– ተመራጮቹም ሕዝበ ሙስሊሙን ለሰላምና ለልማት በማስተባበር እንደሚሠሩ ገለጹ
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የጠቅላላ ጉባዔ እና የሥራ አስፈጻሚ አባላትን ትናንት መርጧል። ጠቅላይ ምክር ቤቱ ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋን በፕሬዚዳንት፣ ሼህ አብዱልከሪም ሼህ በድረዲን እና ሼህ አብዱልዐዚዝ አብዱልወሌን በምክትል ፕሬዚዳንትነት እንዲሁም ሼህ ሀሚድ ሙሳን በዋና ፀሐፊነት መርጧል። ተመራጮቹም ሕዝብ ሙስሊሙን ለሰላምና ለልማት በአንድነት በማስተባበር እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
ከቀድሞው የምክር
ቤቱ አመራሮች
ጋር የቁልፍ
ርክክብ በተደረገበት
ወቅት አዲሱ
የኢትዮጵያ እስልምና
ጉዳዮች ጠቅላይ
ምክር ቤት
ፕሬዚዳንት ሼህ
ሐጂ ኢብራሂም
ቱፋ፤ የሕዝብ
ሙስሊሙን አንድነትን
በማጠናከር ሕዝቡ
ለሰላምና ለልማት
እንዲተባበር እንሠራለን
ብለዋል።
ሰላምና ልማት ወሳኝ ጉዳዮቻችን ናቸው ያሉት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም፤ በዚህ ረገድ ሳንከፋፈል አንድነታችንን ጠብቀን መጓዝ ይኖርብናል። አዲሱን ኃላፊነት ስንረከብ በመፈቃቀርና በመከባበር ላይ በተመሠረተ አግባብ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል። ተለያይተን ሳይሆን ተቀራርበን ለመጓዝ ዝግጁ ነን። በሥራ ዘመናችን ለመላው ሙስሊም ኅብረተሰብና ለሰላም ወዳድ ኢትዮጵያውያን በቻልነው ሁሉ በጎውን ለማድረግ ጥረት እናደርጋለን ብለዋል።
በይፋ ሥራ መጀመራችንን ስናበስር በታላቅ ደስታ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በቀሪው ዘመናችን አንድነታችንን አጠናክረን የተሳካ ጊዜ እንደምናሳልፍ ዕምነት አለኝ ሲሉ ተናግረዋል። በምክትል ፕሬዚዳንትነት የተመረጡት ሼህ አብዱልከሪም ሼህ በድረዲን በበኩላቸው፤ ከሁሉ በፊት ቅድሚያ የምንሰጠው ለአገራችን ሰላም ነው። በሰላም ጉዳይ ላይ አንደራደርም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዲጠናከር አቅም በፈቀደው ሁሉ ጥረት እናደርጋለን፤ ለዚህም ጥረታችን ሕዝብ ሙስሊሙም ሆነ መላው ሕዝብ ከጎናችን እንደሚቆም አንጠራጠርም ሲሉ ተናግረዋል።
ሃብታሙም ደሃውም ፣ ወንዱም ሆነ ሴቱ ማኅበረሰብ ለልማቱም ሆነ ለሰላሙ መረጋገጥ ግንባር ቀደም ሆኖ መገኘት አለበት ያሉት ሼህ አብዱልከሪም፤ የጠቅላይ ምክር ቤቱ አመራሮችም ለዚሁ ተግባር ግንባር ቀደም ሆነው ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። መኮራረፍን ሳይሆን መግባባትንና አንድነትን ነው የምንፈልገው። በዚህ አግባብ ችግሮች ቢኖሩ እንኳን ሁሉም ሳይገፋፋ በሰላማዊ መንገድ ችግሮችን የሚፈቱበትን መንገድ እናመቻቻለን ብለዋል።
በመሆኑም ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ለጋራ ሰላሙ እጅ ለእጅ ተያይዞ ከምክር ቤቱ ጎን ሊሠራ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። በጉባዔው የተመረጡ አመራሮችና 14 የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት መጅሊሱን እንደሚመሩ ታውቋል።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12 ቀን 2014 ዓ.ም