ባለፉት ዓመታት እየደበዘዘ የመጣው የኢትዮ ጵያውያን አትሌቶች የቡድን ሥራ ትናንት በተጠናቀቀው የኦሪገን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ማገገሙ በብዙ አጋጣሚዎች ተስተውሏል። በተለይም ትናንት ሌሊት በተካሄደው የሴቶች 5ሺ ሜትር ፍጻሜ የኢትዮጵያውያን አትሌቶች የቡድን ሥራ በእጅጉ ጎልቶ ታይቷል። ከራስ ክብርና ጥቅም በላይ አገርን ማስቀደም ለተሰንበት ግደይ ራሷን ሰውታ ኢትዮጵያ ወርቅና ነሐስ እንድታጠልቅ በማድረግ ጎልቶ ወጥቷል። እሷም ከድሉ በኋላ ዓላማዋ የቡድን ሥራውን ማገዝ እንደነበር ተናግራለች።
ከሌሎች ውድድሮች በተለየ ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮና የሴቶች 5ሺ ሜትር ውድድር በስኬት የሚስተካከላት ሀገር የለም። አራት ወርቅ፣ሁለት ብር ስድስት ነሐስ ከዚህ ቀደም በርቀቱ የሰበሰበችው የሜዳሊያ ብዛት ሲሆን ከዓለምም ቀዳሚ ያደርጋታል። ዛሬም በዚህ የሜዳሊያ ስብስብ ላይ ኢትዮጵያ ተጨማሪ የወርቅና የነሐስ ሜዳሊያ ወደ ካዝናዋ አስገብታለች።
አስደናቂዎቹ አትሌቶች ጉዳፍ ጸጋይና ዳዊት ስዩም ሜዳሊያዎቹን በኢትዮጵያ ሰማይ ጸሐይ ሳይወጣና የማለዳ ወፎች ሳይዘምሩ በርቀቱ የዓለም ሻምፒዮና ታሪክ የውድድሩ ፈርጦች መፍለቂያ ለሆነችው ሀገር ገቢ አድርገዋል። የዚሁ የኦሪገን ሻምፒዮና የ1500 ሜትር የብር ሜዳሊያ ባለቤቷ ጉዳፍ የወርቃማ ሻምፒዮኖችን ዓለም በተቀላቀለችበት ውድድር የ10ሺ ሜትር ሻምፒዮኗ ለተሰንበት ግደይ ትልቅ የቡድን ስራ ብትሠራም ሜዳሊያ ውስጥ መግባት አለመቻሏ የሚቆጭ ነበር።
በዚህም ኢትዮጵያ ለጥቂት አረንጓዴው ጎርፍ አምልጧታል።”የገባነው ለቡድን ሥራ ተነጋግረን ነው ከ6ኛ ዙር በኋላ ለማፍጠን ተስማማን በ1500 ሜትር ወርቅ ያጣሁትን በ5000 ሜትር ተካስኩ፣ ያጠለኩት ወርቅ መታሰቢያነቱ ለጠንካራዋ እናቴ እንዲሁም ለጠንካራው አሰልጣኜ ህሉፍ ይሁንልኝ” በማለት ጉዳፍ በስፍራው ለነበሩ መገናኛ ብዙኃን ተናግራለች።
በዓለም ሻምፒዮና የሴቶች 5ሺ ሜትር ታሪክ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከዚህ ቀደም በሁለት አጋጣሚዎች የአረንጓዴውን ጎርፍ ታሪክ ሠርተዋል። እኤአ 2005 ሄልሲንኪ ላይ ጥሩነሽ ዲባባ፣መሰረት ደፋር፣እጅጋየሁ ዲባባና መሰለች መልካሙ ከአንድ እስከ አራት ተከታትለው የገቡበት ትልቅ ታሪክ አይዘነጋም። እኤአ በ2015 የቤጂንግ ሻምፒዮናም አልማዝ አያና፣ሰንበሬ ተፈሪና ገንዘቤ ዲባባ ከአንድ እስከ ሶስት ተከታትለው በመግባት ተመሳሳይ ታሪክ ተጋርተዋል።
ኢትዮጵያ እንደ አጠቃላይ በሴቶች የርቀቱ ንግሥናዋ ዘንድሮም ተጠናክሮ ቀጠለ እንጂ የሚደፍረው አልተገኘም። ለዚህም ጀግናዋ የርቀቱ ፈርጥ አትሌት መሠረት ደፋር የአንበሳውን ድርሻ ትወስዳለች። መሰረት በታሪክም በርቀቱ ሁለት ወርቅ፣ሁለት ብርና አንድ ነሐስ በማጥለቅ የሴቶቹን ታሪክ በፊት አውራሪነት ትመራለች። ኬንያዊቷ ቪቪያን ቼሪዮት ሁለት ወርቅና አንድ ብር፣ታሪካዊቷ ሮማንያዊት አትሌት ገብርኤል ዛቦና ጥሩነሽ ዲባባ ሁለት ወርቆችን በማጥለቅ የሚጠቀሱ አትሌቶች ቢሆኑም እንደ መሠረት ደፋር በአምስት ውድድሮች የሜዳሊያ ሽልማት ለመቀበል ወደ መድረኩ አምስት ጊዜ የወጣ አትሌት ማግኘት አይቻልም።
በዓለም ሻምፒዮና ከአርባ በላይ ዓመታት ታሪክ የረጅም ርቀት የምንጊዜም ምርጧ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ እኤአ በ2005 የሄልሲንኪ ሻምፒዮና በ10ና 5ሺ ሜትር ጥምር ወርቆችን በማጥለቅ ብቸኛዋ ነች። 14:26:72 የሻምፒዮናው ክብረወሰን ሲሆን ባለፈው የዶሃ ሻምፒዮና በኬንያዊቷ ሔለን ኦቢሪ ነበር የተሰበረው። የወንዶቹም የርቀቱ የሻምፒዮና ክብረወሰን እኤአ በ2003 በድንቁ ኬንያዊ የማራቶን አትሌት ኢሉድ ኪፕቾጌ በ12:52:79 የተያዘ ነው። አትሌቶች በዓለም ሻምፒዮና በርቀቱ የሚያደርጉት ታክቲክ የበዛበት ፉክክርና የአሯሯጮች አለመኖር በሁለቱም ጾታ የተመዘገቡ የሻምፒዮናው ክብረወሰኖችን በአንድም አጋጣሚ የሚስተካከል ወይም የተሻለ ሰዓት እንዳይመዘገብ ማድረጉ ይታመናል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2014