አቶ ያዛቸው ያየህ እና ወይዘሮ አዲሴ ጥላሁን ስራ ወዳድ ነጋዴዎች ናቸው። የወርቅ እና የብር ጌጣጌጥ በመሸጥ ላይ የተሰማሩ፤ ታታሪ ሆነው በመስራታቸው በሃብት ላይ ሃብት ደራርበው፤ የተትረፈረፈ ንብረት ባለቤት ለመሆን ችለዋል። ቤታቸውን አሳምረው ሰርተው፤ ልጆቻቸውን አንደላቀው ያኖራሉ። ለብሰው አምረው ተሽቀርቅረው እና ተሽቆጥቁጠው ይታያሉ።
ንግዳቸውን በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ ላይ መሰረቱን አድርገው፤ አዲስ አበባ እየሔዱ ለንግድ የሚሆናቸውን ወርቅ፣ ብር እና ሌሎችም የተለያዩ ጌጣጌጦችን እየገዙ አትርፈው ለባህርዳር ሕዝብ ያቀርባሉ። ለፍተው ባጠራቀሙት ሃብት የቅርብ ወዳጅ ዘመድ ብቻ ሳይሆን የቅርብ ጎረቤትም ይደሰታል። በተቃራኒው የሚቀናም አይጠፋም። አንዳንድ የቅርብ ጎረቤታቸው እና በሚሰሩበት ሱቅ አካባቢ ያሉ ግለሰቦች በሃብት ላይ ሃብት መደራረባቸው ቅናት ቢጤ እንዲሞካክራቸው ሳያደርጋቸው አልቀረም። የቅርብ ጎረቤቶችም ሆኑ በሚሰሩበት ሱቅ አካባቢ ወዳጅ መስለው የሚቀርቡ ሰዎች በምን መንገድ የእነ አቶ ያዛቸውን ሃብት እንደሚዘርፉ እና እንደሚያዘርፉ ዕቅድ ማውጣት መሰባሰብ ጀምረዋል።
ከዘራፊዎቹ መካከል አንዱ የሆነው እና ቡድኑን ሲያስተባብር የነበራው አቶ እንዳለማው እነርሱ በሚሰሩበት ወርቅ ቤት አካባቢ የሚሰራ እና ከተለያዩ ሰዎች ጋር የሚግባባ ነው። ግንቦት 14 ቀን 2012 ዓ.ም እነ አቶ ያዛቸው ከአዲስ አበባ ወርቅ እንዳመጡ መረጃ አግኝቷል። ስለዚህ ለእነርሱ የቅርብ ጎረቤት የነበረውን እንደርሱ በእነ ወይዘሮ አዲሴ ሃብት የሚቀናውን ጎረቤታቸውን አግኝቶ ሌሎችንም አስተባብሮ ዘረፋውን ለማካሔደ ወስኗል። በዝርፊያው እንዲሳተፉ የታቀዱት የአካባቢው አንድ የባጃጅ ሹፌር የቅርብ ወዳጅ ነን ባዮቹ አንድ የሱቅ አንድ ደግሞ የሰፈር የቅርብ ወዳጅ ሌሎች ሁለት ተጨማሪ ሰዎችም ተሳታፊ እንዲሆን ታቅዶ እነአቶ ያዛቸው ቤት ዱብ ዕዳ ሆነው ተገኙ።
በዝርፊያው ዕለት
በዕለቱ ወይዘሮ አዲሴም ሆነች አቶ ያዛቸው እንደለመዱት ሲደክሙ ውለው አመሻሽ ላይ ወደ ቤታቸው ገብተዋል። በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ 02 ቀበሌ የሚኖሩበት ቤታቸው ለእነ አቶ ያዛቸው ማደሪያ ብቻ ሳይሆን ሙሉ ሃብታቸው መተዳደሪያቸውን በሙሉ ንብረታቸውን የሚይዝላቸው ሁሉ ነገራቸው ነው።
እንደተለመደው ከአዲስ አበባ ያመጡትን ወርቅም ሆነ ጌጣጌጥ እንዲሁም ማንኛውንም የሚሸጡትን ነገር እና ገንዘባቸውን ጨምሮ ዋናውን ሃብታቸውን የሚያስቀምጡት በካዝና ቤት ውስጥ ነው። ሃብታቸውን አምነው ሱቅ አያስቀምጡም። ወደ ቤት ይዘው ይገባሉ። ለሥራ ሲወጡ መልሰው ይዘው ይወጣሉ። በዚህ መልኩ ዓመታትን አስቆጥረዋል። በዛ ቀንም በተመሳሳይ መልኩ ሃብታቸውን ይዘው ወደቤታቸው ገብተዋል።
ዕለቱ ከሌሎች ቀናቶች የተለየ አልነበረም። ሁለቱም ሥራ ውለው ሃብታቸውን እንደተለመደው በካዝና አስቀምጠው እራት ተቀራርቦ ከነልጆቻቸው በደስታ እየተሳሳቁ ተመገቡ። እራት መብላታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ቡና እየተፈላ መጨዋወት ጀመሩ። ከምሽቱ ሶስት ሰዓት አካባቢ ግን በመኖሪያ ቤታቸው አገር አማን ብለው ተሰብስበው ሲጨዋወቱ የነበሩ የቤተሰብ አባላት ላይ ያልገመቱት እና ያላሰቡት መጣባቸው። አስደንጋጭ መዓት ቤታቸው ውስጥ ገባ።
ያቺን ሰዓት
የፊት መሸፈኛ ማክስ የለበሱ ስለት እና የጦር መሳሪያ የታጠቁ ግለሰቦች ወደ ቤታቸው ገቡ። ሲደክሙ ውለው ወደ ማረፊያቸው ገብተው ከልጆቻቸው ጋር በደስታ ሲዝናኑ የነበሩት ወላጆች ዘራፊዎቹን ለመከላከል የሚያስችል ሁኔታ ላይ አልነበሩም። ከውጪ ድምፅ አልሰሙም፤ ዘራፊ እንደሚመጣ ገምተው ድምፅ ሰምተው ተጠራጥረው ጊቢውን አልቃኙም። እነ አቶ ያዛቸው መሳሪያ አቀባብለው አልተጠባበቁም።
አቶ ያዛቸው ያየኽ በአጋጣሚ በር ሲከፍቱ ከፊት ለፊት መሳሪያ ተደቀነባቸው። እርሳቸውን እየገፉ አምስቱ ዘራፊዎች ወደ ቤት ገቡ፤ እጅ ወደ ላይ ብለው አቶ ያዛቸውን አንበረከኩ። ግንባራቸው ላይ ሽጉጥ አቀባብለው ወደ ኋላ እጃቸው የፊጥኝ አሰሯቸው።
እራት በልተው ቡና እየጠጡ የነበሩት የቤተሰብ አባላት በሙሉ ተደናገጡ። ሁሉም እጅ ወደ ላይ ተባለ። በተለይ የዘጠኝ አመቱ ልጅ የወንጀለኞቹ ድርጊት በጣም አስፈርቶት ነበር። ሁሉም ተንበርከኩ ከተባሉ በኋላ አይናቸው ታሰረ። ዘራፊዎቹ ወደ መኝታ ቤት ሲገቡ ካዝና አገኙ። አቶ ያዛቸውን የካዝና ቁልፍ ሲጠይቋቸው ቁልፉ ሱቅ እንዳለ ቢገልፁም ዘራፊዎቹ መጠየቃቸውን ቀጠሉ።
አቶ ያዛቸው ደጋግመው የካዝናው ቁልፍ ቤት ውስጥ እንደሌለ እንደውም ሱቅ እንደሆነ ተናገሩ። አንደኛው ሊያስፈራራቸው ሞከረ፤ ለመናገር ፈቃደኛ አልሆኑም። ተበሳጨ በቢላዋ ወጋቸው፤ ደማቸው መፍሰስ ጀመረ። ዘራፊዎቹ እየፈጠሩ ያሉት ወከባ እና በቢላዋ መወጋታቸው ተደማምሮ አባወራው ራሳቸውን መቆጣጠር አቃታቸው፤ አንገታቸውን ዘንበል አድርገው ወደቁ፤ በሚወድቁበት ጊዜ ሳያስቡት በጭንቅላታቸው ሶፋውን ሲገፉት ቁልፉ ሶፋው ስር ስለነበር የመንኮሻኮሽ ድምፅ ተሠማ።
የዘራፊዎቹ ፍላጎት ለመሳካት ጫፍ ላይ ደረሰ። ቁልፉን አገኙት። ነገር ግን መክፈት አልቻሉም። የቤቱን አባወራ አስገድደው መኝታ ቤት በማስገባት ካዝናውን እንዲከፈት አደረጉ። 130 ኪሎግራም ብር፣ 2ሺህ 888 ኪሎግራም ወርቅ በተጨማሪ የወይዘሮዋ ማጌጫ የሆነ 50 ግራም ጠገራ ብር እንዲሁም 300 ግራም ወርቅ በተጨማሪ ከቴሌቪዥን ጀምሮ በቤቱ ያሉትን ዕቃዎች ጫኑ። በአጠቃላይ ከእነ አቶ ያዛቸው ቤት ከ8 ሚሊየን ብር በላይ ዘረፉ።
ይህ ሁሉ ዝርፊያ ሲካሔድ ወይዘሮ አዲሴ አይናቸውን ገልጠው ፊታቸውን አዙረው ባለቤታቸው አቶ ያዛቸውን ለማየት አልተፈቀደላቸውም ነበር። ነገር ግን ባለቤታቸው ተጎድተው ይሆናል ብለው በመስጋት ቀስ ብለው ፊታቸውን ሲያዞሩ ከዘራፊዎቹ መካከል ጭንብል ያልለበሰ ትንሽ ተሸፋፍኖ ማክስ ብቻ ያደረገውን ጎረቤታቸውን አዩት። ዘራፊዎቹን ለዩዋቸው። ዘረፋውን ከሚያካሂዱት መካከል አንዱ የሆኑት ጎረቤትየው ደነገጡ። የያዙትን ይዘው ሁሉም ከመውጣታቸው በፊት ደጅ ላይ ተነጋገሩ።
ከዘራፊዎች ጋር ተባብሮ ሲዘርፉ የነበሩ ጎረቤትየው ‹‹ሴትየዋ አይታኛለች ግደሏት›› ሲል አዘዘ። ከዘራፊዎቹ መካከል ሁለቱ ወደ ውስጥ ተመልሰው ገቡ። መለስ ብለው ‹‹ክላሹ ያለበትን ቦታ አሳዬን›› ብለው እማወራዋን ማስጨነቅ ጀመሩ። ‹‹ክላሽ የለንም›› ወይዘሮ አዲሴ የሚል መልስ መስጠታቸውን ተከትሎ የዘጠኝ ዓመት ልጃቸውን ይዘው አንገቱ ላይ ስለት አሳረፉ። ልጁን ከምናርደው ክላሹ ያለበትን ቦታ አሳዬን ብለው እናትና ልጅን ሲያስጨንቁ የወይዘሮዋ መልስ ተመሳሳይ ሲሆን ዘራፊዎች ወይዘሮ አዲሴ ላይ አልጨከኑም። ቀረ ብለው ያሰቡትን ለቃቅመው ወጡ።
ነፍስ የማትረፍ ጥረት
መኝታ ቤት አስገብተው የወረወሯቸው አቶ ያዛቸው ያየህ፤ ብዙ ደም ፈስሷቸው ስለነበር ራሳቸውን ሳቱ። ባለቤታቸው ወይዘሮ አዲሴ ጥላሁን የመኝታ ቤቱን ሴራሚክ ሙሉ ለሙሉ ሽፍኖት የታያቸው የባለቤታቸው ደም ራሳቸውን እንዳይቆጣጠሩ አደረጋቸው። አቶ ያዛቸው የተወጋበትን ቦታ በጨርቅ በመጫን ደሙን ለማስቆም መሞከር ከበዳቸው።
ማክስ ብቻ ያደረገው እንደሌሎቹ ጭንብል ያላጠለቀው ጎረቤት ገብቶ ዕቃ ይዞ ሲወጣ ዓይን ለዓይን መተያየታቸው ትዝ ሲላቸው ጎረቤት ለመጥራት አልፈለጉም። ሳንቲም ሳይቀር ጠራርገው የወሰዱባቸው በመሆኑ፤ ለማሳከሚያ የሚሆን ገንዘብ አልነበራቸውም። እንደምንም ፈለገሕይወት ሆስፒታል ደርሰው አቶ ያዛቸው ህክምና ተከታተሉ። ሞት አፋፍ ደርሰው የነበሩት አቶ ያዛቸው ሕይወታቸው ሊተርፍ ቻለ።
አምስት ሆነው ገብተው ንብረታቸውን ለመዝረፍ ዓቅደው የተነሱት ወንበዴዎች፤ የወርቅ፣ የብር እና ሌሎች ጌጣጌጦችንም ወስደው ባዶ እጅ ቢያስቀሯቸውም ሕይወታቸውን አልነጠቋቸውም። ነገር ግን ከማስፈራራት ባለፈ በስለት የሰነዘሩት ጥቃት አቶ ያዛቸውን በእጅጉ ጎዳቸው።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ ጥቆማው እንደደረሰው ወንጀሉ ወደ ተፈፀመበት ቤት አመራ። ከወይዘሮ አዲሴ ጥላሁን እና ከልጆቻቸው መረጃ በማሰባሰብ የተለያዩ የመመርመሪያ ቴክኒኮችን በመጠቀም ሥራውን ቀጠለ። ከወንጀል ፈፃሚዎች አገባብ ጀምሮ አወጣጣቸውን እና ተክለሰውነታቸውን እንዲሁም የተለያዩ መረጃዎችን እና ማስረጃዎችን አሰባሰበ።
አንድ ቢተው ገብሬ የተባለ የባጃጅ ሹፌር በድርጊቱ ተሳታፊ እንደነበር ታወቀ። እርሱ ብቻ ሳይሆን ሱቅ አካባቢ ያለ አንድ ወዳጅ መሰል ግለሰብ በቼክ ዕቃ የገዛቸው ሰው ዘራፊዎችን በማሰባሰብ ለሁለት እና ለሶስት ቀን መክረው፤ ወርቁን ሱቅ ሳይሆን ወደ ቤት እንደሚወስዱ አጣርተው ለመዝረፍ አቅደው መነሳታቸውን ፖሊስ ደረሰበት።
የጦር መሳሪያ ተጠቅመው፤ በምሽት ቤተሰብ ላይ ዝርፊያ ለማካሔድ ከመንቀሳቀስ በተጨማሪ የምርመራውን አቅጣጫ ለማስቀየር ከጥቆማ አሰጣጥ ጀምሮ በርካታ ምስክሮችን በማስፈራራት የምርመራውን አቅጣጫ ለማስለወጥ ቢሞክሩም የምሽት ዘራፊዎቹ አልተሳካላቸውም።
ፖሊስ ጎረቤትየውን ጨምሮ አምስት ዘራፊዎች ከባድ የዘረፋ ወንጀል መፈፀማቸውን በመመርመር፤ አብሮ ተባብረው ተዋናይ ሆነው የተገኙትን ለፍርድ ለማቅረብ ጉዳዩን ለአቃቤ ሕግ አቀረበ። አቃቤ ሕግ በበኩሉ መርምሮ ድርጊቱን ፈፃሚዎች አጣርቶ በከባድ የዘረፋ ወንጀል እንዲጠየቁ አደረገ።
የወንጀል አፈፃፀሙ ከባድ የዝርፊያ ወንጀልን ውንብድናን የሚያሟላ መሆኑን በመጥቀስ፤ በኢፌዴሪ የወንጀል ህግ 671 ንዑስ 2 ድንጋጌ ውስጥ እንደሚወድቅ በማብራራት ክስ መሰረቱ ። በወርቅ እና በጌጣጌጥ ዝርፊያ፣ በግድያ ሙከራ፣ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘትን ጨምሮ ተደራራቢ የወንጀል ድርጊት መፈፀም በማለት 2ኛ ተከሳሽን አምስት ክስ ሌሎቹ ላይ አራት ክስ መሰረተባቸው።
ሆኖም በጠበቃ ተከራክረው ለቀረበባቸው ምስክር እነርሱም የመከላከያ ምስክር አቅርበው ቢከላከሉም፤ በተከሳሾቹ በኩል የቀረበው የመከላከያ ምስክር በቂ ወይም አሳማኝ ሆኖ ባለመገኘቱ ፍርድ ቤቱ 5ቱንም ተከሳሾች ጥፋተኛ አላቸው። ከተከሳሾች መካከል ሁለቱ ካለመገኘታቸው በተጨማሪ ተበዳዮቹ የተዘረፉትን ንብረት ማግኘት ባይችሉም ሶስቱ ዘራፊዎች ላይ ውሳኔ ተላለፈ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 2 ቀን 2014 ዓ.ም