ውሎና አዳራችን ስልካችን ላይ ሆኗል:: በጋራ ጉዳዮቻችንን ወንበር ስበን ፊት ለፊት መወያየት ትተናል:: ችግሮችን በተግባቦት ከመፍታት ይልቅ ጥራዝ ነጠቅ ሀሳቦቻችን ቴክኖሎጂ በፈጠረልን ሜዳ እንዳሻን በማንሸራሸር እየተቀባበልን መሰዳደብ ቀሎናል:: ማህበራዊ ግንኙነታችን በማህበራዊ ገፆች ምክንያት እጅጉን መላላቱን ልብ ብለነው ይሆን? እንጃ አይመስለኝም:: አብረውን ላሉ ወዳጆቻችን ትኩረት በመንሳት የቅርብ እሩቅ ሆነን ቀርበን ሳናዋያቸውና ሳንረዳቸው ስንቶችን አስቀይመናል፤የስንቶችንስ ስሜት ጎድተናል::
አባወራ ነው፤ በስራ የዛለ አካሉን እየጎተተ ይጓዛል:: ቤቱ ገብቶ አረፍ ማለት በፅኑ ፈልጓል:: ታክሲ ለማግኘት ብዙ ርቀት ተጉዞ ከዚያም ረጅም ሰልፍ ጠብቆ አመሻሽ ላይ ቤቱ ደረሰ:: ትንሽ አረፍ እንዳለ ረሀብ ቢጤ ተሰማውና ምግብ ፈለገ:: እዚያው ያረፈበት ሳሎን ውስጥ ከአንድ የቤቱ ጥግ ላይ ባለ ሶፋ ላይ ጋለል ብላ ስልክዋን የምትጎረጉረው ባለቤቱን ሲመለከት ከረሀቡ ይልቅ ውስጡ ቅሬታ ተሰማው:: እርሷ አንዴ ፌስ ቡክ ሌላ ጊዜ ቴሌግራም እየከፈተችና እየዘጋች እዚያው መንደር ላይ እዚህ እዚያ ትመላለሳለች:: አባወራው ቤት መግባቱን አንኳን ልብ ያለች አትመስልም::
እማወራዋ የቤት እመቤት ናት::ባል በስራ ደክሞት ነበርና በድካሙ መሀል የሁልጊዜ የባለቤቱን ተግባር ወደኋላ ተመልሶ ማየት ጀመረ:: ቤቱን ለማቅናት የሚለፋውን ያህል ትኩረት አትሰጠውም:: ጎጆውን ለማቆም የሚጥረውን ያህል ድጋፍ አታደርግለትም:: በዚህ ሁሌም ይከፋዋል:: እቤት በሚሆንበት ጊዜ እሱን ከማውራት ይልቅ ስልክዋ ላይ አብዝታ ታተኩራለች:: ከእርሱ ጋር ከመወያየት ይልቅ በጣቷ ስልኳ ላይ ፊደል እየተየበች የምታሳልፈው ጊዜ ይበልጥባታል:: ይሄም ያበሽቀዋል:: ለአንድ ሰዓት ያህል በትኩረት ሁኔታዋን ተከታተለ:: ዞር ብላም አላየችው::
እንደደከመውና እራት እንድታቀርብለት ሲነግራት የመለሰችው መልስ ግን ይበልጥ አበሳጭቶት ቱግ አለ::ርቦኛል የሚቀመስ ካለ ለሚለው የአባወራው መማፀኛው “ፍሪጅ ውስጥ አለልህ አሙቀህ ብላ እኔ በቃኝ::” ነበር መልሷ:: ይሄን ማለፍ አልቻለም:: ከዚያ ቀን በፊት ልክ ያልሆነ ተግባሯን እያነሳ ይወቅሳትና ይገስፃት ጀመር::
ይሄኔ ተንጋላ የነበረችው ባለቤቱ ቀና ብላ ከእሷ ብሶ ተቆጣች:: በስልኳ ምክንያት የሚነሳው ሀሳብ እንደሰለቻት፣ወሬ እንደማትወድና ጭቅጭቅም እንደማትፈልግ በቁጣ ጭምር ስሜትዋን መግለፅ ያዘች:: ስልኳን ሳታይ ደቂቃዎች መቆየት እደማትችልና አባወራው ይሄን ካልወደደ ሁሉም ሊቀር እንደሚችል መናገርን መረጠች:: ይሄኔ አባወራ ተቆጣ:: “በቃ ወደ ቤተሰቤ እሄዳለው” ስትለው የተጣሉት ውል ባለው ነገር ባለመሆኑ ሁኔታዋ ግራ አጋባው:: በጉዳዩ ‹‹እናውራበት›› ቢላትም በጀ አላለችም::
ጓዳ ገብታ ልብሷን መሰብሰብ ጀመረች:: በሻንጣም አንጠልጥላ ለመውጣት በር ላይ ስትደርስ ቆም ብላ አንድ ነገር አሰበች:: አባወራ ሁኔታዋን በመገረም ይከታተላል:: እሷ ግን እግሯን ወደፊት የማያራምዳት አንድ ምክንያት ትውስ አላት:: ልትሄድበት ያሰበችው የወላጆቿ ቤት አሁን እንደምትኖርበት ቤት ዋይ ፋይ የለም:: በዳታም ቀጥታ እንዳትጠቀም ያለውን የኔትወርክ ችግር ጠንቅቃ ታውቃለች:: ከባለቤቷ ይልቅ ነጋ ጠባ የምታወራቸው የማህበራዊ ገፅ ጓደኞቿን ማጣት አሳሰባት:: ላለመሄድ ወሰነች::
ይህ ማህበራዊ ገፆች ምንያህል በእያንዳንዱ ቤት እያሳረፉ የሚገኙትን አሉታዊ ተፅዕኖ የት እንደደረሰ የሚያሳይ እውነተኛ ገጠመኝ ነው:: ምንያህል የሚጠቅመንን ትተን ከማይጠቅመን ነገር ጋር እንደተጣበቅን ማሳያም ነው:: ይህን ያህል የቆምንበትን መሰረት ስተን አየር ላይ እያንሳፈፈን የሚገኝ መጥፎ ልማድ እንዳዳበርን ጠቋሚም ነው::
ዛሬ ላይ እንዲ ሆነ እንዲህ ተባለ እያሉ በማህበራዊ ገፆች አጀንዳ የሚያቀብሉን ስራችን ካሉ ሰዎች ሁሉ በልጠውብናል:: የማህበራዊ ገፅና ሚዲያ አጠቃቀማችን ከማህበራዊ ግንኙነት አርቆን ግለኛ አድርጎናል:: አጠገባችን ያለውን ጓደኛ ወይም ቤተሰብ ከማውራት ይልቅ ስልካችንን ከፍተን ውሎና አዳራችን ከማናውቀው ጋር ሆኗል:: ነገር በዓይን ይገባል እንዲሉ ፊት ለፊት ከመወያየት ይልቅ በዚህ ዘመን አመጣሽ መረብ ከተዋወቅነው ጋር ማውራት ቀሎናል::የሚወራው መልካም ሆኖ የምንወያይበት ርዕሰ ጉዳይ እኛን የሚለውጥ አገርን የሚጠቅም ቢሆን መልካም ነበር::
ስንቶቻችን ነን የማህበራዊ ገፅ አጠቃቀማችን ላይ ገደብ አበጅተን ስርዓት ባለውና እኛን በሚጠቅም መንገድ የምንገለገለው? ቴክኖሎጂውን ተገቢ ላልሆነ ነገር የምንጠቀመውስ?:: ቴክኖሎጂውን በተገቢው መንገድ ከተገለገልንበት ይጠቅመናል:: ተገቢ ባልሆነ መንገድ ስንገለገለው ግን አቋምና መስመር እንዳይኖረን ሲያደርገን አይተናል:: በጠንካራ መሰረት ላይ የፀና ማንነት እንዳንላበስ አድርጎናል:: በህይወት ውጣ ውረድ ውስጥ የራሳችን መስመር፣ መርህና ግብ ኖሮን ያንን ለማሳካት ከመጣር ይልቅ የሰው ህልም እየመነዘሩና እየተረጎሙ መኖርን አስለምዶናል::
ከሌሎች በጎ ነገር መውሰድ አንድ ነገር ነው:: ሁሌም የሌሎችን ሀሳብ ውስጣችን ሞልተን እኛን ሆነን የቆምንበትን ማንነነት በሌሎች ሃሳብ መነጠቅ ግን አይበጀንም:: ሰው በስብዕናው ይቆም ዘንድ የራሱን መሰረት ማፅናት፤ የግሉ መርህ ሊኖረው ግድ ይላል::ያ ማንነቱ የተዛነፈ ዕለት ከሰውነት ይወርዳል:: ከራሱ የጎደለም ህልውና አይኖረውም:: ቢኖርም ኑሮው ለሌላ ነው:: ቢንቀሳቀስም ሌሎች ባሰመሩለት መስመርና አቅጣጫ ብቻ ነው::ይህ ሰው ታዲያ እራሱ ሳይሆን ህልውናውን በገዛ ፍቃዱ አስረክቦ የሚንቀሳቀስ ፍጡር ነው::
ሁሉንም ነገር በልክ ካላደረግነው ከልክ በታች ያደርገናል:: ቴክኖሎጂውን እንጠቀምበት እንጂ አይጠቀምብን:: በርካቶች መጠቀሚያ የመሆን እንጂ ተጠቃሚ የመሆን ልማድ አላዳበርንም:: በእርግጥ ማህበራዊ ገፆችን በእጅጉ የሚጠቀሙበትና እራሳቸው የለወጡበት እንዳሉ ይታወቃል:: እድሉን ተጠቅመው እራሳቸውን በተለያየ መንገድ ወደሚፈልጉት በጎ ግብ ያደረሱ በርካቶች ናቸው::
በቴክኖሎጂው መልካምነት ላይ ብዙ ሊባል ይችላል:: እዚህ ምድር ላይ ለበጎ መጠቀም ከተቻለ ሁሉም ነገር መልካም ነው:: ዓለምን ካስተሳሰሩ መልካም ነገሮችም ውስጥ አንዱም ይህ ቴክኖሎጂ ነው:: ችግሩ በምን መልክ እንገልገልበት የሚለው ላይ ነው:: ሰዎችን በአስተሳሰብና ህይወት እንዲለውጥ፣ አኗኗራቸውን እንዲያቀል እንጠቀምበት::
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2015