ኢትዮጵያ የታሪክ፣የተፈጥሮ ቅርሶችና የብዝኃ ባህል ባለቤት ነች። ይሁንና ጥቂት የቱሪዝም መስህብ ካላቸው አገራት ጋር ስትነጻጸር ግን ከዚህ ሀብት የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅምና በእጅጉ አነስተኛ መሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ። ለእዚህ ኬኒያን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል። በኢትዮጵያ ከፍተኛ ነው ተብሎ በቀዳሚነት ከተመዘገበው ከ920 ሺህ በላይ ቱሪስት ፍሰትና የ3ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ጋር ሲነፃፀር የእነርሱ የሩብ ዓመት አፈፃፀም መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። እነዚህ መረጃዎች የሚያመለክቱት የቱሪስት ፍሰቱ በእጅጉ አነስተኛ መሆኑን እንዲሁም ከመጣው ቱሪስት የተገኘው ሀብትም ቢሆን አነስተኛ መሆኑን ነው።
ሀገሪቱ ቱሪስት ብዙ ቆይታ የማያደርግባት በመባልም ትታወቃለች። ቱሪስቶች በኢትዮጵያ ያላቸውን ቆይታ እንዳያራዝሙ ከሚያደርጉና ይዘው የመጡትን ገንዘብ ይዘው እንዲመልሱ ከሚያስገድዱ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ያነሳሉ። ከዚህ ውስጥ አንዱ ደረጃውን የጠበቀ የቱሪስት ታክሲና ራሱን የቻለ የትራንስፖርት አገልግሎት በበቂ ሁኔታ አለመኖር ዋንኛው ነው።
ትራንስፖርቱ ቢገኝ እንኳ የአገልጋይነት ስሜት የተላበሰና ስለኢትዮጵያ (ስለ መዲናዋ አዲስ አበባ) የቱሪስት መዳረሻዎች በቂ እውቀት ያለው አሽከርካሪ አለመኖሩንም ነው እየተጠቆመ ያለው። ይህም የቱሪስቱን የመቆየት ፍላጎት ይቀንሳል። ይህ ችግር እንደ ዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ጥናት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመጡ ቱሪስቶች ይዘው ከመጡት ገንዘብ አብዛኛውን መልሰው ከሚሄዱበት ምክንያት እንደ አንዱ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃትና ከዚያ የሚገኘውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ መንግሥት ሰፋፊ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየሠራ ይገኛል። በዘርፉ የተሰማሩ የግል ባለሃብቶችም ሆነ ማኅበራት ከመቼውም ጊዜ በተሻለ የተነቃቃ እንቅስቃሴ ውስጥ እየገቡ ናቸው።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በቅርቡ የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር ከዚያም በላይ ደግሞ ረጅም የቆይታ ጊዜ እንዲኖረው ከሚያስችሉ አገልግሎቶች መካከል አንዱ የሆነው የትራንስፖርት ዘርፍ ከቱሪዝም ዘርፉ ጋር እንዲጣጣም ለማድረግ የሚሠሩ አካላት ብቅ ብለዋል። በተለይ የቱሪስት ታክሲ ፅንሰ ሃሳብን በአገራችን በማስተዋወቅና ለጎብኚዎች በቂ መረጃ የሚሰጡ ደህንነታቸው በተጠበቀ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርጉ ማኅበራትን በማደራጀት ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ “2ኤም ቲ” የተባለ የግል ማኅበር ከመንግሥት ባለድርሻ አካላት ጋር እየሠራ መሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በተገባደደው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ከቱሪስት ታክሲ ጋር በተያያዘ ከላይ የጠቀስነው ማኅበር የስልጠናና የምክክር መድረክ አዘጋጅቶ ነበር። ይህም የጎብኚዎችን ቆይታ ያራዝማሉ ተብለው ከሚታሰቡ ጉዳዮች መካከል ቀዳሚ የሆነው የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን የታሰበ ነበር። በተለይ ጎብኚዎችን ብቻ ለማስተናገድ ለተደራጁ የቱሪስት ትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ ማኅበራት ስልጠና የሰጠና አዲስ አበባ ያላትን እምቅ የመስህብ ሃብት የተገነዘቡና የአገልጋይነት መንፈስ የተላበሱ ትራንስፖርት ሰጪዎች እንዲኖሩ ታሳቢ ያደረገ ነው።
ስልጠናው በተለይ በኢትዮጵያ ዋና ከተማና የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ስለሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች፣ ስለመልካም መስተ ንግዶና ተግባቦት እና መሰል በዘርፉ ትራንስፖርት አገልግሎት አስፈላጊ ስለሆኑ ጉዳዮችም መድረኩ ተነስቶበታል። ሌላው በቅርብ ጊዜ ውስጥ የአሠራር ሥርዓትና ሕጋዊ ጉዳዮችን አጠናቆ አገልግሎት መስጠት የሚጀምሩ “የቱሪስት ታክሲና” በስሩ ስለተደራጁ ከሦስት ሺ በላይ ሰዎችም መረጃዎችን ሰጥቷል።
“የቱሪዝም ልማቱን ለማዘመን ውጤታማና ዘመናዊ የቱሪዝም አገልግሎት ሰጪ ትራንስፖርት አቅርቦት በሁሉም የቱሪስት መዳረሻ ስፍራ” በሚል መሪ ሃሳብ ስልጠናውን ያዘጋጁት የ2 ኤም ቲ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መሥራች አቶ መሳፍንት ዘውዱ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት፤ 2 ኤም ቲ ቱሪስቱን ብቻ የሚያገለግሉና በሁሉም የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ላይ አገልግሎት የሚሰጡ የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ታክሲዎች መኖር ጠቀሜታው የጎላ ነው። አገልግሎቱ መኖሩ ብቻ ትርጉም ስለማይሰጥ መልከዓ ምድሩን የሚመጥኑና ደረጃቸውን የጠበቁ መኪኖች፣ አገልጋይነት የተላበሰ ሰብዓዊ ልማት ያስፈልጋል። ስልጠናውም ይህን ታሳቢ በማድረግ ነው ለማኅበራቱ የተዘጋጀው።
እንደ አቶ መሳፍንት ገለጻ፤ ሀገራችን ካላት እምቅ የቱሪዝም ሃብት አንፃር የሚገባትን ያህል ተጠቅማለች ለማለት አያስደፍርም። በተለይ ደግሞ ከ10 የሥራ ዕድሎች አንዱ በሆነው ቱሪዝም ሊፈጠር የሚገባው የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ዋናውና ትልቁ ድርሻ የአገልግሎት ሰውን ማሳደግና መዘመን ነው። ይህ ትልቅ ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪና የዘመነ እንዲሆን በቁሳዊ፣ሰብዓዊና ክህሎት ልማት ላይ መሥራት ዋናው ተግባር መሆን ይገባዋል።
“ድርጅታችን ደረጃቸውን የጠበቁ ከ4 እስከ 7 ተሳፋሪ የሚጭኑ ቶዮታ ሰራሽ ታክሲዎች የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ታክሲዎች እንዲኖሩ እየሠራ ነው” የሚሉት አቶ መሳፍንት፤ በተለይ የተቀላጠፈ ምቹና የቱሪስቱን የቆይታ ጊዜ የሚያራዝሙ አገልግሎት ሰጪዎችን መፍጠር፣ ጠንካራ የቱሪስት ታክሲ ማኅበራት እንዲፈጠሩ ማስቻል፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የቱሪስት አገልግሎት እንዲኖሩ ማድረግ፣ ቱሪዝም ታክሲ አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን፣ ኤሌክትሮኒክስ የታክሲ አገልግሎት መስጠት፣ የታክሲ የቱሪስት አገልግሎት አሰጣጥ የመረጃ ማዕከል በመመሥረት ያለውን ክፍተት ለመሙላት ማኅበሩ እየሠራ ነው።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ዓለማየሁ ጌታቸው የቱሪዝም ታክሲ አገልግሎት ለመስጠት የተደራጁ ማኅበራትን በተመለከተ በተዘጋጀው በዚህ የምክክርና የስልጠና መርሐ ግብር ላይ ተገኝተው ልምዳቸውን አካፍለዋል። በእለቱም “እኛ ኢትዮጵያውያን ከፍትፍቱ ፊቱ የሚል አባባል አለን” በማለት ጠቅሰው ቱሪስቶች ወደ አገራችን ሲመጡ በመልካም ስነ ምግባር በአገልጋይነት ስሜት፣ የኢትዮጵያን ገፅታ የሚገነባ በቂ እውቀት በመስጠትና እንግዶች ደህንነት እንዲሰማቸውና ቆይታቸውን አራዝመው እንዲሄዱ የማድረግ ኃላፊነት አለብን ይላሉ። ለዚህ ደግሞ በቀጥታ ከቱሪስቱ ጋር የሚገናኙ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ይህን ኃላፊነት መውሰድ ይገባቸዋል ነው ያሉት።
“በኢትዮጵያ የቱሪስት ታክሲ መኖሩ ፋይዳው ብዙ ነው” የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ አንድ ጎብኚ ወደ አገሪቱ ሲገባ በቀጥታ የሚገናኙት እነርሱ ስለሆኑ በመዲናዋ ሆነ በሀገሪቱ ያሉ መስህቦችን የማስተዋወቅ፣ ደህንነት እንዲሰማው የማድረግ፣ባህልና ማንነትን የማስተዋወቅ ሰፊውን ድርሻ እንደሚወስዱ ይናገራሉ። ይህን የአገልጋይነት መንፈስ ለመላበስ ደግሞ ትራንስፖርት ሰጪዎቹ በቂ እውቀትና የቱሪዝም ዘርፉን መሠረታዊ ከህሎት ሊያዳብሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አቶ አስናቀ ብርሃኑ የቱሪዝም ዘርፍ ባለሙያና ጋዜጠኛ ነው። የ2 ኤም ቲ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባሰናዳው መድረክ ላይ ተገኝቷል። “በቱሪዝም ዘርፉ የተሻለ አገልግሎት ባለማቅረብና ባለመስጠት ምክንያት ቱሪስቱ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም እንዳያገኝ ሆኗል የሚል ሀገር አቀፍም ሆነ ዓለም አቀፍ ጥናቶች አሉ” የሚለው አስናቀ ብርሃኑ፣ “ይሄ መሰበር አለበት” ብሏል። በአግባቡ ቱሪስቱ ላይ ብቻ የሚሠሩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሊመሠረቱ እንደሚገባም ይጠቁማል። በቅርቡ የኮይሻ፣ የወንጪ ደንዲ፣ የጎርጎራና ሌሎችም የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ላይ የሚሰጠው የትራንስፖርት አገልግሎት ደረጃቸውን የጠበቁና በአግባቡ አገልግሎት የሚሰጡ የቱሪስት ታክሲዎች ሊኖሩ እንደሚገባም ይገልፃል።
እንደ ባለሙያው ገለፃ፤ በአብዛኛዎቹ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች በልዩ ሁኔታ አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎችን ማግኘት አስቸጋሪ ነው፤ ቱሪስቱ በተለይ ጉብኝት አድርጎ ጨርሶ ማታ መዝናናት ቢፈልግ በእነዚህ ስፍራዎች ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ አገልግሎት የሚሰጠው የቱሪስት ታክሲ የለም። በተለይ ፓርኮች የመጎብኘት እድል ያጡት፣ ሌሎች መዳረሻ ስፍራዎች ያሉ መስህቦች በሚፈለገው ደረጃ የማይጎበኙትና የመጡት ቱሪስቶች ቆይታቸውን የማያራዝሙት ከዚህና መሰል አገልግሎት አለመኖር ጋር ይገናኛል።
“ቁሳዊ ልማት ላይ መሥራቱ አንድ ነገር ቢሆንም በራሱ ብቻውን ግን ለውጥ አያመጣም” የሚለው አቶ አስናቀ፤ የቱሪስት ታክሲዎቹ ሥራ ለመጀመር መደራጀታቸውና በሂደት ላይ መሆናቸው እንዳለ ሆኖ፤ የአገልጋይነት ሚና የሌለው አሽከርካሪ ከሌለ፣ የቱሪስቱን ስነ ልቦና በአግባቡ የሚረዳና የቱሪስቱን ፍላጎት መፈፀም የሚችል አገልጋይ ካልተፈጠረ፣ የመስህብ ስፍራዎችንና መዳረሻዎችን የማያውቅ ከሆነ እንዲሁም የቱሪዝም አምባሳደር የሆነ የታክሲ አሽከርካሪ ካልተፈጠረ የሚፈለገውን ግብ ለመምታት አይቻልም ይላል።
በተለይ በአዲስ አበባ ያሉትን ከ15 በላይ ሙዚዬሞች፣ በየአደባባዩ ላይ የቆሙ ታሪካዊ ሐውልቶች፣ ፓርኮችና መሰል ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መዳረሻዎችን ጠንቅቆ የሚያውቅ ብሎም የአገርን መልካም ገፅታ የሚገነባ መሠረታዊ እውቀት ያለው የቱሪስት ታክሲ አሽከርካሪ ከቁሳዊ ልማቱ በተጓዳኝ ሊኖር ይገባል ያለው አስናቀ፣ በቅርቡ ከሶስት ሺ በላይ የሚደርሱ የተለያዩ ማኅበራትን ማደራጀት የቻለው የ2 ኤም ቲ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የጀመረው ሥራም “እሰየው” የሚያስብል በጎ ጅምር ነው ሲል ተናግሯል።
በሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲቲዩት ውስጥ በቱሪዝም መምህርነት የሚሠራው አቶ ማሩ “ቱሪዝም ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው ይላል። በዚህ ጊዜ ቱሪስቶች በሚሄዱበት ሀገርም ሆነ አካባቢ የተሻለ አገልግሎትና እንክብካቤ እንደሚፈልጉ ይገልፃል። ቱሪስቶች ወደመጡበት አካባቢ በሚመለሱበት ጊዜ ፎቶና ትውስታ እንደሚኖራቸውም ገልጾ፣ እነዚህ ጎብኚዎች ፍላጎታቸው እንዲሟላ፣ ተደስተውና መልካም ነገር ይዘው እንዲመለሱ አገልግሎት ሰጪዎች ፕሮፌሽናል ሆነው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ይናገራል። ቱሪዝም ሲታሰብ ቀዳሚው የትራንስፖርት አገልግሎት መሆኑንም ነው የገለጸው። ይህ በበቂና እርካታን ሊፈጥር በሚችል መንገድ ሊኖር እንደሚገባ ምክረ ሃሳቡን ሰጥቷል።
በዚህ በኩል 2ኤም ቲ አዲስ መንገድ ይዞ መጥቷል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት የ2ኤም ቲ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር “የቱሪዝም ታክሲ” አገልግሎት የሚሰጡ ማኅበራትን አደራጅቶ ወደ ሥራ ለመግባት በሂደት ላይ ነው። ከመሥራቹ አንዱ የሆኑት አቶ መሳፍንት እንደሚሉት፤ ይህን መሰል አገልግሎት ለመስጠት በማኅበር የተደራጁት ከዚህ ቀደም በመሰል የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ባለንብረቶች ናቸው። ባለንብረቶቹም በቱሪዝም ዘርፉ ላይ በልዩ ሁኔታ ለመሳተፍና አገልጋይ ለመሆን በማሰብም በተነቃቃ መንፈስ እየሠሩ ነው።
የማኅበሩ መረጃ እንደሚያሳየው አገልግሎቱን የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችን ከውጪ ለማስገባትም ከመንግሥት የቀረጥ ነፃ ፍቃድና መሰል ሕጋዊ ጉዳዮች ተጠናቀዋል። ከሚመለከተው አካልም የድጋፍ ደብዳቤ ተገኝቶ ሂደቱ እየተጠናቀቀ ነው። በዚህም ቱሪዝሙን የሚመጥንና የመዲናዋን ደረጃ ከፍ ሊያደርግ የሚችል ተሽከርካሪ በማስገባት አገልግሎቱ በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደሚጀምር ባለንብረቶቹ ይፋ ተደርጓል። ይህ የአሠራር ሂደት በዘርፉ የሚሰሩ ባለድርሻዎችን ከማስተሳሰሩም በላይ ለብዙ ሺዎች የሥራ እድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 3 ን 2014 ዓ.ም