ኬንያውያን እድሜልካቸውን የሚቆጩበት የአትሌቲክስ ውጤት ቢኖር እኤአ በ2000 ሲድኒ ኦሊምፒክ ላይ በ10ሺ ሜትር የገጠማቸው ሽንፈት ነው። በወቅቱ ድንቅ አቋም ላይ የነበረው ታሪካዊው አትሌት ፖል ቴርጋት ከአራት ዓመት በፊት በአታላንታ ኦሊምፒክ በጀግናው አትሌት ሃይሌገብረስላሴ የደረሰበትን ሽንፈት ለመካስ ከቡድን አጋሮቹ ጋር የተለየ ታክቲክ በውድድሩ ላይ ተገበረ።
የእግሮቹ ጣቶች እየደሙ ከነጉዳቱ ለአገሩ ክብር ለመዋደቅ የግዱን ወደ ውድድር የገባው ሃይሌም የዋዛ አልነበረም። ከአራት ዓመት በፊት ሲያሸንፍ የተጠቀመውን ታክቲክ ቀይሮ ሲድኒ ላይ በድንቅ አጨራረስ ብቃት ወርቁን ከቴርጋት መንጋጋ ፈልቅቆ ለራሱ አጠለቀው።
የሁለቱ ድንቅ አትሌቶች የመጨረሻ ትንቅንቅ በርቀቱ ዓለም ከዚያ በፊት ተመልክቶት አያውቅም ነበረና ትንፋሽን ቀጥ የሚያደርገውን ፉክክር በእግሮቹ ጥፍር ቆሞ ነበር የተመለከተው። ይህም ታሪካዊ ውድድር ለኢትዮጵያውያን አስጨናቂና በመጨረሻ ሃሴት የፈጠረ ሆነ።
በአንጻሩ ለኬንያውያን በእጃቸው የገባውን ወርቅ የመነጠቅ ያህል ስሜት የ0.9 ማይክሮ ሰከንዶች ልዩነት የፈጠሩት ዘመን ተሻጋሪ ቁጭት ጥሎ አለፈ። ኬንያ የበርካታ ጠንካራና ኮከብ አትሌቶች ባለቤት ነች። ኢትዮጵያ ግን ከዚያም የበለጠ የአልሸነፍ ባዮችና በታላላቅ መድረኮች ነጥረው የሚወጡ ፈርጦች ባለቤት ናት።
ይህም በኦሪገን እየተካሄደ በሚገኘው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በተመሳሳይ ርቀት ታሪክ ራሱን ደግሞ የዓለም ሕዝብ ሊያየው ችሏል። ከትናንት በስቲያ ምሽት ይህ ታሪክ በሴቶች 10 ሺ ሜትር ሲደገም ወጣቷ ኢትዮጵያዊት ኮከብ ለተሰንበት ግደይ ለኬንያውያን ሌላ የሚቆጩበት ታሪክ አኑራ ወርቁን በሽርፍራፊ ሰከንዶች ተአምር ለማጥለቅ በቅታለች።
ባለፈው የዶሃ 2019 የዓለም ቻምፒዮና እንዲሁም በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በልምድ ማነስና በጥቃቅን የታክቲክ ስህተቶች አቅሙና ብቃቱ እያላት ወርቅ ማጥለቅ ያልቻለችው ለተሰንበት በእለተሰንበት አጥቢያ ኦሪገን ላይ ስህተቶቿን አርማና የአጨራረስ ጉድለቷን ሞልታ የተለየች አትሌት ሆና ቀርባለች።
ባለፉት ዓመታት እየተዳከመ የመጣው የኢትዮጵያውያን አትሌቶች የቡድን ሥራ ላይ ሌላኛዋ ወጣት አትሌት እጅጋየሁ ታዬ ነብስ በዘራችበትና ለወርቁ መመዝገብ የአንበሳውን ድርሻ በተወጣችበት ድንቅ ምሽት ለተሰንበት ባለፉት ሁለት ታላላቅ ውድድሮች ያጣችውን ወርቅ ማጥለቅ ችላለች።
በእነዚያ ውድድሮች ወርቁን የነጠቀቻት ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድስ አትሌት ሲፈን ሃሰን ምንም መፍጠር ባልቻለችበት ፉክክር የርቀቱ የ2015 ቻምፒዮን ኬንያዊቷ ሄለን ኦቢሪ በሲድኒ ኦሊምፒክ ሃይሌ ቴርጋት ላይ የተቀዳጀውን አይነት ድል ለመስራት ተቃርባ ነበር።
ይሁን እንጂ የርቀቱ የክብረወሰን ባለቤት ለተሰንበት ይህ እንዲሆን አልፈቀደችም። ጥርሷን ነክሳና እንደ ሃይሌ አንገቷን አስቀድማ 30:09:94 በሆነ ሰዓት ኬንያውያንን ለሌላ ቁጭት ዳረገች።
ኦቢሪ 30:10:02 በመግባት የብር ሜዳሊያውን ስትወስድ ሌላኛዋ ኬንያዊት ማርጋሬት ቼሊሞ 30:10:07 በሆነ ሰአት ነሐሱን አጥልቃለች።ይህም በርቀቱ ከሃይሌና ቴርጋት ትንቅንቅ በኋላ እጅግ አጓጊው ፉክክር ሲሆን በሴቶች ደግሞ በታሪክ የመጀመሪያው ሊሆን ችሏል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2014