ሃሳቡ የመነጨው በልጅነት አእምሮ ነው። ይህ በምናብ ህይወት ተፀንሶ የነበረ ራዕይ ወደ እውኑ ዓለም መገለጥ የጀመረው ታዲያ በህዳር ወር መጀመሪያ 2014 ዓ.ም ነበር። ከዚህ ግዜ በኋላም በዚህ የስራ ዘርፍ ላይ ተሰጥኦ፣ ፍላጎትና እውቀት ያላቸው የቅርብ ወዳጆች ይሳተፉ ጀመር።
አንድ፣ ሁለት ሶስት እያሉም ቁጥራቸው ዛሬ ላይ ዘጠኝ ደርሷል። ይህ ሀሳብ ‹‹ኬዛ አፍሪካ›› ሲሰኝ ቋንቋው ከስዋሂሊኛ የተወሰደ ሆኖ ‹‹ውብ አፍሪካ›› የሚል ትርጉም ይሰጣል። የዚህ ፅንሰ ሃሳብ ጠንሳሽና መስራች፤ እንዲሁም ዋና ስራ አስኪያጅ ደግሞ ወጣት ሰላሙ ጫነ ይባላል።
ወጣት ሰላሙ እንደሚለው ‹‹ኬዛ አፍሪካ›› ዛሬ ያለበት ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት ሶስት ሂደቶችን አልፏል። አንደኛው ሃሳቡ ሲሆን በተለይ እርሱ በትምህርት ቤት ውስጥ እያለ አፍሪካና የአፍሪካ ወጣቶች ላይ መስራት መቻል አለብን የሚል ሃሳብ በውስጡ ይንሸራሸር ነበር። ትልቅና ውብ አፍሪካን ለመገንባት መስራት አለብን የሚል ሃሳብም በውስጡ ነበር።
ሁለተኛው ደግሞ ሃሳቡ እንዳለ ሆኖ ውብ አፍሪካን ለመገንባት መሳሪያው ምንድን ነው? የሚለው ሲሆን በኋላ ላይ ሃሳቡን የማስተላለፊያው መንገድ ጥበብ ሆኖ ተገኝቷል። ይህ ጥበብ ደግሞ በፊልም፣ ቲያትር፣ ዶክመንተሪ፣ ስዕልና በሌሎችም ሊገለፅ ይችላል። ጥበብን አፍሪካን ለማሳያና መገንቢያ መጠቀም እንደሚቻልም ማወቅ ተችሏል። ሶስተኛውና የመጨረሻው ሂደት ደግሞ ለስራ አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን ማሟላት ሲሆን ይህንኑ በማድረግ ‹‹ኬዛ አፍሪካ›› የሚለውን መለያ (ብራንድ) በመያዝ ህዳር 7 ቀን 2014 ዓ.ም ስራውን በይፋ ጀምሯል።
እንደ ስራ አስኪያጁ ገለፃ የ‹‹ኬዛ አፍሪካ›› ዋነኛ ፅንሰ ሃሳብ አፍሪካዊነትንና ፓናፍሪካኒዝምን በስነ ጥበብ አማካኝነት ለማህበረሰቡ ማስተዋወቅ ሲሆን የድርጅቱ ራዕይም በ2036 ዓ.ም አህጉር በቀል እውቀቶችን በመያዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባህሉን፣ ፍልስፍናውን፣ ጥበቡንና ቋንቋውን የሚያሰርፅባቸውን ማእከላትን መገንባት ነው።
በሚያስገነባቸው ማእከላትም በስነ ምግባር የታነፀ፣ ባህሉን የሚያከብር፣ ማንነቱን የሚያውቅ፣ ለአህጉር በቀለም ሆነ በአለም አቀፋዊ እውቀት የበቃ ዜጋን ለመላው ዓለም ማበርከትንም ተጨማሪ ራዕዩ አድርጎ ተነስቷል።
የድርጅቱ ተልእኮም በመላው አፍሪካ አገራት ተደራሽ በመሆን የአህጉሪቱን ማህበረሰብ ማእከል ያደረጉ የጥበብ ስራዎች፣ ትምህርቶችና ስልጠናዎችን ማዘጋጀት፣ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የሚገኙ አህጉራትን መልካም ገፅታ መገንባት፣ የተገነባውን መልካም ገፅታና የአህጉሪቱን ተፈጥሯዊ መልከአ ምድር ለዓለም ማሳየት ነው።
ድርጅቱ ስራውን ሲጀምር ነገሮች አልጋ በአልጋ አልነበሩም። ይሁንና በአሁኑ ጊዜ በዋልታ ኤፍ ኤም 105 ነጥብ 3 ላይ ቅዳሜ ከአምስት ሰአት ጀምሮ ‹‹ኬዛ አፍሪካ›› የተሰኘ ፕሮግራም አለው። ይህም ራዕዩን የሚያሳውቅበት ሁኔታ ፈጥሮለታል። አዲስ የዩቲዩብ ቻናልም አስጀምሯል።
አገር በቀል በሆኑ ሀሳቦች ላይ ዘጋቢ ፊልሞችን በመስራት በቴሌቪዥን ለማቅረብም አስቧል። ከአንዳንድ ሆቴሎችና ባለተስጥኦ ወጣቶች ጋር በመሆን የቲያትር ስራዎችም ተጀምረዋል። ፊልሞችንም ወደፊት የሚሰራ ይሆናል። ለድርጅቱ ራዕይ መሳካትም ዘጠኝ የሚሆኑ ወጣቶች በኬዛ አፍሪካ ውስጥ ሆነው እየሰሩ ይገኛል።
በዋልታ ኤፍ ኤም 105 ነጥብ 3 ላይ ድርጅቱ በዋናነት የሚሰራው ስራ የአፍሪካን ታሪክ በሚገባ ለህብረተሰቡ ማስተላለፍ ነው። ለአብነትም ‹‹ኬዛ አፍሪካ›› እየሰራ ካለው የአፍሪካ ታሪኮች ውስጥ አንዱ የኔልሰን ማንዴላ ታሪክ ሲሆን ይህ ታሪክ በኢትዮጵያ ውስጥ ለተደረጉም፤ ለሚደረጉም ትግሎች ምሳሌ ሊሆን የሚችል ነው። አሁን ላይ የሚታገልና ወደፊት ወደነፃነት ትግል ለመግባት የሚያስብ ሰው ይህን የኔልሰን ማንዴላ ታሪክ በተገቢው ሁኔታ ማወቅ መቻል አለበት።
ስራ አስኪያጁ እንደሚለው አፍሪካ ብቻዋን ሆና ልትሄድ አትችልም። ለዛም ነው ድርጅቱ ማንነቱን የሚያውቅ፣ ለአህጉር በቀልም ሆነ በአለም አቀፋዊ እውቀት የበቃ ዜጋን ለመላው አለም ማበርከትን ራእዩ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ያለው። የጥበብ ስራዎችም ሲሰሩ ከአፍሪካኒዝም አንፃር ተቃኝተው ነው።
የበጎ አድራጎት ስራን በሚመለከት ድርጅቱ በሁለት መንገድ ስራዎችን ይሰራል። አንደኛው የእውቀት ስልጠናዎችን መስጠት ሲሆን ወጣቶች ከድርጅቱ መፅሃፍቶችን በውሰት ወስደው በማንበብ የእውቀት አድማሳቸውን እንዲያሰፉ ይደረጋል። በወረዳዎች አካባቢም ተመሳሳይ ስራዎች ይሰራሉ። ሁለተኛው ደግሞ ድርጅቱ ፊልም ሲሰራ በስልጠና ያበቃቸውን ሰዎች ይዞ የማላመድ ስራ ይሰራል።
በመጀመሪያ ምእራፍ በኬዛ አፍሪካ ራእይ ውስጥ ያሉ ሰዎች መለወጥ ስላለባቸው ዘጠኙን ወጣቶች በዚህ ራእይ ውስጥ መለወጥ ተችሏል። በሁለተኛ ምእራፍ እነዚህ ዘጠኝ የድርጅቱ ወጣቶች ደግሞ ቤተሰባቸውን በተለይ ደግሞ ወጣቱን ብሎም አካባቢያቸውን ለመለወጥ በዋልታ ኤፍ ኤም 105 ነጥብ 3 የተጀመረው ስራ ተጠቃሽ ነው። ለሰው ይህን የአፍሪካን ሀብት ለመንገርና ለማሳወቅም ድርጅቱ ጉጉ ነው።
በሶስተኛው ምእራፍ ደግሞ ድርጅቱ በሚሰራቸው የጥበብና የቲያትር ስራ፣ የፊልምና የዘጋቢ ፊልሞች ስራ አፍሪካን እያስተዋወቀ ይገኛል። በገዳ ስርዓት ላይ የሚያተኩር ዘጋቢ ፊልምም እየተሰራ ነው። በዚህ ዘጋቢ ፊልም ውስጥ የሚሳተፉ ሰዎችም በዚሁ የገዳ ስርዓት ዙሪያ እውቀቱ ያላቸው ናቸው። ይህም አፍሪካ ተኮር ያስብለዋል። በዚህም ሆነ በሌላ መንገድ አፍሪካ ያላትን አገር በቀል እውቀት፣ ሃብትና ሌሎችንም ነገሮች ጥበብን በመጠቀም ለህብረተሰቡ ማስተዋወቅ የ‹‹ኬዛ አፍሪካ›› ትልቁ ህልም ነው።
‹‹ኬዛ አፍሪካ›› የአፍሪካን እውቀት፣ ሃብትና ሌሎችንም ነገሮች ጥበብን ለህብረተሰቡ ለማስተላለፍ እያደረገ ያለው ጥረት በህብረተሰቡ በኩል በጎ ተቀባይነት አለው። እያንዳንዱ ሰውም ቢያንስ አንድ ነገር ያውቃል። ይኸውም የሰው ዘር መገኛ አፍሪካ መሆኗንና ያውም የዚህ ምንጭ ኢትዮጵያ እንደሆነች ነው። በተለይ ደግሞ ይህን የአፍሪካኒዝም አስተሳሰብ በህብረተሰቡ ውስጥ ለማስረፅ አባቶችና እናቶች ለዚህ ትውልድ ያወረሷቸው ትውፊቶችና ሌሎችም ባህሎች ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው።
ለአብነትም እያንዳንዱ ያለፍንባቸው የስልጣኔ መንገዶች ሲታዩ ሊነሱ የማይችሉ ናቸው። ከዚህ አኳያ እነዚህን ስልጣኔዎች ለማንሳትና ወደእነሱ ለመሄድ እነዚሁ አባቶችና እናቶች ያወረሷቸው ትውፊትና ባህሎች ጠቅመዋል። ዋናው ጉዳይ የ‹‹ኬዛ አፍሪካ›› ራእይ በዚህ ትውልድ ዛሬ ላይ መጀመሩ ነው እንጂ ረጅም ርቀት መጓዙ አይቀርም። ሆኖም በዚህ ሂደት ውጣውረዶች አያጋጥሙም ማለት አይደለም። ልክ እንደሌሎች ጉዳዮች አንዳንድ ሰዎች ይህን ራዕይ ላይቀበሉትም ይችላሉ። ይህንኑ ውጣውረድ በስነልቦና ለመጋፈጠም ዝግጁነት አለ።
ስራ አስኪያጁ እንደሚገልፀው በቀጣይ ‹‹ኬዛ አፍሪካ›› ትልልቅ የማሰልጠኛ ተቋማትን ለመገንባት ያስባል። እነዚህም ስልጠናዎች ቋንቋን፣ ባህልን፣ ፍልስፍናን ስነጥበብንና ታሪክን ያካትታሉ። በተለይ ቋንቋን በሚመለከት ሁሉም አፍሪካውያን አምስት ቋንቋዎችን ማወቅ አለባቸው ብሎ ድርጅቱ ያምናል። እነዚህም በአፍረካ ህብረት የሚነገሩት ሶስቱ የእንግሊዘኛ፣ አረብኛና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎች ሲሆኑ በተጨማሪ በቅርቡ በአፍሪካ ህብረት የተጨመረውን ስዋሂሊንና የኢትዮጵያ የምርምር ቋንቋ የሆነውን ግእዝን የሚያሰለጥኑ ተቋማትን ለመፍጠር እቅድ ይዟል።
ተቋማቱም በምስራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ነው። በሂደት ደግሞ እነዚህኑ ተቋማት በምእራብ አፍሪካ በተለይ ደግሞ ቡርኪናፋሶ ላይ፣ በሰሜን አፍሪካ አልጄሪያ ላይ፣ መካከለኛው አፍሪካ ቻድ ላይ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ ደቡብ አፍሪካ ወይም ቦትስዋና ላይ የመገንባት ውጥን አለ። ይህም እቅድ የሚሳካው በዚህ ትውልድ ዘመን ነው።
በሂደት ደግሞ ተቋማቱ በሁሉም የአፍሪካ አገራት እየሰፉ እንዲሄዱ ይደረጋል። እነዚህ ተቋማት በቀጣይ ሲገነቡ ወጣቱን ያቀራርቡታል። በስነ ጥበብ አማካኝነት የራሳቸውን አፍሪካዊ ስራ ይዘው ብቅ እንዲሉም እድል ይሰጣል።
ከዚህ ባሻገር ድርጅቱ የአፍሪካን ባህል፣ ፍልስፍናና ታሪክ ማስተማሪያ፣ በዓለም የኪነ ጥበብ ዘርፍ ተወዳዳሪ የሆኑ ፊልሞችን፣ ቲያትሮችን፣ ዘጋቢ ፊልሞችንና ሌሎች የጥበብ ስራዎችንና የመፅሃፍት ህትመት ሥራዎችን የመስራት ሃሳቦችም አሉት።
‹‹ወጣቱ ራሱን ወደማብቃት መምጣት መቻል አለበት›› በማለት የሚናገረው ወጣት ሰላሙ ማወቅ መጀመር ያለበት ደግሞ ራሱን ነው ይላል። በወጣቱ ውስጥ ከሚጠቃለሉት ነገሮች ውስጥ ደግሞ አንዱ አፍሪካ በመሆኑ በተለይ በዚህ የክረምት ወቅት ሶስት አይነት መፅሃፎችን ለማንበብ ማቀድ እንዳለበት ይጠቁማል።
በመጀመሪያ በኢትዮጵያ ታሪክ ዙሪያ የተፃፉ፣ በምስራቅ አፍሪካ ውስጥ የተፃፉ እንዲሁም በሶስተኛ ደረጃ በአፍሪካ እሳቤ ዙሪያ የተፃፉ መፅሃፍቶችን እንዲያነቡ ይጋብዛል። ይህም ስለአገራቸው፣ ስለምስራቅ አፍሪካ ቀጠናና ስለ አፍሪካ አህጉር ጠለቅ ያለ እውቀት እንዲኖራቸው ያስችላል።
በአሁኑ ግዜ ኬዛ አፍሪካ እንዲህ ነው የሚባል ገቢ እንደሌለው የሚናገረው ወጣት ሰላሙ ነገር ግን በሬዲዮ ስራዎች ደጋፊዎች (ስፖንሰሮችን) እንደሚያገኝና አንዳንድ የቲያትር ስራዎችን ለመስራት ሲያስብም ከሆቴሎች ጋር በጋራ እንደሚሰራ ይጠቁማል።
ድርጅቱ በአብዛኛው የሚሰራቸው ስራዎች ከስነ ጥበብ ጋር የተያያዙ በመሆናቸውና ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር መስራት ስለሚፈልግ በዚህ አጋጣሚ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለዚህ ቀና ሀሳብ በሩን ክፍት እንዲያደርግም በዚህ አጋጣሚ ይጠይቃል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8/2014