ፈረንጆቹ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ዝናን ለመግለጽ‹‹15 minutes of fame›› የሚል ብሂል አላቸው። ፌስቡክ ለዚህ የሚሆን አደባባይ ነው። ማንም ሰው ከመሬት ተነስቶ ለጥቂት ሰዓታት፤ ቀናት ፤ ሳምንታት ፤ ወራት የሚቆይ ዝናን ሊያተርፍ ይችላል።አብዛኛው ዝና በአጋጣሚ የሚመጣ ነው።አንዳንዱ ደግሞ ታስቦበት የሚገኝ ነው።ለምሳሌ ያህል ስለ አንድ ሰው ድብቅ መረጃ በማውጣት ለጥቂት ሰዓታት መረጃ አውጪውም መረጃ የወጣበትም ሰው ዝነኛ ሆነዋል።በሌላ መልኩ ስራዬ ብለው አቅደው ፎቶ ቤት ሄደው አወዛጋቢ ፎቶ ተነስተው ዝነኛ የሆኑም አሉ። ሁሉም የየራሱ ምክንያት አለው። የሆነ ሆኖ በዚህ መልኩ ብዙ ሰው ለ15 ደቂቃ የሚቆይ ዝናን በማህበራዊ ሚዲያ አግኝቷል። ሌሎች ብዙዎች ደግሞ ያቺን የ15 ደቂቃ ዝና ለማግኘት የአቅማቸውን ጥረት እያደረጉ ነው።
ዝናን ማግኘት መፈለግ የሰው ልጅ ባህሪ ነው። ሁሉም ሰው መወደድን ይፈልጋል፤ መከበርን ይፈልጋል፤ መታወቅን ይፈልጋል። ብቸኛው ልዩነት እነዚህ ፍላጎቶች እንዴት ነው የሚሳኩት የሚለው ነው። ደራሲው በእውቀቱ ስዩም “የትህትናም ሆነ የጉራ አላማ አንድ እንደሆነ ነገርኳት ። የሁለቱም አላማ የበላይነትን ማግኘት ነው ። ልዩነቱ ጉረኛው የበላይነትን ተንጠራርቶ ይሸመጥጣል ። ትሁቱ አጎንብሶ ይለቅማል” በማለት የበላይ መሆን እና መታወቅ የሁሉም ሰው የጋራ ፍላጎት እንደሆነ እና ልዩነቱ የአካሄድ እንደሆነ ይገልጻል።
ታዲያ ይቺ ዝና እና የበላይነትን የመፈለግ ጉዞ ብዙዎችን ወደ ማህበራዊ ሚዲያ በተለይም ወደ ፌስቡክ እንዲጎርፉ እና የማይጠቅም ነገር እንዲያደርጉ እያረጋቸው ነው። እውነት ይሁን ውሸትነቱን ባለቤቶቹ እና ፈጣሪ የሚያውቁት ቢሆንም አንዳንዶች ይቺን ዝና ለማግኘት ራሳቸውን በመንግስት ለመታሰር እስከመጣር የደረሱ አሉ ይባላል። ሌሎች በበኩላቸው ወጣ ያለ አጀንዳ መዝዞ በመነታረክ እና በማነታረክ ትኩረት ለማግኘት ሲጥሩ ወጣ ያለ ፎቶ አነሳስ በመነሳትም እንዲሁ የ15 ደቂቃ ዝናን ለማግኘት የሚሞክሩ አሉ። የፌስቡኩን የሚያስንቅ የፎቶ ትርኢት በኢንስታግራም የሚካሄድ ሲሆን በዩቲዩብ ደግሞ ይቺኑ እንደ ጤዛ የምትበን ዝና ለማግኘት ከፎቶ እና ቪዲዮ ትርኢት ያለፈ ብዙ አስቀያሚ ታሪክ ሲነገር እና ተግባር እናያለን።
ይህ የ15 ደቂቃ ዝና ግን ብዙ ጊዜ እንደታየው የሚያጠፋ ነው። ብዙዎች ዝና ለማግኘት ብለው የሚያደርጉት ተግባር በኋላ ህይወታቸው ላይ የሚጸጸቱበት እንደሆነ የሚታይ ነው። ለምሳሌ ያህል በቅርቡ አንድ ታዳጊ የፍቅር ጓደኛዬ ናት ከሚላት ከሱ በእድሜ የምታንስ ልጅ ጋር በዩቲዩብ የገዛ እናቱን እያንጓጠጠ የተቀረጸው ቪዲዮ ተለቆ ብዙ እይታ አግኝቶ ነበር። ለጊዜው ልጁ ለጥቂት ሳምንታት እየተደነቀም እየተተቸም ዝናን ቢያገኝም በኋላ ላይ ወደ ቀልቡ ሲመለስ ግን ነገሩ ጥፋት መሆኑን አውቆ ይቅርታ ጠይቋል። ሁለት ወጣት ሴቶች እና አንድ ወንድ ልጅም እንዲሁ በተመሳሳይ ከባህል ያፈነገጠ ነገር (አንድን ወንድ ለሁለት ማግባት) በዩቲዩብ ቃለመጠይቅ ሰርተው በኋላ ላይ በቴሌቪዥን ሁሉ ቀርበው ይቅርታ ጠይቀዋል።
ልቾቹ ይህን ያደረጉት አንድም ካለመብሰል አንድም እንደ ብዙው ሰው ዝናን ከመፈለግ ነው። ነገር ግን ብዙ ትልልቅ እና ነፍስ ያወቁ ናቸው የምንላቸው ሰዎች በዚሁ የ15 ደቂቃ ዝና ወጥመድ ተጠልፈው ሲስቱም እናያለን። ይቺኑ ዝና ፈልገው ቀኑን ሙሉ መንግስትን ሲተቹ የሚውሉ፤ በማህረበሰቡ ዘንድ እንደ ነውር የሚቆጠሩ ጉዳዮችን አደባባይ ላይ ካላቀረብን የሚሉ ፤ የሀይማኖት አባቶችን የሚያንቋሽሹ ፤ ሀሰተኛ ወሬ የሚፈበርኩ ፤ ብሄርን ከብሄር ሀይማኖትን ከሀይማኖት የሚጋጩ ወዘተ ብዙዎች ናቸው። አንዳንዶቹ በለስ ቀንቷቸው በዚሁ ዝናን የሚያተተርፉ ሲሆን ከዚህች የዝና መድረክ ላለመውረድ የሚያደርጉት ጥረት ደግሞ የበለጠ አደገኛ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።
ይቺ ርካሽ ዝና (cheap popularity) ግን ብዙም አትሰነብትም። ልክ እንደ ንጉስ አይዞር የስልጣን ዘመን ስልብ የምትል ናት። በኢትዮጵያ ታሪክ በጣም አጭር የንግሥና ታሪክ ያለው ንጉሥ አይዞር በመባል ይታወቃል። ይህ ንጉሥ በ772ዓ.ም ተቀብተው የነገሱ ቢሆንም በህይወት መቆየት የቻሉት እስከቀትር 6 ሰዓት ብቻ ነው። የንግሥናቸው ማጠር ዋነኛ ምክንያት ከንግሥና ሥነ ሥርዓት በኋላ እየዞሩ የተሰበሰበውን ህዝብ ሰላም ሲሉ በነበረው ግፊያ ተረጋግጠው ህይወታቸው በማለፉ በታሪክ አጭሩ የንግሥና ጊዜ ተብሎ ተመዝግቧል።
የብዙዎች የፌስቡክ ዝናም እንዲሁ ናት። ለአመታት እንደተከበሩ እና እንደታመኑ የሰነበቱ ሰዎች እና ሀሳቦች ጥቂት ናቸው። ብዙዎቹ የፌስቡክ ዝነኞች በሆነ ጊዜ ብቅ ይላሉ። እንደ ንጉስ አይዞርም ሰላም የሚላቸው የሚያደንቃቸው ሰው ይበዛል። ከዚያ በኋላ ግን ያለ አቅማቸው የመጣው ዝና ጨፍልቋቸው ሀሳባቸው ሲሞት ይታያል።
ስለዚህም ሰዎች ለቅጽበት በሚቆየው የፌስቡክ ዝና እንዳይጠለፉ ለማድረግ ማስተማር ያስፈልጋል። የዩቲዩብ ገንዘብ እንዳያሰክራቸው መምከር ያስፈልጋል። የቲክቶክ ተከታይ ብዛት ማስተዋላቸውን እንዳይጋርደው መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ደህና የምንላቸው ሰዎች ሁሉ የ15 ደቂቃ ዝናን ለማግኘት ሲሉ በገቡበት አላስፈላጊ መስመር በዚያው ቀልጠው ሲቀሩ ተመልክተናል። በጠራ የፖለቲካ አመለካከታቸው የምናውቃቸው ሰዎች ዛሬ አንድ ብሄር ወይም አንድ ሀይማኖት ጉያ ውስጥ ተደብቀው ሲሸቅጡ የምናገኛቸው እንደ አጋጣሚ በቀመሷት ዝና ተታለው ነው።
ሚዛናዊ በሆነ እይታቸው የምናከብራቸው ሰዎች ጽንፈኛ የሆኑት በ15 ደቂቃ የዝና ጊዜያቸው ባገኙት ብዙ ላይክ እና ኮመንት ተሳስተው ነው። ሰዎች የራሳቸውን ቀለም አጥተው ሌላ ሰው የሆኑት በአንድ ወቅት ያገኙት ዝና ሁሌ የሚዘልቅ መስሏቸው ቦታቸውን ለቅቀው ነው። ይቺ በአንድ ወቅት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የምትገኝ ሞቅታ ብዙዎችን አስታለች። የሁሉም መጨረሻ እንደ ንጉስ አይዞር እንዳይሆን ከጭብጨባው በላይ ራሳቸውን እንዲሰሙ ማድረግ ያስፈልጋል።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2014