በአሸባሪነት የተፈረጀው የሕወሓት ቡድን በተለይም በሰሜኑ ኢትዮጵያ ላይ ያደረሰው ጉዳት ተዘርዝሮ የሚያበቃ አይደለም። የሰው ሕይወትን ጨምሮ ብዙ ተስፋ ሰጪ ሕልሞችን አጨናግፏል። የተረጋጋ የመማር ማስተማር ሥራ ጭምር እንዳይኖር አድርጓል። በእርግጥ ይህንን አጸያፊ ተግባር እንዲከውን ያደረገው የትምህርት ኃያልነትን አገር የማዳኑን አላማ ስለሚረዳ ነው።
አገር ጠል ለሆነ ቡድን ደግሞ ትምህርቱ እንዳይቀጥል ማድረጊያ መንገዶችን መከተል ግድም ነው ግብም ይሆናል። በዚህም ንብረቶችን ከመዝረፍ ባለፈ አውድሟቸዋል። አልፈርስ ያለውን ደግሞ ጣሪያቸውን ሳይቀር ነቃቅሎ በታትኖታል። ከማጥፋቱ በተጓዳኝ ሕዝብ በእውቀት በልጽጎ አገርን አሻጋሪ እንዳይሆን ያደረገበት ቅጽበት ከሁሉም እንደሚልቅም የተለያዩ በትምህርት ዘርፉ ላይ የተሰማሩ ምሁራን ይናገራሉ። ምክንያቱም እርሱ ተረጋግቶ የመማርን ሁኔታን ጭምር ድንገት እየተነሳ የሚያደፈርስ ነው።
በአማራ ክልልና አፋር ክልሎች የወደሙ ትምህርትቤቶች ደግሞ ለዚህ ድርጊቱ ዋና ማሳያ ናቸው። ይሁን እንጂ የሕወሓትን ሴራ እንዲከሽፍ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን አይተናል። ሰሞኑንም የወደሙ ትምህርት ቤቶችን ዳግም በተሻለ ደረጃና ጥራት ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ተጥሏል። ለዚህ ደግሞ የፌዴራልና የክልል መንግሥስታት እንዲሁም ማህበረሰቡና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ትልቁን ድርሻ ወስደዋል።
የአዲሲቱ ኢትዮጵያ መጀመሪያ ምዕራፍ የትምህርቤት ግንባታ አካል የሆነው ይህ ሥራ በአፋር ክልል አደአር ወረዳ በደርሳ-ጊታ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤትና በደሴ ሆጤ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምርትቤቶች እንደማሳያነት ከሰኞ ጀምሮ ይጀመራል። ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ በመድረኩ የተገኙት የአፋርና አማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች እንዲሁም የትምህርት ሚኒስትርና የቢሮ ኃላፊዎች እንዲሁም መምህራን ሀሳባቸውን አስተላልፈዋል።
የሆጤ ሁለተኛና መሰናዶ ትምህርትቤት የፊዚክስ መምህሩ ኡመር መሀመድ አንዱ ሲሆኑ፤ 29 ዓመታትን በመምህርነት አገልግለዋል። ብዙ መንግሥታትንም በመምህርነትና በትምህርት አይተው አሳልፈዋል። እንደ ሕወሓት ጨካኝና አገር ጠል ቡድን አይተው እንደማያውቁ ይናገራሉ። በሕይወታቸው ገጠመኝ የሚሉት ፈተናም አሁን የተደረገውን ጦርነት ላይ የገጠማቸው ነው። ይህንን ሴራ ለማክሸፍም መምህር ቢሆኑም ታግለዋል፤ ቁስለኛ ተሸክመው አግልለዋል። ውሃና ምግብ አቀባይም ሆነዋል። ነገር ግን በቻሉት ልክ ቢደክሙም የፈለጉትን አለማሳካታቸው ያስቆጫቸዋል።
‹‹ሕወሓት ሰውኛ ባህሪ የሌለው ነው። ሰውን በሰውነቱ የማያከብርም ቡድን እንደእርሱ አላየሁም። ምክንያቱም እርሱ ያሰማራው ወታደር ተብዬ የ19 ዓመት ልጅ የ80 ዓመት አዛውንት ይደበድባል። ከዚያም አልፎ ሴቶችን ይደፍራል፤ ሕፃናትን ያሰቃያል። በቃ ያላደረሰው ስቃይ አልነበረም። እናም መፈጠሬንም ማወቄንም የጠላሁበት ጊዜ ቢኖር ይህ ወቅት ነው›› የሚሉት መምህር ኡመር፤ ለጭካኔው ምላሹ ጨካኝነት ሳይሆን ተለውጦ ማሳየት እንደሆነ የሚያሳዩ ተግባራት መጀመራቸው እጅግ የሚያስደስት እንደሆነ ያነሳሉ።
በወራሪው ሕወሓት ቡድን ጉዳት የደረሰባቸው 10 ትምህርት ቤቶች በደሴ ከተማ ብቻ ሊገነቡ እንደሆነ ሲሰሙ የእነርሱ ትምህርትቤት ደግሞ የመጀመሪያው መሆኑ ደስታን እንደፈጠረባቸው የገለጹት መምህሩ፤ ጅማሮው እንደዚህ ቀደሙ ለይስሙላና ጊዜ መቁጠሪያ እንዳይሆን ይላሉ። ለዚህ ደግሞ መነሻቸው ያደረጉት ኮምፒዩተር ሊመጣላችሁ ነው ተብለው እስካሁን አለመድረሱን በማንሳት ነው። ትምህርትቤቶች አሁን ላይ ከግንባታው በላይ የቤተሙከራ ቁሳቁሶች ያስፈልጓቸዋል። ምክንያቱም ግማሹ ሲወሰድ ሌላው ተሰባብሯል። የቀረ መጠቀሚያም የለም። ስለሆነም ተማሪዎችን በንድፈ ሀሳብ ትምህርት ብቻ እያስቀጠልን እንገኛለን። እናም ይህ በአፋጣኝ መመለስ እንዳለበትም ገልጸዋል።
የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ዳግም ችግር ውስጥ እንዳይገቡ መንግሥት ዳግመኛ ግንባታውን እንዳሰበ ሁሉ በጁንታው የወደመብንን ቤተሙከራ ቢያሟላልን መልካም ነው ያሉት መምህር ኡመር፤ እንደመንግሥት ካልተቻለ ረጂ ድርጅቶች እንዲያደርጉት ዕድሉ ሊመቻች እንደሚገባም አስገንዝበዋል። መምህራንም ትግላቸውን እንደዚህ ቀደሙ መሰዋዕት ጭምር ከፍለው ማስቀጠል አለባቸው። በተለይ ጊዜው የወደመውን መመለስ ላይ ያተኮረበት ስለሆነ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። የክልሉን ክብር ዳግመኛ የሚመልሱት ይህንን ሲያደርጉም እንደሆነ ያስረዳሉ።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ወያኔ ትምህርትቤቶችን ቢያፈራርስም በጥይት ሳይሆን የተሻለውን በማሳየት እንዋጋዋለን። ለዚህ ደግሞ ትምህርትቤቶችን በተሻለ መንገድ መገንባቱ አንዱ ይሆናል። እነዚህ ትምህርት ቤቶች ሲገነቡ የልጆች እውቀት መቅሰሚያና መጫወቻ ብቻ ሆነው አይደለም። ከዚያም የላቀ ተግባር እንዲኖራቸው ተደርገው ነው። ከእነዚህ መካከልም አንዱ ማህበረሰቡ የሚገለገልባቸው የእውቀትም የአገልግሎትም ማዕከል ሆነው ነው።
ተማሪዎች ተፈትነው ቢወድቁ እንኳን የማይጥላቸውን እውቀት የሚጨብጡበትም ይደረጋል። ምክንያቱም ትምህርት ቤቶቹ የተግባርና የሙያ ትምህርትቤቶችን ያካተቱ ተደርገው ይገነባሉ። እናም ተማሪዎች ኮሌጅ አለያም ዩኒቨርሲቲ መግባት ሳይጠበቅባቸው ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን እንዲሁም አገራቸውን የሚጠቅሙበትን ዕድል ያገኛሉ። ከማህበረሰቡ ጋርም ተቀላቅለው የራሳቸውን ሥራ ይሠራሉ ብለዋልም።
በአሸባሪው ሕወሓት ውድመት የተፈፀመባቸውን ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደተደረገ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በ27 ዓመታት የትምህርት ተቋማት ግንባታ ቢከናወንም ከቁጥር የዘለለና የሚጨበጥ ሥራ አልተከናወነም። በተለይም የጥራትና የትውልድ ቀረፃ ጉዳይ ትኩረት ተነፍጎት ቆይቷል። እናም ይህንን በሚያመጣ መልኩ አሁን የሚሠሩት ትምህርትቤቶች ይገነባሉ ብለዋል።
የትምህርት ቤቶቹ ዘረፋና ውድመት በአገርና ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ያስከተለ ቢሆንም ችግሩን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ለተሻለ ግንባታ ዕድሉን መጠቀም ይገባል የሚሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ የትምህርት ቤቶቹ መልሰው ሲገነቡ ለመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲሁም ለተማሪዎች ምቹና ማራኪ እንዲሆኑ ተደርገው ነው። የግንባታ ዲዛይናቸውም እንደየአካባቢው መልክአ ምድር፣ የማህበረሰቡ የአኗኗር ዘይቤ እና እሴቶቻቸውን የተከተሉ እንደሚሆኑም ይናገራሉ።
እንደ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ገለጻ፤ አሸባሪው ሕወሓት በወረራ በቆየባቸው በአማራና አፋር ክልሎች ከ1 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶችን ሙሉ ለሙሉ አውድሟል። በአፋር ከ65 በላይ ትምህርትቤቶች ሙሉ ለሙሉ ጠፍተዋል። ስለሆነም ለእርሱ ምላሻችን የሚሆነው የተሻለውን ገንብቶ ማሳየት ብቻ ነውና ተግባሩ ተጀምሯል።
በዚህም እስከሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ 200 ትምህርትቤቶች ተገንብተው ይጠናቀቃሉ። በሁለቱ ክልሎች በሽብር ቡድኑ የወደሙ ከ1300 በላይ የትምህርት ተቋማት በቀጣዮቹ አራት ዓመታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ በመገንባት ወደ አገልግሎት የሚገቡ ሲሆን፤ በሁለቱ ክልሎች በኢትዮጵያ ትረስት ፈንድ ወጪ የተደረገባቸው አራት ትምህርት ቤቶች ደግሞ ከሰኞ ጀምረው ሥራቸውን የሚጀምሩ ይሆናሉ።
የትምህርትቤት ግንባታው በመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ብቻ እንደማያበቃ የጠቀሱት ፕሮፌሰሩ፤ አዳሪ ትምህርትቤቶችን የመገንባት ሀሳብም አለ። በሁሉም ክልሎች አንዳንድ የሚሠራ ሲሆን፤ 13 ደረጃቸውን የጠበቁ አዳሪ ትምህርትቤቶችም ይኖሩናል ብለዋል። በእነዚህም ሆነ በሌሎች ትምህርትቤቶች ላይ ከዚህ በኋላ በፖለቲካ ሹመት የሚገባ ርዕሰ መምህርም እንደማይኖር ተናግረዋል። አሁን ላይ 1000 የሚሆኑ ዳይሬክተሮች እየሰለጠኑ እንደሆነም አስረድተዋል።
በመርሃግብሩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ አሸባሪው ሕወሓት ንፁሃንን በግፍ ከመግደሉ ባለፈ ንብረት በመዝረፍና በማውደም የከፋ ግፍ ፈፅሟል። ይሁን እንጂ መንግሥት ኅብረተሰቡንና ተቋማትን በማስተባበር በተሻለ ደረጃና ጥራት የመልሶ ግንባታ ተግባሩን ጀምሯል። ወደፊትም በዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ይሆናል። ምክንያቱም ሕወሓትን ማሸነፍ የሚቻለው አንድ ሆኖ በመስራትና በመማር ብቻ ነው።
ኅብረተሰቡ አንድነቱንና ሰላሙን በጋራ ጠብቆ የኢትዮጵያን ልማት ማስቀጠል ከቻለ የሕወሓት ሀሳብ ድል ይመታል። ትምህርት ቤቶች ብቁና አምራች፣ አገር ወዳድ ዜጋን መፍጠር ከቻሉም እንዲሁ። ለዚህ ደግሞ የትምህርት ቤቶች በጥራት መገንባት በር ከፋች ነው። የተሠበረውን ስነልቦናችንንም የምንጠግንበት ይሆናል። ለዚህ ግን ያላሰለሰ ጥረት ያስፈልጋል። እናም እንደክልል ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራል ብለዋል።
‹‹የክልሉ ትምህርት ቤቶች ከ84 በመቶ በላይ ከደረጃ በታች ናቸው። ይህንን ደግሞ አሁን ጀምረነዋል በቀጣይም በጠነከረ ክንድ ተባብረን የምናሻሽለው ይሆናል›› ያሉት ዶክተር ይልቃል፤ ትምህርትቤት ብቻ መገንባት በራሱ ግብ አይደለም። አጋዥ ሥራዎችን ይፈልጋል። አንዱ ደግሞ ከትምህርት ቤቱ ግንባታ ጎን ለጎንም ተማሪዎችን ወደትምህርት ቤት በማምጣት የተሻሉና ከሌሎች አካባቢና ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ተወዳዳሪ ማድረግ ነው። ጥራቱ ላይ ትኩረት ያደረገ ትምህርትም መስጠት ነው። እናም ከመምህራን እስከ አስተዳደሩ ድረስ በቅንጅት መሥራት ይጠበቃል። ማህበረሰቡም እንደሚያግዘን እምነት አለኝ። ስለዚህም አሁን እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ማጠንከር እንደሚገባ አስረድተዋል።
የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው፤ አሸባሪው ሕወሓት ወረራ ፈጽሞባቸው በነበሩ አካባቢዎች አዛውንት፣ ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኞችና ሴቶች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከዚያም ጎን ለጎን የወደፊት ተስፋ የሚሆኑ ተማሪዎች የሚፈሩበትን ትምህርትቤት አውድሟል። ከዚህ አኳያ በክልሉ ውድመት የደረሰባቸው የትምህርት ተቋማት ብዙ እንዲሆኑ ማድረጉን አብራርተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ሀጂ አወል እንደሚሉት፤ ከጦርነት ሁሉ ከባዱ ጦርነት ራስን ማሸነፍ ነው፣ ለዚህ ማሸነፊያው ደግሞ እውቀት ብቻ ነው። እውቀት ደግሞ ከትምህርት ቤት እንጂ ከሌላ የሚቀሰምበት መንገድ አናሳ ነው። እናም የእውቀት ምሰሶ የሆኑትን ትምህርትቤቶች መገንባት ላይ ሁላችንም ርብርብ ማድረግ አለብን። ዓለም ያድገው በእውቀት ተመርቶ በተሠራ የለውጥ አስተሳሰብ ውስጥ ነው። እኛም ያንን ተከትለን ለመራመዱ ትምህርትቤቶቻችንን በጥራት መገንባት የውዴታ ግዴታችን ማድረግ ይገባናልም ብለዋል።
ስኬት ላይ ለመድረስ ትምህርት መሪም አድራሽም እንደሆነ የሚናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በአፋር አሁን ሁለተኛ ጦርነት ተጀምሯል። ይህም ድህነትን የምንዋጋበትና መሃይምነትን የምናጠፋበት ትምህርት ነው። ለዚህ ደግሞ የለውጥ አስተሳሰብ ላይ መሥራት ከምንም በላይ ያስፈልጋል። የለውጥ አስተሳሰብ በምርቃና ሳይሆን በእውቀት የሚመጣ በመሆኑ ትምህርት ቤቶችን እየገነባን የነቃና ዘመኑን የሚመጥን አገር ወዳድ ትውልድ መፍጠር እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በእነርሱ በኩልም ትምህርትቤቱ በአግባቡ ተጠናቆ ለአገልግሎት እስኪበቃ ድረስም አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ አንስተዋል።
በአማራ ክልል ከአንድ ሺህ 145 በላይ ትምህርት ቤቶች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፤ ከ5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ውድመት እንደደረሰም ቀደም ሲል በተካሄደ ጥናት መረጋገጡን ያነሱት ደግሞ የአማራ ክልል ትምህር ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ማተቤ ታፈረ ናቸው። እርሳቸው እንዳሉት፤ ከ1ነጥብ ዘጠኝ በላይ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታቸው የለየውን ሕወሓትን የምናሳፍረው ተማሪዎችን በብቃትና በጥራት ስናስተምራቸው ነው። ለዚህ ደግሞ የትምህርትቤቶች መልሶ ግንባታ ከምንም በላይ ያስፈልጋልና አሁን አሀዱ ማለት ተችሏል። እስከፍጻሜውም በጥራትና በክትትል በጊዜው እንዲጠናቀቅ ይደረጋል።
በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው በአማራ ክልል ውስጥ ከሚገነቡት ሰባት ትምህርት ቤቶች ውስጥ በደቡብ ወሎ፣ ደሴ ከተማ አስተዳደር፣ ሰሜን ሸዋ፣ ሰሜን ወሎ፣ ዋግ ኽምራና ደቡብ ጎንደር የሚገኙት ሲሆኑ፤ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የሚገነቡ ይሆናሉም። እነዚህን ተቋማቶች መልሶ መገንባት ብቻም ሳይሆን በተሻለ ደረጃ አሻሽሎ በእውቀትና ስነ-ምግባር የታነጸ ብቁ አገር ተረካቢ ዜጋ የማፍራት አገራዊ ተልዕኳቸውን መወጣት በሚችሉበት ሁኔታ አደራጅቶ ለአገልግሎት ማብቃት እንደሆነም ያስረዳሉ።
ኃላፊው እንደሚሉት፤ ለዚህ ተግባር እውን መሆን እጁን የማይዘረጋ ኢትዮጵያዊ ሊኖር አይገባም። ምክንያቱም ትምህርትቤት ገነባ ማለት አገሩን አተረፈ፤ ወደፊት አሻገረ ነው። እናም ሁሉም አስቦበት ከትምህርት ሴክተሩ ጎን ይቁም። እኛም ለመልካም ሥራ መልካም ኢትዮጵያውያን አይጠፉምና ለግቡ ይረባረቡ በማለት አበቃን። ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2014