራሽ ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ሚኒስትሮች፣ አምባሳደሮችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት አበርክተዋል፡፡
• ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰሜን አሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ‹‹ግንቡን እናፍርስ፤ ድልድዩን እንገንባ›› በሚል መልዕክት ለስድስት ቀናት ውይይት አካሂደዋል፡፡ በተለይም በቆይታቸው በአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፋ ያለ ውይይት አድርገዋል፡፡ ለተነሱላቸው ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል። በውይይቱ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ «አፍሪካ በእኛ አፍራለች፡፡ ምክንያቱም ነፃነትን ያስተማርናት እኛ ሆነን ሳለን በመከፋፈላችንና በእኛ ስንፍና ምክንያት አፍሪካ መሪ አጥታ ለማኝ ሆናለች። ስለዚህም ኢትዮጵያውያን ኃላፊነት እንዳለባቸው፤ ኃላፊነቱም ከእያንዳንዱ ግለሰብ የጀመረ መሆን ይገባዋል» ማለታቸው አይዘነጋም፡፡ በቆይታቸው ከተለያዩ የዳያስፖራው ማህበረሰብ ጋር ከነበራቸው ውይይት ጎን ለጎን ከመብት ተሟጋቾችና ከፖለቲካ ድርጅቶች ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውም የሚታወስ ነው፡፡
• የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራሮች እና ለረጅም ጊዜ የመንግሥት ተቃዋሚ የነበረው ጃዋር መሃመድ እንዲሁም አርቲስት ታማኝ በየነ ወደ አገር እንደሚመጡ የገለፁትም በዚሁ ወር በአሜሪካ በነበራቸው የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡
• በአሜሪካ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተገኙበት የሃይማኖት አባቶች እርቀ ሠላም አውርደዋል፡፡ ለ26 ዓመታት በስደት ላይ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ጨምሮ ሊቃነ ጳጳሳት ትናንት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር