ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ገናና ስም ያተረፈችው በ10ሺ ሜትር ውድድሮች ነው። በዚህ ርቀት ከታሪካዊው ማርሽ ቀያሪ አትሌት ምሩጽ ይፍጠር አንስቶ በየዘመኑ መተኪያ የሌላቸው ብርቅዬ አትሌቶች በሁለቱም ጾታ ኢትዮጵያን በአለም አደባባይ በወርቅ አጥለቅልቀዋል። ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን በዚህ ርቀት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከወርቅ ርቀው ቆይተዋል። ባለፈው ቶኪዮ ኦሊምፒክ ግን የርቀቱን ክብር ወጣቱ አትሌት ሰለሞን ባረጋ በታላቅ ተጋድሎ ወደ ኢትዮጵያ መልሷል።
ከቶኪዮ ኦሊምፒክ ማግስት ከነገ ጀምሮ በሚካሄደው የኦሪገን የአለም ቻምፒዮናም ኢትዮጵያ በውድድሩ ከ12 አመት በኋላ ወደ ክብሯ እንደምትመለስ ይጠበቃል። ይህም በምክንያት መደገፍ የሚችል ቅድመ ውድድር እይታ እንጂ በተስፋ ላይ የተመሰረተ ላለመሆኑ ጠንካራ ማስረጃዎች አሉ።
የኦሊምፒክ ቻምፒዮኑ ሰለሞን ዘንድሮ በርቀቱ በርካታ የውድድር አማራጮችን አግኝቶ በአስደናቂ ብቃቱ ላይ እንደሚገኝ ደጋግሞ ማሳየት ባይችልም እሁድ ሌሊት በሚካሄደው ፍልሚያ ወርቁን የማጥለቅ አቅም እንዳለው ይታመናል። ከወር በፊት ሄንግሎ ላይ ኢትዮጵያውያን ተፎካካሪዎቹን ያሸነፈበትም መንገድ ሰለሞን አሁንም በርቀቱ ኮከብ መሆኑን በግልጽ ያሳየ ነው። ሰለሞን በሄንግሎው የማጣሪያ ውድድር በቀላሉ ያሸነፋቸው ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ በርቀቱ ልምድና ችሎታቸው እየዳበረ የመጣና ወጣት እንደመሆናቸው የአትሌቱን ምርጥ ብቃት አውጥቶ ያሳየ ነው።
ሰለሞን እንደ ቀደምቶቹ የርቀቱ ፈርጦች ሃይሌ ገብረስላሴና ቀነኒሳ በቀለ በመካከለኛ ርቀቶች እንዲሁም በቤት ውስጥ ውድድሮች ጭምር ስኬታማ መሆኑን በዚህ የውድድር አመት አሳይቷል። ይህም በ10ሺ ሜትር ያለውን ጠንካራ ትንፋሽና የማይደክም የአካል ብቃት በአስደናቂ አጨራረስ አጅቦ ወርቁን ለማጥለቅ ከተፎካካሪዎቹ የተሻለ እንደሚያደርገው ይጠበቃል።
እድሜው ገና በ20ዎቹ መጀመሪያ የሚገኝ እንደመሆኑም የኦሊምፒክ አሸናፊ ከመሆኑ ጋር ተደምሮ ከተፎካካሪዎቹ የተሻለ የስነልቦና ጥንካሬ ላይ እንዲገኝ የሚያደርገው በመሆኑ እኤአ ከ2011 የዴጉ የአለም ቻምፒዮና የኢብራሂም ጀይላን የማይረሳ ድል በኋላ ኢትዮጵያን በርቀቱ ወደ ድል እንድትመለስ ያደርጋታል ተብሎ ይጠበቃል።
በዚህ ርቀት ከሰለሞን ባሻገር ኢትዮጵያ ሜዳሊያ የምትጠብቅባቸው ወጣት አትሌቶች በሪሁ አረጋዊና ታደሰ ወርቁም ቀላል ግምት የሚሰጣቸው አይደሉም። በተለይም በርቀቱ ብርቱ ተፎካካሪ እንደሚሆን የሚጠበቀው የርቀቱ ባለ ክብረወሰን ዩጋንዳዊው አትሌት ጆሽዋ ቺፕቴጌን የ5 ኪሎ ሜትር ክብረወሰን በዚህ አመት የግሉ ያደረገው በሪሁ በእሁዱ ፍልሚያ የተለየ ነገር ሊፈጥር እንደሚችል ብዙዎች ተስፋ ጥለውበታል።
በሪሁ ከተፎካካሪዎቹ አኳያ በእድሜ ትንሹ አትሌት ቢሆንም በተለያዩ ርቀቶች የሚያሳየው አስደናቂ ብቃት የተፎካካሪዎቹ ስጋት አድርጎታል። ባለፈው የሪዮ ኦሊምፒክም ሰለሞን ወርቅ ሲያጠልቅ አራተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው በጥቃቅን የቴክኒክ ስህተቶችና በልምድ ማነስ ነበር። አሁን ይህ አትሌት ራሱን በተሻለ ደረጃ ላይ እንዳስቀመጠ ሄንግሎ ላይ ሰለሞንን ተከትሎ ሲያጠናቅቅና በዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ላይ አስመስክሯል። የ20 አመቱ ታደሰ ወርቁም የኢትዮጵያውያኑን ስብስብ አስፈሪ ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዱ ነው። ባለፈው አመት በአለም ከ20 አመት በታች ቻምፒዮና በ3ሺ ሜትር ወርቅ ያጠለቀው ይህ ወጣት አትሌት በአጭር ጊዜ ራሱን አብቅቶ በእሁዱ ፍልሚያ ወርቅ ባያጠልቅ እንኳን የወርቅ ምክንያት ሊሆን ይችላል።
የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ስብስብ ይህን ያህል አስፈሪ ቢሆንም በተለይም ከዩጋንዳውያን አትሌቶች የሚጠብቃቸው ከባድ ፈተና የሚደበቅ አይደለም። በተለይም የርቀቱ የአለም ቻምፒዮንና ባለክብረወሰን ጆሽዋ ቺፕቴጌ ከሰለሞን ያልተናነሰ የወርቅ ሜዳሊያ እድል ያለው አትሌት እንደመሆኑ ለኢትዮጵያውያኑ ቀላል ፈተና እንደማይሆን ግልጽ ነው።
ቅዳሜ ምሽት 5ሰአት በሚካሄደው የሴቶች ተመሳሳይ ርቀት የፍጻሜ ውድድርም ኢትዮጵያ ትልቅ የወርቅ ተስፋ አላት። በተለይም የርቀቱ የአለምና የኦሊምፒክ ቻምፒዮን የሆነችው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድስ አትሌት ሲፈን ሃሰን ዘንድሮ መወዳደሯ አጠራጣሪ መሆኑ ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትልቅ እድል ነው። ሲፈን የውድድር አመቱን በጉዳት ማሳለፏ ወቅታዊ አቋሟ ላይ ጥርጣሬ አሳድሯል። በዚህም ብትወዳደር እንኳን ለኢትዮጵያውያኑ እንዳለፉት አመታት ፈታኝ ላትሆን የምትችልበት እድል ጠባብ አይደለም።
ይህም ዶሃ ላይ የብር ሜዳሊያ በርቀቱ ላጠለቀችው የርቀቱ ክብረወሰን ባለቤት ለተሰንበት ግደይ የምስራች ብቻ ሳይሆን ወደ ቻምፒዮንነት ክብር የምትመጣበት መልካም አጋጣሚ ነው። በ5ና 10ሺ ሜትር የአለም ክብረወሰኖቿ ላይ በዚሁ አመት የግማሽ ማራቶን ክብርን የደረበችው የ24 አመቷ ለተሰንበት ሄንግሎ ላይ ቀዳሚ ሆና ባታጠናቅቅም በርቀቱ ያላት ድንቅ ብቃት አያጠራጥርም። ባለፉት ውድድሮቿ የነበረባት ልምድ የማነስ ችግርም ዘንድሮ ሊቀረፍ እንደሚችል ይታመናል።
በዚህ አመት የቤልግሬድ የአለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና የ3ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊዋ አትሌት እጅጋየሁ ታዬም የሜዳሊያ ተፎካካሪነት አቅም ያላት አትሌት ስትሆን ለተሰንበትን ጭምር መፈተን እንደምትችል በቅርቡ አሳይታለች። በዚህ ላይ የ20 አመቷ አትሌት ቦሰና ሙላቴ ኢትዮጵያን የምትወክል አዲስ ሆና ብቅ ብላለች። ይህም ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ የሚጠበቁ ኬንያውያን አትሌቶችን ለመመከት ለኢትዮጵያውያኑ ተጨማሪ አዲስ ጉልበት እንደሚሆን ይጠበቃል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 7/2014