አዲስ አበባ፤ የህዝብ ተወካዮች መክር ቤት እና የሚዲያ ተቋማት ተቀራርበው መስራት እንደሚገባቸው ተገለጸ። የህዝብ ተወካዮች መክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ አባላት ሰብሳቢዎች፣ የብዙሃን መገናኛ እና ንግድ ሚዲያ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ዛሬ መጋቢት 18 ቀን 2011 ዓ.ም በምክር ቤቱ እና በሚዲያ ተቋማት መካከል ስላለው ግንኙነት ላይ ውይይት አካሂደዋል።
ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የህዝብ ተወካዮች መክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ እንዳሉት ምክር ቤትና የሚዲያ ተቋማት ተቀራረበው መስራት ለአገርና ህዝብ ጥቅም መረጋገጥ ያለውን ፋይዳ ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሁለቱ ተቋማት ግንኙነት እየጠነከረ እንደመጣ ተናግረዋል። ለዚህም ጥሩ ማሳያው ይላሉ ወ/ሮ ሽታዬ ሚዲያዎች ለምክር ቤቱ ስራዎች የሚሰጡት የሚዲያ ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል ነው።
ይሁንና ይላሉ ምክትል አፈ ጉባዔዋ ምክር ቤቱ ማክሰኞ እና ሐሙስ ከሚያካሂዳቸው መደበኛ ስብሰባዎች ባሻገር ለሚያከናውናቸው በርካታ ስብሰባዎችና ውይይቶች ሚዲያው ተገቢውን ሽፋን እየሰጠ አይደለም ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ ይላሉ ወ/ሮ ሽታዬ ሚዲያው ዘገባዎችን የሚያቀርበው ከራሱ ፍላጎት አኳያ እንጂ የምክር ቤቱን ስራዎች በአግባቡ ተንትኖ አይደለም፤ አልፎ አልፎም ይላሉ አፈ ጉባዔዋ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች አስፈጻሚዎችን በሚገመግሙበት ልክ ሚዲያዎች ዘገባዎችን አያቀርቡም።
ከዚህም ባሻገር ይላሉ ወ/ሮ ሽታዬ ሚዲያዎች ከቃላት አመራረጥ፣ ዋና ፍሬ ሃሳቦችን ከመለየትና ከዘገባ አቀራረብ እንዲሁም የምክር ቤቱን ስብሰባዎችንና ውይይቶች እስከመጨረሻው ተከታትሎ ከመዘገብ አኳያ ውስኑነቶች ይስተዋልባቸዋል።
አቶ ሳልፊሶ ኪታቦ በፓርላማና በሚዲያ መካከል ስለሚኖር ግንኙነት ዙሪያ ባቀረቡት ጽሁፍ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ሚዲያው ለአገሪቱ እጅግ አስፈላጊ ተቋማት መሆናቸውን አንስተው የሁለቱ ተቋማት ተቀራርቦና ተናቦ መስራት ለአገር ሰላም መስፈንና ልማት መረጋገጥ አስፈላጊ ነው ብለዋል። እንደ አቶ ሳልፊሶ ምክር ቤቱ ሁሉንም ሚዲያዎች እኩል ማየት እንደሚገባ ጠቅሰው ሚዲያውም ሙያዊ ግዴታውን በአግባቡ መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል።
በውይይቱ ላይ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል አንዳንድ የምክር ቤት አባላት ለሚዲያዎች መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ አለመሆን፣ አንዳንዴም የሚሰጡት መረጃ የተሟላ አለመሆን፣ የአቅም ክፍተት፣ ሁሉንም ሚዲያ እኩል ያለማስተናገድ እንዲሁም የምክር ቤቱ አባላት መረጃን ከመስጠት አኳያ ፍረሃት ያለባቸው መሆኑ ናቸው ።
ለጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ወ/ሮ ሽታዬ፣ ፓርላማው ሁሌም ለጋዜጠኞች ክፍት ተቋም መሆኑን፤ ፓርላማው የትኛውንም ሚዲያ አግልሎ ወይም በተለየ ሁኔታ አቅርቦ የሚያውቀው ሚዲያ እንደሌለ ገልጸው፤ ይሁንና መረጃ በወቅቱንና ተገቢው ሁኔታ ከመስጠት አኳያ ችግር መኖሩን ተናግረዋል። ይሁንና አሁን ላይ መረጃ ከመስጠት አኳያ መሻሻሎች መኖራቸውን መካድ አይቻልም ያሉት አፈ ጉባዔዋ ከቆየንበት ባህል አኳያ ከፍረሃት ገና ጨርሰን እንዳልተላቀቅን ሊታወቅ ይገባል ብለዋል።
ወ/ሮ ሽታዬ አክለውም የምክር ቤቱ አባላት የአቅም ክፍተታቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻሉ የመጡበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰው በዚህም አስፈጻሚውን ለመቆጣጠር እያተደረገ ያለው አካሄድ ከፍተኛ መሻሻል እንደታየበት ገልጸዋል። በመጨረሻም ወ/ሮ ሽታዬ እንዳሉት ለህዝብና አገር ጥቅም ምክር ቤቱና ሚዲያው በቀጣይም የበለጠ ተቀራርበውና ተናበው መስራት እንደሚገባቸው፤ ምክር ቤቱ ለጋዜጠኞች መቼም ቢሆን ክፍት እንደሚሆን አስረግጠው ተናግረዋል።
መጋቢት 18 ቀን 2011 ዓ.ም
ተ . ተ
ፎቶ በገባቦ ገብሬ