ወጣት ካሊድ ታረቀኝ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአዲስ ከተማ ክፍለከተማ ወረዳ አራት ነዋሪ ነው። የሰከላ ፊልም ፕሮዳክሽን ማኔጀርም ሲሆን የዛሬ አመት እርሱ በሚኖርበት ወረዳ በተዘጋጀ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የቪዲዮና ካሜራ ስልጠና አግኝቷል። በኋላም ደግሞ ይህንኑ የቪዲዮና ካሜራ ትምህርት ከግራፊክ ዲዛይን ጋር አጣምሮ በግሉ ተምሯል።
በዘንድሮው የክረምት ወቅት ደግሞ እርሱም በተራው ከዚሁ የቪዲዮና ካሜራ ጥበብ ጋር በተያያዘ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከሚሰጡ ወጣቶች ውስጥ አንዱ ለመሆን በቅቷል። በዚህ የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር በቪዲዮ ኤዲቲንግና ካሜራ ሞያ ወጣቶችን ለማሰልጠንም ወጣቶችን እየመዘገበ ይገኛል።
እስካሁንም ከዘጠና በላይ የሚሆኑ ተማሪዎችን መዝግቦ ከመጪው ሐምሌ 8 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ስልጠናውን ለመስጠት ዝግጅቱን አጠናቋል። በሂደት ደግሞ ከቪዲዮ ኤዲቲንግና የካሜራ ሞያ ስልጠና በተጨማሪ ለወጣቶች የቋንቋ ስልጠናዎችን ለመስጠት እቅድ ይዟል።
‹‹ለእኔ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ካለኝ ነገር ላይ ጥቂቱን ለሌሎች ማካፈል ነው›› የሚለው ወጣት ካሊድ፤ ያለኝን የቪዲዮ፣ ካሜራና የግራፊክ ዲዛይን ሞያ ለወጣቶች በነፃ ሳካፍል ትልቅ ክብር ይሰማኛል ሲል ይናገራል። ይህን በማድረጌ ከገንዘብ በላይ ትልቅ የአእምሮ ርካታም ይሰማኛል ይላል። በተለይ ደግሞ ይህን ሞያውን የሚያካፍለው እዚያው ራሱ የኖረበት አካባቢ ላሉ ወጣቶች በመሆኑ ራሱ ተምሮ መልሶ የአካባቢውን ወጣት እያገለገለ በመሆኑ ደስታው ወደር እንደሌለው ይገልፃል።
በተመሳሳይ በሌሎች ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ሥራዎችን እየሠሩ ያሉ ወጣቶች ከሚያገኙት ትርፍ በዘለለ ባላቸው ሞያ በበጎ ፍቃደኝነት ሌሎችን ማስተማር፣ ማገዝና መርዳት እንዳለባቸውም ይመክራል።
ወጣት ልዑለሥላሴ ፀጉም በተመሳሳይ የዚሁ ወረዳ ነዋሪ ሲሆን የኬዛ አፍሪካ ፕሮዳክሽን ምክትል ሥራ አስኪያጅ ነው። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2009 ዓ.ም የፍልስፍና ትምህርት ምሩቅም ነው። ከዚሁ ጎን ለጎንም በፊልም ሥራ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ራሱን አስተምሯል። ከምርቃት በኋላ ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት በመግባት የፊልም ሥራ ተምሯል።
እርሱ እንደሚለው ኬዛ አፍሪካ በዋልታ ኤፍ ኤም 105 ነጥብ 3 ላይ የሬዲዮ ፕሮዳክሽን ይሠራል። አፍሪካዊነትንና ፓን አፍሪካኒዝምን በፊልሞች፣ በተለያዩ የሥነጽሑፍ ዝግጅቶችና በፓናል ውይይቶች ለሕዝቡ ለማስተዋወቅ ደግሞ የኬዝ አፍሪካ ፕሮዳክሽን ዋነኛ አላማ ነው። በተለያዩ ዘርፎችና መንገዶች ውብ አፍሪካን ለመፍጠርና አፍሪካ ተፅእኖ ፈጣሪ እንድትሆን እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። በወረዳውም ቤተ መጽሐፍት ለመክፈት እቅድ ይዟል።
በወረዳው የዘንድሮው የክረምት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መርሀግብር ከሚሳተፉት ውስጥም አንዱ ኬዛ አፍሪካ ሲሆን በፊልም ሥራ፣ በትወና፣ ዳይሬክቲንግ፣ ኤዲቲንግ ስክሪፕት ራይቲንግ ወጣቶችን ለማሰልጠን ምዝገባ ጀምሯል። እስካሁንም ዘጠና የሚሆኑ ተማሪዎች ይህን ስልጠና ለመከታተል ተመዝግበዋል።
ከዚህ ባለፈ በሥነጽሑፍ ሊትሬቸርና በቋንቋ /እንግሊዝኛ፣ ስዋሂሽ፣ ፈረንሳይኛና አረብኛ ቋንቋ/ ከወረዳው ጋር በመነጋገር ወጣቶችን ለማስተማር አቅዷል። እስከ ሐምሌ 2 ቀን 2014 ዓ.ም ለወጣቶቹ ገለጻ ለመስጠት ታስቧል።
‹‹ባለኝ ሞያ ሌላውን ሰው መጥቀም መቻሌ ትልቅ ደስታ ይሰጠኛል›› የሚለው ወጣት ልዑለሥላሴ በግሌ እንኳን ስኬት ባመጣ በአገር ደረጃ ውጤት የማያመጣ በመሆኑ ይህን ለውጥ ለማምጣት ሁሉም ወጣት ከሌላው ጋር ተባብሮ ሊሠራ እንደሚገባ ይጠቁማል። ለወጣቶች በሞያው እያበረከተ ያለውን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለአገር እንደሚያበረክተው አስተዋፅኦ አድርጎ እንደሚቆጥረውም ይናገራል።
ራስን ለመደጎም ለትርፍ መሥራት አስፈላጊ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ወጣቶች ከሥራ ውጪ ያላቸውን ጊዜ፣ እውቀት፣ ገንዘብ ሌላም ነገር በበጎ ፍቃደኝነት ለሌሎች ወጣቶች ቢያበረክቱ በሥራቸው ከሚያገኙት ትርፍ በዘለለ የአእምሮ እርካታም እንደሚያገኙ ወጣት ልዑለሥላሴ ይገልፃል። ከዚህ አንፃር ወጣቶች ባላቸው ትርፍ ጊዜ በበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ላይ መሳተፍ ማኅበረሰቡን መጥቀም እንዳለባቸው መልዕክቱን ያስተላልፋል።
በተለይ ደግሞ ወጣቶች ያላቸው ትርፍ ሰዓት በሻይ ቡና እንደሚቃጠልና ሆኖም ይህ ጊዜ ለሌሎች ትልቅ ዋጋ እንዳለው በማሰብ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ ቢያውሉት ራሳቸውም ረክተው ሌላውም ተጠቃሚ የሚሆንበት ዕድል ያለ በመሆኑ ትርፍ ጊዜያቸውን በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ እንዲያውሉት ይመክራል።
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት አስተዳደር ኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሴ አድነው እንደሚሉት የክረምት የወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት መርሃግብር በየአመቱ ይካሄዳል። የዘንድሮው መርሃግብር ግን ቀደም ብሎ የተጀመረ በመሆኑ ከበፊቱ ለየት ያደርገዋል።
በዚህ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መርሃ ግብርም ወደ ዘጠኝ የሚደርሱ ወሳኝ ተግባራት አሉ። እነዚህ ዘጠኝ ተግባራት ደግሞ አሥራ አራት የሚጠጉ ዝርዝር የበጎ ፍቃድ ተግባራትን አቅፈዋል። 567 የሚሆኑ ወጣቶችም በተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዘርፎች እየተሳተፉ ይገኛሉ። ወጣቶቹ ከሚሳተፉባቸው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዘርፎች ውስጥም የቤት እድሳት፣ ትራፊክ ማስተባበር፣ ደም ልገሳ፣ ችግኝ ተከላና የመሳሰሉት ይገኙበታል።
ኃላፊው እንደሚሉት በበጎ ፍቃድ አገልግሎት መርሃ ግብሩ የሚሳተፉት ወጣቶች በወረዳው በኩል በተሠሩ የማስታወቂያና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ነው። ወጣቶች በብዛት በሚገኙባቸው አካባቢዎች ላይ በማናገር፣ ስልጠና በመስጠትና ድጋፍና ክትትል በማድረግ በዚህ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር እንዲሳተፉም ተደርጓል። የተለያዩ ወጣት እድሮችና ማህበራትን በመጠቀምም ወጣቶቹ ወደዚህ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እንዲታቀፉ ሥራዎች ተሠርተዋል።
ከአምናው ጋር ሲነፃፀርም የዘንድሮው የክረምት ወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት መሻሻል ያሳየና በቁጥርም በዓይነትም ከፍ ያለ ነው። አምና 300 አካባቢ የነበረው የወጣት በጎ ፍቃደኞች ቁጥርም ዘንድሮ ወደ 567 ከፍ ብሏል። በየጊዜው ወጣቶችን ሊስቡ የሚችሉ ተግባራት በወረዳው በኩል መከናወናቸው ደግሞ ለቁጥሩ መሻሻል አስተዋፅኦ አድርጓል።
ለአብነትም አምና የቪዲዮና ፎቶግራፍ ኤዲቲንግ ትምህርቶች በመጀመራቸው በዚህ ዘርፍ ሌሎች ወጣቶችን የሚያስተምሩ በጎ ፍቃድ ወጣቶች ቁጥር ከፍ ብሏል። ትምህርቱን ተምረው ዳግም በጎ ፍቃደኛ የሆኑ ወጣቶችም ተፈጥረዋል። በዘንድሮው የክረምት ወቅት ደግሞ አገልግሎቱን ሰፋ በማድረግና የተለያዩ ማበረታቻዎችን ለምሳሌ እውቅናና ሽልማት በመስጠት በአጠቃላይ የፊልም ሥራና የሥነ ጽሑፍ ትምህርቶች እንዲሁም በዲሽ ጥገና ትምህርት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች ቁጥር እንዲጨምር ተደርጓል።
በዚህ የክረምት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ወጣቶች ከሚሳተፉባቸው ዘርፎች ውስጥ አንዱ የቤት እድሳት ሲሆን እንደ ወረዳ አራት 29 የሚሆኑ ቤቶችን ለማደስ እቅድ ተይዞ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። በደም ልገሳም ከ500 ዩኒት በላይ ደም ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሠራ ነው። በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም 25 ሺ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ተከላው ተጀምሯል።
በተመሳሳይ በፅዳት ዘርፍም የተደፈኑ ቦዮችንና አካባቢን የማፅዳት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።ከ60 በላይ ወጣቶች የሚሳተፉበት የትራፊክ አገልግሎትም በወረዳው በሚገኙ ሦስት አደባባዮች ላይ በፈረቃ እየተካሄደ ነው። ከዚሁ ጎን ለጎንም በትራፊክ ደህንነት ዙሪያ በነዚሁ ወጣቶች አማካኝነት የግንዛቤ ማስጨበጫዎች ይሰጣሉ።
ከጤና ጋር በተያያዘም በተለይ በኤች አይ ቪ ኤድስ ዙሪያና ሌሎች ተዛማች በሽታዎች ላይ በጎ ፍቃድ ወጣቶቹ ለኅብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን እየሰጡ ይገኛሉ።
አሁን ባለው ሁኔታም የዘንድሮው የክረምት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛል። 29 ቤቶችን ለማደስ እቅድ ተይዞም ከእቅድ በላይ 47 ቤቶችን ማደስ ተችሏል። የትራፊክ አገልግሎቱም በጥሩ እየሄደ ነው። የደም ልገሳውም በተያዘለት ቀን የሚከናወን ይሆናል። የችግኝ ተከላውም እየተከናወነ ነው።
ከሞያ ነክ ስልጠናዎች ጋር በተያያዘም ምዝገባ ተካሂዶ ከሐምሌ 8 ቀን 2014 ዓ.ም ትምህርቱ ይጀመራል። በወረዳው በኩልም በተለያየ መልኩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ በአግባቡ እንዲሄድ የማስተባበርና የድጋፍ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
የወጣት ካሊድንና ልዑለሥላሴን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተግባር ሌሎች ወጣቶችም እንደየሞያቸው፣ እውቀታቸውና እንዳላቸው ጊዜ ቢተገብሩት በርካታ ወገኖች ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ መገመት አያዳግትም። በኅብረተሰቡ ዘንድ ለበጎ ፍቃድ ያለው አመለካከት ቢሻሻልና መንግሥትም ለዚህ ዘርፍ የሚያደርገው ድጋፍ ቢጠናከር ደግሞ ከሚታሰበው በላይ አገርንና ወገንን መጥቀም እንደሚቻል ሁሉንም ያስማማል።
በርግጥ በአሁኑ ጊዜ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በዓይነትም በብዛትም እየጨመረ መጥቷል። የወጣት ካሊድንና ልዑለሥላሴን የበጎ ፍቃድ አገልግሎትም ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው። የዘንድሮው የክረምት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎትም በአስራ አንድ የተለያዩ ዘርፎች በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እየተሰጠ ይገኛል። በመላው አገሪቱ የሚገኙ ከ19 ሚሊዮን በላይ ወጣቶችም ተሳትፈውበታል። በዚሁ የበጎ ፍቃድ አገልግሎትም መንግሥትና ኅብረተሰቡ ሊያወጡ የሚችሉት 11 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ወጪ ይድናል ተብሎ ይጠበቃል።
አገልግሎቱ ሰኔ 15 ቀን 2014 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን እስካሁን ድረስ በአረንጓዴ አሻራ፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ ሰላም፣ መንገድ ደህንነት፣ ኮቪድ-19 መከላከልና ሌሎችም የጤና አጠባበቅ ሥራዎችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት ግንዛቤ መፍጠር ላይ ያተኮሩ ዘርፎች ላይ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት፣ የአረጋውያንና አቅመ ደካማ ቤት እድሳት፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን መከላከልና ግንዛቤ መፍጠርን ጨምሮ በሌሎች አስራ አንድ ዘርፎች ላይም ተመሳሳይ ሥራዎች እየተሠሩ ነው።
በዋናነት ደግሞ የወጣቶችን እርስ በእርስ ግንኙነቶች እንዲያጠናከሩና አጠቃላይ የወጣቶች ተሳትፎ የጎላ ሚና እንዲኖረው በሰላም ዙሪያ ያተኮሩ ግንኙነቶችም ተካሂደው አገልግሎቱ መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 1/2014