በፖርትላንድ ኦሪገን ዛሬ በሚጀመረው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ኢትዮጵያ ሜዳሊያ ከምትጠብቅባቸው የፍጻሜ ውድድሮች አንዱ ማራቶን ሲሆን በሁለቱም ፆታ ነገና ከነገ በስቲያ የሚካሄድ ይሆናል። በወንዶች ማራቶን በዓለም ቻምፒዮኑ አትሌት ሌሊሳ ዴሲሳ ፊታውራሪነት የሚመራው የኢትዮጵያ ቡድን አራት አትሌቶችን ያካተተ ሲሆን፤ በዶሃው የዓለም ቻምፒዮና በርቀቱ የተመዘገበውን የወርቅ ሜዳሊያ ለመድገም የሚያስችል ዝግጅት ሲያከናወን ቆይቷል።
የርቀቱ የዓለም ቻምፒዮን አትሌት ሌሊሳ ዴሲሳ፤ ቡድኑ ውጤታማ ሊያደርገው የሚችለውን ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ለአዲስ ዘመን በሰጠው አስተያየት ተናግሯል። ብዙ ጊዜ ኦሊምፒክና የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናን የመሳሰሉ ውድድሮች የርቀቱን አትሌቶች ከአየር ሁኔታ ጋር ተያይዞ ይፈትናሉ። ውድድር የሚካሄድባቸው አገራት በአብዛኛው እጅግ ሞቃታማ የአየር ሁኔታ ያላቸው መሆኑ ለዚህ ፈተና ዋነኛው ምክንያት ነው። ኦሪገን የሚገኘው የኢትዮጵያ የማራቶን ቡድን ይህንን ሙቀት ሊቋቋም የሚችልበትን ዝግጅት በቂ ዝግጅት ሲያከናውን እንደቆየ ሌሊሳ ይናገራል። እሱና ጓደኞቹ እንደ ቡድን አስፈላጊውን ዝግጅት ያደረጉ በመሆናቸውም እንደ ዶሃው የዓለም ቻምፒዮና በኦሪገንም ጥሩ ውጤት ሊመዘገብ እንደሚችል ያለውን እምነት ገልጿል።
ማራቶን መሮጥን ከጀመረ አንስቶ በአትሌቲክስ ሕይወቱ ስኬታማ ጊዜን እያሳለፈ የሚገኘው አትሌት ሞስነት ገረመው፤ በዶሃው ቻምፒዮና የብር ሜዳሊያ ማጥለቁ የሚታወስ ነው። በተያዘው ዓመት በሶስት ማራቶኖች ላይ ተሳታፊ የነበረው ሞስነት በአንዱ ጉዳት ከማስተናገዱ ባለፈ ባስመዘገበው ውጤት በዓለም የማራቶን ሯጮች ደረጃ ሶስተኛ ላይ መቀመጥ ችሏል። በትልቁ የአትሌቲክስ ውድድር የዓለም ቻምፒዮናም ውጤታማ ሊያደርገው የሚችለውን ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ተናግሯል። በኢትዮጵያ ያለው የአየር ሁኔታ ዝናባማ በመሆኑ ዝግጅቱ ጊዜ ጠብቆ የሚደረግ ቢሆንም፤ በዶሃ የተመዘገበውን ውጤት አስጠብቆ ለማጠናቀቅ ከቡድን አጋሮቹ ጋር ማቀዳቸውንም ጠቁሟል።
የማራቶን ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ሃጂ አዴሎ፤ በዚህ ርቀት አትሌቶች ከተመረጡ ጀምሮ አንድ ወር ከሁለት ሳምንት የፈጀ ከወትሮው የተሻለ ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ይናገራሉ። ከዚህ ቀደም እጅግ ይረብሽ የነበረው ክረምት ሳይበረታባቸው ዝግጅቱን ሲያካሂዱ ቆይተው አሁን ላይ ለውድድሩ ዝግጁ መሆናቸውንም አክለዋል።
በዚህም ጥሩ ውጤት ይመዘገባል የሚል ተስፋ አላቸው። የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ቻምፒዮናው ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረግ ሲሆን፤ አትሌቶች ከዚያ ቀደም እንደነበረው በቂ ውድድሮችን አላደረጉም። ቢሆንም በተካሄዱ ውድድሮች ተካፍለው ጥሩ ሰዓት ለማስመዝገብ ችለዋል። በዚህ መሰረት የተመረጡ በመሆናቸውም ውጤታማ ይሆናሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
አሸናፊውን ለመገመት አስቸጋሪ በሆነው የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን የሚፎካከሩ የሌሎች አገራትን አትሌቶች በተመለከተ ‹‹አብዛኞቹ በሌሎች ዓለም አቀፍ ማራቶኖች ላይ አብረውን የሚሮጡ አትሌቶች ናቸው፣ ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሙቀቱ ካልከበዳቸው በቀር ለአሸናፊነት ይፎካከራሉ።
በእርግጥ ሁሉም አትሌት ለማሸነፍ ተዘጋጅቶ ነው ውድድሩ ላይ የሚሳተፈው ነገር ግን በአቋምም በአእምሮም የተሻለው አሸናፊ ይሆናል›› በማለት ቻምፒዮኑ ሌሊሳ ይናገራል። የኢትዮጵያ የማራቶን ቡድን በተለይ በዚህ ውድድር ከፍተኛ ዝግጅት ከማድረጉ ባለፈ፤ በዶሃ ቻምፒዮን በመሆኑ ኦሪገን ላይ አራት አትሌቶችን የማሳተፍ እድል አለው። ይህም በቡድን ስራ ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ ያለው ሲሆን ከአንድ በላይ ሜዳሊያዎችን ለማስመዝገብም አቅም እንደሚሆነው ይጠበቃል።
ከዚህ ቀደም የነበሩት አብዛኛዎቹ የርቀቱ ተፎካካሪዎች ኬንያዊያን ቢሆኑም አሁን ግን በአሜሪካ፣ በአውሮፓ እና በጃፓን ጥሩ ሰዓት የሚሮጡ አትሌቶች እየታዩ እንደሚገኙ የጠቆመው አትሌት ሞስነት፤ ትልቅ ውድድር እንደመሆኑ ሁሉም አሸናፊ ለመሆን እንደሚዘጋጅ ይናገራል። ኢትዮጵያን የሚወክለው ቡድንም ዝግጁ ከመሆኑ ባለፈ ሁሉም አትሌት በመልካም ጤንነት ላይ የሚገኙ በመሆኑ ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆኑም እምነት አለው።
በርካታ የማራቶን አትሌቶችን ያፈሩት አሰልጣኝ ሃጂ አዴሎ በበኩላቸው ተፎካካሪያቸው እንደ ቀድሞው ኬንያዊያን ብቻም ሳይሆኑ ከአፍሪካ ወጥተው ለሌላ አገራት የሚሮጡ አትሌቶች መሆናቸውን ያብራራሉ። ‹‹እነዚህ አትሌቶች ቀላል ግምት የሚሰጣቸው ባይሆኑም በበርካታ ውድድሮች፤ ከኢትዮጵያዊያኑ ጋር አብረው በመሮጣቸው ይተዋወቃሉ፤ በመሆኑም ያን ያህል የሚያሰጋ አትሌት አይኖርም፣ በልበሙሉነት ውድድሩ ላይ ከተሳተፉ ውጤታማ የማይኮንበት ምክንያት የለም›› ሲሉም ስኬታማው የማራቶን አሰልጣኝ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የዓለም ቻምፒዮኑ ሌሊሳ የቡድኑ አባላት ተስፋ ያላቸውና ጠንካራ አትሌቶች መሆናቸውን በማስታወስ፤ በተለያዩ ውድድሮች ላይም አሸናፊዎች እንደነበሩ ያስቀምጣል። በሞስኮው ዓለም ቻምፒዮና እሱ የብር የቡድን አጋሩ ደግሞ የነሃስ ሜዳሊያ ሲያገኙ፤ በዶሃው ደግሞ የወርቅና የብር ሜዳሊያዎች ተመዝግበዋል። በመሆኑም ‹‹በዚህ ውድድር ላይ ከአንድ እስከ ሶስት በመውጣት ወርቅና ብር እንዲሁም የቀረንን የነሃስ ሜዳሊያ ለማግኘት ጥረት እናደርጋለን›› ሲልም ተስፋውን ገልጿል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8/2014