ባለፉት አራት ዓመታት በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ነገር በታሪኳ ያልሆነና ሊታሰብ የሚችል አይደለም። የዜጎች ህይወት ባልተገባ መልኩ ለህልፈት ሲዳረግ በአደባባይ እየታየ ነው። በሰሜኑ ክፍል የእርስ በርስ ጦርነት ተደርጎ በአጠቃላይ የበርካቶች ህይወት አልፏል። ጦርነቱም የተቋጨ መስሎ ጋብ ብሎ ቢከርምም በየፊናው የተመሠቃቀለው የሚሊዮኖች ህይወት ግን በፍፁም አልተቃናም። አገርን ለማፍረስ የትኛውንም ምቹ አጋጣሚ ለመጠቀም ወደ ኋላ የማይሉ ዘር ቆጣሪ ሰው በላ ቡድኖች በንፁሃን ደም ጨቅይተዋል። በየፊናቸው የቀጠፏቸው ነፍሶችም ቁጥር ቀላል ሊባል የሚችል አይደለም። በመንግስት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ባንዳዎች ጨምሮ ሀገር በባንዳዎች እየታመሰች ነው።
በርግጥ ብዙዎች ከዚህ ሁሉ ግድያና መፈናቀል በስተጀርባ ያለው ማነው ብለው ለመጠየቅና ጥያቄውን ለማክበድ ይሞክራሉ። መንግስት ላይ ጣቱን የሚቀስረውን ጨምሮ መንግስትን ሙሉ ለሙሉ ከተጠያቂነት ውጪ የሚያደርገውም ቁጥሩ ብዙ ነው። ገለልተኛ ሆኖ የሚመለከት ፤ ውዥንብሩ ውስጥ ገብቶ የሚባክነውም ቀላል አይደለም። እውነታው ግን የቱ ጋር ነው?
ባለፉት 4 ዓመታት ለምዕራባውያኑ እንደ ኢትዮጵያ ራስ ምታት የሆነ ሀገር እንደሌለ ለማንም የተደበቀ አይደለም። ምእራባውያን መንግስትን እንዳሻቸው መጠምዘዝ ካለመቻላቸው እኩል በትልቁ እንቅልፍ የነሳቸው ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ የመሠረቱት የጠበቀ ወዳጅነትና ትስስር ነው። ይህ ነገር ያለነሱ እውቅና፣ ምንም መረጃ ሳይኖራቸው እውን መሆኑ በራሱ ለማመን ከብዷቸው የሚይዙት የሚጨብጡትን አሳጥቷቸዋል።
በተለይ ለወትሮ እንዳሻቸው ይዘውሩት የነበረው በባብኤል መንደብ ላይ የሚካሄደው የንግድ ስርዓት ከእጃቸው ሊወጣ ከጫፍ መድረሱ አቅላቸውን አስቷቸዋል። ስለዚህ ምን አረጉ? የቀድሞውን መንግስት እንደ መሳሪያ በመጠቀም ወገን ከገዛ ወገኑ ጋር የእርስ በርስ ጦርነት እንዲያደርግ አስደረጉ፣ ውጤቱ ግን እንደሚፈልጉት አልሆነም። ይህን በሚዲያዎቻቸው ይዘግቡት የነበረው አሳፋሪ ውሸት ምን እንደሚፈልጉ ፍንትው አርጎ አሳይቷል። ሱዳን ውስጥ የነበረውን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሃይል ‹‹አገልግሎትህ ይበቃል›› ብለው ሰራዊቱን የቀድሞውን መንግስት ጦር እንዲቀላቀል አሳምነው በጥቂቱም ቢሆን ተሳካላቸው።
የኢትዮጵያ መንግስት ወዳጅ የነበረውን የሶማሊያን ፕሬዚዳንት በምርጫ አስወግደው ለእነሱ ደንገጡር የሆነን ፕሬዚዳንት አስመረጡ። ይህ በሆነ በ36 ሰዓታት ውስጥ ቁጥሩ ከ450 በላይ የሆነ ጦር ሰራዊታቸውን ወደ ሶማሊያ አስገቡ። በምዕራቡ የሀገራችን ክፍል አንጻራዊ መረጋጋት ከመፈጠሩ በፊት ስለ ሸኔ በየሚዲያዎቻቸው በሳተላይትና በአካል በመገኘት ሰፊ ሽፋኖችን ሰጡ።
ከፍተኛ የቁሳቁስና የሎጂስቲክ እገዛን አደረጉ። (ልክ በፓኪስታንና አፍጋኒስታን ሙጅሀዲኖችን እንዳቋቋሙት ማለት ነው።) ከዛም ገና ጭፍጨፋው ሳያባራ በስምና በመረጃ የዳበረ መረጃዎችንና ዜናዎች መስራት ጀመሩ። የሚጠቀሟቸው ቃላትም ከዘገባ ይልቅ ቅስቀሳ ያመዘነባቸው እንደነበሩ ዓለም ሁሉ ታዝቧቸዋል።
ይህን እኩይና የአርዮስ ተግባርን የሚያስፈፅሙት ደግሞ በራሳቸው ሳይሆን በራሳችን ዜጋና ወገን ነው። ይህን መሪር እውነት ዋጥ አርገን ካጤነው ሶስት ነገሮችን እንረዳለን። በመጀመሪያ ኢትዮጵያ የለየለት የእርስ በርስ እልቂት ላይ ናት ተብሎ ሰላም አስከባሪ ሀይል ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት፣ ብሎም ያሻቸውን መንግስት መመስረት።
ያዘኑና የተቆጩ ይመስል ‹‹በገለልተኛ አቋም ይጣራ›› ተብሎ ገለልተኛ የተባለው ስብስብ ወደ ሃገር እንዲገባ ማድረግ ተከታዩ ርምጃ ይሆናል። ከዛም የጥቂት ሟቾችን አስክሬን ለማንሳት በሚል ወደ ሀገር ገብተው እንዴት በአጭር ወራት ውስጥ በንፁሃን እልቂት የታጀበ የመንግስት ለውጥ እንዳደረጉ የበርካታ ሀገራት ታሪክ በቂ ማሳያ ነው። ቀጥሎም ሀገር አፍርሰው የዜጎቿን ሰቆቃና መከራ እንደ ፊልም ቁጭ ብለው ያያሉ። ለዚህ ደግሞ ኢራቅ በቂ ማሳያ ናት።
ሌላው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ማስቆም ከማይችልበት ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት የቻሉትን ሁሉ ነገር አድርገው ሙሌቱን ማጨናገፍና ቆሞ እንዲቀር ማድረግ ነው። ለዚህ (ከሳምንት በፊት የአውሮፓ ህብረትና የአፍሪካ ህብረት የሰጡትን መግለጫ ማስታወስ በቂ ነው።)ኢትዮጵያ በነዚህ ወጥመዶች ውስጥ እንድትወድቅ የፈለጉትን አጀንዳ አስቀድመው በሚዲያዎቻቸው እንዲያስፈፅሙና ተቀባይነት እንዲያገኙ ማድረግ የሴራዎቹ ማጀቢያ ናቸው፡፡
ለዚህ ተፈፃሚነት ደግሞ ያላቸው ብቸኛው አማራጭ በአንድ በተመረጠ ዘር ላይ እልቂትን በማወጅ፣ በገዛ ዜጎቻችን በማስፈጀትና ይህን ፍጅት በጣም በማራገብ ለ24 ሰዓት ዜና በማድረግ የእርስ በርስ እልቂት እንዲፈጠር ማድረግ ነው። ምክንያቱም ይህ ህዝብ አንድ ከሆነ የፈለጉትን ነገር ማድረግ እንደማይችሉና ቀጠናው ከእጃቸው እንደሚወጣ ያውቃሉና። ሌላው ቀርቶ አይደለም ዛሬ ያኔ ገና በአድዋ ጦርነት ዋዜማ ኤርትራ አቅራቢያ ሰፍሮ ሀገርህን ለመውረር ሲዘጋጅ ለነበረው የጣሊያን ጦር ሰራዊትም በሴራ የተካኑ የስለላ ድርጅቶቻቸው መስራቾች ሳይቀሩ ስፍራው ድረስ በመገኘት ለጣሊያን ጦር የቁሳቁስና የሎጅስቲክ ድጋፍ ማድረጋቸው መዘንጋት የሌለበት በቂ ማሳያ ነው።
ይህን ያህል ነው የኢትዮጵያውያን አንድነት የሚያስበረግጋቸው። አሁንም ወገን የገዛ ወገኑን በገጀራ እንዲያርድና በጥይት እንዲቆላ እያደረጉ ነው። ግን እኛ ኢትዮጵያውያን ስለሆንን ነው እንጂ እነዚህ የ4 ዓመታት ተግባራት ሌላ የአፍሪካ ወይም የኤሺያ ሀገር ላይ ተከስቶ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ላይ ከባድ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በተገኙ ነበር።
ከዚህ አንፃር መንግስትም ሆነ በቀና ልብ አገራቸውን እያገለገሉ የሚገኙ አመራሮች፣ ምሁራን፣ የፖለቲካ ምሁራን፣ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች፣ ሚዲያዎቻችንም ሆኑ መላው ህዝብ ‹‹ምን ብናደርግ ይበጃል? የዜጎቻችንን እልቂት እንዴት ማስቆም ይቻላል? እውን መፍትሄው ምንድን ነው?›› በሚለው ጉዳይ ዙሪያ ግልፅና ሁሉንም አካታች በሆነው ሀገር አቀፍ ውይይት ላይ ቁጭ ብለው መነጋገርና ኢትዮጵያን ከተዘጋጀላት ወጥመድ መታደግ ትልቁ የኢትዮጵያ ተስፋ ይሆናል፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሰሞኑ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ቀርበው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት ማብራሪያም ኢትዮጵያ ምን አይነት ወጥመድ እንደተዘረጋላት ሰፊ ጊዜ ሰጥተው አብራርተዋል። እርግጥ ነው እንኳን የንጹሃን ዜጎቻችን ደም የአንዲት እንስሳ ነፍስም የምታንገበግበንና የምታስቆጣን መሆኑ አይካድም። ቁጣና ንዴታችን ግን መንግስት አልባ አገር አትርፎልን ዛሬ በመቶና በሺዎች የቆጠርነው የንጹህ ዜጎቻችን ሬሳ ነገ በሚሊየን እንዲሆን መፍቀድ የለብንም። ሰከን ብለን አገር በታቀደላት ወጥመድ ተጠልፋ እንዳትወድቅ የመታደግ የዜግነት ግዴታ አለብን።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 2 ቀን 2014 ዓ.ም