በመም ላይ ሩጫዎች ፈታኝ ከሆኑትና ጽናትን ከሚጠይቁ ውድድሮች መካከል የ3ሺ ሜትር መሰናክል አንዱ ነው፡፡ በዚህ ርቀት የሚወዳደሩ አትሌቶች በአጠቃላይ 28 መሰናክሎችንና 7 ውሃማ ስፍራዎችን ከሚሮጡበት ፍጥነት ጋር አጣጥመው በቴክኒክና በብልሃት ፈተናውን ማለፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ ውድድር ከዓለም ኬንያ የተሻለ ስኬትን ማስመዝገብ የቻለች አገር ብቻ ሳትሆን እንደ ባህልም አድርጋ ለበርካታ ዓመታት ዘልቃለች፡፡ ኦሊምፒክን ጨምሮ በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናዎች በሁለቱም ጾታ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብም ኬንያን የሚስተካከል የለም፡፡ በአንጻሩ በረጅም ርቀትና በማራቶን ውድድሮች የምንጊዜም ቀንደኛ ተፎካካሪዋ ኢትዮጵያ በዚህ ርቀት እምብዛም የሚነሳ ድልና ስኬት የላትም፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት በዚህ ርቀት የኢትዮጵያ የድል ብቻም ሳይሆን የተሳትፎ ታሪኳም ጠንካራ የማይባል ነበር፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ኢትዮጵያ ከተሳትፎ አልፋ በድንቅ አትልቶቿ ትልልቅ ውጤቶችን ማስመዝገብ እየቻለች ትገኛለች፡፡ በኦሊምፒክ መድረክ አንጋፋው አትሌት ሻምበል እሸቱ ቱራ በርቀቱ የነሐስ ሜዳሊያ በማስመዝገብ ፈር ቀዳጅ ቢሆንም የእሱን ፋና ተከትሎ ውጤት የሚያስመዘግብ አትሌት ለማግኘት ኢትዮጵያ በርካታ ዓመታትን ታግሳለች፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናም ይሁን በኦሊምፒክ መድረክ ከእሸቱ በኋላ በርቀቱ ለኢትዮጵያ ሜዳሊያ ያስመዘገበችው አትሌት ሶፊያ አሰፋ ናት፡፡ በዓለም ቻምፒዮና በዚህ ርቀት የሴቶች ውድድር መካሄድ የጀመረው ከወንዶቹ እጅግ ዘግይቶ እኤአ ከ2005 ሄልሲንኪ አንስቶ ነው፡፡ ሶፊያም ለአገሯ ቀዳሚ የሆነውን የነሐስ ሜዳሊያ እአአ በ2013ቱ የሞስኮ ቻምፒዮና ላይ ነበር ያስመዘገበችው፡፡ ከዚያም በፊት እኤአ በ2010 የለንደን ኦሊምፒክ የብር ሜዳሊያ ማጥለቋ አይዘነጋም፡፡
በወንዶች ረገድ በአትሌት ለሜቻ ግርማ ባለፈው የዓለም ቻምፒዮና ዶሃ ላይ የመጀመሪያውን የብር ሜዳሊያ ከተመዘገበ በኋላ ግን ኢትዮጵያ በርቀቱ በተለያዩ መድረኮች ወደ ስኬት እየተሸጋገረች ትገኛለች፡፡ ለሜቻ ከዶሃ በኋላ በቶኪዮ ኦሊምፒክም ተመሳሳይ የብር ሜዳሊያ ለማጥለቅ አልተቸገረም፡፡ በኦሪገን እየተካሄደ በሚገኘው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናም ከቀናት በፊት የብር ሜዳሊያ ከማጥለቅ ያቆመው አልነበረም፡፡
ከተጀመረ አንድ ሳምንት ያስቆጠረው የኦሪጎኑ የዓለም ቻምፒዮና ኢትዮጵያውያን በርካታ ታሪኮችን የቀየሩ ድሎችን ባለፉት ቀናት ሲያስመዘግቡ በሴቶች 3ሺ ሜትር መሰናክልም ትናንት ማለዳ በርቀቱ አዲስ ታሪክ ተመዝግቧል፡፡ ይህም በርቀቱ ኢትዮጵያ በአንድ ቻምፒዮና በሁለቱም ፆታ ሦስት ሜዳሊያዎችን እንድትሰበስብ በማድረግ ከተሳትፎ ወደ ውጤት ያሸጋገራት ሆኗል፡፡
ድንቅ ፉክክር በታየበት ውድድር ኢትዮጵያ በዓለም ቻምፒዮና በታሪክ የመጀመሪያውን የብር ሜዳሊያ በአትሌት ወርቅውሃ ጌታቸው አማካኝነት ማሳካት ችላለች፡፡ በውድድሩ የነሐስ ሜዳሊያውም በአትሌት መቅደስ አበበ የኢትዮጵያ ሆኗል፡፡ አስደናቂውን ፉክክር በድንቅ ብቃት የተወጡት ሁለቱ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከዚህ የበለጠ ታሪክ መሥራት እንደሚችሉ አሳይተዋል።
ወርቅውሃ ለጥቂት የወርቅ ሜዳሊያው ቢያመልጣትም የቻምፒዮናውና የኢትዮጵያ የርቀቱ ክብረወሰን የተሻሻለበትን እልህ አስጨራሽ ፉክክር 8:54:61 ሰዓት አጠናቃ የመጀመሪያውን ብር ማስመዝገብ ችላለች። ወርቅውሃ በቶኪዮ ኦሊምፒክ በደረሰባት መጉላላትና በውድድሩ ባለመሳተፏ ምክንያት እንደአገር ሜዳሊያ መታጣቱ ብዙዎችን ያስቆጨ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ሌላኛዋ ጀግና አትሌት መቅደስ አበበ በበኩሏ በ8:56:08 በኦሪገኑ ቻምፒዮና ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የነሐስ ሜዳሊያ ስታስመዘግብ የሶፊያ አሰፋን ክብረወሰን ተጋርታለች። በቶኪዮ ኦሊምፒክ አራተኛ ሆና ውድድሯን የፈጸመችው መቅደስ ኦሪጎን ላይ ያስመዘገበችው ሰዓት የግሏ ምርጥ ሰዓት ሆኖ ተመዝግቦላታል፡፡ ወጣቷ አትሌት እአአ 2019 በሞሮኮዋ ራባት በተካሄደው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቋ ይታወሳል፡፡
በውድድሩ ትውልደ ኬንያዊቷ የካዛኪስታን አትሌት ኖራህ ጄሩቶ በ8:53:02 ሰዓት ትንሿን የመካከለኛው ምሥራቅ አገር የወርቁ ተቋዳሽ አድርጋታለች። ያስመዘገበችው ሰዓትም በጥቂት ሰከንዶች ብቻ ዘግይቶ በርቀቱ የዓለም ሦስተኛው ፈጣን ሰዓት፤ በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ደግሞ ቀዳሚው ፈጣን ሰዓት በመሆን ተመዝግቦላታል፡፡
በዚህ ርቀት ከዚህ ቀደም እምብዛም የማይታወቁት ኢትዮጵያውያን ውጤታማ ብቻም ሳይሆኑ የርቀቱ ስኬታማና አስፈሪ ተፎካካሪ መሆናቸውን አስመስክረዋል፡፡ የወርቅ ሜዳሊያ ስላልተመዘገበ ጠንካራ ተፎካካሪ ተብሎ ይገለፅ እንጂ ኢትዮጵያውያን ከምንም ተነስተው በርቀቱ በጥቂት ዓመታት የውጤት አብዮት ላይ እንደሚገኙ በሁለቱም ፆታ የተመዘገቡ ሜዳሊያዎች ማሳያ ናቸው፡፡ በትናንት ማለዳው ውድድር ድል የቀናት ካዛኪስታናዊቷ ጄሩቶም፣ ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ከፍተኛ ስጋቷ እንደነበሩ በመግለፅ ምስክርነቷን ሰጥታለች፡፡ ‹‹ከመነሻውም የፈራኋቸው ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን ነበር፤ እነሱ ቻምፒዮኖች በመሆናቸው አስፈርተውኛል፡፡ ፉክክሩ ከባድ ቢሆንም አሸናፊ ሆኛለሁ›› በማለትም ተናግራለች፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 15/2014