በአትሌቶች ዘንድ ትልቅ ከበሬታና ቦታ ከሚሰጣቸው ውድድሮች መካከል የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና አንዱ ነው። ጠንካራ ፉክክር በሚደረግበት በዚህ ውድድር ሌሎችን ረትቶ ለራስና ለሃገር ውጤት ማስመዝገብ ደግሞ ከሜዳሊያም በላይ የሆነ ከበሬታን ያስገኛል። በዚህ የተካኑት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶችም የሃገራቸውን ስም በድል ሲያስጠሩ ባንዲራዋንም ከሌሎች በላይ ሲያውለበልቡ ዘመናትን ተሻግረዋል።
ከተጀመረ ዛሬ ስድስተኛ ቀኑን ባስቆጠረው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናም የኢትዮጵያውያን የተለመደ ድል በተለያዩ ርቀቶች ቀጥሏል። ኢትዮጵያ እስካሁን በሰበሰበቻቸው ሜዳሊያዎች ብዛት አዘጋጇን ሃገር አሜሪካንን ተከትላ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጧት ሁለት የብር ሜዳሊያዎችም ትናንት የማለዳ ብስራት ሆነዋል። የወንዶች 3ሺ ሜትር መሰናክል እና 1ሺ500 ሜትር የሴቶች ውድድር ሜዳሊያዎቹ የተገኙባቸው ርቀቶች ናቸው።
አስቀድሞ በተካሄደው የ3ሺ ሜትር መሰናክል ቅድሚያ ግምት እንደተሰጠው ሁሉ የአሸናፊነት ፉክክሩ በሰሜን እና ምስራቅ አፍሪካዊያን አትሌቶች መካከል አይሎ ነበር። በዚህ ውድድር በርቀቱ ለረጅም ዓመታት የበላይነቱን ይዘው የቆዩት ኬንያዊያን አትሌቶችም ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ቢጠበቅም የአሸናፊነት ግምቱ ግን የኦሊምፒክ ቻምፒዮኑ ሞሮኳዊው ሶፊያን ኤል ባካሊ እና በተፎካካሪው የኦሊምፒክ የብር ሜዳሊያ ባለቤት ለሜቻ ግርማ መካከል እንደሚቀር ይጠበቅ ነበር። ጌትነት ዋለ እና ኃይለማርያም አማረም በኢትዮጵያ በኩል የውድድሩ ፈተናዎችና የሜዳሊያ ሯጮች እንደሚሆኑም ተገምቶ ነበር።
ብርቱ ፉክክር በታየበት በዚህ ውድድርም ተጠባቂው ባካሊ ርቀቱ 200 ሜትር ሲቀረው አፈትልኮ በመውጣት አሳማኝ በሆነ ብቃት ሲያሸንፍ፤ ኢትዮጵያዊው አትሌት ለሜቻ ደግሞ የብር ሜዳሊያውን አጥልቋል። በዶሃ የዓለም ቻምፒዮና፣ በቶኪዮ ኦሊምፒክ እንዲሁም በቤልግሬዱ የቤት ውስጥ የዓለም ቻምፒዮና የብር ሜዳሊያዎችን የሰበሰበው ለሜቻ (ሌላኛው ሲልቨር ማን) በኦሪገንም ሁለተኛ በመሆን የብር ሜዳሊያ ለሃገሩ አበርክቷል። ከውድድሩ አስቀድሞ በነበረው የዝግጅት ጊዜ የወርቅ ሜዳሊያውን ለማጥለቅ በቁጭት ወደ ስፍራው እንደሚጓዝ አሳውቆ የነበረው ለሜቻ፤ ከውድድሩ በኋላም ሌላ ቁጭት ላይ መሆኑን አንጸባርቋል።
ከሩጫው በኋላ ከዓለም አትሌቲክስ ድረገጽ ጋር በነበረው ቆይታም ‹‹በጣም ዝግ ያለሩጫ ስለነበር የአሯሯጥ ስልቴን ለመቀየር ብሞክርም እንደፈለኩት እንዳልሮጥ ገድቦኛል። ይኸውም ወርቁን የግሌ እንዳይሆን አድርጓል። በቀጣይ ግን የወርቅ ሜዳሊያው የኔ ነው፤ ዝግጅቴም ከአሁን ይጀምራል›› ማለቱን አስነብቧል።
በንፋሳማ የአየር ሁኔታ በተካሄደው ውድድር ከፍተኛ ፉክክር ሲያደርግ የታየው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ጌትነት ዋለም ብርቱ ተፎካካሪነቱን አስመስክሯል። ጌትነት ከሞሮኳዊው አትሌት አሸናፊነቱን ሊቀማ የሚችልበትን አቅም እስከመጨረሻው ዙር አሳይቷል። ይሁንና ርቀቱ ሊጠናቀቅ ጥቂት ሜትሮች መሰናክሉን ሲዘል በሰራው ስህተት ወደ ኋላ በመቅረቱ አራተኛ ደረጃን ይዞ ዲፕሎማ ተሸላሚነት ሊያጠናቅቅ ችሏል። ኬንያዊው አትሌት ኮንሴስለስ ሊፕሩቶ ደግሞ ሶስተኛ በመሆን የነሃስ ሜዳሊያው ለሃገሩ አስገኝቷል።
በተከታይነት የተካሄደው ሌላኛው የፍጻሜ ውድድር የሴቶች 1ሺ500ሜትር ውድድር ሲሆን፤ በዚህም የብር ሜዳሊያው የኢትዮጵያ ሆኗል። ከመነሻው ጥቂት አትሌቶች ከፊት ቀድመው በመውጣት ባከረሩት በዚህ ውድድር በዓለም ቻምፒዮና ታሪክ እጅግ ስኬታማዋ አትሌት ኬንያዊቷ ፌዝ ኪፕዬጎን ሌላኛውን ስኬቷን አስመዝግባለች። በቤልግሬድ የቤት ውስጥ ቻምፒዮና በርቀቱ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የነበረችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ ደግሞ ለሃገሯ ሶስተኛውን የብር ሜዳሊያ ልታስቆጥር ችላለች። አትሌቷ ከኬንያዊቷ ጋር ብርቱ ፉክክክር እስከመጨረሻው ስታደርግ ብትቆይም እንዳሰበችው የወርቅ ሜዳሊያውን ግን የግሏ ለማድረግ አልታደለችም።
የዩጂን እና የዶሃ የነሃስና የብር ሜዳሊያ ባለቤቷ ጉዳፍ በዚህ የውድድር መድረክም ሶስተኛውን ሜዳሊያዋን አግኝታለች። ከውድድሩ መጠናቀቅ በኋላም ‹‹ከዚህ ውድድር የተሻለ ውጤት እጠብቅ ነበር፤ ይሁንና ተፎካካሪዬ የተሻለ ልምድ ያላትና እድለኛም ነበረች። የብር ሜዳሊያ በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ›› ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች። አትሌቷ በ5ሺ ሜትር ውድድርም ተካፋይ መሆኗ ይታወቃል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 13/2014