በትናንት ክፍል ሁለት እትማችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የለውጡ ጉዞ ያለበትን ደረጃና ፈተናዎቹን ፤ ስለ ሰላማዊ ሰልፍ መከልከል፤በሽግግር መንግስትና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ለተነሱ ጥያቄዎች የሰጡትን ማብራሪያ ማስነበባችን ይታወሳል። በዛሬም ክፍል ሶስት እትማችን ደግሞ በበጀት፤በኤክስፖርት ፣በፕሮጀክት አፈጻጸምና በመሳሰሉት ዙሪያ የሰጡትን ማብራሪያ ይዘን ቀርበናል።
ክፍል ሶስት
ብድር እንቀንስ፤ ብድር ብዙ ጣጣ አለበት፤ ካለ አግባብ ሰብስበን ከተበደርን ቀጥሎ እንግዛ የሚባል ነገር ይመጣል፤ ብድር ብዙ ሀገራት ላይ ጣጣ አምጥቷልና ብድር መቀነስን ልክ እንደ ልማት መውሰድ አለብን። ባለፈው የነበረው የብድር ክመራ ትንሽ ቆይቶ ቴሌ ኮምን አምጡ ምናምን አምጡ ወደ ሚል ስለሚሄድ አደገኛ ነው የሚል በሪፎርማችን ስንሠራ እንደቆየን ይታወቃል። አሁንም የዚህ በጀት ዓመት ትኩረት እርሱ ነው። እርሱን ማድረግ ካልቻልንና ብድር ካልቀነስን ተከትሎ የሚመጣ ጣጣ ስላለ ማለት ነው።
ሁለተኛው የበጀት ጉድለትን መገደብ ነው፤ ፍላጎት እንዳያችሁት በጣም እየሰፋ ነው፤ የበጀት ጉድለትን መገደብ ያስፈልጋል። ሶስተኛ ያለንን ሃብት በቁጠባ መጠቀም ነው። ውሱን ሃብት ነው ያለን፤ ፍላጎታችን እጅግ ግዙፍ ነው፤ ያን ቆጥበን መጠቀም ካልቻልን የፊዚካል ኮንሶሌሺን ማረጋገጥ አንችልም። አንዱ የሚያተኩረው እዚህ ላይ ነው።
ሌላው የዋጋ ንረትን ማረጋጋት ነው፡ የዋጋ ንረት ላለፉት 17፣ 18 ፣ 19 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በቀጣይነት በየዓመቱ እያደገ የመጣ ጉዳይ ነው። ባለፈው እንዳነሳሁላችሁ ለሁለት አስርት ዓመታት ሳይቋረጥ የዋጋ ንረት ኢትዮጵያ ውስጥ ይካሄድ ነበር። አንዳንድ ጊዜ እድገትም እንደዚህ አይነት ችግር ያስከትላል። ባለፉት ሁለት ሶስት ዓመታት ዋጋ ንረቱን ለመከላከል ሰፊ ሥራ ባይሠራ ኖሮ በነበርንበት ውጊያ፣ በነበርንበት ኮሮና፣ አሁን በዩኩሬን ባጋጠመው ችግር እጅግ የገዘፈ ነገር ያጋጥመን ነበር። ግን ቀደም ሲል ሙከራዎች ስለነበሩ የዚያ ሙከራ ውጤት በተወሰነ ደረጃ አግዞናል፤ሙሉ በሙሉ መቅረፍ ባንችልም አግዞናል። አሁንም የዋጋ ንረትን ለማረጋጋትና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ህይወት እየደረሰባቸው ያለውን ፈተና በተወሰነ መልኩ ለማቃለል መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይጠበቅበታል። ከዚህ ውስጥ አንደኛው የገንዘብ አስተዳደርን በጥብቅ መቆጣጠር ነው። ገንዘብ ያለአግባብ ኢኮኖሚው ውስጥ ከተረጨ የሚያስከትለው ጣጣ ስላለ ያን ለመቀነስ የገንዘብ አስተዳደርን በጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል። የእናንተም አንድ አንኳር ሥራ እርሱ ይሆናል።
ሁለተኛው ፕሮዳክቲቪቲን ማሳደግ ነው። በግብርና የጀመርነውን አስደማሚ ውጤት ማስቀጠል ነው። ሁላችሁም ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ወረዳዎች ስለመጣችሁ በየቦታው ከግብርና ጋር ተያይዞ በተለይ አምራች አካባቢዎች ላይ የመጣውን ለውጥ ታውቁታላችሁ። ዛሬ ይህንን ንግግር እያደረግን ወደ 20ሺ የሚጠጋ ፓምፕ እየገጠምን እንገኛለን፤ ዛሬ። ፕሮዳክቲቪቲ ላይ የጀመርነው ነገር ፓምፖችን በማብዛት የውሃ አጠቃቀም በማብዛት፤ በብዛት ማምረት ከቻልን ገበያ ለማረጋጋትም ይሁን ሽጠን ለመጠቀም ያግዛል። በጀቱ ይህንን ጉዳይ እንደ አንኳር ሀሳብ ይወስዳል።
ሶስተኛው ፕሮጀክትን ማጠናቀቅ ነው። ፕሮጀክቶች ካላግባብ እየተራዘሙ ሲሄዱ ኢኮኖሚን በከፍተኛ ደረጃ ይጎዳሉ። ፕሮጀክት ማጠናቀቅ ሲባል፤ የምናወራው ስለ ቢሊዮን ዶላር ነው፤ ትንሽ ብር አይደለም፤ ግድቦቻችን ብቻ በጣም ብዙ ቢሊዮን ናቸው ። በመንግሥት የሚሠሩ ኢንቨስትመንቶች በጣም ሰፊ ስለሆኑ ሁሉም ማለቅም አለባቸው። ፕሮጀክት ካላለቀ ብዙ ጣጣ ስላለበት ነው።
አራተኛው የመልሶ ግንባታና ሰብአዊ እርዳታ ነው። የተፈናቀሉ፣ የተጎዱ ሰዎችን መልሶ ማቋቋም፣ መርዳት አቅም በፈቀደ በመንግሥትም በሁሉም ሪሶርስ ሕይወታቸው ወደ ቀደመው እንዲመለስ ማድረግ የበጀቱ ትኩረት ነው።
አምስተኛው የሀገርን ደህንነትና ሰላም ማስጠበቅ ነው። ቀደም ሲል እንዳነሳሁት ሀገራችንን ለማፈራረስ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለ ስለምናውቅ ተቋማቱን በእጅጉ ማጠናከር አስፈልጓል፤ ይህንን ሥራ እናስቀጥላለን። በድምሩ ሙሉ አቅማችንን በመጠቀም የጀመርነውን እድገት ማስቀጠል ነው። ባለፈው ዓመትም ፖዘቲቭ እድገት ኢትዮጵያ ውስጥ ታይቷል። በችግር ውስጥ ሆነን፤ አሁንም ከአፍሪካ ውስጥ ሻል ያለ እድገት ካላቸው ሀገራት ከመጀመሪያ ተርታ ኢትዮጵያ ትመደባለች።
ይህ የዓለም የፋይናንስ ተቋማት ያረጋገጡት ነገር ነው። ባለፈው ዓመት ያቀረብኩላችሁን ሪፖርት እንዳለ አይ ኤም ኤፍ ተቀብሎታል። የኢትዮጵያን እድገት የባለፈው ዓመት ለፓርላማ የቀረበውን እንዳለ ተቀብሎታል፤ ዘንድሮም ፖዘቲቭ እድገት እንዳለ ያምናሉ ። አጠቃላይ ውጤቱ የሚታወቀው መስከረም አካባቢ ቢሆንም ሻል ያለ እድገት ይጠበቃል።
ከዚህ በመነሳት የመንግሥት ገቢ የ12ኛው ወር የሰኔ ስላልተጠናቀቀ እስከ ግንቦት ያለውን የ11 ወር ስንመለከት እቅዳችን 330 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ነበር። በ11 ወር ውስጥ፤ ያስገባነው 309 ቢሊዮን ብር ነው። ከዕቅዳችን 93 በመቶ መሰብሰብ ተችሏል። የተከበረው ምክር ቤት ይሄንን ነገር ማየት የሚገባው አምና 11 ወር ከሰበሰብነው ዘንድሮ በ11 ወር የሰበሰብነው በ50 ቢሊዮን ብር ጭማሪ አለው። ወይም ከአምናው በ19 ነጥብ 4 በመቶ ጭማሪ አለው፤ ገቢያችን።
ገቢን እናሳድጋለን ብለን የነገርናችሁ ጉዳይ እያመጣ ያለው ውጤት ብዙ የኢትዮጵያ ቀጠና ውስጥ በግጭት ምክንያት የገቢ መሰብሰቢያ ቢሮዎች ተዘግተው እያሉ፤ ብዙ ቦታ ባለው የንግድ ሥርዓት መዛባት ምክንያት በገቢ ወጪ ንግዶች ላይ ጫና የፈጠረ እንኳን ቢሆን ገቢያችን በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ እያለ የ50 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ወይም 19 ነጥብ 4 በመቶ እድገት አምጥቷል። ይህን ያመጣው አንደኛ በገቢ መሥሪያ ቤት ያሉ ሠራተኞችና አመራሮች በከፍተኛ ጥረት ሥለሠሩ ነው። ምስጋና ይገባቸዋል።
በገቢ ተቋማችን ችግር የለም፣ ኮራፕሽን (Corruuption) ዜሮ ነው፣ ሰርቪስ (service ወይም አገልግሎት) በጣም ተሻሽሏል ብለን መፎከር ባንችልም ለውጥ እያመጡ ስለሆነ ገቢ ማሻሻል ችለዋል። ምስጋና ይገባቸዋል።
ሁለተኛ የኛ ነጋዴዎች ሙሉ በሙሉ ባይባልም ብዙዎቹ ዋና ብድር/ ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ብድር ለመክፈል እያሳዩ ያሉት ልምምድ በጣም ጥሩ ነው። የሚሸሽጉ እንዳሉ ሁሉ ቀደም ብለው የሚጠበቅባቸውን በመክፈል ለሀገርና ለመንግስት የሚጠበቅባቸውን ግዴታ የሚወጡ ነጋዴዎች እየተበራከቱ ስለመጡም ጭምር ነው። እነርሱም እንደዚሁ ምስጋና ያስፈልጋቸዋል።
ነገር ግን መጠናከር አለበት። አሁንም ኢትዮጵያ መሰብሰብ ከሚገባት ገቢ እጅግ አነስተኛ ነው። ዘንድሮ የፌዴራል መንግሥትን ነው ያነሳሁላችሁ ። በየክልሉም እንዲሁ ከፍተኛ የገቢ እድገት አለ ፤ አዲስ አበባን ጨምሮ። አቅም እንዳለ ያሳያል። ይህ መጠናከር አለበት።
ወጪ በሚመለከት ግን 500 ቢሊዮን ገደማ ነው ያወጣነው በ11 ወር። 309 ቢሊዮን ብር ገቢ አስገብተን 500 ቢሊዮን አወጣን ስንል የወጪና ገቢ ዴፊሲቱ (deficit/ ኪሳራ) የሚሞላበት መንገድ በጣም በጣም ወሳኝ ነው። ወጪያችንን ካበዙ ጉዳዮች አንደኛው እና ዋነኛው እዳ ነው። በዚህ ዓመት አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር እዳ ከፍለናል። ኦልሞስት (almost/ ትንሽ የቀረው) መቶ ቢሊዮን ብር ገደማ እዳ ነው የከፈልነው።
ከነበረን ሀብት ቀንሰን ማለት ነው። ለምን? እዳ እንዳልኳችሁ ነው እየቆየ ሲሄድ ጣጣ አለው። ልክ ልማት ላይ ርብርብ እንደምናደርገው እዳችንን በፍጥነት ከፍለን ከስጋት ቀጠና ነጻ ለመውጣት ባለን ቁርጠኝነት ምክንያት ከፍተኛ ሃብት ለዕዳ አውለናል። ይሄን ስላችሁ እንግዲህ ከውጭ የምንጠብቀው ብዙ ሀብት እንደምታውቁት ሆኖ ሳይመጣ ቀርቶ ማለት ነው።
ሌላው ቃል የገባንላችሁ እና እጅግ ከፍተኛ ውጤት ያገኘንበት የማክሮ ቲሙን ማመስገን የሚያስፈልግበት አጠቃላይ ኢኮኖሚ ሴክተር ላይ የተሳተፉ ግለሰቦች፣ ባለሀብቶች እና የመንሥት ሠራተኞች ምስጋና የሚያስፈልጋቸው ኤክስፖርት ላይ ነው። ኤክስፖርት ላይ ያመጣነው እምርታ በጣም በጣም ግዙፍ ነው። ይሄንን ነገር ጠብቀን ለጥቂት ዓመታት ማስቀጠል ከቻልን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የንግድ መዛባትና የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል።
ኢትዮጵያ በ2002 ዓ.ም ሁለት ቢሊዮን ዶላር ኤክስፖርት አድርጋ ነበር፤ ጉድስ (goods/ ሸቀጦች)። ከ2002 እስከ 2012 ዓ.ም ሶስት ቢሊዮን ለመድረስ ትንገዳገድ ነበር። ትንሽ የቀረው። በ10 ዓመት ውስጥ አንድ ቢሊዮን ገደማ ነው የጨመርነው። ባለፈው ዓመትና በዘንድሮው ዓመት በሠራነው ሪፎርም በሁለት ዓመት ውስጥ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በመጨመር ዛሬ በጉድስ እና ሰርቪስ ኤክስፖርት ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ አግኝተናል፤ በጉድስና በሰርቪስ ።
ጉድስ ባለፈው ዓመት ከነበረው ዘንድሮ ጭማሪ አሳይቶ ከአራት ቢሊዮን ዳላር በላይ ኤክስፖርት ውጤት ተገኝቷል። ሰርቪስ ደግሞ በ25 ፐርሰንት አድጎ ከስድስት ቢሊዮን በላይ አግኝተናል። በሰርቪስና በኤክስፖርት አስር ቢሊዮን ስንገባ በሁለቱ ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዳላር አካባቢ የሚገመት ተጨማሪ ሃብት አፍርተናል። የሰርቪስ ከፍ ይላል፤ በዚህ ደግሞ በሁለቱ ዓመት ውስጥ አንድ እንጨምርበታለን። ይሄ በጣም ትልቅ እምርታ ነው። ግን ሊያዘናጋን አይገባል ከምንፈልገው አሁንም ሩቅ ስለሆንን ብዙ ሥራ ይጠበቅብናል።
በኤክስፖርት የተገኘው ውጤት ግን የሪፎርሙን ስኬት የሚያሳይ እጅግ ተስፋ ሰጪ ጅማሮ መሆኑን ያመላክታል። ያ እንደተጠበቀ ሆኖ ከየት መጣ ደሞ ያላችሁ እንደሆነ ግብርና ካገኘነው ከጉድስ ኤክስፖርት ኦልሞስት ሃያ ፐርሰንት እድገት ያመጣው ግብርና ነው። ቡና በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዳላር ኤክስፖርት አድርገናል። ይሄ የግሪን ሌጋሲ ውጤት ነው። በያመቱ የምንተክላቸው የምንጎነት(ድ)ላቸው የቡና ምርት ውጤት እያመጣ ነው።
በሻይ የጀመርነውን ካፋጠን፣ በአቦካዶ በማንጎ የጀመርነውን ካፋጠን በፍሩት በቪጅቴብልስና ቡናና ሻይን ጨምሮ ከፍ ያለ ገንዘብ ልናገኝ እንደምንችል እርግጠኞች እድሉ እንዳለ ያመለክታል። ትምህርት ወስደን አበክረን ከሰራን በጉድስ የተገኘው ሰርቪስ የማደግ እድሉ ሰፊ ነው። ሰርቪስም ቢሆን በሰርቪስ ኤክስፖርትም ቢሆን ከአምናው የተሻለ የቱሪዝም ዴስቲኔሽን እያሰፋን ስለሆነ በሚቀጥለው አመት ቱሪዝማችን የተሻለ ከፍ ይላል።
ከሁለት ከሶስት ዓመት በኋላ ግን በደንብ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል። ሰላማችን እየተረጋገጠ ሲሄድ መዳረሻዎች ደግሞ እየተዋወቁ ሲሄዱ ብዙ ውጤት እንጠብቃለን። ኤክስፖርት በሰርቪስም በጉድስም ከአስር ቢሊዮን ዳላር በላይ ማግኘታችን ትልቅ ድል ሲሆን የእናንተ ቁጥጥርና ድጋፍ የህዝቦች ተሳትፎ የአርሶ አደሮች ቁርጠኝነት የማክሮ ቲሙ የእለት ተእለት አመራር ውጤት ነው። በዚህ ሁላችንም ደስ ሊለን ይገባል። ነገር ግን እንዳንዘናጋ ደግሞ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።
ነገ ከሀምሌ አንድ ጀምሮ የአዲሱን ዓመት ኤክስፖርት መምራት ይፈልጋል። ነገ ካልጀመርን ከአስር ወር ከአስራ አንድ ወር በኋላ የምንፈልገውን ውጤት ልናገኝ እንቸገራለን። እና ከኤክስፖርቱ አንጻር እጅግ ጥሩ ውጤት ታይቷል ሊባል ይችላል። ሁለተኛው ፎሬይን ዳይሬክት ኢንቨስትመንት ነው፤ ኤፍ.ዲ.አይ ነው። ኤፍ.ዲ.አይ ኢትዮጵያ ላይ መከራና ችግር ቢወራም ከባለፈው አመት ዘንድሮ አስር ፐርሰንት እድገት አለው።
ከሶስት ቢሊዮን ዳላር በላይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ኢትዮጵያ መጥቷል። አንዳንዴ ግራ ያጋባል፤ ኢትዮጵያ ችግር ነው ይላሉ በየቦታው ስትሄዱ ችግሩን የሚያባብሱ ሰዎች ያጣብቡታል፤ እንጦጦን የሞሉት እነሱ ናቸው። ኢትዮጵያ ችግር ነው ይላሉ እኛ ለኢንቨስትመንት ብዙ ድጋፍ ባልሰጠንበትና ባላመቻቸንበት ሁኔታም እያደገ ነው ያለው። ግን እዚህ አገር ተስፋ አለ፤ ከገባን ከሰራን ተስፋ እንዳለን ያሳያል።
ኤክስፖርታችን ማደጉ ገቢያችን ማደጉ ፎሬይን ዳይሬክት ኢንቨስትመንት ማደጉ የኢኮኖሚው አካሄድ ምን ምልክት እንዳለው ያመለክታል። ሶስተኛ አራተኛ ፋይናንሻል ሴክተር ነው። ፋይናንሻል ሴክተር በየዓመቱ በቀጣይነት እንዳቀረብኩላችሁ ሪፖርት ከሪፎርም ማሻሻያ በኋላ ሃያ ሰባት ፐርሰንት ቦንድ አንዳንድ ክልከላዎች ካነሳን በኋላና ብድር ወደ መንግስት የሚሄደውን ወደ ፕራይቬት ሴክተር እንዲፈስ ካደረግን በኋላ ከፍተኛ መነቃቃቶች ታይተዋል።
የባንኮች አጠቃላይ ሃብት 2 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ብር ደርሷል። እዚህም ሃያ አንድ ፐርሰንት አድገናል፤ አጠቃላይ ሃብታችን። የቅርንጫፍ ቁጥር ደግሞ ስትመለከቱ 8242 ደርሷል። ቅርንጫፎች ከአምናው በአስራ ሰባት ፐርሰንት አድገዋል። ተደራሽነት ሰፍቷል ማለት ነው። ቅርንጫፎች እየሰፉ በመሄዳቸው ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የባንክ ደብተር ያላቸው ተገልጋዮች ከስተመሮች 82 ነጥብ 4 ሚሊዮን ህዝብ የባንክ ደብተር አለው።
አንዳንዱ አራት አምስት ሊኖረው እንደሚችል ታሳቢ አድርጋችሁ ማለት ነው። በቡክ ደረጃ ግን 82 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሰው ቡክ አለው። እነዚህ ቡክ ካላቸው ሰዎች ውስጥ ዲፖሲት የተደረገው ገንዘብ 1 ነጥብ 6 ትሪሊየን ብር ነው። ቅርንጫፍ በበዛ ቁጥር ደንበኛ በበዛ ቁጥር ሴቭ የሚያደርገውም ቁጥር ስለሚያድግ ከዚያ ሴቭ ከምናደርገው ሃብት ላይ ለማበደር ትልቅ እድል እናገኛለን ማለት ነው።
ዘንድሮ ለብድር የዋለው ሃብት 353 ቢሊየን ብር ነው ። ከዚህ ውስጥ ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት ዋናውን ድርሻ የሚወስደው የግሉ ዘርፍ ነው።በገቢ ተስፋ ሰጪ እድገት አለ። በኤክስፖርት ተስፋ ሰጪ እድገት አለ። በቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ተስፋ ሰጪ እድገት አለ ። ፋይናንሺያል ሴክተሩ በቀጣይነት እያደገ ነው ።
ይሄንን ትተን በሴክተር ብንመለከት ግብርና ከንግግር ወጥቶ ምርታማነቱ እንዲያድግ አንደኛው ያልነው ኩታገጠም ያልነው ሀሳብ ሁለት ጎን ለጎን ያሉ መሬቶች አስተሳስሮ ማረስ ብቻ ሳይሆን ፤ ሁለት አርሶ አደሮች አርቴፊሻል ድንበር አበጅተው ምርታቸው እንዳያንስ አዕምሯቸው ውስጥ መደመር ነው ፤ አዕምሯቸው ውስጥ ማስተሳሰር ነው። በጋራ ብናለማ፣ ማሽን ብንጠቀም የተሻለ ምርት እናገኛለን ብለው እንዲያምኑ ማድረግ ነው።
ሰው በአዕምሮው ሲደመር መሬት ማስተሳሰር ቀላል ስለሚሆን ኩታ ገጠም ትልቅ ውጤት እያገኘንበት ነው። አሁንም ስራ ይፈልጋል። የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዘንድሮ በተለያየ አለም እንደሰማችሁት አለም የመሰከረው ጉዳይ ነው ። ማዳበሪያ ውድ ሲሆን መንግስት ጫና ሲፈጥር መንግስት ከፍተኛ ሃብት ልክ እንደ ብድሩ ወደ አንድ ነጥብ 23 የሚጠጋ ቢሊየን ዶላር ለማዳበሪያ አውጥተናል፤ ከአምናው እጥፍ ነው ያወጣነው። ያ በቂ ስላልሆነ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በየአካባቢው እንዲመረት ሰፊ ስራ ተሰርቷል። ትልቅ ውጤት ተገኝቶበታል። ይሄም በቂ አይደለም ።
ኩታ ገጠም፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ካደረግን በኋላ ቅድም እንደተነሳው ደግሞ ለግብአት የሚሆን ፣ ለማሽነሪ ግብአት ታክስ እንዲነሳ ተደርጓል። ግብርናውን ለመደገፍ እንዲቻል። የውሃ አጠቃቀም ላይ አሁንም ብዙ ሥራ የሚጠበቅብን ቢሆንም ባለፉት ሁለት ዓመታት በሺህ የሚቆጠሩ ፓምፖች መጠቀማችን ከአንድ ጊዜ በላይ ለማምረትና ምርት ለማሳደግ አግዘውናል። ማሽነሪ አጠቃቀማችን እያደገ ነው። ኮምባይነር ፣ትራክተር በየቦታው እያደገ ነው።አሁንም ግን ሰፊ እንቅስቃሴ አለ።
የፋይናንስ አቅርቦትን በሚመለከት በበጀት ለግብርና ሚኒስቴር ለቆላማና ሎላንድ ሚኒስቴር ከተሰጠው በጀት በተጨማሪ በብድር ቅድም ያነሳሁላችሁ ብድር ፕራይቬት ከፈሰሰው ሃብት 34 በመቶው ለአርሶ አደር ለግብርና የሄደ ነው። አልነበረም የግብርና ኢንቨስትመንት ያንሳል፤ ሃብቱ ወደዛ ማፍሰስ አለብን ባልነው መሰረት 34 በመቶ ብድር ከግብርና ጋር ለሚያያዝ ኢንቨስትመንት የዋለ ነው። በዚህ ምክንያት ነው ውጤቱ እየተሻሻለ የመጣው። እዚህ ውስጥ ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱት ኤስኤምኤስ ናቸው።
እነዚህ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ከአነስተኛ ጥቃቅን ጋር በመሆን ከአርሶ አደር ጋር በመሆን እየሰሩ ያሉት ነገር ምንም እንኳን ውስን ሃብት ያላቸው ቢሆንም በጣም ከፍተኛ ነው። የማይክሮ ፋይናንስ ዘንድሮ ለ3 ነጥብ 8 ሚሊየን አርሶ አደሮች ብድር አቅርበዋል። ቅድም ያነሳሁላችሁ በትሪሊየን የሚቆጠር ብር የሚያንቀሳቅሱ ባንኮች 350 ሺህ ሰው አይሞላም የተበደራቸው ። ከ100 ሚሊየን ውስጥ 350 ሺህ ሰው የማይሞላ ነው የባንክ ሃብት ላይ በብድር የሚነቃነቀው። በማይክሮ ፋይናንስ ካላቸው ጥቂት ሃብት ግን 3 ነጥብ 8 ሚሊየን የሚጠጋ አርሶ አደር ብድር አግኝቷል።
እነዚህ እንደ አግሪካልቸር ባንክም የሚያግዙ ስለሆነ የክልል መንግስታት እናንተ እኛ ተጋግዘን አቅማቸውን ከፍ ብናደርግ ተደራሽነታቸው ሰፊ ስለሆነ በግብርና ላይ ከፍተኛ ውጤት ያመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። በፋይናንስና በተሰጠው አመራር ምክንያት የግብርና ምርታማነት ያው ሁላችሁም እንደምትታዘቡት አድጓል።
ባለፈውም ብዬዋለሁ አሁንም እደግመዋለሁ ! ንፁሃን አለአግባብ እየተገደሉም፤ በየቦታው ከሳሾች ጠዋት ማታ እየነዘነዙን በሚቀጥለው አመት ስንዴ ኤክስፖርት እናደርጋለን ። ስንዴን ኤክስፖርት ማድረግ እንዳንችል ሲያደርጉ ተሳክቶላቸዋል ። ስንዴን ኤክስፖርት ማድረግ ችለን መስዋዕትነት ካስከፈሉን አሸንፈናቸዋል ። ድላችን የሚረጋገጠው ያሰብነውን በማሳካት ነው።
ስንዴን ኤክስፖርት እናደርጋለን፤ ለዛ የሚያበቃ ሰፋፊ ስራ በዚህ ክረምት በሚቀጥለው በጋ እየተሰራ ነው። ኤክስፖርት ቅድም እንዳነሳሁት ትልቅ ውጤት ነው ያገኘነው። በግብርና አትክልትና ፍራፍሬ መጨመር በተወሰነ ደረጃ ሻይ ካስፋፋን ፤ቡናችን ካደገ ፤ማእድን ላይ የምንሰራውም ተስፋ ከሰጠ በሚቀጥለው አራት አመት አንዱ ትኩረት ማድረግና ውጤት ልናመጣ የሚጠበቀው ኤክስፖርት ላይ ነው።
በኤክስፖርት አመርቂ ስራ የሰሩ አገራት ናቸው የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት ማረጋገጥ የቻሉት። ይሕ ሁሉ መልካም ዜና እያለ ግሽበት ግን አሁንም የኑሮ ውድነት እያስቸገረን ነው። የኑሮ ውድነት ባለፉት አመታት እንዳልኩት ለሁለት አሰርት አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ እያደገ የመጣ ጉዳይ ነው። በዚህ ላይ በአለም አቀፍ ደረጃ የሚያጋጥሙ ቀውሶች ኢምፖርት ግሽበት ስላላቸው የራሳቸው የሆነ ጣጣ አምጥተውብናል። ነገር ግን በጀት ከኑሮ ውድነት ጋር ያለው ትስስር በጀት ስለሆነ እያየን ያለነው አንደኛ የበጀት ጉድለት ከየት ይሞላል ነው። ይሕ በጀት የኑሮ ውድነት ያባብሳል ወይንስ ይገራል ተብሎ የሚጠየቀው ጉድለት ከየት አምጥተት እንሞላላን ነው። ቀጥታ ከብሄራዊ ባንክ የምንበደር ከሆነ ግሽበት ይባባሳል። በተቻለ መጠን ጉድለታችንን ለማሟላት የምንጥረው ከግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ ነው። ይሕ የራሱ የሆነ ጠቀሜታ አለው። በተቻለ መጠን ከብሄራዊ ባንክ በቀጥታ ብድር ላለመሸፈን ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። አሁንም በቁጥጥር የምንመራው እሱን ይሆናል።
ሁለተኛ የገንዘብና ፊዚካል ፖሊሲ ቁጥጥርን ማጠናከር ነው። የሚፈሱ ሃብቶች በትክክለኛ መንገድ የሚፈሱ መሆናቸውን ይበልጥ መቆጣጠር ያስፈልጋል። ሶስተኛ ለድህነት ተኮር ዘርፎች ቅድሚያ ሰጥቶ በጀቱን መጠቀም ነው። ይሕ ሲባል ጤና፣ትምህርት ፣መሰረተ ልማት ያካትታል።
ለምሳሌ ጤናን ብንመለከት አዲስ አበባ ውስጥ በጣም በርካታ የግልና የመንግስት ሆስፒታሎች እየተሰሩ ነው። ጳውሎስ ብቻ ብትሄዱ ከአንድ ሺ አልጋ በላይ አቅም ያለው በዋና ዋና የኢትዮጵያ ችግሮች ላይ የሚያተኩር በካንሰር በኩላሊት ንቅለ ተከላ ላይ የሚያተኩር የሆስፒታል ማስፋፊያ ከ 80 በመቶ በላይ ደርሷል። ምናልባት በሚቀጥለው አመት እናጠናቅቃለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
ይሕ በህክምና አካባቢ ያለውን ችግር በእጅጉ የሚፈታ ነው። በትምህርት ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት በጣም በርካታ ሁለተኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ ነው። እነዚህ ነገሮች የሚደግፍ በጀት መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። 59 በመቶው የሚሆነው የዘንድሮው በጀት የሚውለው ድህነት ቅነሳ ላይ ነው። ይሕን በቁጥጥር እና ክትትል ስኬታማ ማድረግ ከቻልን ዜሮ ባያደርገውም ለድህነት ቅነሳ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል። ሌላው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አቅመ ደካሞች አዛውንቶች ቤት መስራትና ቤት ማደስ ነው። ይሕ ነገር ጨዋታ አይደለም። የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት የአሮጊቶች ቤት ማደስ ጨዋታ አይደለም። ትልቅ ስራ ነው። ተረባርበን ልናደርገው ይገባል። በየቦታው የእነርሱን ጩኸት እና ለቅሶ በእጅጉ ዋጋ ይደግፋል። የእናቶችን ከንፁህ ልብ የሚቀዳ ፀሎትና እንባ ፈጣሪ ያያል። ለእነርሱ የምናደርገው ማንኛውም ድጋፍ መልሶ አገር ይደግፋል። ብዙ ሙከራዎች አሉ። የግሉ ዘርፍ ከምትጠብቁት በላይ በዚህ ጉዳት ላይ እያገዘን ነው።
ሁላችንም መረባረብ አለብን። ይሕ ምክር ቤት ከደመወዙ ቀንሶ ደመወዝ የለውም አዎ ከደመወዙ ቀንሶ አንድ ሁለት ሶስት አሮጊቶች ቤት ቢያድስ በሚቀጥለው የተሻለ ምክር ቤት ይሆናል። የሚጠይቅ ብቻ ሳይሆን ችግር የሚፈታ ሲሆን ማለት ነው። ለሌላውም አርአያ ስለምትሆኑ፣ በየተቋማት ስለምትሄዱ ስንት ቤት ገነባህ፣ ስንት ቤት አደስክ ስለምትሉ የእናንተ መሳተፍ በእጅጉ ስለሚያግዝ መስራትም፤ መምራትም ይጠበቅባችኋል።
እንደምታውቁት 25 በመቶ የሚጠጋው የኢትዮጵያ ምግብ ነክ ነገር ከውጭ ነው እየገባ ያለው። ይህን ተሸክመን ኢንፍሌሽን ኢምፖርት እንዳይደረግ ማድረግ አንችልም። ሁሉም ይቅር እንዴት የማንጎ ጁስ ኢምፖርት እናደርጋለን። ማንጎ በአንዳንድ አካባቢ በኢትዮጵያ ውስጥ ከዛፍ ላይ ወድቆ እንደ ቡና ከመሬት ይለቀማል። ልናመርት፣ልናስፋፋ አንችላለን። ሙዝ ላይ የጀመርነው ፣አቡካዶ ላይ የጀመርነው፣ ማንጎ ላይ የጀመርነው ጉዳይ፤ በከተማ ውስጥ ሰላጣ ቆስጣ በርበሬ ድንች የጀመርነው ጉዳይ ቢስፋፋ ብዙ ችግር ሊያቃል ይችላል። ስንጀምረው ቀልድ ነው እየቆየን ስንሄድና ባህል ስናደርገው ግን ውጤቱ ከፍተኛ ነው።
ይህን ታሳቢ አድርገን ብንረባረብ ምርት ካደገ የገንዘብ ስርአትን ከተቆጣጠርን ግሽበት ዘንድሮም ቢሆን ከብዙ ሀገራት አንጻር የጀመረነው ነገር ስላገዘን ጥሩ ነገር አለ። የበለጠ ይጠናከራል። አሁን ግን ዛሬ አነስተኛ ገቢ ያላቸው የመንግስት ሰራተኞች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች በጥቅሉ በእለት መኖር እየተሰቃዩ ነው። በእለት መኖር ኢትዮጵያ ውስጥ ፈተና እየሆነ ነው። ይህንን ጉዳይ ለመፍታት እንደው የግሽበትን ጉዳይ ምን እናድርግ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ባለው አቅምና ቦታ መስራት እኛ ደግሞ ባለን ሃላፊነት ገንዘብ ላይ ቁጥጥር ማድረግ፤ፖሊሲዎቻችንን መፈተሽ ምርታማነትን ማሳደግና አንድም ማረጋጋት ሁለተኛም ደግሞ የሚበላ ነገር እንዲበዛ ማድረግ ይኖርብናል። በዚህ አካሄድ ከሄድን ምን አልባት የተሻለ ውጤት እናገኛለን ተብሎ ይጠበቃል።
የህዝብ ቆጠራ ሳይደረግ በጀት ሲመደብ ኢፍትሃዊ አይሆንም ወይ ለተባለው፤ ቆጠራ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። የህዝብ ቆጠራ ለሁሉም አይነት ጋኒክ ያግዛል ማንኛውም የምናስበው ነገር ይሄ ከጠባቂነት ከፌዴራል መንግስት ከሚሰጠው ገንዘብ አንጻር ሳይሆን ለማንኛውም ፕላኒንግ ቆጥረን አውቀን የምናደርገው ነገር ጠቃሚ ነው። እና ቢሰራበት የሚለው ምክረ ሀሳብ እንደ ጥሩ ነገር ነው የሚወሰደው።
ነገር ግን አሁን ፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀመር ሲወስኑ ሙሉ ስልጣኑ የእነሱም ቢሆን እናንተ ስልጣናችሁ በቀረበው ቀመር ላይ በጀት ማጽደቅ ቢሆንም እንኳን ግን ፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀመር ሲያጸድቅ ሁላችሁም እንደምታውቁት ሳይንሳዊ ፕሮጀክሽን ታሳቢ አድርጎ ነው። ዝም ብሎ አይደለም ፤ሙያተኞች አሏቸው አጥንተው፣ ክልሎች ተወያይተው ነው የሚወስኑት። ያ ነገር ትክክል አይደለም ካልን በተናጥል የሚጎዳው፤በተናጥል የሚጠቅመው ሰው የለም። ምክንያቱም የተቆጠረ ሰው ወይንም ክልል የለም፤ሁሉም ክልል አልተቆጠረም።አደገኛ የሚሆነው ከፊሉ ተቆጥሮ ከፊሉ ያልተቆጠረ ቢሆን ነው።
አሁን የነበረውን ቆጠራ አዲስ ቆጠራ አድርገን እስክናስተካክል ድረስ ሳይንሳዊ ፕሮጀክሽን እያደረጉ ከፍ ከፍ ያለ በጀት የሚጠቀሙ ክልሎች ደግሞ አሁን አሁን ፌዴሬሽን ሲሰበሰብ ሰምታችሁ ከሆነ እየተነጋገሩ እየቀነሱ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ክልሎች ኮታቸውን እየለቀቁም ጭምር ነው።ትክክል የሆነ የቁጥር ስራ ብቻ ሳይሆን የድርድር ነገርም ያለበት አቀራረብ ስለሆነ ከፍትሃዊነት አንጻር ችግር አለበት ብዬ ብዙ አልገምትም።
ግን ቆጠራው ያስፈልጋል፤ ቆጠራ አድርገን ፕላን እናድርግ የሚለው ሀሳብ ትክክል ይመስለኛል። ወደፊት ሁኔታዎች ሲስተካከሉ ወደዛ መሄድ ይኖርብናል ። አሁን ለግዜው ግን ፌዴሬሽን ምክር ቤት ባቀረበው ቀመር መሰረት የእኛ ስልጣን በዚህ አግባብ መወሰን ስለሆነ እሱን ማየት የሚሻል ይመስለኛል።
መሰረተ ልማትን በሚመለከት ብዙ ጥያቄዎች ተነስተዋል። በመንገድ፣ በኤሌክትሪክ ፣በውሃ ፣በስኳር፣የመንገድን መሰረተ ልማት ብቻ የተከበረው ምክር ቤት ግንዛቤ እንዲኖረው ወደ ሶስት መቶ ሰላሳ አንድ የግንባታ ፕሮጀክቶች የፌዴራል መንግስት (ኢራ) ያስተዳድራል። ከአርባ ዘጠኝ በላይ ከባድ ጥገና እየተሰራ ይገኛል። ከሶስት መቶ ሰላሳ አንድ የግንባታ ፕሮጀክቶች ውስጥ ሁለት መቶ ሀያ ስድስቱ ብቻ ሶስት መቶ ሰባ ዘጠኝ ቢሊየን ብር ፋይናንስ ይደረግባቸዋል።
ኢራ የምንለው ትንሽ ተቋም በመቶዎች በሚቆጠር ፕሮጀክት በቢሊየን የሚቆጠር ብር ያስተዳድራል። በዚህ ምክንያት ብዙ ኮንትራት የሚያስተዳድር ስለሆነ እያንዳንዷን ፕሮጀክት ተቆጣጥሮ ሁሉን በእኩል ፍጥነት ማስኬድ ምን ያክል አዳጋች ስራ እንደሚሆን እናንተም መገመት ትችላላችሁ። መቶ አምስት የሚደርሱ ፕሮጀክቶች በዲዛይን በጨረታ ፕሮሰስ ላይ ያሉ ናቸው።
አንዳንዴ ዲዛይኑና ጨረታው ካለቀ በኋላ የፌዴራል መንግስት በጀት ይዞ በራይት ኦፍ ዌይ ምክንያት ክልሎች በሚፈጥሩት በጣም አስቸጋሪ ጉዳይ ፕሮጀክቶች አይጀመሩም ይጓተታሉ። ከተጀመሩም በኋላ ግማሹ ሄዶ ግማሹ ላይ እንደምታውቁት ችግር አለ። ነገር ግን ኢራ በአዲሱ ሪፎርም በከፍተኛ ደረጃ ፕሮጀክት መጨረስ የሚለው ሀሳብ አንዱ ኢምፕልመንት የምናደርገው።እነሱ ጋር ስለሆነ በጣም ስለሚረባረቡ እንደተቋም ስለሚረባረቡ እየተገኘ ያለው ውጤት ከፍተኛ ነው ሊባል ይችላል።
የጀመርናቸው አብዛኛው መንገዶች በግጭት ራይት ኦፍ ዌይ አይነት ምክንያቶች ካልሆነ በስተቀር የተጀመሩት መንገዶች በሙሉ በጥሩ ሂደት ላይ ይገኛሉ። አልፎ አልፎ ቀደም ሲል እንደተነሳው ችግር ያለባቸው ፕሮጀክቶችም አሉ። ለምሳሌ ከአርበረከቴ እስከ መቻራ ሐረር አካባቢ የሚሰራው የተጀመረው የዛሬ 7 ዓመት አካባቢ ነው፤ የቆየ መንገድ ነው። እና ይሄ መንገድ በቆየ ኮንትራት ውስጥ ከመኖሩ ባሻገር መጀመሪያ ራይት ኦፍ ዌይ ችግር ነበረበት። እሱ ሲፈታ ኩባንያው ከገቢዎች ሚኒስቴር ጋር የማይግባባበት ከግብር ጋር የሚያያዝ ጉዳይ ሁለት ዓመት ሙሉ አካውንት ተዘግቶበት ነበር።
ኩባንያው በዛ ምክንያት ሥራው ተጓቷል፤ በቅርቡ ተፈቶላቸው ሥራ ጀምረዋል። በፍጥነት እንደሚጠናቀቅ ተስፋ እናደርጋለን፤ አመራርም እየተሰጠበት ነው ያለው። እንደተባለው የሐረር አካባቢ ማሕበረሰብ ሕይወቱን ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል። ከፕሮጀክት አንጻር የተጀማመሩ ነገሮች አሉ ።ያን አጠናክረን እንቀጥላለን። ቀድሞ የተበላሸውን እናስተካክላለን፤እኛ የጀመርነውን እናፋጥናለን፤ እናንተም በቁጥጥር ታግዛላችሁ፤ እንደሚሳካ ተስፋ አለኝ።
ከጎዴ ጊኒር የሚሄደው መንገድ እንዲህ ቀላል አርገን የምናነሳው መንገድ አይደለም። 220 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል። ከሆነ ክፍለ ሀገር አዲስ አበባ ያለ ዋና ዋና መንገድ ብላችሁ አስቡት። ከጎዴ ጊኒር የሚሄደው መንገድ 220 መሆኑ ብቻ ሳይሆን ላንድስኬፑም ቀላል አይደለም። ዳገታማ፣ ሞቃታማ አካባቢ ሰፊ የዲዛይን ሥራ የሚጠይቅ ቦታ ነው።
መንገዱ ሲሳካ በከፍተኛ ደረጃ ሱማሌን ከመካከለኛው ገበያ ጋር የሚያገናኝ ስለሆነ እጅግ ጠቃሚ ነው። እና ተለቅ ያለ ፕሮጀክት አሁን ዘንድሮ ከያዝናቸው ሰፋፊ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ መሆኑን ከግምት ማስገባት ፤ይሄም በብዙ ሎት ተከፋፍሎ የሚሰራ ነው፤ ሰፊ ስለሆነ። የመጀመሪያው ሎት በቅርቡ ይጀምራል። እናንተም ድጋፍና ቁጥጥር ካረጋችሁ በተያዘለት ጊዜ ይከናወናል የሚል ተስፋ አለኝ።
ኤሌክትሪክ በሚመለከት፤ ያው ኤሌክትሪክ አንደኛ ኃይል ማመንጨት፣ ሁለተኛ የመነጨውን ኃይል ማስተላለፍ፣ ሦስተኛ የተላለፈውን ኃይል ማከፋፈል፣ የተከፋፈለውን ኃይል ደግሞ ማሰራጨት የሚባሉ አራት አንጓዎች አሉት። ስላመረትን ብቻ ሄዶ ኢነርጂ አይሆንም። ካመረትነው ምርት ውስጥ በማስተላለፍ ሲስተም ውስንነት ምክንያት ከ30 ፐርሰንት ያላነሰ ሎስ ያጋጥማል።
ኢነርጂው እያለ ከአንዱ ጫፍ አንዱ ጫፍ እስኪሄድ ይንጠባጠባል ኃይል፤ ያው ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን በነበረው አሰራር እንደምታውቁት ናሽናል ግሪድ ነው የምንጠቀመው፤ የትም ተመርቶ ኢነርጂው ወደ ናሽናል ግሪድ ገብቶ ኢነርጂው ይሰራጫል። ይሄ የራሱ ጥቅምም ጉዳትም አለው።
እንደ ኢትዮጵያ ያለ እዚህም አንድ ሺ ሰው እዛም አንድ ሺ ሰው ከተማ ከተማ የሚባልበት የተበተነ ሕዝብ ሲኖር በጣም አስቸጋሪ ነው። እኛ አርባናይዝ አይደለንም፤ በሦስት አራት ከተማ የምንኖር ሕዝቦች አይደለንም። በየቦታው ስትሄዱ ትናንሽ መንደሮች አሉ። ሁሉም ደግሞ ኤሌክትሪክ ዲማንድ ያደርጋል፤ ይፈልጋል።
አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ 110 ሺ ኪሎ ሜትር የማሰራጫ መስመር አለ። 110 ይፈለጋል፣ ይበጠሳል። ከተበጠሰ በኋላ ጥገና በጣም አስቸጋሪ ነው። አሁን ለምሳሌ ሲዳማም የራሱ ሎካላይዝ የሆነ ግሪድ የሚጠቀም ቢሆን ጥገናውም ምናምን ይቀንሳል። አርባምንጭም የራሱ የሚጠቀም ቢሆን ይቀንሳል፤ እዛው እያመነጨ የሚጠቀም ቢሆን ከተወሰነ ቦታ መንጭቶ ትራንስፖርት ሲደረግ ግን ችግር አለበት።
ሲዳማ ባልተፈጠረ ችግር አዳማ ባለ ችግር ሲዳማ ጨለማ ውስጥ ሊያድር ይችላል። ከናሽናል ግሪድ ስለሚሄድ ማለት ነው። ይሄንን ችግር ለመፍታት በሂደት ናሽናል ሄድን ወደ ኦፍ ግሪድ የምንቀይርባቸውን መንገዶች በተለይ ለአዲስ ፕሮጀክቶች እያሰብን እየሰራንበት እንገኛለን። ሁለተኛ ደግሞ አርበናይዜሽን እየሰፋ ሲሄድ በተወሰነ ደረጃ ይሄንን ይቀንሰዋል የሚል እምነት አለ።
አሁን ባለው ሁኔታ ግን በአራቱም በ ማ ምረ ት ም ፣ በ ማ ስ ተ ላ ለ ፍ ም ፣ በ ማ ከ ፋ ፈ ል ም በማሰራጨትም በጣም ሰፊ ሀብት ፈሶ እየተሠራ ነው። ኢትዮጵያ አሁን የያዘችውን ፕሮጀክቶች ስታጠናቅቅ አሁን ካለው ኢነርጂ እጥፍ በላይ ታገኛለች። በምርት ማለት ነው። ምርቱ ብቻውን በቂ አይደለም። ህዳሴ እኮ ምርት አልጀመረም በምንልበት ጊዜ ምርት ከህዳሴ ወደ ናሽናል የሚያስተላልፈው መሥመር ከተሰራ ሥንት አመት አልፎታ፤ተቀምጧል ኢነርጂው ሳይኖር። አሁን ሲጀመር ደግሞ ጠግኑኝ ይላል ማለት ነው። ብዙ ዓመት ስለተቀመጠ ጠግኑኝ ይላል። ቴስት መደረግ ስላለበት። በዚህ አግባብ ቢታይ ጥሩ ነው ።
ሲዳማ ላይ አራት ሰብስቴሽን ነው ያለን ሐዋሳ ቁጥር አንድ፣ ሐዋሳ ቁጥር ሁለት ፣ይርጋም እና አዋራ ላይ ሰብስቴሽኖች አሉ። 70 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ መካከለኛ ጥገና ዘንድሮ አካሂደናል። ሲዳማ ክልል ብቻ። 33 ኪሎ ሜትር ዝቅተኛ መስመር ግንባታ ሰርተናል ። 27 የሚጠጉ ትራንስፎርመሮች አቅማቸው ከፍ እንዲል ተሰርቷል። በዚህም ከ83 ሚሊዮን በላይ ወጪ አድርጓል የፌዴራል መንግስት። ለሲዳማ ክልል ብቻ ። ኤሌክትሪክ ላይ ማለት ነው።
ከይርጋለም ወደ አለታ ወንዶ የሚሄደውን መሥመር በሚመለከት ከወርልድ ባንክ ጋር ድርድር ጀምረናል። ፋይናንሱ ሲገኝ የሚጀመር ይሆናል። ሁላችሁም እንደምታውቁት ኢትዮጵያ ሁለም ጫፍ መንገድ ይፈልጋል፤ሁሉም ጫፍ መብራት ይፈልጋል፤ ሁሉም ጫፍ ከፍተኛ ሰርቪስ ይፈልጋል። ይሄን አንድ ጊዜ ማሟላት ይከብዳል። አቅም በፈቀደ መጠን ግን ለመመለስ ጥረት እየተደረገ እንዳለ ከግምት እንዲገባ ነው።
ውሃን በሚመለከት የጎዴ መስኖ በደርግ ጊዜ የተሠራ ነው። በጣም ትልቅ ጠቀሜታ ያለው ፕሮጀክት ነው። ባለፉት 30 ዓመታት ግን ምንም ጥገና ሳይደረግለት ስለ ቆየ ያ ፕሮጀክቱ በጣም ሰፊ ሥራ ይፈልጋል። የመስኖ እና ሎላንድ ሚኒስትሪ አንዱ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ከለበት ፕሮጀክት ውስጥ የጎዴ መስኖ ነው። ከተሳካልን ብዙ ሺህ ሄክታር ልናርስበት እንችላለን። ቀላል ሥራ ግን አይደለም።
ረዥም ጊዜ የቆየ ነው፤ በጣም ብዙ ሀብት እና ጊዜን ይጠይቃል። የሸናሌ ከርሰ ምድር እንደዚሁ በሚኒስትሪው እየተሞከረ ነው ያለው። ሚኒስትሪው አዲስ በዚህ ዓመት የተቋቋመ ስለሆነ በፕራዮሪቲ ለይቶ እየሠራባቸው ካሉ ሴክተሮች እና ፕሮጀክቶች መካከል ውስጥ ስላሉ በእነሱ ውስጥ ውጤቱን ወደ ፊት የምናይ ይሆናል።
ስኳርን በሚመለከት በቀደም እንስቼላችኋለሁ። አምስት ተጨማሪ ፋብሪካዎች ጨምረን ምርት ለማሳደግ ሞክረናል። አሁንም ሠፊ ሥራ ያስፈልጋል። በተለይ አገዳ ላይ ። ፋብሪካ ሲሠራ አገዳ የለም ፤ አገዳው ሲመጣ ፋብሪካው አይሠራም ።እንደዚህ አይነት ችግር ፈተን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ እና በሀገር ውስጥ ያለውን ፍጆታ ማሻሻል ያስፈልጋል።
ስኳር ኢምፖርታንት ነው። በሌላ መንገድ ደግሞ በተቻለ መጠን ምቹ ሁኔታ ሲያጋጥም ስኳር የመጠቀም ልምዳችን እንዲቀንስ ማድረግ ጥሩ ነው። ስኳር ከጥቅሙ ያላነሰ ጉዳት ስላለው በተቻለ መጠን በተለይ የምክር ቤት አባላት በተቻለ መጠን ስኳር እኛቤት በቤት ደረጃ ህግ አውጥተናል ስኳር እንዳይገዛ ብለን። ልጆቻችን ጋር ጸብ ነው።
ውድ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ስኳር ያው የጎንዮሽ ጣጣ ስላለበት መመጠን ጥሩ ይሆናል ከተቻለ። እንደው ዜሮም ባይሆን መመጠን ጥሩ ነው ያምቢሆን ግን አምርተን ፍላጎቱ ከፍተኛ ስለሆነ ሰፊ ስራ መሥራት ያስፈልጋል። በጎን ማስተማር በጎን ማምረት ሁለቱ ጎን ለጎን ከሄዱ ውጤቱ ያማረ ይሆናል።
ደረቅ ወደብን በሚመለከት አሁን ስምንት አሉን በተለያዩ ካፓሲቲ የሚሠሩ ስምንት ደረቅ ወደቦች አሉን። በ10 ዓመት እቅዳችን ወደ 11 እናሳድጋቸው ብለናል። ወደብ ማሳደግ የሚያስፈልገው የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር በጣም ከፍተኛ ነው ።የእኛን አይነት የሕዝብ ቁጥር ያለው ወደብ የሌለው ሀገር ዓለም ላይ የለም ። ከመቶ ሚሊዮን በላይ ህዝብ ኖሮት ወደብ የሌለው ሀገር የለም። ይሄ ኢኮኖሚያችን ላይ ከፍተኛ ጫና ያመጣል። በዚህ ምክንያት በአገራችን ውስጥ ደረቅ ወደቦችን እያስፋፋን እንገኛለን።
ከባህር ላይ ስናመጣ አብዛኛውን ስራ በሀገር ውስጥ ለመስራት እንዲያመቸን። ምርት እያደገ ነው፤ ኤክስፖርት እያደገ ነው ፤ ኢምፖርት እያደገ ነው። በጣም ኢምፖርታንት ነው ይሄ ነገር። ሎጀስቲክስ ላይ ባወጣነው ስትራቴጂ መሰረት የሎጀስቲክስ መሰረት ማዘመን ካልቻልን ኤክስፖርት አያድግም። ኢምፖርት አያድግም። አጠቃላይ ኢኮኖሚው አያድግም ። ምርታማነት አለ ግን ገበያ ሊወጣ አይችልም። ሎጀስቲክስን ማጠናከር ወደፊትም ያስፈልጋል። የጀመርነውን ስራ ከዛው ጋር ተያይዞ የሚታይ ነው። ደረቅ ወደብ ለግሉ ዘርፍ ከፍተናል። መንግስት ባይሰራም የግሉ ዘርፍ ገብቶ እንዲያለማ በፖሊሲ ያሻሻልንበት ዋናው ምክንያት ኢምፖርታንት ሴክተር በመሆኑ ነው። ዘንድሮ ቡና አንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ገብተናል ።ለመጀመሪያ ጊዜ ብያችኋለሁ። በአፍሪካ ትልቁን ኤክስፖርት ያረግነው እኛ ነን ። ያገኘነውም እድገት በጣም ከፍተኛ ነው።
እዚህ እድገት ውስጥ እጥረት የንግድ ስርዓቱ እንደተጠበቀ ሆኖ የሎጂስቲክስ ስርዓቱ በጣም ከፍተኛ ነው። እስካሁን እኛ ቡና በጆንያ ነበር የምንልከው። በጆንያ ስንልክ ሁለት ችግር አለ። አንድ የጥራት ችግር አለ ሁለት ደግሞ ቅሸባ አለ። በየመንገዱ ይቀሸባል። ዘንድሮ 98 በመቶ ቡና ኤክስፖርት የተደረገው በኮንቴነር ነው።
በዚህ ምክንያት ብዙ አክተሮች የለፉበት ጉዳይ ቢሆንም በሎጂስቲክስ ድጋፍ ምክንያት ኤክስፖርታችን ማዘመን ተችሏል። ለአቦካዶና ለፍሩት እንደዚህ አይነት አቅም እየፈጠርን ከሄድን የራሱ የሆነ ትራክ ስለሚፈልግ ለኤክስፖርታችን ከፍተኛ ትርጉም ይኖረዋል። እሱን በርብርብ ለመስራት ጥረት ይደረጋል።
ኮይሻ ጎርጎራ መሰል ፕሮጀክቶች የተባለው ፕሮጀክቶቻችን ቃል በተገባው መሰረት በከፍተኛ ርብርብ እየተሰራ ነው። ጎርጎራ ሙሉ ግንባታውን ለማጠናቀቅና ፊኒሺንግ ላይ ለመድረስ ለፊኒሺንግ ማቴሪያል ኮንትራት የገባናቸው በሙሉ ተሰረዙብን። የጎርጎራ የፊኒሺንግ እቃ በአንዳንዱ ለምሳሌ የሲሊንግ ማቴሪያል መብራት ሊሆን ይችላል፤ ፈርኒቸር ሊሆን ይችላል። እያንዳንዱ ፕሮጀክት ከመቶ ፐርሰንት በላይ ዋጋ ጨምሯል። ይሄ ለምነን የምንሰራው ፕሮጀክት ስለሆነ በኮንትራክተሩ ላይና በፕሮጀክት ማኔጅመንቱ ላይ ከፍተኛ ችግር አስከትሏል።
ያም ሆኖ ተጨማሪ ጥረቶች በማድረግ ጊዜውን ጠብቆ እንዲጨረስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው። ጎርጎራ ኮይሻ ሲባል ሰዎች ቀላል አድርገው ነው የሚያዩት ጎርጎራ አጠናቀን ስራ ስንጀምር በአፍሪካ ካሉት ጥቂት ሁለት ሶስት ምርጥ ዴስትኔሽኖች አንዱ ነው የሚሆነው። እጅግ በከፍተኛ ኳሊቲ ለመቶ ዓመታት እንዲቆይ ተደርጎ ከአካባቢ ጋር ተዋህዶ የተሰራ ነው። ነገር ግን ጎርጎራ የሚሰራው ቦታና መነሻ ጋር ሲሆን ጎርጎራ የምትባል ትንሽዬ ከተማ ጎኑ አለች።
ጎርጎራ የሚባለው ፕሮጀክት አሜሪካ ማለት ነው። ጎርጎራ የምትባለው ከተማ ኢትዮጵያ ማለት ነው። ይሄን ፕሮጀክት የሚመጥን የህዝብ ኑሮ አብረን ማሰብ ካልቻልን እዚህ ጋር ገነት እዚህ ጋር ረሀብ ማስተናገድ አይቻልም። መስራታችን መልካም ነው። ይሄ ፕሮጀክት ከተሰራ ትሩፋቱ የእነዛ ከተማ ወጣቶች ድሀዎች ስራ አጦች ሂወት እንዲይዝ ሌላ ድልድይ ያስፈልጋል ማለት ነው። አለበለዚያ ሰው እዚህ ሀብታም እያስተናደ እሱ ችግር እየሆነ ይቸገራል። ስራው ግን እጅግ አስደማሚና የኢትዮጵያ ቱሪዝም ብዙ ነገር ከፍ የሚያደርግ ነው። ኮይሻም እጅግ በጣም በጣም ጥሩ ፕሮጀክት ነው ወደፊት እንግዲህ እድል ሲገኝ እየሄዳችሁ ታዩታላችሁ። ከሚቀጥለው ዓመት የመጀመሪያው ኳርተር አካባቢ ጀምሮ አብዛኛዎቹ መመረቅ ይጀምራሉ። ጊዜውን ጠብቀው ይጠናቀቃሉ ለህዝባችን ቃል በገባነው መሰረት ከሰራን በኋላ ተመልሰን ገበያ የሚመጣበትን መንገድ እንሰራለን።
ከነዚህ ውጪ ያጠናናቸው ቦታዎች አሉ። በርከት ያሉ ቦታዎች ያጠናናቸው አሉ ነገሮች ሲረጋጉና ገንዘብ የምናገኝባቸው መንገድ ሲፈጠር እነሱን እያለማን ሀያ ሰላሳ አርባ ዴስትኔሽን ኢትዮጵያ ውስጥ እንፈጥርና ወደ ውጪ የወጣውን ገበያ በተለይ ሎካል ቱሪዝሙን እናስቀራለን።
ለምሳሌ እዚህ አካባቢ ሁሌ የምታነሱት ከላይብረሪ ጀምሮ ሳይንስ ሙዚየም ፓርኪንግና ዩኒቲ ፓርክ ሙሉ ለሙሉ መስከረም ስራ ላይ ይውላሉ። እስከ መስከረም የምንቆየው ክረምቱን ሳሩ አበባውን ለመትከል እንጂ ፕሮጀክቱ እንዳያችሁት እያለቀ ነው። ይሄ በሚጠናቀቅበት ሰዓት በአለም ላይ ዋሽንግተን ፓርክ፣ እንግሊዝ ለንደን ከተማቸው መሀል እንደዚህ አይነት መዳረሻ የላቸውም።
የናንተ ስለሆነ እንዳትንቁት እዚህ ቦታ ላይ ታሪክ አለ የመጀመሪያው አልፋ ቤት አለ ፤የመንግስታት ታሪክ አለ፤ ጥንታዊነት አለ፤ላንደስኬፕ አለ ፤ኔቸር አለ ፤ እርሻ አለ። ብዙ ኪሎ ሜትር ሰዎች በእግራቸው ተጉዘው ብዙ እውቀት የሚቀስሙበት ነው ። ለንደን ከሄድን አንዱን እዚህ ጋር አንዱን ማዶ ታገኛለህ እንጂ አንድላይ አታገኝም። ዋሽንግተን ከሄድ አታገኝም። ከነሱ የምንማረው ብቻ ሳይሆን ከእኛ የሚማሩት እንዳለ ማሰብ ጥሩ ነው፡፤
ይሄ ብቻ አደለም የታችኛው ቤተ መንግስት እድሳት ተጀምሯል። መሀል ላይ ያለው ቆሻሻ ቦታዎች ፈርሰዋል። ታችናው ቤተ መንግስት ውስጥ ያሉት የኢትዮጵያ ሀብቶች ታሪኮች በትክክል ግልጥ ብለው ለህዝብ ከታዩ ብዙ ችግር ይፈታሉ። ሌላው አሁን የምንጣላባቸው የወሰን ጉዳዮች ቁልጭ ብለው በካርታ የዛሬ መቶ አመት ቤተ መንግስት አለ። አያውቀውም ህዝቡ። እሱን ስናወጣ ታሪካችን ሲወጣ ቱሪዝም ብቻ አይደለም ልካችንም ከፍ ይላል።
ይሄንን ሰዎች ስለማያውቁ ሲያናንቁት ይታያሉ። በዚህ አትቸገሩ ይሄን ማወቅና ማልማት ቢችሉ ለምን ደሀ ሆነን ቀረን። ስላልቻሉ ነው እኮ ያልሆነው። እነሱ እየተቹ እኛ እየሰራን ፍሬ ስናመጣ የነሱ ልጆች ለኛ ዘብ ይቆማሉ። አሁን ያለው ሰው አልተረዳም በሚል መቸገር የለባችሁም ። የሚሰራው ፕሮጀክት ሁሉ የኢትዮጵያን ከፍታ አሁን ካለበት ወደሚቀጥለው ደረጃ የሚወስድ ነው። ይሄን አስበን አጥንተን አልመን በኢምጅነሪ ፓወር የምንሰራው ስለሆነ ብዙ የሚያሰጋ ነገር አይኖርም ፤እናንተም እያያችሁ ድጋፍ ማድረግ። ባለፈው እንደጎበኛችሁት ብዙ ግብዓት እንደሰጣችሁ አውቃለሁ። እሱን ማጠናከር ያስፈልጋል። በጊዜው ያልቃል የሚል ተስፋ አለኝ።
(ይቀጥላል)
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 4 ቀን 2014 ዓ.ም