18ኛው የኦሪገን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ነገ ፍጻሜ ከማግኘቱ አስቀድሞ ዛሬ ሌሊት 10:25 ላይ አንድ አጓጊ ፉክክር ይጠበቃል። ይህ ፉክክር የሴቶች 5ሺ ሜትር ነው። በዚህ ውድድር አዲስ የዓለም ቻምፒዮን ብቅ እንደሚልም ብዙዎች ግምታቸውን አስቀምጠዋል። የርቀቱ አዲስ የዓለም ቻምፒዮን የመሆን ዕድሉም ከኢትዮጵያውያን ሦስት ኮከብ አትሌቶች የዘለለ እንደማይሆን ተገምቷል።
ያለፉትን ሁለት ቻምፒዮናዎች በርቀቱ ወርቅ ያጠለቀችው ኬንያዊቷ አትሌት ሄለን ኦቢሪ ኦሪገን ላይ በ10ሺ ሜትር ላይ ትኩረት ለማድረግ በመምረጧ በ5ሺ ሜትር አትሳተፍም። በኢትዮጵያም በኩል የርቀቱ የቀድሞ ቻምፒዮን አልማዝ አያና ኦሪገን አትገኝም። የርቀቱ የዓለምና የኦሊምፒክ ቻምፒዮን የሆነችው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድስ አትሌት ሲፈን ሃሰንም በ10ሺ ሜትር ያሳየችው ደካማ አቋም ዘንድሮ ትኩረት ውስጥ እንዳትገባ አድርጓታል። ይህም በዚህ የውድድር አመት በርቀቱ ነጥረው የወጡ ወጣት አትሌቶች ወደ ቻምፒዮንነት ክብር እንዲመጡ ገፊ ምክንያት ተደርጎ ተወስዷል።
በውድድር አመቱ ድንቅ አቋምና ፈጣን ሰዓቶችን ያስመዘገቡት ደግሞ ሦስት እንቁና የወቅቱ የርቀቱ ኮከብ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው። ከሳምንት በፊት በ10ሺ ሜትር ወርቅ ያጠለቀችው ለተሰንበት ግደይ፣ ከቀናት በፊት በ1500 ሜትር በብር ሜዳሊያ ያጌጠችው ጉዳፍ ጸጋይ፣ ትኩስ ጉልበት ይዛ የዛሬውን የፍጻሜ ውድድር የምትጠባበቀው ዳዊት ስዩም የዓለም ትኩረት ናቸው። ሦስቱም አትሌቶች ማጣሪያውን በድንቅ ብቃት አልፈው ለዛሬው ፍጻሜ ቀርበዋል።
በዚህ የውድድር አመት በ5ሺ ሜትር ዩጂን ዳይመንድሊግ ላይ እጅጋየሁ ታዬን ተከትላ ሁለተኛ ሆና ያጠናቀቀችው የርቀቱ ባለክብረወሰን ለተሰንበት፣ ከወር በፊትም በኦስሎ ዳይመንድሊግ ዛሬ አብረዋት የሚፋለሙት የአገሯን ልጆች ዳዊት ስዩምና ጉዳፍ ጸጋይን ተከትላ ሦስተኛ ሆና ማጠናቀቋ ይታወሳል። ይህ ሲታይ ለተሰንበት ከሦስቱ ኢትዮጵያውያን አንጻር አነስ ያለ ስኬት ነው። ይሁን እንጂ የዛሬው ውድድር ዳይመንድሊግ አይደለም። ለተሰንበትም ከአመት በፊት የምናውቃት አትሌት አይደለችም። የቻምፒዮኖቹን ዓለም ከሳምንት በፊት ተቀላቅላ በትልልቅ ውድድሮች እንዴት ማሸነፍ እንደምትችል በቂ ልምድ አካብታለች። የርቀቱ ባለክብረወሰን መሆኗም መዘንጋት የለበትም። ይህም በቻምፒዮናው ጥምር ወርቅ የማጥለቅ ህልሟን እውን ለማድረግ ትክክለኛው ቀን ዛሬ እንደሆነ ማሳያ ነው።
በ1500 ሜትር ከቀናት በፊት ብር ያጠለቀችው ጉዳፍ ጸጋይ ቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ በ5ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ አሸንፋለች። የቤልግሬዱ የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ወርቅ ያጠለቀችው ጉዳፍ ከቤት ውጪ ቻምፒዮናዎች የወርቅ ሜዳሊያ ህልሟና ጥረቷ የሚሳካበት ትክክለኛው ቀን ዛሬ የሚሆንበት ዕድል ጠባብ አይደለም። ጉዳፍን በዚህ ርቀት ከለተሰንበት የሚለያት አንድ ነገር አለ። ጉዳፍ በርቀቱ እንደለተሰንበት ልምድ ያላት አትሌት ስትሆን የ1500 ሜትር ተወዳዳሪ መሆኗ የተሻለ ተጠቃሚ ያደርጋታል ተብሎ ይታመናል። በብዙ አጋጣሚዎች ለመታዘብ እንደተቻለው የ1500 ሜትር ተወዳዳሪዎች ወደ 5ሺ ሜትር ሲመጡ በአጨራረስ ብቃት ከሌሎች በተለየ የተሻሉ ናቸው።
ከጉዳፍ ጋር በተመሳሳይ ሌላኛዋ ድንቅ አትሌት ዳዊት ስዩም መነሻዋ 1500 ሜትር ቢሆንም በዚህ አመት ወደ 5ሺ ሜትር መጥታ ስኬታማ መሆኗን አስመስክራለች። ዳዊት ባለፈው የኦስሎ ዳይመንድሊግ ለተሰንበትንና ጉዳፍን በድንቅ የአጨራረስ ብቃት ማሸነፏ እዚህ ጋር ሲታወስ ዛሬ የርቀቱ አዲስ ቻምፒዮን ልትሆን እንደምትችል ፍንጭ ይሰጣል።
እነዚህ ሦስት ድንቅ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ወረቀት ላይ ብቻ ሳይሆን በተግባር የርቀቱ የወቅቱ ፈርጦች ናቸው። ውድድሩ ላይ አንዳች ነገር ካልተፈጠረም ወርቁ ከነዚህ እንስቶች እጅ የሚወጣበት ዕድል ዝቅተኛ ነው። እንዲያውም ሦስቱም ሜዳሊያዎች በነዚህ ከዋክብቶች እጅ አስቀድመው ወድቀዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይህም ኢትዮጵያን በዚህ ቻምፒዮና ወደ ላቀ ስኬት ከማሸጋገሩ ባሻገር የአረንጓዴውን ጎርፍ ታሪክ እንዲደግሙ ሊያደርጋቸው ይችላል።
እነዚህ አትሌቶች ሦስቱንም ሜዳሊያ ከጠቀለሉም በዓለም ቻምፒዮና የርቀቱ ታሪክ ለሦስተኛ ጊዜ የሚመዘገብ ይሆናል። በዓለም ቻምፒዮና የሴቶች 5ሺ ሜትር ታሪክ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከዚህ ቀደም በሁለት አጋጣሚ አረንጓዴውን ጎርፍ አሳይተዋል። እኤአ 2005 ሄልሲንኪ ላይ ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሠረት ደፋር፣ እጅጋየሁ ዲባባና መሰለች መልካሙ ከአንድ እስከ አራት ተከታትለው የገቡበት ትልቅ ታሪክ አይዘነጋም። እኤአ በ2015 የቤጂንግ ቻምፒዮናም አልማዝ አያና፣ሰንበሬ ተፈሪና ገንዘቤ ዲባባ ከአንድ እስከ ሦስት ተከታትለው በመግባት ተመሳሳይ ታሪክ ተጋርተዋል። ዘንድሮስ? የዛሬ ሌሊቱ ፍልሚያ መልስ ይኖረዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2015