አዲስ አበባ፡- 52 ኪሎ ሜትር ከሚሸፍነው የአዲስ አበባ ከተማ የወንዝ ዳርቻዎችን ለመናፈሻ የማዋል ሥራ ውስጥ ሁለት ኪሎ ሜትሩን የጣሊያኑ ቫርኔሮ ኩባንያ ስራ መጀመሩን የተፋሰስና አረንጓዴ አካባቢዎች ኤጀንሲ አስታወቀ። በሸራተን ማስፋፊያ አካባቢ የሚሰራው ሁለገብ አገልግሎት ያለው የመናፈሻ ፓርክ ሥራም ከኩባንያው ጋር የውል ስምምነት ለመፈጸም በሂደት ላይ መሆኑም ተጠቁሟል።
የኤጀንሲው ዳይሬክተር ዶክተር ስለሺ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት የአዲስ አበባ ከተማ የወንዝ ዳርቻዎችን ለመናፈሻ የማዋል ሥራ አጣዳፊ የጎርፍ ችግር ሲያጋጥምና የአካባቢውን ነዋሪዎች ለአደጋ ሲያጋልጥ አደጋውን ከመከላከል ጎን ለጎን ወንዞችን ለመናፈሻ የማዋል ሥራ ቀድሞም ሲከናወን የቆየ ነው። ይህ የሚለየው የፕሮጀክቱ ግዝፈትና ከላይኛው እስከ ታችኛው ተፋሰስ ድረስ ወጥ በሆነ መልኩ መከናወኑ ነው ብለዋል።
በፕሮጀክቱ አምስት ገባር ወንዞችንና ሰባት የከተማዋን የወንዝ ዳርቻዎች ለመናፈሻ ለማዋል በጥናት ተለይተዋል የሚሉት ዳይሬክተሩ የሁለት ኪሎ ሜትሩ ሥራ ቢጀመርም ቀሪው ጥናት ላይ መሆኑንና በምዕራፍ ተከፋፍሎ አጠቃላይ ሥራውን በሶስት አመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱን አመልክተዋል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ የአካባቢውን ነዋሪ ብዛት ታሳቢ በማድረግና የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ከእንጦጦ፣አፍንጮ በርና ቡልቡላ አድርጎ አቃቂ የሚሄደው ወንዝ በፕሮጀክቱ በቅድሚያ ተካትቷል፡፡
ፕሮጀክቱ በፌዴራል መንግሥት፣በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣በብድር፣በገቢ ማሰባሰብና በተለያዩ ድጋፎች የሚከናወን ሆኖ በአጠቃላይ 29 ቢሊዮን ብር እንደሚፈጅ አስረድተዋል፡፡ ቻይና መንግሥት ከእንጦጦ እስከ ቡልቡላ ያለውን በገንዘብ ለመደገፍ ፍላጎት ማሳየቱን አስታውሰው በተመሳሳይ መንገድ ፕሮጀክቱን ለመደገፍ ፍላጎት ያላቸው ዓለምአቀፍ ድርጅቶች መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡ የልማቱ ሥራ ከሚከናወንበት አካባቢ 32ሺ ተነሽዎች እንደሚኖሩት የሚጠበቀው ይህ ፕሮጀክት ለሚነሱ ነዋሪዎች ምትክ ቦታና አስፈላጊውን ካሳ አሟልቶ ከቦታው አስነስቶ ወደ ሥራ ለመግባት የተባባሪ አካላት ድጋፍ ወሳኝ እንደሆነ ዶክተር ስለሺ አስረድተዋል፡፡
የፕሮጀክት መጓተት እንዳይኖርም በቅድ መዘጋጀቱ ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ በሸራተን ማስፋፊያ አካባቢ በሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ወጪ የአረጓዴ ቦታ፣ የልጆች መጫወቻ፣አንፊ ቲያትር፣ የገበያና የተለያየ አገልግሎት መስጫ ያለው የፓርክ ሥራም የወንዝ ዳርቻና መናፈሻ ሥራው አካል መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ የፕሮጀክቱ የአዋጭነት ጥናት መካሄዱንም ይናገራሉ፡፡
በወንዞች ዳር መናፈሻ ፕሮጀክት ጥናቱ ላይ የተሳተፉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ሳይንስ መምህር ፕሮፌሰር ተሾመ ሶሮምሳ እንደገለጹት ጥናቱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አማካኝነት እኤአ በ2016 የተጀመረ ሲሆን፣ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ መጠናቀቁን ያስታውሳሉ፡፡
ጥናቱ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን የዳሰሰና አምስት ዋና ዋና ጉዳዮችን ያካተተ ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ በከተማዋ የ127 አመት ታሪክ ውስጥ ሰፊ የሆነ የወንዝ ዳር ልማት ሥራ በመሆኑ አዲስና ሥር ነቀል ለውጥ እንደሚያመጣ አመልክተዋል፡፡ በጥናቱ ግኝት በከተማዋ 607 ኪሎሜትር ርዝመት ያላቸው 76 ወንዞች ይገኛሉ፡ ፡ አሁን በተጀመረው የልማት ሥራ በ20 አመት ጊዜ ውስጥ ሁሉንም መናፈሻ ማድረግ የሚቻልበት ዕድል መኖሩን ፕሮፌሰሩ አመልክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 19/2011
በለምለም መንግሥቱ