ሴቶች ለተለያዩ ማህበራዊና የጤና ችግሮች ውስጥ የማለፍ እድላቸው ከወንዶች ጋር ሲነጻጸር ሰፋ ያለ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በርካታ ምክንያቶችን ማንሳት ቢቻልም ዋናው ግን ተፈጥሯዊና ባህላዊ ጫናዎች ናቸው። ተፈጥሯዊውን እንኳን ብንመለከት በማርገዝ። በመውለድ ኋላም ልጆች በማሳደግ በኩል በሚያልፏቸው ሂደቶች እንዲሁም ሰውነታቸው ላይ በሚፈጠሩ የተለያዩ ለውጦች ለበርካታ አይነት ህመሞች ድካም የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ ነው። አንዲት እናት መጸነሷን ካወቀችበት ጊዜ አንስቶ እስክትወልድ ድረስ አስፈላጊውን የአመጋገብ ሂደት ካልተከተለች ብሎም ተገቢውን የህክምና እርዳታ ማግኘት ካልቻለች የሚከሰቱ የጤና ችግሮች በርካታ ናቸው። እነዚህ ችግሮች ደግሞ በወቅቱ ተገቢውን ትኩረት ካላገኙ ከወሊድ በኋላም ተጠናክረው በመቀጠል ምናልባትም ሴቲቱን ለከፋ የጤና አደጋ የማጋለጣቸው ሁኔታ እጅግ በጣም ሰፊ ነው።
በሌላ በኩልም ሴቶች ቤተሰብ በማስተዳደር የሚሸከሙት ሀላፊነት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ይህ ደግሞ ለራሳቸው ጊዜ እንዳይሰጡ ያደርጋል። እራሳቸውን መንከባከብ ብሎም ሲያማቸው “ይሻለኛል” ከማለት ባለፈ ጠንከር ያለ ህክምናን በመውሰድ በኩል ክፍተቶች ይስተዋላሉ። እዚህ ላይ ግን ቁጥራቸው ብዙ ባይሆንም ያለቻቸውን ጊዜ አብቃቅተው ጤናቸውን የሚንከባከቡ ሴቶች የሉም ማለትም አይደለም። ነገር ግን አብዛኞቹ ሴቶች የሚያልፉበት የሕይወት መንገድ ለራስ ከመኖር ይልቅ ሌሎችን ማስቀደም ነውና በትንሹ ሊያልፉት በሚችሉት በሽታ ሁሉ ዋጋ ስከፍሉ ይስተዋላል።
ሴቶች በቀላሉ ሊድኑ በሚችሉ በሽታዎች ለሞት የመዳረግ መጠናቸው ላቅ ያለ መሆኑን ብዙ ጥናቶች ያመለክታሉ። ከዚህም መካከል የማህጸን ኢንፌክሽን ብዙ ሴቶች ላይ የሚከሰት በዛው መጠን ደግሞ ትኩረት ባለመስጠታቸው ምክንያት ከፍ ላለ የጤና ችግር የሚጋለጡበት የህመም አይነት ሆኖ ተመዝግቧል።
የማህጸን ኢንፌክሽን መከሰቻ ምክንያቱ፣ ከተከሰተም በኋላ ሊደረግ ስለሚገባው ህክምናና ተያያዥ ጉዳዮች በዚህ ጽሁፍ ለመዳሰስ እንሞክራለን።
የማህጸን ኢንፌክሽን ምንድን ነው?
በጥቅል መጠሪያው የማህጸን ኢንፌክሽ (Pelvic Inflammatory Disease (PID)) የሚባለው የሴቶች የመራቢያ አካላትን (ስርዓትን) የሚያጠቃ በሽታ ሲሆን የሴቶች የመራቢያ አካላት ስንል የሚከተሉትን ያቀፈ ነው፣ ማሕፀን፣ ሴት ልጅ ነፍሰ ጡር ስትሆን ልጅ የሚሸከመው አካል፣ ኦቫሪ በየወሩ እንቁላል የሚያዘጋጁ አካላት፣ የፋሎፕያን ቱቦዎች ኦቫሪዎችን ከማህፀን ጋር የሚያገናኙ ቱቦዎች፣ ብልት ማህፀን ከውጭ ጋር የሚያገናኘው ክፍል ናቸው ።
የማህጸን ኢንፌክሽን ሲከሰት መለስተኛ የሆኑ ምልክቶች ሊታዩ አሊያም ምንም አይነት ምልክት ላይታይ ይችላል። በዚህም ምክንያት አንዲት ሴት ይህ የጤና ችግር እንዳለባት ሳታውቅ ልትቆይና ችግሩ እየቆየ ውስጥ ውስጡን ተባብሶ ለማርገዝ እስከመቸገርና ከፍተኛ ለሆነ የዳሌ ህመም እስከማጋለጥ ሊያደርሳት ይችላል።
የማህጸን ኢንፌክሽን ምልክቶቹ ምንድናቸው?
አንዲት ሴት የማህጸን ኢንፌክሽን አጋጥሟታል ለማለት የተለያዩ ምልክቶችን ማሳየት ይኖርባታል። ነገር ግን ከላይ እንዳልነው አንዳንድ ጊዜ ምንም ምልክት ሳያሳይ ውስጥ ውስጡን ችግሩ አድጎ ከፍ ወዳለ የጤና ችግር ሊደርስ ይችላል።
ከምልክቶቹ መካከል ማህፀን እና የወገብ ህመም፣ በወሲብ ጊዜ የሚያጋጥም ህመም፣ ከብልት የሚወጣ ፈሳሽ (ሽታ ያለው)፣ ሽንት በሚሸናበት ጊዜ የሚያጋጥም ህመም፣ ትኩሳት ወይም ብርድ ብርድ ማለት፣ ድካም፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስ፣ በወር አበባ ጊዜ የሚመጣ ህመም መጨመርና ሌሎችም መሆናቸውን ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የማህጸን ኢንፌክሽን በምን ምክንያት ይከሰታል?
ሁሉም አይነት ህመሞች የመከሰቻ መንገዳቸው የተለያየ ነው። የማህጸን ኢንፌክሽንም ብዙ ዓይነት መከሰቻ ምክንያቶች ያሉት ሲሆን ዋናው ግን ባክቴሪያዎች የማህጸን ኢንፌክሽንን ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ በዋነኝነት ደግሞ የዚህ በሽታ መንስዔ ተደርገው የሚጠቀሰው ግኖሪሃን ( gonorrhea) የሚባለው የባክቴሪያ ዓይነት ነው።
ይህ ባክቴሪያ ጥንቃቄ በጎደለው የግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት ወደ ሴቷ ማህጸን ሊገባና በሽታው እንዲከሰት ሊያደርግ እንደሚችልም መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከዚህም በተጨማሪ በወር አበባ ጊዜ፣ በወሊድ ወቅት እንዲሁም በማህጸን ውስጥ በሚቀመጡ የእርግዝና መከላከያዎች አማካይነት ባክቴሪያው ወደ ሰውነት ሊገባ የሚችልበት እድልም ሰፊ መሆኑ ይነገራል። ይህ ባክቴሪያ ደግሞ እንደዚህ ባሉት ጊዜያት በሚፈጠሩ የጥንቃቄ ጉድለቶች ወደ ማህጸን ሊገባና በሽታውን ሊያስከትል ይችላል።
የማህጸን ኢንፌክሽን የሚያስከትለው ጉዳት
የማህጸን ኢንፌክሽን በጊዜ ካልታከመ ብዙ የጤና መቃወሶችን ሊያስከትል ይችላል። ከነዚህም መካከል ከማህጸን ውጪ እርግዝና (Ectopic pregnancy)። የማህጸን ኢንፌክሽን በሽታ በፋሎፒያን ቲዩብ ውስጥ ጠባሳ እንዲፈጠር ማድረግ፤ ይህም ጠባሳ ደግሞ ለጽንሰት የደረሰው የሴቷ እንቁላል ጽንስ ወደሚፈጠርበት ማህጸን እንዳይሄድ በማገድ ጽንሱ ከማህጸን ውጭ እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል። መሃንነት (infertility) በማህጸን ኢንፌክሽን በተደጋጋሚ የተጠቃች ሴት የመራቢያ አካላቷ ስለሚጎዱ ለመሃንነት የመጋለጥ እድሏ ከፍተኛ ነው ። የተራዘመ የዳሌ ህመም (chronic pelvic pain) ሌላው በኢንፌክሽኑ ምክንያት የሚከሰት ችግር ነው።
የማህፀን ኢንፌክሸን ህክምና
አንዲት ሴት የማህፀን ኢንፌክሽን እንደያዛት የሚታወቀው ወደ ሃኪም ሄዳ አስፈላጊ የሆኑ ምርመራዎች ከተደረጉላት በኋላ ነው። ከነዚህ ምርመራዎች መካከል የሽንትና የደም ምርመራ፤ የማህፀን ምርመራ ወይም አልትራሳውንድ ሲሆኑ ከምርመራዎቹ በኋላ ሃኪሙ አስፈላጊ የሆኑ ፀረ- ባክቴሪያ መድሃኒቶችን ሊያዝ ይችላል።
የሚታዘዘውን መድሃኒት በትክክልና በሰዓቱ ካልተወሰደ ግን የማህፀን ኢንፌክሽንን ማዳን በጣም ከባድ ነው የሚሆነው ። እዚህ ላይ አንዲት ሴት የማህጸን ኢንፌክሽን እንዳጋጠማት ከታወቀ የፍቅር ጓደኛዋ አልያም የትዳር አጋሯ አብሯት እንዲታከም ቢደረግ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት ይቻላል።
እንዲሁም መድሃኒቱን በትክክል ከወሰዱ በኋላ እንደገና ተመርምሮ ነፃ መሆን አለመሆን እስኪታወቅ ድረስ ወሲብ አለመፈጸም ህክምናው ውጤታማ እንዲሆን ያግዘዋል።
የማህጸን ኢንፌክሽን ያለባት ሴት ማርገዝ ብትፈልግ?
በአንዲት ሴት ላይ የማህጸን ኢንፌክሽን ተከስቶ ከነበረ ምናልባት ለማርገዝ ልትቸገር ትችላለች። ምክንያቱም በሽታው በፋሎፕያን ቱቦዎች ላይ ጠባሳ ሊያስከትል ስለሚችል ነው። ምናልባት እርግዝና እንኳን ቢፈጠር ከማህጸን ውጭ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው። በመሆኑም ሴትየዋ ለማርገዝ በምትሞክርበት ጊዜ በማህጸን ኢንፌክሽን ተጠቅታ እንደነበር ለሃኪሟ መንገር በጣም አስፈላጊ ብሎም የጽንሱንም የእናትየዋንም ጤና ለመጠበቅ በጣም ወሳኝ በመሆኑ ለሀኪም መንገር ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል።
የማህጸን ኢንፌክሽን ምልክቶች ከታዩ በአፋጣኝ ሃኪም ጋር በመቅረብና አስፈላጊውን ህክምና በማድረግ በመራቢያ አካላት ላይ በማህጸን ኢንፌክሽን ምክንያት ሊፈጠር የሚችልን ጠባሳ መከላከልም እንደሚቻል መረጃዎች ያሳያሉ።
የማህጸን ኢንፌክሽን እንዳይከሰት እንዴት እንከላከል
የማህጸን ኢንፌክሽን እንዳይከሰት የሚከተሉትን ማድረግ ያስፈልጋል። ወሲብ በሚያደርጉበት በማንኛውም ጊዜ የላቴክስ ኮንዶም መጠቀም፣ የአባላዘር በሽታ ምልክቶች ካለው ሰው ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ከማድረግ መቆጠብ፣ ህመሙ ከተፈጠረ በኋላ ወሲብ ላለመፈጸም (መታቀብ) ከመከላከያ መንገዶቹ መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2014