በኢትዮጵያ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በየአመቱ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል። ከዚህ በተቃራኒ ግን ተመራቂ ተማሪዎቹ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ሲሠሩ አልያም በራሳቸው ሥራ ፈጥረው ሲንቀሳቀሱ አይታይም።
በተመሳሳይ ከቴክኒክና ሞያ ማሰልጠኛ ተቋማት በርካታ ተማሪዎች ቢመረቁም ተቀጥሮ ለመሥራት ወይም ሥራን በራሳቸው ለመሥራት ፈተና ሲሆንባቸው ይታያል። ሌሎች ወጣቶችም እንዲሁ ሥራ አጥተው ሲንከራተቱ፤ በየመንገድ ዳርቻው ተኮልኩለው ሲቆሙ ማየት የተለመደ ነው።
መንግሥትም ለተመራቂ ተማሪዎች ወጣቶቹ በተለያዩ መስኮች የሥራ ዕድል እፈጥራለሁ፤ ለሥራ ፈጠራም ምቹ ሁኔታ እፈጥራለሁ ሲል በተደጋጋሚ ቢደመጥም ጥቂቱን ነካው እንጂ ብዙውን አልዳሰሰውም። ለምን? በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የአግሪካልቸራል ኢንጂነሪንግ መምህር የሆኑት ኢንጂነር ዳንኤል ገብረማርያም እንደሚሉት፣ መንግሥት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚችለውን ሁሉ ያህል ያደርጋል። ሆኖም የሚያደርገው ጥረት የተቀናጀ አይደለም። ከዚህ አኳያ በቅድሚያ ወጣቶች ሥራ እንዳያገኙና በራሳቸውም ሥራ እንዳይፈጥሩ የሚያግዱ መሠረታዊ ችግሮችን መለየት ያስፈልጋል። ይህም የመፍትሄውን ሃምሳ ከመቶ ለማግኘት ያስችላል።
በቅድሚያ ለሥራ ፈጠራ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር ይገባል። በተለይ ደግሞ በአብዛኛው የሥራ ዕድል በስፋት የሚገኘውና ሥራ ፈላጊ ወጣትም በብዛት ተከማችቶ ያለው በአዲስ አበባ ከተማ በመሆኑ በሌሎች የአገሪቱ ትላልቅ ከተማዎች ላይ ለወጣቱ የሥራ ዕድል በመፍጠር መበተን ያስፈልጋል። መንግሥትም ቢሆን ወጣቶች ባሉበት በየማዕከሉና በየከተሞች እንዲቆዩ በማድረግ በእሴት ሰንሰለት ገበሬው እንዲጠቀም የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ማሟላት ይጠበቅበታል።
ሁሉም ወጣት ሥራ ፈጣሪ መሆን ስለማይችል መንግሥት በቅድሚያ ያለውን ሀብት ቆጥሮ ማወቅ አለበት። በመቀጠል ደግሞ ሀብቱን ለማን ነው የምሰጠው? ማነውስ ችግረኛ? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ይኖርበታል። የሥራ ፈጠራና ጥቃቅንና አነስተኛ ሥነ ምህዳሩን ማመቻቸት ብሎም በዚህ ረገድ ወጣቶች የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያመጡ መሥራት አለበት። ለአብነት የአገር ውስጥ ምርት መጠቀም ላይ ብዙ ሊሠራ ይገባል።
ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ከፖሊሲና ስትራቴጂ አንፃር ያሉ ችግሮችንም መፈተሽና ለችግሮቹ መፍትሄ ማበጀት ይጠበቅበታል። ለውጦች ያሉ ቢሆንም አሁንም ለወጣቱ እንቅፋት የሆኑና በመንግሥት ተቋማት በኩል የሚታዩ ውጣውረዶችን ማስተካከል ይኖርበታል።
መምህሩ እንደሚሉት በአገሪቱ በየዓመቱ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ተማሪዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው። አብዛኛው ተመራቂ ተማሪ መቀጠር የሚፈልገውም ከወረዳ እስከላይኛው መዋቅር ስር ባሉ የመንግሥት የሲቪል ሰርቪስ መስሪያ ቤቶች ውስጥ ነው እንጂ በራሱ ሥራ መፍጠር የሚፈልግ የለም።
በንድፈ ሀሳብ የተማሩትን ትምህርት በተግባር የሚያሳዩበት አጋጣሚና የሥራ ላይ ስልጠና ባለመኖሩ ወጣቶቹ በመንግሥት የሲቪል ሰርቪስ መስሪያቤቶች ውስጥ መቀጠር ቢፈልጉ አያስደንቅም። በዚህ አጋጣሚ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ወጣቶቹ ገና ከዩኒቨርሲቲ ሳይወጡ የሥራውን ዓለም በሚመለከት ስልጠናና የግንዛቤ ማስጨበጫ የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይኖርበታል።
በመቀጠል ደግሞ በተማሩበት የትምህርት ሞያ ያሉትን የሥራ ዕድሎች መለየትና በእነዚህ የሥራ መስኮች ውስጥ ወጣቶቹ ገብተው እንዲሠሩ ማድረግ አለበት። ይህም ጥቃቅንና አነስተኛ የሥራ መስኮችን የሚያካትትና በቀጣይ ለሚሠማሩበት የሥራ ዘርፍ እንደመነሻ ሆኖ የሚያገለግልና ሌሎች የሥራ መስኮችን ለማየት ዕድል የሚፈጥርላቸው ነው።
ወጣቶቹ በአነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማት አማካኝነት የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙበትን ሁኔታም ማመቻቸት ያስፈልጋል። የግል ባንኮችም ለአዳዲስ የዩኒቨርሲቲ ተመራቂና አዳዲስ የቢዝነስ ሀሳብ ይዘው ለሚመጡ ወጣቶች የብድር አገልግሎት የሚያገኙበትን መንገድ መቀየስ ይኖርባቸዋል። መንግሥትም የግል ባንኮችን ጨምሮ ከሌሎች አነስተኛና ጥቃቅን የፋይናንስ ተቋማት ጋር በቅንጅት ሊሠራ ይገባል።
መንግሥት ለወጣቶቹ ከፋይናንስ ጀምሮ እያንዳንዱን ሀብት ቆጥሮ በመስጠትና በውድድር ላይ የተመሠረተ ሥራ እንዲያከናውኑ በማድረግ የራሳቸውን ሥራ እንዲፈጥሩ ማድረግ ይችላል። የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የጀመረው ውድድር ተኮር ፈንድም ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። ያለውን ውስን ሀብት ወድድር ተኮር ባደረገ መልኩ ማቅረብም ይቻላል። የኢትዮጵያ ልማት ባንክም ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው። የመንግሥት ጥቃቅንና አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማትም ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ ከቴክኒክና ትምህርት ስልጠና ተቋም ጋር በደንብ ተሳስረው ሊሠሩ ይገባል።
በብሩህማይንድስ አማካሪ ድርጅት ከፍተኛ የፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ለማወርቅ ዴክሲሶ በበኩላቸው እንደሚገልፁት፤ድርጅቱ ወጣቶች በተለይ በአምራች ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ከኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ጋር የጋራ ስምምነት ሰነድ ተፈራርሟል። የዚህ ስምምነት ዋነኛ አላማም ሁለቱ ተቋማት በተባበረና በተቀናጀ መልኩ በጋራ በመሥራት ወጣቶች ሥራ እንዲፈጥሩ ማስቻል ነው።
ተቀናጅቶና ተባብሮ መሥራት ሲባል ታዲያ የመንግሥት ተቋማት ከግሉ ዘርፍ፣ የመንግሥት ተቋማት ከዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ጋር፤ የመንግሥት አካላት ከሌሎች የልማት አጋሮች ጋር ተናበውና ተቀናጅተው መሥራት መቻል ነው። ሆኖም በዚህ መልኩ መሥራት ካልተቻለ አሁን የሚታየውን የልማት ተግዳሮት መቅረፍ አይቻልም። ከዚህ አንፃር ትብብሩና ትስስሩ ወሳኝ ነው።
በአሁኑ ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበሩ ካሉ እንቅስቃሴዎች ውስጥም አንዱ የግልና የመንግሥት አጋርነት ሲሆን ብሩህማይንድስ ከኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ጋር ያደረገው ስምምነትም የዚህ ማሳያ ነው። ይህም አብሮ በጋራ ተቀናጅቶ በመሥራት ብሩህማይንድስ ጋር ያለውን ባለሞያና ሞያዊ ድጋፍ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ከያዘው ግብ ጋር በማናበብ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተንቀሳቀሱና አዳዲስ እየተመሠረቱ ያሉ አምራች ኢንተርፕራይዞች የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። የሥራ ዕድል ፈጠራ መሠረቱንም እንዲሰፋ ያደርገዋል። በየዘርፉ ያሉ አቅሞችን በሚገባ ለመጠቀምም ያግዛል።
ብሩህማይንድስ የቢዝነስና ማህበራዊ አማካሪ ድርጅት በዚህ ስምምነት ሥራዎችን የማመቻቸት፣ የቢዝነስ ማበልፀጊያ ድጋፎችን የማድረግ፣ ለኢንተርፕራይዞች አስፈላጊ የሞያና ሞያ ነክ ልምድ ድጋፎችን የማድረግ፣ ስልጠናዎችን የማመቻቸት ድርሻ ይኖረዋል።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ብሩ ወልዴ እንደሚናገሩት፤ በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ዙሪያ በቅንጅት ለመሥራት በተለያዩ መድረኮች ላይ የተለያዩ ሃሳቦች ይነሳሉ። በቅንጅት ለመሥራት ከባለድርሻ አካላት ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ደግሞ የግሉ ዘርፍ ነው። በተለይ አማካሪዎች በግሉ ዘርፍ ላይ የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ ነው። ከዚህ አንፃር የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና የግሉ ዘርፍ ወጣቶች በሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በቅንጅት ሊሠሩ ይገባል።
እንደአገር በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትልቅ የቤት ሥራ አለ። በርካታ ወጣቶችም የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ይፈልጋሉ። አገሪቷም በርካታ የሚሠራ ወጣት የሰው ኃይል ያለባት ናት። የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት እንዲያከናውነው ከተሰጠው ሥራ ውስጥ አንዱና ዋነኛውም የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ነው።
ይህ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚጀምረው ከጥቃቅንና አነስተኛ ደረጃ ሲሆን ይህ ደረጃ አነስተኛ ቢዝነስን ለመጀመር ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ። ወደሥራ በሚገባበት ጊዜም ሥራን ላልለመደ አካል ቢዝነስ የሚጀምርበት አካባቢ ምህዳሩ በጣም ቀላል መሆንም ይጠበቅበታል። ይህንን የማመቻት ሁኔታ መንግሥት ብቻ ሊወጣው ስለማይችል የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሊሳተፉ ይገባል።
ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚሉት በዚህ አመት በርካታ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው ይወጣሉ። ከተመረቁ ደግሞ ወደ ሥራ መግባት ይጠበቅባቸዋል። የመንግሥትን ሥራ ብቻም መጠበቅ የለባቸውም። ከዩኒቨርሲቲ የተማሩትን እውቀት ይዘው በራሳቸው ሃሳብ ወደ ሥራ መግባት ይኖርባቸዋል። በዚህ ላይ የኢንተርፕሪነርሺፕ ስልጠና ከተለያዩ ባለድርደሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ተቋሙ ይሰጣል። ለዚህም ከብሩህማይንድስ ኮንሰልት ጋር የጋራ ስምምነት ሰነድ ተፈራርሟል።
ከዚሁ በተጓዳኝ ተቋሙ የንግድ ልማት አገልግሎቱ ላይ እንዴት ቢዝነስ እንደሚጀመርና ንግዱ እንዴት መካሄድ እንደሚችል የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ሰርቪስ ያካተተ አገልግሎት ይሰጣል። ይህም ወጣቶች የሚሳተፉባቸው የአምራች ኢንተርፕራይዞችን ተወዳዳሪነት ያሳድጋል።
ይህም ተወዳዳሪነት በአገር ውስጥ በሚመረቱና ወደ ውጭ አገር በሚላኩ ምርቶች ይለካል። ውጣውረዶችን መቋቋም ችለው ከጥቃቅን ወደ አነስተኛ፣ ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ፣ ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ እንዲሸጋገሩም ያስችላቸዋል። ከዚህ አንፃር የወጣቱን ሕይወት በመቀየር ላይ አስተዋፅኦ ከሚያደርጉ የልማት ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያ በበርካታ መልኩ ትልቅ እምቅ ሀብት ያላት አገር ናት። ይህም ለሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ምቹ ነው። ኢንተርፕሪነርሺፕ የሚያተኩረው ደግሞ በአካባቢው ባለው ሀብት ላይ ነው። አማራጭ ጥሬ ዕቃዎችን በመጠቀም ምርቶችን ለማምረት ለሥራ ፈጣሪዎች በእጅጉ ይረዳል። ከዚህ አንፃር ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ይዘው ወደሥራ የሚገቡ ከሆነ ፋይናንስ ያስፈልጋቸዋል።
ከዚህ አኳያም በተለይ በሊዝ ፋይናንሲንግ በአገሪቱ ትልቁን ድርሻ እየተወጣ ያለው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ነው። በዚህ አሠራርም ሥራ ፈጣሪዎች 20 ከመቶ የማሽን ግዢ ሸፍነው ቀሪውን በኮንትራት ከፍለው ማሽኑን የግላቸው የሚያደርጉበት አሠራር በመሆኑ ሊበረታታና ሊሰፋ ይገባል።
በሌላ በኩል ደግሞ ሥራ ማስኬጂያ ላይ ብድሩን በቀላሉ የሚያገኙበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ የግል ባንኮችም ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ብድር በልዩ ሁኔታ ማመቻቸት ይገባቸዋል።
ለዚህም በቅርቡ ፓርሺያል ኮላተራል የሚባልና ከዓለም ባንክ ጋር በመነጋገር የተለየ ሃሳብ ይዘው የሚመጡ /Idia financing/፤ በተለይ ወደውጭ ምርቶችን ለመላክ የሚያተኩሩ ወጣቶች 50 ከመቶ የኮላተራል ሪስክ በሚመደብ ሀብት እንዲወስዱ የማድረግ አሠራር በቅርቡ ይጀመራል። ይህም ሥራ ፈጣሪዎችን ያበረታታል። በፋይናንስ ተቋማት በኩል ያሉ የብድር ቅድመ ሁኔታዎችና ውጣ ውረዶችም ሊስተካከሉ ይገባል። የወጣቶችን አቅምና ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘቡም መሆን ይጠበቅባቸዋል።
ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ለሚወጡና ወደ አምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ መቀላቀል ለሚፈልጉ ወጣቶች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደሮች ጋር በጋራ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ይገኛል። ንድፈሃሳብ የተማሩትን ወደ ተግባር ትምህርት ለማምጣት ለየት ያለና የ2014 ዓ.ም እቅድ ተዘጋጅቷል። ገና ከዩኒቨርሲቲ ሳይመረቁ ለየት ያለና ሃሳብ ያላቸውንና ፈጣሪ የሆኑ ወጣቶችን ፍላጎትን መሠረት ያደረገ ድጋፍ ለማደረግም ጥረት እየተደረገ ነው።
ይህም ሥራ የሚከናወኑ ከተቋሙ ከሚሠሩ የልማት አጋሮች ጋር በመተባበር ሲሆን፣ ተማሪዎቹ ገና ከዩኒቨርሲቲ ሳይመረቁ እዚያው ሆነው ተጓዳኝ የሞያ ስልጠናዎችን እንዲወስዱ እየተደረገ ይገኛል። ከተመረቁ በኋላ ደግሞ ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደሮች ጋር በመነጋገር የሚጀመሩ ሥራዎች ይኖራሉ።
ብሩህማይንድስና የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ሰነድ ተፈራርመዋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 15/2014