‹‹ካይሮፕራክቲክ›› የአጥንት፣ የነርቭ ፣ ጡንቻና በተለይ ደግሞ የአከርካሪ አጥንት ላይ የሚያተኩር የህክምና ዘርፍ መሆኑን በዚህ ዘርፍ ያሉ የህክምና ባለሞያዎች ያስረዳሉ። ይህ የህክምና ዘርፍ ግን በኢትዮጵያ ብዙም የተለመደ ባለመሆኑ ትምህርቱ በኮሌጅ አልያም በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ሲሰጥ አይታይም። በአፍሪካም ቢሆን ከደቡብ አፍሪካ በስተቀር በሌሎች አገራት ትምህርቱ አይሰጥም።
ከዚህ በመነሳት ታዲያ አንድ የአገር ባለውለታ በአገራቸው ያዩትን የአከርካሪ አጥንት ጤና ችግር በዝምታ ለማለፍ አልፈቀዱም። ይልቁንም በአሜሪካን አገር ለአስራ ሁለት አመታት ሲሰሩበት የቆዩትን የአከርካሪ አጥንት ህክምና ሞያ ይዘው ከሃያ አንድ አመት በፊት ወደ አገራቸው በመመለስ የመጀመሪያውን የአከርካሪ አጥንት ህክምና ማእከል አቋቁመዋል።
እኚህ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ የሆኑት የአከርካሪ አጥንት ሀኪም የተለያዩ በጎና አነቃቂ ንግግሮችን በማድረግም ይታወቃሉ። በህክምና ሳይንስ ውስጥ በተቻለ መጠን አብዛኛው ህክምና የአከርካሪ አጥንትን በማስተካከል ቢጀመር የተሻለ ነው የሚል እሳቤም አላቸው። በኢትዮጵያ የአከርካሪ አጥንት ህክምና ማዕከል ለማቋቋም የተነሱበት አላማም ይኸው ነው።
በተለይ ደግሞ ‹‹አስር ለጤና›› በሚለው መርሀግብራቸው ሰዎች ከባድ ስራ ከመስራታቸው በፊት ሰውነታቸውን እንዲያሟሙቁ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉና ከውስጣቸው እንዲተነፍሱ በማድረግ ውጤታማና ጤነኛ ሰራተኛ እንዲፈጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።
በትምህርት ቤቶችም ‹‹ቀጥ በልጅነት›› የሚለውን መርሃግብር ተግባራዊ በማድረግ ልጆች የአከርካሪ አጥንታቸው ተስተካክሎ እንዲያድግ በሰውነት ማጎልመሻ መምህራን በኩል በርካታ ስራዎችን ያከናውናሉ። ሰዎች ስራ ከመጀመራቸው በፊት ለአስር ደቂቃ ያህል ከስራ ሰአታቸው ላይ ወስደው እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ መንግስት በይፋ እንዲፈቅድ ግፊት እያደረጉም ነው- በአከርካሪ አጥንት ህክምና ሞያ ከሰላሳ አመት በላይ የቆዩት የፈርስት ስፓይን ሴንተር መስራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ሰላም አክሊሉ።
ዶክተር ሰላም አክሊሉ እድገትና ውልደታቸው በድሬዳዋ ከተማ ነው። ለቤተሰባቸው ስምንተኛና የመጨረሻ ልጅ ናቸው። በእናትና አባታቸው፣ በታላላቅ እህትና ወንድሞቻቸው ፍቅርና እንክብካቤ አግኝተው ነው ያደጉት። ለእድገታቸውና ለዛሬ ማንነታቸው የበርካታ ሰዎች አስተዋፅኦ ያለበት ቢሆንም የአባታቸው ድጋፍ ግን የተለየ ነው። አባታቸው በተለይ ለሴት ልጆች ያላቸው አስተሳሰብም ከፍተኛ የነበረ በመሆኑ በማንነታቸው ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል።
ዶክተር ሰላም ገና የአስራ ሰባት ዓመት ታዳጊ እያሉ ወደ አሜሪካን አገር የመሄድ እድል ቢገጥማቸውም እርሳቸው ወደአሜሪካን አገር የሄዱበት ግዜ ግን ጥሩ አልነበርም። ወቅቱም በኢትዮጵያ ቀይ ሽብር በከፍተኛ ሁኔታ የተፋፋመበት ነበር። ‹‹ከነገ ዛሬ እሞት ይሆን›› ብለው የሚሰጉበትም ግዜም ነበር።
በግዜው በርካቶች በእርሳቸው እድሜ ያሉ ወጣቶችም በስጋት የሚኖሩበት ከባድ ውቅት የነበረ ቢሆንም አሜሪካን አገር ከሄዱ በኋላ ቀድመው የሄዱ እህቶቻቸውና ወንድማቸው ስለነበሩ እዛ ብዙ አልተቸገሩም። አሜሪካን አገር ከገቡ በኋላም ከመጡበት የአገራችው ልምድ ተነስተው በፍፁም እንደ እድሜያቸው መሆን እንደማይችሉ ያውቁ ነበር። የኋላ ኋላ ግን ራሳቸውን ማስተማርና ህይወታቸውን መለወጥ እንዳለባቸው ተረድተዋል።
ከዚህም በመነሳት ገና በአስረኛው ቀን ነበር አሜሪካ ስራ የጀመሩት። በአሜሪካ ትምህርት ለመማር አስቸጋሪ ስለነበርም ለስድስት አመታት ያህል በምሽት እየሰሩ ነበር ትምህርታቸውን የተከታተሉት።
ከልጅነታቸው ጀምሮ ሃኪም የመሆን ህልም የነበራቸው ዶክተር ሰላም አክሊሉ ይህ ምኞታቸው የጀመረው ገና የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ሳሉ ነበር። የ9ኛ ክፍል ተማሪ እያሉ ቁጭ ብለው ሲያጠኑ በሃያ ሰባት አመታቸው ዶክተር እንደሚሆኑ እቅድ ያወጡ ነበር። ዶክተር ሆነው ተመልሰው አብረዋቸው የተማሩ ተማሪዎችን እንደሚያናግሯቸውም ያስባሉ። ፡
በአሜሪካን አገር ቆይታቸው ዶክተር ሰላም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኬሚካል ቴክኖሎጂ ኬሚስትሪ ሜጀር ከካሊፎርኒያ ትሬድ ቴክኒካል ኮሌጅ አግኝተዋል። በካይሮፕራክቲክ ህክምና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከክሊቭላንድ ካይሮፕራክቲክ ሴንተር ተቀብለዋል። ገና ልጅ እያሉ ሀኪም የመሆን ምኞታቸውንም ያውም በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት የአከርካሪ አጥንት ሃኪም በመሆን የኋላ ኋላ ማሳካት ችለዋል። በመቀጠል ደግሞ በዶክተር ኦፍ ሜዲስን ከሶቼካልኮ ሜክሲኮ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል።
በተማሩበት የካይሮፕራክቲክ ህክምና ሞያ የመጀመሪያዎቹን አስራ ሁለት አመታት በዛው አሜሪካን አገር ካሊፎርኒያ በሚገኝ አንድ የህክምና ማእከል ውስጥ ሰርተውበታል። ወደዚህ ሞያ የገቡትም በታላቅ እህታቸው አነሳሽነት ነበር። በተለይ ደግሞ በአፄ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ወደ አሜሪካን አገር ሄደው የካይሮፕራክተር ህክምና ትምህርት ከተከታተሉት የመጀመሪያዎቹ ሀኪሞች ውስጥ አንዱ ከነበሩት ከዶክተር ተስፋ ወሰኔ ጋር መገናኘታቸውና ማውራታቸው ወደዚህ ሙያ ለመግባት ይበልጥ ገፋፍቷቸዋል።
ከባለቤታቸው ጋር የተገናኙትም በዛው አሜሪካን አገር ሲሆን ከትዳር አጋራቸው ሁለት ወንድና ሁለት ሴት ልጆችን አፍርተዋል። በባለቤታቸው ሀሳብ ጠንሳሽነት ልጆቻውን ወደ አገራቸው ተመልሰው በኢትዮጵያዊ ባህል ማሳደግ ስለፈለጉ ከዛሬ ሃያ አንድ አመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል። ነገር ግን ወቅቱ ሰው ወደ አገሩ የሚመለስበት ምቹ ግዜ አልነበረም። ሆኖም ወደአገራቸው መመለሳቸውን በህይወታቸው ከወሰኗቸው ትክክለኛ ውሳኔዎች ውስጥ እንደዋና ይቆጥሩታል።
ከዛሬ ሀያ አንድ አመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የመጀመሪያዋ ካይሮፕራክቲክ ሀኪም የነበሩት ዶክተር ሰላም፤ በኢትዮጵያ የካይሮፕራክቲክ ህክምና ማእከል በማቋቋምም ቀዳሚ ናቸው። ፈርስት ስፓይን ሴንተር የተሰኘና በአከርካሪ አጥንት ህክምና ላይ የሚሰራ ማእከልም አቋቁመዋል።
ማእከሉ በአዲስ አበባ ሶስት ክሊኒኮች ያሉት ሲሆን ከአዲስ አበባ ውጪ በድሬዳዋና ጅማ ከተቋማት ጋር በትብብር ይሰራል። ዘጠና ሰባት የጤና ባለሞያዎችንም በውስጡ አቅፏል። በዋናነትም በአከርካሪ አጥንት ችግር ላይ አተኩሮ ይሰራል። በተጨማሪም የአንገት፣ ወገብ፣ ጀርባ፣ ትከሻ፣ እጅ፣ ዳሌ፣ ጉልበት፣እግር፣መገጣጠሚያ፣ ጡንቻና የነርቭ ህመም ህክምና አገልግሎቶችን ይሰጣል።
ማዕከሉ በኢትዮጵያ በአብዛኛው በቀዶ ህክምና ሲስተካከል የሚታወቀውን የዲስክ መንሸራተት ከቀዶ ህክምና ጋር በተያያዘ በርካታ አደጋዎች ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ችግሩን ያለቀዶ ህክምና በተፈጥሯዊ መንገድ ለማስተካከል የፊዚዮቴራፒና የካይሮፕራክቲክ ሞያን ቀላቅሎ የተዛባውን የአከርካሪ አጥንት የማስተካከል ስራ ይሰራል። ይህም ዲስኩ ላይ ያለውን ጫና በማንሳት ነርቩ ላይ ያለውን እክል ማስተካከልን ያካትታል።
ማእከሉ ብዙ ሰዎች የቀዶ ህክምና እንዳያደርጉ በማስቆም የሚታወቅ ሲሆን በተቻለ መጠን ሰዎች ወደ ቀዶ ህክምና እንዳይሄዱ የመከላከልና የበለጠ ደግሞ ቀጣይነት ያለው የአከርካሪ አጥንት ማስተካከል ስራዎችን በማከናወን የተሻለና ጤናማ ህይወት እንዲኖራቸው ጥረት ያደርጋል።
በአሁኑ ግዜ ማእከሉ የመጀመሪያውን ከህመም ማገገሚያ ሆስፒታል እየገነባ ይገኛል። ከዚሁ ፕሮጀክት ጎን ለጎንም በውጭ አገራት ስራ ሰርተው አቁመው ወደአገራቸው የሚመለሱ ሰዎች በአንድ ላይ የሚሰባሰቡበት ማእከል እያዘጋጀ ነው። ማእከሉ 150 ሰዎች አብረው ሊኖሩበት የሚችል ሲሆን ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ከውጭ አገር የሚመለሱ ዲያስፖራዎች ናቸው።
‹‹የመላው ሰውነት ጤንነት መሰረቱ የአከርካሪ አጥንት አቀማመጥ ትክክል መሆን ነው›› የሚሉት ዶክተር ሰላም ይህ ካልሆነ የሰዎች መላው ሰውነታቸው ጤነኛ ሊሆን እንደማይችል ይገልፃሉ። ከዚህ አንፃር በተለይ በግንባታና ኢንዱስትሪ ዘርፎች ውስጥ ከባድ ስራዎችን የሚሰሩ ሠዎች ችግሩን እንዲገነዘቡት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያመለክታሉ። የአከርካሪ አጥንት ጤንነት ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ ባለሞያውም ጭምር ስለማያውቀው ስለጉዳዩ የማስገነዘብ ስራ እንደሚያስፈልግም ይጠቅሳሉ።
በዚህ መነሻነት ፈርስት ስፓይን ሴንተር ‹‹አስር ለጤና የሚል›› አገራዊ ንቅናቄ እንዳስጀመረ ገልፀው፤ ይህም ሰዎች ሥራቸውን ከመጀመራቸው በፊት ለአስር ደቂቃ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከልባቸውና ከትንፋሻቸው ጋር እንዲሆኑ ብሎም ሠውነታቸውን ለስራ እንዲያዘጋጁ የሚያስችላቸው መሆኑን ያብራራሉ።
ይህ አገራዊ ንቅናቄ ሰዎች የተረጋጋ ማንነትና ለስራ ተነሳሽነት እንዲኖራቸው በማድረግ በስራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ከማድረጉም በዘለለ አሰሪዎችም ምርታማ የሰው ሃይል እንዲኖራቸውና በዚህም ትርፋማ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው እንደሆነም ዶክተር ሰላም ይጠቁማሉ። ይህ ደግሞ ተደምሮ ሲታይ ጤናማ ህዝብ እንዲኖርና ለአገር ብልፅግናም ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው ያስረዳሉ።
‹‹አስር ለጤና›› የተሰኘው ፕሮግራም በሁሉም የግንባታና የኢንዱስትሪ ዘርፎች ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆን በጤና ሚኒስቴር በኩል እንደፀደቀና በተመሳሳይ በሰራተኛና ማህራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩልም አውቅና እንዳገኘም ይገልፃሉ። ፕሮግራሙ በሁሉም የግልም ሆነ የመንግስት ተቋማት ቢተገበር ጤናማና የተሻለ ብሎም ምርታማ የሰው ሃይል እንዲኖር የሚያስችል መሆኑንም ይጠቁማሉ።
የፈርስት ካይሮፕራክቲክ ሴንተር ዋነኛ አላማም ይህንኑ ‹‹አስር ለጤና›› የተሰኘውን ፕሮግራም በሁሉም ተቋማት ውስጥ በስፋት ተግባራዊ እንዲሆን የማድረግና በቀጣዮቹ አምስት አመታት ይህንኑ ፕሮግራም ተግባራዊ የሚያደርጉ አስር ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን መፍጠር መሆኑንም ዶክተር ሰላም ያብራራሉ።
‹‹ይህ ፕሮግራም ከተጀመረ ወዲህ ውጤት እያመጣም ነው›› የሚሉት ዶክተር ሰላም፤ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ሰራተኞቻቸው ላይ የጀመሩት ስራ ለዚህ ጥሩ ማሳያ መሆኑን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ። አንድ መስሪያ ቤት ወይም ተቋም ቢያንስ ለአንድ አመት ይህን ፕሮግራም ልምድ አድርጎ ሰርቶበት ለስራ ዝግጁ የሆነ የሰው ሃይል ይዞ መስራት ከቻለ የፕሮግራሙ ውጤታማነት እንደሚረጋገጥም ያስረዳሉ። ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ ትምህርት ቤቶችም ጭምር ተማሪዎቻቸው ፕሮግራሙን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ማድረግ የማእከሉ ሌላኛው አላማ መሆኑንም ይጠቁማሉ።
በቀጣይም ማእከሉ እያንዳንዱ ሰው ሰውነት ራሱን የማዳን ሃይል እንዳለው ተገንዝቦ የራሱን ጤና እንዲጠብቅ የማብቃት ስራዎች በስልጠናና በልዩ ልዩ መንገዶች ለመስጠት እቅድ እንዳለው ይገልፃሉ። የአኗኗር ዘይቤዎችን ማስተካከል ላይ ማእከሉ በቀጣይ አተኩሮ ከሚሰራባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ መሆኑንም ይጠቁማሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች ኃላፊነት ወስደው የራሳቸውን ጤና እንዲጠብቁ የሚያበቁ የጤና ባለሞያዎችን የማስልጠን ስራም ማእከሉ በቀጣይ እንደሚያከናውን ይገልፃሉ።
በተለይ ደግሞ ማዕከሉ ሰዎች ስራ ከመጀመራቸው በፊት ከስራ ሰአታቸው ላይ አስር ደቂቃ ተወስዶ ‹‹አስር ለጤና›› የሚለውን ፕሮግራም ተግባራዊ እንዲያደርጉ በመንግስት በይፋ እንዲፈቀድ ሰፊ ጥረቶችን እንደሚያደርግም ዶክተር ሰላም ይናገራሉ።
እምብዛም ባልተለመደው አከርካሪ አጥንት ህክምና ሞያ ለሰላሳ ሶስት አመታት ያህል የቆዩት ዶክተር ሰላም ከሃያ አንድ አመታት በላይ በዚሁ ሞያ አገራቸውን በማገልገላቸው ይህን እንደ አንድ ስኬት ይቆጥሩታል። ወደአገራቸው ሞያውን ይዘው እንደመጡ ከጤና ሚንስቴር ጀምሮ ህብረተሰቡ ለሞያው የነበረው ግንዛቤ አነስተኛ እንደነበር ነገር ግን ዛሬ ላይ ይሄ ተለውጦ የካርይሮፕራክቲክ ህክምና ለጤና ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ህብረተሰቡ እየተረዳው መምጣቱም ለኔ ተጨማሪ ስኬት ነው ይላሉ። ሆኖም አሁንም በርካቶች በዚህ የአከርካሪ አጥንት ችግር ተጠቂ ከመሆናቸው በፊት መከላከል ላይ ያተኮሩ ስራዎችን በመስራት በሞያቸው ከዚህም በላይ ስኬታማ መሆን እንደሚፈልጉ ይናገራሉ።
የአከርካሪ አጥንት ጤናን መጠበቅ መሰረታዊ፣ ብዙ ወጪ የማያስወጣና ብዙ መድሃኒት የማያስገዛ የጤና አጠባበቅ ዘይቤ ስለሆነ በተለይ ለአፍሪካ ብቸኛው መልስ ይሆናል ብለው እንደሚያስቡና ይህ ጉዳይ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም እንዲሆን ለማድረግ እንደሚሰሩም ያማላክታሉ።
የአገር መሰረቱ ሰው ነውና የአከርካሪ አጥንት ጤንነት ጉዳይ ከሚንስቴር መስሪያ ቤቶች ጀምሮ የሁሉም ሰው ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባም ገልፀው፤ በተለይ ደግሞ የአከርካሪ አጥንት ችግርን አስቀድሞ መከላከል ላይ በስፋት ሊሰራ እንደሚገባ ያሳስባሉ። በመንግስት በኩል ያሉ ጅምር ስራዎች ቢኖሩም በቀጣይ ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባቸውም ይጠቁማሉ።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 6/2014