የወንዶች 10ሺ ሜትር የአለም ቻምፒዮና ድል ከ11 አመታት በኋላም ወደ ቤቱ መመለስ አልቻለም። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በጀግኖቹ አትሌቶች ኃይሌ ገብረስላሴና ቀነኒሳ በቀለ ተከታታይ አራት ቻምፒዮናዎች የበላይነት ተይዞ የቆየው የርቀቱ የበላይነት እኤአ በ2011 የዴጉ ቻምፒዮናም ባልተጠበቀው ድንቅ አትሌት ኢብራሂም ጀይላን ቀጥሎ ነበር። ኢብራሂም አለም ምንጊዜም በማይረሳው ድንቅ የአጨራረስ ብቃት እንግሊዛዊውን አትሌት ሞ ፋራህን ካሸነፈ ወዲህ ግን ኢትዮጵያውያን ባለፉት አራት ቻምፒዮናዎች የርቀቱን ክብር ደግመው ወደ ቤቱ ማምጣት አልቻሉም።
በኦሪገን እየተካሄደ በሚገኘው የአለም ቻምፒዮና ኢትዮጵያ በርቀቱ ካሏት ድንቅ ድንቅ አትሌቶች አኳያ ለአምስተኛ ጊዜ ድሉ ከእጃቸው ይወጣል ብሎ የገመተ አልነበረም። በተለይም ከአመት በፊት በቶኪዮ ኦሊምፒክ በርቀቱ አስደናቂ ብቃት አሳይቶ ወርቅ ያጠለቀው ወጣቱ ባለተሰጥኦ አትሌት ሰለሞን ባረጋ በዚህ የአለም ቻምፒዮና ድሉን ይደግማል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት ነበር። ይሁን እንጂ በርቀቱ አስፈሪ ተፎካካሪ ከመሆን አልፈው ውጤታማ እየሆኑ የሚገኙት ዩጋንዳውያን አትሌቶች የኢትዮጵያውያኑን ተስፋ ከንቱ አድርገውታል። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተሻለ አቅምና ብቃት እያላቸው በብዙ ምክንያቶች ድሉን ማሳካት አለመቻላቸውም እየተመዘገበ ከሚገኘው አስደናቂ ውጤት ጎን ለጎን ብዙዎችን አስቆጭቷል።
በአንጻሩ በቶኪዮ ኦሊምፒክ በርቀቱ የገጠማቸውን ሽንፈት መርምረውና ድክመቶቻቸውን አርመው የመጡት ዩጋንዳውያን ጠንካራ ስራቸው በውጤት ክሷቸዋል፣የዘሩትንም አጭደዋል። ለሁለተኛ ጊዜ የርቀቱ ቻምፒዮን መሆኑን ባለፈው እሁድ ምሽት ኦሪገን ላይ ያረጋገጠው የርቀቱ ባለክብረወሰን ዩጋንዳዊው ጆሽዋ ቺፕቴጌ በአገሩ ልጆች ጠንካራ የቡድን ስራ ታግዞ በኦሊምፒክ የነበረውን ስህተት አርሞና በታክቲክ በስሎ ለድል በቅቷል።
ዩጋንዳውያን ከቶኪዮ ኦሊምፒክ በኋላ አመቱን ሙሉ ከሌሎች ውድድሮች ታቅበው በራቸውን በመዝጋት ሲዘጋጁ ቆይተዋል። ቶኪዮ ላይ የነበራቸውን የታክቲክ ድክመት በተንቀሳቃሽ ምስል ደጋግመው በማጤን ክፍተቶችን ለመሙላት ጠንካራ ስራ ሰርተዋል። ይህንን ጥረትም በቡድን ስራ አጅበውት ታይተዋል። በአንጻሩ ኢትዮጵያውያን ደካማ የቡድን ስራና ከልክ ያለፈ በራስ መተማመን ወይም ለተፎካካሪያቸው የሰጡት አነስተኛ ግምት ዋጋ አስከፍሏቸዋል።
ዩጋንዳውያኑ የነበረባቸው ድክመት ላይ ጠንካራ ስራ ሰርተው እንደሚመጡ ኢትዮጵያውያኑ አሰልጣኞችም ሆኑ አትሌቶቹ ከግምት በማስገባት ዝግጅታቸውን በዚያ መልኩ ማድረግ ነበረባቸው። ይህ ግን አልሆነም። ዩጋንዳውያን በተለይም ቻምፒዮኑ ጆሽዋ ቺፕቴጌ ቶኪዮ ላይ የነበረውን ድክመት ከማረም ባሻገር ብቃቱን አሳድጎ ተገኝቷል። ኢትዮጵያውያኑ በተለይም ሰለሞን ግን ቶኪዮ ላይ የነበረውን ብቃት አሳድጎ አልታየም። ይህም ድክመት ውድድሩ ላይ ዩጋንዳዎች መጠንከራቸው ከታወቀ ወደ ታክቲክ ፍልሚያ ተቀይሮ ኢትዮጵያውያኑን ለድል የማብቃት እድሉ ጠባብ አልነበረም። ሆኖም ኢትዮጵያውያን ቶኪዮ ላይ ይዘው የቀረቡትን ተመሳሳይ ታክቲክ ኦሪገን ላይ መድገማቸው ወርቁ ቢቀር ቢያንስ ሜዳሊያ ውስጥ መግባት የሚችሉበትን እድል አምክኗል። ዩጋንዳዎች ደግሞ ኢትዮጵያውያኑ ቶኪዮ ላይ ለተጠቀሙት ታክቲክ ጊዜ ሰጥተው ተዘጋጅተውበታል። በአንድ ውድድር ላይ የተገበሩትን ታክቲክ በሌላኛው ላይ መቀየር ለተፎካካሪ ተገማች እንደማያደርግ ሁሉ ወቅታዊ ብቃቱ የተሻለ የሆነን አትሌት እቅድ ማምከን እንደሚችል ለማንም ግልጽ ነው። ለዚህም ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በአትላንታና ሲድኒ ኦሊምፒኮች የተሻለ ወቅታዊ ብቃት የነበረውን ኬንያዊ ኮከብ አትሌት ፖል ቴርጋትን እንዴት ታክቲክ በመቀያየር ማሸነፍ እንደቻለ ማስታወስ በቂ ነው።
ያም ሆኖ በተለይም የኦሊምፒክ ቻምፒዮኑ ሰለሞን ከአለም የሁለት ጊዜ የ5ሺ ሜትር ቻምፒዮኑ ሙክታር ኢድሪስ፣ዮሚፍ ቀጄልቻ፣ በሪሁ አረጋዊና ጥላሁን ሀይሌ ጋር አስፈሪውን የዩጋንዳውያን ጥምረት የመገርሰስና የ10ሺ ሜትሩን ቁጭት በ5ሺ ሜትር ወርቅ የመካስ እድሉ አሁንም በእጃቸው ይገኛል።
ቺፕቴጌ ኦሊምፒክ ላይ በ10ሺ ሜትር የደረሰበትን ሽንፈት እዚያው ኦሊምፒክ ላይ በ5ሺ ሜትር አሸንፎ ቁጭቱን እንደተወጣው ሁሉ ሰለሞንም ተመሳሳይ ስሜት ውስጥ ይገኛል። ይህን ቁጭት ለመወጣትም ኢትዮጵያውያኑ ከሌሎች አገራት በተለየ አራት አትሌቶች ስለሚሳተፉ የቁጥር ብልጫቸውን በቡድን ስራው መጠቀም ይገባቸዋል። ያለፉት ሁለት ቻምፒዮናዎች አሸናፊው ሙክታር ኢድሪስ በቡድኑ ውስጥ መኖሩም ለኢትዮጵያውያኑ የስነልቦና የበላይነት የሚጫወተው ሚና ቀላል እንደማይሆን ይታመናል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 14 ቀን 2014 ዓ.ም